የኢስላም ልዩ ባህሪያት (ክፍል 2) – ሰብአዊነት (አል-ኢንሳኒያ)

0
2240

ሰብአዊነት ሁለተኛው የኢስላም መለያ ባህሪ ነው፤ ሰብአዊነት ሲባል ኢስላም ለሰው ልጅ ከፍተኛ ቦታና ክብር የሚሰጥ ሐይማኖት መሆኑን ለመግለጽ ነው፤ኢስላም እምነቱም ሆነ ህግጋቶቹ እንዲሁም አላማው የሰውን ልጅ ለመንከባከብ፤ መብቱን ለማስጠበቅና በጠቅላላው የሰው ልጆችን ህይዎት በደስታ የተሞላ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ይህም በኢስላም አስተምሮቶች ውስጥ ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሆኖ ይታያል።

ኢስላም ሰብዓዊ መሆኑን አይነተኛ ምሳሌ ለመጥቀስ፣ የአላህን ዲን ያስተላለፉልን የአላህ መልክተኛ ከሰው ልጅ መሆናቸው ነው፤ አላህ እንድህ ይላል፡-

قُلْ إِنَّمَا أَنَا بَشَرٌ مِّثْلُكُمْ يُوحَىٰ إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ فَاسْتَقِيمُوا إِلَيْهِ وَاسْتَغْفِرُوهُ وَوَيْلٌ لِّلْمُشْرِكِينَ

“(እንዲህ) በላቸው ‘እኔ መሰላችሁ ሰው ብቻ ነኝ። አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ወደእርሱም ቀጥ በሉ ምሕረትንም ለምኑት ማለት ወደእኔ ይወረድልኛል። ለአጋሪዎቹም ወዮላቸው’።” (ፉሲለት 41፤6)

የሁሉም የአላህ መልክተኞች ጥሪ የነብያችን ሙሃመድ (ሶ.ዐ.ወ) ጨምሮ መሠረታቸው ወደ አላህ አንድነት (ተውሂድ) ጥሪ ማድረግና አላህን ብቻ ነጥሎ መገዛት ነው፤ ከዚያ በመቀጠል ለሰው ልጅ ህይዎት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ኑሮውን ማሻሻል ነው፤ ስለዚህም አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን ውስጥ የተረከልንን የነቢያት ታሪክ ስንመለከት ሁሉም ነብያቶች በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን ከመስመር የለቀቀ አስተሳሰብና ተግባር ማስተካከል ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች ሆኖ እናገኘዋለን።

ለዚህም እንደማሳያ ነቢዩላህ ሹዐይብ (ዐ.ሰ) ለህዝባቸው ሲያስተምሩ እንዲህ ይላሉ፡-

يَا قَوْمِ اعْبُدُوا اللَّهَ مَا لَكُم مِّنْ إِلَٰهٍ غَيْرُهُ وَلَا تَنقُصُوا الْمِكْيَالَ وَالْمِيزَانَ

“ሕዝቦቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ከእርሱ ሌላ ለናንተ አምላክ የላችሁም። ስፍርንና ሚዛንንም አታጉድሉ” (ሁድ 11፤84)

ከላይ ከተገለጸው የቁርኣን አንቀጽ እንደምንረዳው ነቢ ሽዐይብ (ዐ.ሰ) ለህዝባቸው ተውሂድ ከማስተማራቸው በተጨማሪ ሚዛንና ስፍር ማጉደልን እንዲተውና ሲገዙና ሲሸጡ ሰውን እንዳያታልሉ ምክር ይለግሰዋቸው ነበር።

ነቢዩላህ ሉጥ (ዐ.ሰ) ገብረሶዶማዊያን የነበሩትን ህዝቦቻቸው ከዚህ አስቀያሚ ሥነ ምግባር እንዲርቁ ሲመክሯቸው እንድህ ይላሉ፡-

وَلُوطًا إِذْ قَالَ لِقَوْمِهِ أَتَأْتُونَ الْفَاحِشَةَ مَا سَبَقَكُم بِهَا مِنْ أَحَدٍ مِّنَ الْعَالَمِينَ

“ሉጥንም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)። ‘አስቀያሚን ሥራ ትሠራላችሁን? በእርሷ ከዓለማት አንድም አልቀደማችሁም’።” (አል-አዕራፍ 7፤80)

