ኢስላምና ዴሞክራሲ

0
2348

አንድ አሣዛኝ እውነት አለ። ብዙሃኑ ሙስሊም ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍል ስለ ኢስላም ያለውን እምነትና ኢስላምን የሚያይበትን መነፅር የተዋሰው ከብዙሃን መገናኛው ነው። መገናኛ ብዙሃኑ ደግሞ የሠሩት መነጽር እጅግ የተዛባ ነው። በዚህ ምክንያት ሠዎች ኢስላምን ፍፁም ኋላቀር አድርገው እንዲያስቡ ተደርጓል።

በተለያዩ የአረብና ሙስሊም ብዙሃን ሐገራት የሚታየው አምባገነንትና አምባገነናዊ ሥርዓት ከህግ በላይ የሆኑ ሠዎች መበርከት የኢስላም አስተምህሮ ውጤትና የሙስሊሙ ህብረተሰብ የዲሞክራሲ ጥላቻ እንዳለው እስኪመስል ተስፋፍቶ ቆይቷል። ነገር ግን፤ Gallup (ጋሉፕ) የተባለው ዓለማቀፍ ሥመ-ጥር የጥናት ተቋም በአለም ላይ የሙስሊሙን ህብረተሰብ 80 ከመቶ በያዙት አሥር ሐገራት ባደረገው ሠፊ ጥናት ሙስሊሞች በሐይማኖት እሴቶችና በዲሞክሲያዊ አስተሣሠቦች መሠረታዊ ግንዛቤዎች መካከል ልዩነት እንደማያስተውሉ አረጋግጧል። ሙስሊሞች በሸሪዐና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መካከል ያለውን መስማማት የሚያውቁት ከኢስላም አስተምህሮ ነው። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሚገለጽባቸው ነገሮች አንዱ ምርጫ ነው። ዜጎች በራሳቸው መስፈርት ይበጀናል የሚሉትን መሪ መምረጥ እንደሚችሉ ኢስላም አስቀምጧል። ለአብነት ያህል ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ህልፈት በኋላ የሙስሊሞች መሪ የነበረው ታላቁ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረባ አቡበከር ሲዲቅ (ረ.ዐ) የተመረጠው በህዝቡ ይሁንታ ነበር። ከሱ በኋላ የመጡ መሪዎችም የህዝቡን ይሁንታ አግኝተው ነው።

ኢስላም ህዝቡ ሳይፈልገው በጉልበቱ መሪ (ኢማም) የሆነን ግለሰብ ሆነ ቡድን አይቀበልም። ለምሳሌ፡- ሠው እየጠላው ኢማም (መሪ) የሆነን ግለሰብ ረሱል (ሶ.ዐ.ወ) በአንድ ሐዲሳቸው ማወገዛቸው ለአብነት ያህል ይጠቀሣል።

በህዝቡ ይሁንታ ስልጣን የያዘ መሪም በሥልጣን ዘመኑ ህዝቡን በታማኝነት እንዲያገለግል ይገደዳል። ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) ህዝቡ በፈለገው ጊዜ ሁሉ ጆሮ በመስጠት ይታወቁ ነበር። የሳቸውን ፈለግ የተከተሉት ሰሃቦችም ይህን በማድረግ የተመሠገነ ምግባር ፈፅመዋል። በአንድ ወቅት ሁለተኛው ኸሊፋ ዑመር (ረ.ዐ) ሚንበር ላይ ወጥቶ ከአሁን በኋላ ለሴቶች የሚሠጠው መህር ከዚህ ማለፍ የለበትም ብሎ ገደብ ሲያስቀምጥ አንዲት ሴት በመቆጣት ገስጻዋለች። የሱ አዋጅም ውድቅ ሆኗል።

የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሌላኛው መገለጫ ሐሳብን የመግለጽ መብት ነው። ሠዎች በየትኛውም አጋጣሚ ሐሳባቸውን መግለጽ እንደሚችሉ የኢስላም ታሪክ ያስረዳል። ሐሳባቸውን አቅርበውም ፖለቲካዊ ውሣኔዎችን እንኳ እስከማስቀየር ደርሰዋል። በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘመን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሠሃቦች ሐሳባቸውን በማቅረብ የነብዩን ውሳኔ አስቀይረዋል፤ የጦር ስትራቴጂ አስለውጠዋል፤ ሌላም ሌላም።

የሐሳብ ልዩነትን ማቻቻል የሰዎችን ልዩነት ማክበርም የዲሞክራሲ መገለጫ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የኢስላም ምሁራንም “በተለያየንበት ጉዳይ ምክንያት እንሰጣጥ” የሚል ወርቃማ አባባል አላቸው።

በምዕራቡ ዓለም በመካከለኛው ዘመን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እጅግ ብዙ ሠዎችን በአስተሳሰባቸው ምክንያት ብቻ ስትጨፈጭፍ በመኖሯ ምክንያት ኃይማኖቶችን ሁሉ በአንድ ቅርጫት የመክተት ሁኔታ ይስተዋላል። ሆኖም፤ ይህ ኃይማኖት ኢስላም “ኃይማኖት” ከመባልም በላይ ነው። ሠዎች በመሠረቱ የሁሉም መብት ባለቤቶች ናቸው። የመሠብሠብ፣ የመደራጀት መብትን ኢስላም ካስጠበቀ 14 መቶ አመታት አልፈዋል።

