ፍትህ – ትክክለኛ ትርጉሙና ትግበራው

0
9339

ፍትህ ሲጠፋ ምን ሊከሠት እንደሚችል እንጠያየቅ … አዎን ፍትህ ሲጠፋ በደል ይበዛል፤ ጠንካራው ጉልበት የሌለውን ይበላል፤ ሀይል ያለው የደካማውን መብት ይነጥቃል፤ አሸናፊው የተሸናፊውን ደም ያፈሣል፤ ገዠ የተገዠውን ሀቅ ያድበሰብሣል።

ከዚህ ሁሉ የጦርነት ምስቅልቅል መውጣት የሚቻለው ፍትህን በማስፈን ብቻ መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም።

ለመሆኑ ፍትህ ማለት ምን ማለት ነው? አይነቱስ?

የአሜሪካ ፍትህ

እስቲ የፍትህን ትርጉም ከመግለፃችን በፊት የመገናኛ ብዙሃን በሰፊው ስለሚያወሩለትና ዘወትር ለዓለማችን አማራጭ ሆኖ ስለሚቀርበው ፍትህ እንመልከት፣-

በኒውዮርክ ከተማ በአንድ መናፈሻ ውስጥ ሲዘዋወር የነበረ አንድ ሰው አንድ ውሻ አንዲት ወጣት ሴት ሲያጠቃ ይመለከታል። ወዲያው ወደቦታው በመሮጥ ከውሻው ጋር ተፋልሞ ውሻውን በመግደል የልጅቷን ህይወት ያተርፋል። በወቅቱ በአካባቢው የነበር አንድ ፖሊስ ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተል ነበር። ፖሊሱ ወደሰውዬው በመምጣት “አንተ እውነትም ጀግና ነህ” በማለት አድናቆቱን ከገለፀለት በኋላ ነገ ያንተ ዜና በጋዜጣ ላይ “አንድ የኒውዮርክ ነዋሪ ጀግና ሰውዬ የአንዲትን ወጣት ህይወት አዳነ” በሚል አርእስት ስር ይወጣል” አለው። ሰውዬው ግን “እኔ እኮ የኒውዮርክ ሰው አይደለሁም” አለው

ፖሊሱም ግድ የለም እንግዲያውስ “አንድ አሜሪካዊ በሚለው እናወጣለን” አለው

ሰውዬውም “እኔ አሜሪካዊም አይደለሁም” አለ

ፖሊሱ በመገረም “እንግዲያውስ ከየት ነህ” ይለዋል

ሰውዬዉም “እኔ ፓኪስታናዊ ነኝ” አለ

በሚቀጥለዉ ቀን ጋዜጣው ይዞ የወጣው ዜና እንዲህ የሚል ነበር “አንድ አክራሪ ሙስሊም ያለምንም ጥፋት አንድ አሜሪካዊ ውሻ ገደለ”

እንጊዲያውስ እነሱ የሚኩራሩበት ፍትህ ምን እንደሚመስል አየን። ቀጥሎ ደግሞ ትክክለኛ ፍትህ ምን ማለት እንደሆነ ለማየት እንሞክራለን።

ትክክለኛና እውነተኛ ፍትህ

የትክክለኛ ፍትህ እውነታና ትርጉሙ በሦስት ነገሮች ላይ የቆመ ነው:-

إعطاء كل ذي حق حقه، وإن خيرًا فخير، وإن شرًّا فشر، ومن غير تفريق بين أحد

ለያንዳንዱ የሀቅ ባለቤት ሀቁን መስጠት፤ ጥሩም ከሆነ ጥሩውን፤ መጥፎም ከሆነ መጥፎውን። ይህም አንዱን ከሌላኛ ሣይለዩ ያለምንም አድልዎ መሆን ይኖርበታል።