በሌላ የቁርኣን አንቀጽም እንዲህ ሲሉ መጥፎ ተግባራቸውን አውግዘዋል፡-

أَتَأْتُونَ الذُّكْرَانَ مِنَ الْعَالَمِينَ 

“ከዓለማት ሰዎች ወንዶችን ትመጣላችሁን?” (አል-ሹዐራእ 26፤165)

ሁሉም የኢስላም ህግጋቶች መንፈሳዊም ይሁኑ ማህበራዊ የሰውን ጥቅም ለማስከበር የቆሙ ሆነው እናገኛቸዋለን፤ ዘካት ከሐብታሞች ተወሰዶ ለድሆች ይሰጣል፤ ሶላትና ጾም ሰዎች በእለት ከእለት ኑሯቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለማቃል ይረዳሉ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اسْتَعِينُوا بِالصَّبْرِ وَالصَّلَاةِ إِنَّ اللَّهَ مَعَ الصَّابِرِينَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በመታገስና በሶላት ተረዱ። አላህ (በእርዳታው) ከታጋሾች ጋር ነውና።” (አል-በቀራ ፤153)

ኢስላም የሰዎች ህይዎት በፍትህ የተሞላ እንዲሆን ለማድረግ በሰዎች ላይ ችግር የሚፈጥሩ ስምምነቶችና ውሎችን ሀራም (ክልክል) አድርጓል፤ በአንጻሩ ደግሞ የሰውን ልጅ ክብር የሚጠብቁ ሥነ መግባራትንና ሥርዐቶችን ደንግጓል።

ኢስላም ለሰው ልጅ ከሰጠው ሰብአዊ ክብር መገለጫዎች:-

1. የሰውን ልጅ በመሬት ላይ ምትክ (ኸሊፋ) ማድረጉ

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَإِذْ قَالَ رَبُّكَ لِلْمَلَائِكَةِ إِنِّي جَاعِلٌ فِي الْأَرْضِ خَلِيفَةً

“(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- ‘እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤’ ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)” (አል-በቀራ 2፤30)

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ የርሱ ምትክ ሆኖ መሬትን የማልማትና የመገንባት ክብር ሰጥቶታል፤ ይህንንም መፈጸም እንዲችል አእምሮ ሰጥቶት መማርና ማወቅ እንዲችል አስችሎታል፤ በዚህም ምክኒያት የሰው ልጅ ከመላእክት በለይ ደረጃ እንዲኖረው ሆኗል።

2. የሰው ልጅ ባማረና በተስተካከለ ሁኔታ መፈጠሩ

አላህ (ሱ.ወ) የሰውን ልጅ ባማረና በተስተካከለ ቅርጽና ቁመና ፈጥሮት ከሌሎች ፍጡራን የተለየና የተከበረ እንዲሆን አድርጎታል።

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

لَقَدْ خَلَقْنَا الْإِنسَانَ فِي أَحْسَنِ تَقْوِيمٍ

“ሰውን በጣም በአማረ አቋም ላይ ፈጠርነው።” (አት-ቲን 95፤4)

በሌላም የቁርኣን አንቀጽ እንዲህ ይላል፡-

اللَّهُ الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ قَرَارًا وَالسَّمَاءَ بِنَاءً وَصَوَّرَكُمْ فَأَحْسَنَ صُوَرَكُمْ وَرَزَقَكُم مِّنَ الطَّيِّبَاتِ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ فَتَبَارَكَ اللَّهُ رَبُّ الْعَالَمِينَ

“አላህ ያ ምድርን መርጊያ ሰማይንም ጣሪያ ያደረገላችሁ ነው። የቀረጻችኁም ቅርጻችሁንም ያሳመረ ከጣፋጮችም ሲሳዮች የሰጣችሁ ነው። ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው። የዓለማትም ጌታ አላህ ላቀ።” (ጋፊር 40፤64)

3. አላህ (ሱ.ወ) የፈጣራትን ሩህ በሰው ልጅ ውስጥ ነፋበት

ይህችንም ሩህ (ነፍስ) ወደ ተቀደሰው የአላህ ዛቱ በማስጠጋት የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን አረጋግጧል፤ እንዲሀም ይላል፡-

إِذْ قَالَ رَبُّكَ لِلْمَلَائِكَةِ إِنِّي خَالِقٌ بَشَرًا مِّن طِينٍ فَإِذَا سَوَّيْتُهُ وَنَفَخْتُ فِيهِ مِن رُّوحِي فَقَعُوا لَهُ سَاجِدِينَ