የሐገር ፍቅር (Patriotism)

የሐገር ፍቅር (Patriotism) ቀደም ባሉት ጊዜያት ትርጉሙ በጦርሜዳ በከፍተኛ ጀግንነት ጠላትን መዋጋት ብቻ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ በጦርነት ወቅት ጀግንነትን መላበስ የሐገር ፍቅር መገለጫ ቢሆንም፡፡ የሐገር ፍቅር ከዚህ የሠፋ ትርጓሜ አለው፡፡ ኢስላምም ይህን ሠፊ ትርጉም ይቀበላል፡፡ አይነሥውራን መምራትና ከመንገድ ላይ አስቸጋሪ እንቅፋቶችን ማስወገድ እንኳ የዚህ አካል ነው፡፡

ሰብዓዊ መብት በኢስላም

አላህ ፍፁምና ብቸኛው የዓለም ተቆጣጣሪ፣ የሠዎች ሁሉ ጌታ በመሆኑ ለሠዎችም ሠብዓዊ ክብርና ልዕልና በመሥጠቱ እንዲሁም የራሱን መንፈስ ስለነፋበት ሠው ሁሉ በርሱ ፊት የተከበረ ነው። በመሠረቱ ምንም እንኳ በሠው ልጆች መካከል ዜግነት፣ ቀለም እና ዘር የተባሉ ጥቃቅን ልዩነቶች ቢታዩም በመሠረቱ ሁሉም መብታቸው የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ኢስላም ያምናል።

ኢስላማዊ ሥርዓት የትም ሊመሠረት ይችላል። የሥርዓቱ መገኛም መልክአ ምድራዊ ውስንነት ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን፤ አላህ ለሠው ልጆች የሠጣቸው መብትና ክብር ግን አይገደብም። ቁርኣን እነዚህን ዓለማቀፋዊ መብቶች “መሠረታዊ” ሲል ይጠራቸዋል። ሁሉም ግለሠብም በየትኛውም ሁኔታና ግዜ ቢሆን እንኳ ይህ መብቱ ሊጠበቅለት እንደሚገባ ያሰምርበታል።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ لِلَّهِ شُهَدَاءَ بِالْقِسْطِ وَلَا يَجْرِمَنَّكُمْ شَنَآنُ قَوْمٍ عَلَىٰ أَلَّا تَعْدِلُوا اعْدِلُوا هُوَ أَقْرَبُ لِلتَّقْوَىٰ وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ خَبِيرٌ بِمَا تَعْمَلُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ኹኑ። ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ። አስተካክሉ። እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው። አላህንም ፍሩ። አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።”(ሱረቱ ማኢዳ 5፤8)

የሠው ደም ክቡር ነው። በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ተገቢው ሥልጣን ካለው ፍርድ ቤት ውጭ ደሙን የማፍሠሥ መብት ያለው የለም። ይህን ህግ ተላልፎ የአንድን ሠው ህይወት የቀጠፈ ሠው መላውን የሠው ዘር እንደገደለ ይቆጠራል።

مَن قَتَلَ نَفْسًا بِغَيْرِ نَفْسٍ أَوْ فَسَادٍ فِي الْأَرْضِ فَكَأَنَّمَا قَتَلَ النَّاسَ جَمِيعًا وَمَنْ أَحْيَاهَا فَكَأَنَّمَا أَحْيَا النَّاسَ جَمِيعًا وَلَقَدْ جَاءَتْهُمْ رُسُلُنَا بِالْبَيِّنَاتِ ثُمَّ إِنَّ كَثِيرًا مِّنْهُم بَعْدَ ذَٰلِكَ فِي الْأَرْضِ لَمُسْرِفُونَ

“ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው ማለትን ጻፍን። መልክተኞቻችንም በግልጽ ተዓምራት በእርግጥ መጡዋቸው። ከዚያም ከዚህ በኋላ ከእነሱ ብዙዎቹ በምድር ላይ ወሰንን አላፊዎች ናቸው።” (ሱረቱል ማኢዳ 5፤32)

ሴቶችን፣ ህፃናቶችን፣ አዛውንቶችን፣ በሽተኞችንና ቁስለኞችን የአቅማቸውን መድከም፣ የጉልበታቸውን ማነስ ተገን አድርጎ መበደልና መጨቆን ኢስላም በምንም መሥፈርት የማይቀበለው ድርጊት ነው። የራበው ምግብ ሊቀርብለት የታረዘው ልብስ ሊለብሥ፣ የታመመው ሊታከም፣ የቆሠለ ሊጠገን ግድ መሆኑን ኢስላም ያስተምራል። ያለምንም የኃይማኖትና የአስተሳሰብ ልዩነት።

ኢስላም ሠብዓዊ መብቶች ከአላህ የተሠጡ መሆናቸውን ያምናል። እነዚህ መብቶች በነገሥታት በጎ ፍቃድ፣ በህግ አውጪው ደግነት የተሠጡ አይደሉም። ስለሆነም፤ ሠብዓዊ መብቶች በምንም መልኩ በማንም ሊነጠቁ አይችሉም። እነዚህ ሠብዓዊ መብቶች በተግባር መታየት የሚገባቸው እንጂ እንደብዙዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌዎች ወይም እንደ ተራ ፍልሥፍና የወረቀት ላይ ነበር ሆነው መቅረት የላባቸውም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here