ኢስላማዊ ፍትህ ስንል ትክክለኛ አገላለፁ ከላይ የተመለከተው ነው ። ትንታኔውም በማህበረሰቡ ውስጥ ስለ ትርጉሙ መጥፎ ገፅታ እንዲጠፋ ያስችላል ። ከነኚህ ሦስት መሠረታዊ የፍትህ ማእዘናት ውስጥ ከቸልተኝነት የተነሣ አንዱ እንኳን የተጓደለ እንደሆነ በትክክለኛው ፍትህ ውስጥ ክፍተት ይፈፀማል ። እነኚህ ሦስቱ ነገሮች የተያያዙ ናቸው። ለምሣሌ- መጥፎ ክፍያውን አሊያም ቅጣት የሚገባውን ሆነ ብሎ በመዝለል ለያንዳንዱ የሀቅ ባለቤት ጥሩ ነገር የሚገባውን ብቻ መስጠት ተገቢ አይደለም ። በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩም ይሁን መጥፎ ለያንዳንዱ ሰው የድርሻውን የመስጠቱ ነገር እንዳለ ሆኖ ትላልቅ አሊያም የተከበሩ የሚባሉ ሰዎችን በመተው አንዳንድ ነገሮችን በደካሞችና በድሆች ላይ ብቻ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ አይደለም። በእስልምና ህግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል ነው ። በመብት ባለቤቶች መካከልም አድልዎ ማድረግ የተከለከለ ነው።

ፍትህ ሁልጊዜም ያስፈልገናል ። አላህ መልእክተኞችን የላከውና መፃህፍትን ያወረደው ፍትህን በምድር ላይ ሊያፀና ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

لَقَدْ أَرْسَلْنَا رُسُلَنَا بِالْبَيِّنَاتِ وَأَنزَلْنَا مَعَهُمُ الْكِتَابَ وَالْمِيزَانَ لِيَقُومَ النَّاسُ بِالْقِسْطِ [٥٧:٢٥]

“መልእክተኞችን በግልፅ ማስረጃዎች በርግጥ ላክን፤ ሰዎችም በፍትህ ይቆሙ ዘንድ መፅሃፍትንና ሚዛንን ወደነርሱ አወረድን” (አል ሀዲድ:-25 )

አላህ ፍትህን በሚዛን አመሣስሎታል። ሚዛን በራሱ አይሰርቅምና። ስህተት ቢፈጠር እንኳ ጉድለቱን ያስከተሉበት ሰዎች እንጂ ስህተቱ የሱ ሆኖ አይደለም።ሰዎች መብታቸውን ሲነጠቁ ይከፋቸዋል። ትክክለኛ ፍትህ ማህበረሰቡን ከጥፋት ያድናል። ሁሉም የሸሪዓ መንገዶች ከፍትህ ባህሪ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ማወቅ አለብን ። የአስተዳደር ሥራ ፣ የዳኝነት ህግ፣ የፍርድ አፈፃፀም፣ የቤተሰብ ሀላፊነት፣የኢኮኖሚ ሥርኣት፣የማህበረሰብ አኗኗር፣ የሥነምግባር … እነኚህ ሁሉ ከፍትህ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ፍትህ እንዴት ይረጋገጣል ?

1.በዱኒያ ላይ ፍትሃዊነት

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ ፡-

لَقَدْ أَرْسَلْنَا رُسُلَنَا بِالْبَيِّنَاتِ وَأَنزَلْنَا مَعَهُمُ الْكِتَابَ وَالْمِيزَانَ لِيَقُومَ النَّاسُ بِالْقِسْطِ [٥٧:٢٥]

“መልእክተኞችን በግልፅ ማስረጃዎች በርግጥ ላክን፤ ሰዎችም በፍትህ ይቆሙ ዘንድ መፅሃፍትንና ሚዛንን ወደነርሱ አወረድን” (አል ሀዲድ:- 25)

ከሰዎች ላይ በደልን እንዲያነሱ፤ ጉዳቱን እንዲያስቆሙ እንዲሁም ፍትህን ያስፋፉ ዘንድ ነቢያትና የአላህ መልእክተኞች በየዘመናቱ ተልከዋል። ይህም የሆነው ወንጀል በምድር ላይ በተፀፈመው የመጀመሪያው ወንጀልና በፍጥረተ ዓለሙ ቀደምት በሆነውና ንፁሁን የሰው ልጅ ህይወት በቀጠፈው ሀጢኣት ይብቃ ለማለት ነው።

