ቁርኣን በጣም ግልፅ በሆነ ሁኔታ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሰው ልጆች የመጨረሻ ፍፃሜና አጠቃላይ ታሪካቸው ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር እንዳለ ይነግረናል። የታሪክን ሂደት መለስ ብለን ብንመለከት ገለልተኛ እና ፍፁም በሆነ መልኩ የፀዳ ሆኖ አናገኝም።
በዚህም አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በምድር ላይ ሣሉ ጥሩ የሠሩትን ሊመነዳና መጥፎ የሠሩትን ደግሞ ሊቀጣ ቃል ገብቷል። ለያንዳንዱ የሰው ልጅም ከፊት ለፊት የሚጠብቀዉ ታላቅ የፍርድ ቀን አለለት። እስከዚያው ግን በዓለም ላይ ያሉ ሀገራትም ሆኑ ህዝቦች በአላህ ፈቃድና ፍትህ ላይ ተመስርተው ይወድቃሉ ይነሣሉም።
አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ በማለት ይመክረናል ፡-
“ሰማይንም አጓናት፤ ትክክለኛነትንም ደነገገ። መመዘንንም በትክክል መዝኑ፤ ተመዛኙንም አታጓድሉ።” ( አል ረህማን፤7 -9 )
በሌላ የቁርኣን አንቀፅም እንዲህ አለ
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትህ) ቋሚዎች በነፍሦቻችሁ ወይም በወላጆቻችሁና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢሆንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ሁኑ። ሀብታም ወይም ደሃ ቢሆን አላህ (በነርሱ) ከናንተ ይበልጥ ተገቢ ነዉ። እንዳታደሉም ዝንባሌን አትከተሉ። ብታጣምሙም ወይም (መመስከርን) ብትተዉ አላህ በምትሠሩት ነገር ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነው።” ( አን ኒሣእ 4፤135)
ፍትህ በዐረብኛ “ዐድል/ቂስጥ” የምንለው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከሰው ልጆች በእጅጉ የሚፈልገው ነገር ነው። የሰው ልጆች ሁሉ በግላዊም ሆነ በማህበራዊ ህይወታቸው ወቅት በፍትህ ይሠሩ ዘንድ አላህ አዟል። በመሆኑም ግለሰቦችም ሆኑ ሀገራት የሌሎችን መብት ማክበርና እውቅና መስጠት ግድ ይላቸዋል። የፍትህ ተቃራኒው ጭቆና ነው። ፍትህ በትክክል ያልተሠራበት እንደሆነ ጭቆና በቅርብም ይሁን በሩቅ ጊዜ ውስጥ ብቅ ማለቱ አይቀርም።
ሰዎች ከፍትህ ጎዳና ያፈነገጡ እንደሆነ አላህ እንዲመለሱና መንገዳቸውንም ያስተካክሉ ዘንድ እድሎችን እንደሚሠጣቸው በቁርኣን ውስጥ በተደጋጋሚ ቦታዎች ላይ እናነባለን። ነገር ግን ሰዎች ትእቢተኞች ሲሆኑና ደግመው ደጋግመው ባስታወሷቸው ቁጥርም ባህሪያቸው የማይሻሻል ከሆነ የአላህ ቁጣና ቅጣት ይወርድባቸዋል። ከዚህ በፊት የነበሩ ህዝቦችም በአላህ ቅጣት የጠፉት ኢፍትሃዊነትንና ጭቆናን ያራምዱ ስለነበረ ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል
“ጌታህም በጣም መሀሪውና የእዝነት ባለቤቱ ነው። (ሰዎች) በሠሩት ሥራ ቢይዛቸው ኖሮ ቅጣቱን ለነሱ ባስቸኮለባቸው ነበር። ግን ለነሱ ከሱ ሌላ መጠጊያን ፈፅሞ የማያገኙበት ቀጠሮ አላቸው። እነዚህ ከተሞችም በበደሉ ጊዜ አጠፋናቸው። ለመጥፊያቸውም የተወሠነ ጊዜ አደረግን።” (አል ከህፍ 18፤58-59)
በሌላም የቀርኣን አንቀፅ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል
“የጌታህም ቅጣት የከተሞችን ሰዎች እነሱ በዳዮች ሲሆኑ በቀጣቸው ጊዜ እንደዚህ ነው፤ ቅጣቱ በርግጥ አሣማሚ ብርቱ ነው።”(ሁድ፤102 )