“ጌታህ ‘ለመላእክት እኔ ሰውን ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ’ (አስታውስ)። ‘ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበት ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ’ (አልኩ)።” (ሷድ 38፤71-72)

በሌላም የቁርኣን አንቀጽ እንዲህ ብሏል፡-

ثُمَّ جَعَلَ نَسْلَهُ مِن سُلَالَةٍ مِّن مَّاءٍ مَّهِينٍ ثُمَّ سَوَّاهُ وَنَفَخَ فِيهِ مِن رُّوحِهِ وَجَعَلَ لَكُمُ السَّمْعَ وَالْأَبْصَارَ وَالْأَفْئِدَةَ قَلِيلًا مَّا تَشْكُرُونَ

ከዚያም ዘሮቹን ከተንጣለለ፣ ከደካማ ውሃ ያደረገ ነው። ከዚያም (ቅርጹን) አስተካከለው። በእርሱ ውስጥም ከመንፈሱ ነፋበት፤ (ነፍስ ዘራበት)። ለእናንተም ጆሮዎችን፣ ዓይኖችንና ልቦችንም አደረገላችሁ። በጣም ጥቂትን ብቻ ታመሰግናላችሁ።” (አስ-ሰጅዳህ 32፤8-9)

4. ፍጥረተ አለሙ ሁሉ ለሰው ለጅ መገልገያና መጠቀሚያ መደረጉ

በኢስለም አመለካከት አላህ (ሱ.ወ) በዚህ አለም ያሉ ነገሮችን ሁሉ ለሰው ልጆች መገልገያና መጠቀሚያ አድርጓል፤ ይህም የሰውን ልጅ ከሌሎች ፍጡራን አንጻር ምን ያህል አላህ እንዳከበረውና እንዳላቀው የሚያሳይ ነው። በአንጻሩ የሰው ልጅ ይህን አላህ የሰጠውን ፀጋ ተጠቅሞ በዱንያ አለም ሲኖር ጌታውን ለማምለክ ሊታገዝበት ይገባል እንጅ የፈጠረውንና ፀጋውን በመለገስ ያኖረውን ጌታ ሊረሳና ሊክድ አይገባም። አለህ (ሱ.ወ) ሰዎችን ሁሉ በዚህ ጉዳይ ሲያናግር እንዲህ ይላል፡-

اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَأَنزَلَ مِنَ السَّمَاءِ مَاءً فَأَخْرَجَ بِهِ مِنَ الثَّمَرَاتِ رِزْقًا لَّكُمْ وَسَخَّرَ لَكُمُ الْفُلْكَ لِتَجْرِيَ فِي الْبَحْرِ بِأَمْرِهِ وَسَخَّرَ لَكُمُ الْأَنْهَارَ

“አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ከሰማይም ውሃን ያወረደ በእርሱም ከፍሬዎች ሲሳይን ለእናንተ ያወጣ መርከቦችንም በፈቃዱ በባሕር ላይ ይንሻለሉ ዘንድ ለናንተ የገራ ወንዞችንም ለናንተ የገራ ነው።” (ኢብራሂም 14፤32-34)

በሌላ የቁርኣን አንቀጽም እንዲህ ይላል፡-

أَلَمْ تَرَوْا أَنَّ اللَّهَ سَخَّرَ لَكُم مَّا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ وَأَسْبَغَ عَلَيْكُمْ نِعَمَهُ ظَاهِرَةً وَبَاطِنَةً وَمِنَ النَّاسِ مَن يُجَادِلُ فِي اللَّهِ بِغَيْرِ عِلْمٍ وَلَا هُدًى وَلَا كِتَابٍ مُّنِيرٍ

“አላህ በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ ለእናንተ ያገራላችሁ ጸጋዎቹንም ግልጽም ድብቅም ሲኾኑ የሞላላችሁ መኾኑን አታዩምን? ከሰዎችም ያለ ዕውቀትና ያለ መሪ፣ ያለግልጽ መጽሐፍም በአላህ የሚከራከር አልለ።” (ሉቅማን 31፤20)