2.በአኺራ ፍትህ

እሱም አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለእለተ ትንሣኤ ቃል የገባውና ሀላፊነቱን ለራሱ የወሰደው ነው። በደለኛ በሠራው ወንጀል በቅርቢቱ ዓለም ያመለጠ ቢሆንም እንኳ ነገ ከመቀጣት አያመልጥም፤ አላህ ያቆይ ቢሆን እንጂ ነገሮችን አይረሣም፤ በመሆኑም ለበደለኛ ቀጠሮ ተይዞለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ከፍትህ አድራጊ ሰው የሚጓደል ምንም ነገር የለም። አላህ ይህ ሰው ሁኔታዎችን መቻሉና በመልካም ትእግስቱ ያዘጋጀለት ድግስ አለ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَنَضَعُ الْمَوَازِينَ الْقِسْطَ لِيَوْمِ الْقِيَامَةِ فَلَا تُظْلَمُ نَفْسٌ شَيْئًا وَإِن كَانَ مِثْقَالَ حَبَّةٍ مِّنْ خَرْدَلٍ أَتَيْنَا بِهَا وَكَفَىٰ بِنَا حَاسِبِينَ [٢١:٤٧]

“በትንሣኤ ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን፡ ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም” (አል አንቢያእ:-47)

3.በተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ፍትህ

ይህም ሁሉን አቀፍ የሆነ ፍትህ ነው ። በዚህ ሥር ሁሉም ፍጥረታት የሚካተቱ ሲሆን የሰው ልጅም ሃይማኖቱ ፣ አመለካከቱ ፣ ባላንጣውና ጠላቱ የተለያየ ከመሆኑ ጋር በዚህ ፍትህ ሥር ይጠቃለላል ። ሱረቱ አልማኢዳህ ቁጥር 8 ላይ የተገለፀውም ይህንኑ አመላካች ነው ።

كُونُوا قَوَّامِينَ لِلَّهِ شُهَدَاءَ بِالْقِسْطِ وَلَا يَجْرِمَنَّكُمْ شَنَآنُ قَوْمٍ عَلَىٰ أَلَّا تَعْدِلُوا [٥:٨]

“ለአላህ ቀጥተኞች መስካሪዎች ሁኑ። ህዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ” (አል ማኢዳህ:-፡ 8)

እንስሣትም በዚህ ዓይነቱ ፍትህ ሥር ይካተታሉ። እስልምና በየትኛውም መልኩ ሊሆን ይችላል…በማሰር፣ በመደብደብ፣ በማስራብ ወይንም ከአቅማቸው በላይ የሆነ ከባድ ሸክም በመጫን እንስሣት እንዳይበደሉ አፅድቋል፤ አዟልም። ሙስሊሞች ሁሉ ባሠረችው ድመት የተነሣ እሣት ስለገባችው አማኝ ሴትዮና የተጠማ ውሻ አጠጥታ ከሞት በማትረፏ ምክኒያት ጀነት ስለገባችው ሴትኛ አዳሪ ታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የድመቷ ሴቲዮ ድመቷን ብታስርም በታሰረችበት ሁኔታ ላይ ምግብም ሆነ መጠጥ አትሠጣትም ነበር። ወጥታ የሚታደን ትፈልግ ዘንድም እድሉን አልሠጠቻትም። በውሻ ምክኒያት ጀነት የገባችው ሴትኛ አዳሪ ውሻውን ‘ነጃሣ ነው’ ብላ አልተጠየፈችውም። መጠማቱን አይታ ለፍጥረቱ በማዘኗ አዛኙ ጌታ አዘነላትና ጀነት አስገባት። ፍጥረተ ዓለሙ በመላ በፍትህ ላይ የቆመ ነው። ፀሐይ ጨረቃን አትቀድምም፤ ለሊቱ ቀኑን አይሽቀዳደምም፤ የሰው ልጅ ውስጣዊ አፈጣጠሩና ስሪቱ እንዲሁም ምላሽ አሠጣጡ አንዱ ከሌላኛው በማይጋጭበት መልኩ በፍትህ ላይ የቆመ ነው።