“በዳይ ከነበረች ከተማ ያጠፋናትና ከኋላዋም ሌሎችን ህዝቦች ያስገኘነው ብዙ ናት። ቅጣታችንም በተሠማቸው ጊዜ እነርሱ ወዲያውኑ (ከርሷ) ለመሸሽ ይገሠግሣሉ። አትገስግሱ ትለመኑም ይሆናልና በርሱ ወደ ተቀማጠላችሁበት ፀጋ ወደ መኖሪያዎቻችሁ ተመለሱ (ይባላሉ)። ዋ ጥፋታችን! እኛ በርግጥ በዳዮች ነበርን ይላሉ። የታጨዱ ሬሣዎችም እስካደረግናቸው ድረስ ይህች ጥሪያቸው ከመሆን አልተወገደችም።” (አል-አንቢያእ 21፤ 11-15)
ህዝቦች ፍትሃዊ የሆኑ መሪዎችን የመምረጥ ግዴታ አለባቸው። ከመረጡም በኋላ መሪዎቻቸውን ማክበርና ማመን ይገባቸዋል። ነገር ግን በጥንቃቄ ሊከታተሏቸውና ሊያስተካክሏቸው ጥፋታቸው የበዛ እንደሆነም በነሱ ቦታ ሌላ መተካት ይኖርባቸዋል። ካልሆነ መጥፎ መሪዎች በህዝቡ ላይ የእርግማን መንስኤ ይሆናሉ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ፡-
“ወደነዚያ የአላህን ፀጋ በክህደት ወደለወጡት ህዝቦቻቸውንም በጥፋት አገር ወዳሰፈሩት አላየህምን? (አገሪቱም) የሚገቧት ስትሆን ገሀነም ናት፤ ምን ትከፋም መርጊያ!” (ኢብራሂም 14፤28-29)
አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የተወሰኑ ህዝቦችን መቅጣት ሲፈልግ በፈለገው መንገድና መልኩ ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ የተወሰኑ መጥፎ ሠሪ ቡድኖችን በሌሎች መጥፎ ቡድኖች ይቀጣል (አንዱን በሌላኛው ላይ ያነሣሣል)። የኢስራኤል ህዝቦች መጥፎ በሰሩ ጊዜ አላህ ናቡሻድኑዛርንና የባቢሎናውያንን መንጋ ላከባቸው። በዚህም ለቅጣቱ መሳሪያው አደረጋቸው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“ከሁለቱ (ጊዜያቶች) የመጀመሪያይቱ ቀጠሮ በመጣችም ጊዜ ለኛ የሆኑ ባሮች የብርቱ ሀይል ባለቤቶች የሆኑትን በናንተ ላይ እንልካለን፤ በቤቶችም መካከል ይመላለሣሉ (ይበረብሩታል)፤ (ይህ) ተፈፃሚ ቀጠሮም ነበር።” (አል-ኢስራዕ 17፤5 )
በሱረቱ አል-አንዓም ላይም
“እንዲሁ የበደለኞችን ከፊል በከፊሉ ላይ ይሠሩት በነበረ ጥፋት እንሾማለን።” ብሏል (አል-አንዓም፤129)
ልንወስዳቸው የሚገቡ ትምህርቶች
ዛሬ በዓለማችን ላይ እየተከሠቱ ካሉት ነገሮ እኛ ሙስሊሞች ብዙ ትምህርት እናገኝበታለን፡-
- በዋናነት ፍትህ እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ነው። ፍትህ ደህንነትን፣ ዋስትናንና ብልፅግናን ያመጣል። በመሆኑም ኢፍትሃዊ መሆን አሊያም ሰውን መበደል የለብንም። ኢፍትሃዊነት የአላህን ቁጣ ሊያወርድብን ይችላልና።
- መሪዎች ሀላፊነት በተሞላበት መልኩ መሥራት ይኖርባቸዋል። ዛሬ በቱኒዚያ፣ በግብፅ፣ በሊቢያና በየመን የሆነውና በሶሪያና እየሆነ ያለው ነገር ለበርካታ መሪዎች ትልቅ ትምህርት ሊሆን ይገባል።
- ዛሬ በዓለም ላይ ያሉ ሙስሊሞች በተሾሙባቸው መጥፎ መሪዎችና እንዲሁም እርስ በርሣቸው ተግባብተው መሥራት ባለመቻላቸው ምክኒያት ስቃይ ውሠጥ ናቸው። በፍትሃዊ መሪ ሥር የሚፈጠር አንድነት ጥንካሬንና እድገትን ያስገኛል።
- ኢፍትሃዊ መሆን ለግለሰብም ሆነ ለሀገር አደጋ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። መተናነስና በመንፈስም ሆነ በሞራል ረገድ እራሳችንን ማሻሻል ይኖርብናል።
- ሥልጣንና ሀይል ያላቸው ሰዎች ሥልጣን እንደ ሁለት ስለታማ ጫፍ ሰይፍ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም። በትክክል ያልተገለገሉበት እንደሆነ መልሦ የሥልጣን ባለቤቱን መጉዳቱ አይቀርም።
- ለጥፋታችንና ስህተታች ሁሉ ይቅር እንዲለን ልባዊ በሆነ መልኩ ወደ አላህ መመለስ ይኖርብናል። ቀጥተኛውን መንገድ እንዲመራንና በዚህች ምድር ላይ ፍትህንና ሠላምን እንዲሠጠን መለመን ይኖርብናል።