5. በኢስላማዊ ህግ መሠረት በሰዎችና በፈጣሪያቸው መካከል ግርዶሽም ሆነ ሌላ አገናኝ የለም

ይህም አላህ (ሱ.ወ) ለሰው ልጅ የሰጠው ክብር ሌላው መገለጫ ነው። በኢስላም ማንኛውም ሰው የሰራው ወንጀል እንዲማርለትና ጉዳዩ እንደፈጸምለት ከፈለገ በቀጥታ እጁን ወደ ጌታው ዘርግቶ መጠየቅ ብቻ ነው የሚጠበቅበት። በሰውና በጌታው አላህ (ሱ.ወ) መካከል ከመልካም ስራ ውጭ አገኛኝ መስመር አይኖርም ማለት ነው። ሌሎች ሐይማኖቶቸን ስንመለከት ግን በሰዎችና በጌታቸው መካከል አገናኝ አካላትን አድርገው እናያቸዋለን። ለምሳሌ በክርስትና እምነት የሰውን ልጅ የዘላለም ደስታና ማህርታ ማግኘትን በግለሰቦች እጅ በማድረግ ካሕናትና ጳጳሳት ሰዎች ከወንጀልህ ተፈታሃል በማለትና የማህርታ ትኬት የማደል ስልጣን አላቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَإِذَا سَأَلَكَ عِبَادِي عَنِّي فَإِنِّي قَرِيبٌ أُجِيبُ دَعْوَةَ الدَّاعِ إِذَا دَعَانِ فَلْيَسْتَجِيبُوا لِي وَلْيُؤْمِنُوا بِي لَعَلَّهُمْ يَرْشُدُونَ

“ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ፡- እኔ ቅርብ ነኝ። የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ። ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና።” (አል-በቀራ 2፤186)

6. በኢስላም የማንኛው ሰው ክብርና ገንዘብ (ንብረት) የተጠበቁ ናቸው

ኢስላም የማንኛውንም ሰው ሕይወት፣ ገንዘብና ክብር የተጠበቁ የተከበሩ መሆናቸውን አረጋግጧል። ያለ አግባብ የማንኛውንም ሰው ወይም ሌላ ፍጡር ደም ማፍሰስ፣ ገንዘብን መብላትም ሆነ ክብርን መንካት በኢስላም እርም የተደረጉ ጉዳዮች ናቸው። ይህን አስመልክተው ነቢያችን ሙሃመድ (ሶ.ዐወ) በዚች አለም በህይዎት ከቆዩባቸው ጊዜያት በመጨረሻው አመት በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው በተገኙበትና የመሰናባቻ ሐጅ ባከናወኑበት ወቅት ባደረጉት ወሳኝ ንግግራቸው እንዲህ ይላሉ፡-

“ሰዎች ሆይ የዛሬውን ወር፣ የዛሬውን ቀን ይህች ከተማ (መካ) የተቀደሰች መሆናቸውን የምታውቁትን ያህል የእያንዳንዱን ሰው ሰላም፣ ህይዎትና ንብረትም በክብር እንድትይዙ አደራ ተጥሎባችኋል። በእጃችሁ የሚገኙትን የአደራ እቃዎች መልሱ፤ ማንም ሰው እንዳያጠቃችሁ በማንም ሰው ላይ ጥቃት እትፈጽሙ። ከዚያም ራሳቸውን ወደ ላይ ቀና እያደረጉ ያ አላህ መልክቴን በትክክል ማድረሴን መስክር! በማለት ሶስት ጊዜ ተናገሩ፤ በመጨረሻም የሰማ ላልሰማ ያድርስ፣ ከኔ በኋላ ወደ ኩፍር ተመልሳችሁ እርስ በርሳችሁ እንዳትጫረሱ ሲሉ ንግግራቸውን ደመደሙ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ይህ ቃል ኢስላም ከአስራ አራት ክ/ዘመናት በፊት ለሰብአዊ መብቶች እውቅና ማረጋገጫ እንደሰጠ ያሳያል።

ኢስላም የሰው ልጅ በሕይዎት እያለ ብቻ ሳይሆን ከሞት በኋላም ክብሩ እንዲጠበቅ አዟል። ነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

كَسْرُ عَظْمِ الْمَيِّتِ كَكَسْرِهِ حَيًّا

“የሙትን አጥንት መስበር በሕይዎት እያለ እንደመስበር ነው።” (አህመድ ዘግበውታል)