ለሰው ብቻ የሆነ ፍትህ ስንል- አንድ ሰው ከነፍሱ፣ ከሌሎች ሰዎች፣ አሊያም ከመንግስት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ይመለከታል። ከራስ ጋር ፍትሃዊ መሆን ሲባል አእምሮን እንዲያገናዝብና እንዲያመዛዝን በማድረግ በቁጣም ሆነ በስሜት ወቅት ፍትሃዊ መሆንን ነው። ያ ፍትሃዊነትም ምንጩ ከአንዳች ነገር የሚነሣ አካላዊ አሊያም ከውጭ ተፅእኖ ከእውቀት፣ ከግንዛቤና ነገሮችን ከመረዳትና ከመሣሠሉት የሚመጣ ሊሆን ይችላል። ከነፍስ ጋር ፍትሃዊነት በብዙ ቦታዎች ላይ ጎልቶና በተለያየ ሁኔታም ሊታይ ይችላል… ለዚህም በሥጋና መንፈስ ፍላጎት፣ በአእምሮና በአስተሣሰብ፣ በሥራና በእረፍት፤ በመስጠትና በመቀበል መካከል ማመዛዘንና ፍትሃዊ ማድረግ ተጠቃሽ ምሣሌዎች ናቸው።

ከሰዎች ጋር ፍትህ ስንል ደግሞ- መብትና ግዴታዎችን በትክክል ለይቶ በማወቅና በመተግበሩ ረገድ ሚዛናዊ መሆንን ይመለከታል። ይህም በግዠና በሽያጭ፤ በፍርድና በዳኝነት፤ በአደራና በምስክርነት፤ በመስጠትና በመከልከል … በመሣሠሉት ላይ ሁሉ ወቅት ፍትህ ማድረግን ነው። ይህም ሲባል ከቅርብ እስከ ሩቅ ያሉትን ሰዎች ባል ይሁን እናት አባት አሊያም የሀገሪቱ አስተዳዳሪ ጭምር ያጠቃልላል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ :-

إِنَّ اللَّهَ يَأْمُرُكُمْ أَن تُؤَدُّوا الْأَمَانَاتِ إِلَىٰ أَهْلِهَا وَإِذَا حَكَمْتُم بَيْنَ النَّاسِ أَن تَحْكُمُوا بِالْعَدْلِ [٤:٥٨]

“አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድትመልሱ ያዛችኋል በሰዎች መካከልም በምትፈርዱበት ጊዜ በትክክል እንድትፈርዱ”(አንኒሣእ:- 58)

ከመንግስት አንፃር ፍትህ ማለት- በማህበረሰቡ መካከል እርጋታና ደህንነት እንዲሰፍን መሥራት፤ በሥራና በምርት ሂደት ተሣትፎ በማድረግ የህዝቡ ገቢ ከፍ ይል ዘንድ በማህበረሰቡ መካከል ታማኝ በመሆን ልማትና ብልፅግናን ማስገኘት ነው። ኢብኑ ኸልዱን እንዲህ ይላል

اعلم أن العدوان على الناس في أموالهم ذاهب بآمالهم في تحصيلها واكتسابها، لما يرونه حينئذ من أن غايتها ومصيرها انتهابها بين أيديهم، وعلى قدر الاعتداء ونسبته يكون انقباض الرعايا عن السعي في الاكتساب والعمران

“በሰዎች ሀብትና ንብረት ላይ ድንበር ማለፍ ሀብትን ለማግኘትና ለማፍራት የሚያደርጉትን የተስፋ ሩጫ ማጨለም ነው። ምክኒያቱም ያኔ የሚያሰላስሉት ነገር ቢኖር የሀብታቸው የመጨረሻ እጣ ፈንታ ከእጃቸው ሲቀማ ማየት ነውና። በበደሉ ልክና ደረጃም ሰዎች ለሥራና ለልማት የመነሣሣታቸው ጉዳይ ይቀዛቀዛል።”

ለዚህም ነው ዛሬ ከቅኝ አገዛዝ፣ ከፅዮናዊነት እንዲሁም ከአምባገነን መሪዎች አንፃር ግፍና በደል እንዲነሣላቸው አደባባይ የወጡ ህዝባዊ ተቃውሞዎችንና አብዮቶችን በየሀገራቱ የምናየው። ይህ ተጨባጭ ክስተት በዋናነት የሚያመላክተን ነገር ቢኖር የፍትህ መጥፋት ሊያስከትል የሚችለውን የህዝብ ማእበል ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here