ይህ ለሰው ልጅ በኢስላም የተሰጠ ክብር በሌሎች ምድራዊ ህጎችና እምነቶች ዘንድ ካለው የተለየ ሆኖ እናገኛወለን። እነዚህ ምድራዊ ሰው ሰራሽ ህጎችና ሥርዓቶች ለተወሰነው የህይዎት ዘርፍ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመስጠት ሌላውን የህይዎት ዘርፍ ደግሞ ችላ በማለት የሰው ልጅ እራሱን እንዲጎዳና እንዲያወድም ሲፈቅዱ እናያቸዋለን።

7. ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው

ኢስላም ለሁሉም የሰው ልጆች እኩል ደረጃ መስጠቱ ሌላው ለሰው ልጅ ክብር መቆሙን የሚገልጽ ጉዳይ ነው። በኢስላም ሰዎች በቀለም ነጭ፣ ቀይ ወይም ጥቁር ስለሆኑ አይበላለጡም። በሰዎች መካከል ያለው ብቸኛ መበላለጫና መለያያ ጉዳይ ቢኖር ተቅዋ (አላህን መፍራት) እና መልካም ስራ ብቻ ነው። አላህ (ሡ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنَّا خَلَقْنَاكُم مِّن ذَكَرٍ وَأُنثَىٰ وَجَعَلْنَاكُمْ شُعُوبًا وَقَبَائِلَ لِتَعَارَفُوا إِنَّ أَكْرَمَكُمْ عِندَ اللَّهِ أَتْقَاكُمْ إِنَّ اللَّهَ عَلِيمٌ خَبِيرٌ

“እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ። እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ። አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው። አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነው።” (አል ሑጅራት 49፤13)

ነብያችን ሙህመድ (ሶ.ዐ.ወ) ይህን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ أَلَا إِنَّ رَبَّكُمْ وَاحِدٌ وَإِنَّ أَبَاكُمْ وَاحِدٌ، أَلَا لَا فَضْلَ لِعَرَبِيٍّ عَلَى أَعْجَمِيٍّ وَلَا لِعَجَمِيٍّ عَلَى عَرَبِيٍّ، وَلَا لِأَحْمَرَ عَلَى أَسْوَدَ وَلَا أَسْوَدَ عَلَى أَحْمَرَ إِلَّا بِالتَّقْوَى

“ሰዎች ሆይ ጌታችሁ አንድ ነው፤ አባታችሁም (አደም ) አንድ ነው፤ (በጥሞና አዳምጡኝ!) አረብ አረብ ባለሆነው ላይ ብልጫ የለውም፤ አረብ ያልሆነም በአረብ ላይ ብልጫ የለውም፤ ቀይም ጥቁርን አይበልጥም፤ ጥቁርም ቀይን አይበልጥም፤ በተቅዋ (አላህን በመፍራት) ቢሆን እንጂ።” (አህመድ ዘግበውታል)

ከዚህ በተጨማሪም ኢስላም በወንጀለኞችና ጥፋተኞች ላይ የደነገጋቸው የቅጣት ህጎች በሰዎች መካከል ልዩነት ሳይኖር፣ እገሌ ክቡር እገሌ ወራዳ፣ እገሌ ሐብታም እገሌ ድሃ ተብሎ ልዩነት ሳይደረግ በሁሉም ላይ እኩል ይፈጸማሉ።

ነብያን (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

إِنَّمَا أَهْلَكَ الَّذِينَ قَبْلَكُمْ أَنَّهُمْ كَانُوا إِذَا سَرَقَ فِيهِمْ الشَّرِيفُ تَرَكُوهُ وَإِذَا سَرَقَ فِيهِمْ الضَّعِيفُ أَقَامُوا عَلَيْهِ الْحَدَّ، وَايْمُ اللَّهِ لَوْ أَنَّ فَاطِمَةَ بِنْتَ مُحَمَّدٍ سَرَقَتْ لَقَطَعْتُ يَدَها

“ከናንተ በፊት የነበሩ ሰዎችን ያጠፋቸው ከነሱ መካከል ሃይል ያለው ሰው ሲሰርቅ ቅጣት ሳይፈጸሙበት ያልፉታል፤ ደካማ ሰው በሰረቀ ጊዜ ግን ቅጣት ይፈጽሙበታል፤ በአላህ እምላለሁ (ልጄ) ፋጡማ ቢንት ሙሃመድ ሰርቃ ብትገኝ እጇን እቆርጣት ነበር!” (ቡኻሪ ዘግበውታል)።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here