ሠብዓዊ መብቶች- ኢስላማዊ እይታ

0
4217

ኢስላም “መቃሲድ አሸሪዐ” (የሸሪዐ ግቦች) በማለት ያስቀመጣቸው አምስት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች የሠው ልጆችን መሠረታዊ ጉዳይ ለማክበርና

ለማስከበር እንደ ዋነኛ መንደርደሪያ ያገለግላሉ። በዚህ አነስተኛ ጽሁፍ የተወሰኑት ኢስላማዊ የሠብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እይታዎች በአጭሩ ሠፍረዋል።

1. የህይወትና የንብረት ጥበቃ ነፃነት

ነብዩ /ሰ.ዐ.ወ/ በመጨረሻው የሐጅ ንግግራቸው

“ህይወታችሁና ንብረታችሁ በእናንተ ዘንድ ጌታችሁን እስክትገናኙ (የማይደፈሩ) የተከለከሉ ናቸው።” በማለት ተናዝዘዋል።

በሌላ ሐዲስ፤

“በሙስሊም ሀገር ውስጥ በስምምነት የሚኖርን ሙስሊም ያልሆነ ሠው የገደለ ሠው የጀነትን ሽታ አያገኝም።” ሲሉ ተናግረዋል።

2. ክብር መጠበቅ

ሙስሊም ሊቃውንት እንደሚሉት ከሸሪዓ ዓላማዎች አንዱ የሠውን ክብር ማስጠበቅ ነው። ቁርኣንም የሠዎች ክብር እንዳያንስ አጥብቆ ያስጠነቅቃል።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا يَسْخَرْ قَوْمٌ مِّن قَوْمٍ عَسَىٰ أَن يَكُونُوا خَيْرًا مِّنْهُمْ وَلَا نِسَاءٌ مِّن نِّسَاءٍ عَسَىٰ أَن يَكُنَّ خَيْرًا مِّنْهُنَّ وَلَا تَلْمِزُوا أَنفُسَكُمْ وَلَا تَنَابَزُوا بِالْأَلْقَابِ بِئْسَ الِاسْمُ الْفُسُوقُ بَعْدَ الْإِيمَانِ وَمَن لَّمْ يَتُبْ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الظَّالِمُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወንዶች ከወንዶች አይቀልዱ። ከእነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና። ሴቶችም ከሴቶች (አይሳለቁ)። ከእነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና። ነፍሶቻችሁንም አታነውሩ። በመጥፎ ስሞችም አትጠራሩ። ከእምነት በኋላ የማመጽ ስም ከፋ። ያልተጸጸተም ሰው እነዚያ እነርሱ በዳዮቹ ናቸው።” (ሱረቱል ሀጁራት 49፤11)

ከዚህ በተጨማሪ ቁርአን ሠዎችን በግል ሕይወታቸው ገብተን እንዳንሠልላቸው (privacy እንድንጠብቅ) ያዘናል።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اجْتَنِبُوا كَثِيرًا مِّنَ الظَّنِّ إِنَّ بَعْضَ الظَّنِّ إِثْمٌ وَلَا تَجَسَّسُوا وَلَا يَغْتَب بَّعْضُكُم بَعْضًا أَيُحِبُّ أَحَدُكُمْ أَن يَأْكُلَ لَحْمَ أَخِيهِ مَيْتًا فَكَرِهْتُمُوهُ وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ تَوَّابٌ رَّحِيمٌ 

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከጥርጣሬ ብዙውን ራቁ፤ ከጥርጣሬ ከፊሉ ኃጢአት ነውና። ነውርንም አትከታተሉ። ከፊላችሁም ከፊሉን አይማ። አንደኛችሁ የወንድሙን ስጋ የሞተ ኾኖ ሊበላው ይወዳልን? (መብላቱን) ጠላችሁትም፤ (ሐሜቱንም ጥሉት)። አላህንም ፍሩ። አላህ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና።” (ሱረቱል ሀጁራት 49፤12)

3. በፍትህ መተዳደር

ኢስላም የሚያስተምረን ሥልጣን ከአላህ የተሠጠ የአደራ ንብረት መሆኑን ነው። ስለሆነም፤ አላህን የፈሩ ሠዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡና በትክክለኛው መንገድ ይወጣሉ። ለዚህ የመጀመሪያው የኢስላም ኸሊፋ ጥሩ ምሳሌ ነው። አቡበከር ገና ሥልጣኑን እንደተረከበ የሚከተለውን ተናግሯል፡- “ትክክል ስሆን ተከተሉኝ፤ ስሳሳት አርሙኝ።”

4. ሐሳብን የመግለፅ ነጻነት

ኢስላም በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት እስካልፈጠረና የሌሎችን ክብር እስካልነካ ድረስ በነፃነት የማሠብም ሆነ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ሙሉ መብትን አጎናፅፏል። ሐሳብን በመግለጽ ስም ግን የሌሎችን ክብርና ሞራል የሚነካ አገላለጽ ክልክል ነው። ከዚህ ውጭ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ጉዳይ ከመሠረቱ የተፈቀደ ተግባር ነው። ኃይማኖታዊ በሆኑ ጎዳዮች እንኳ ነብዩ የወረደላቸው ወህይ (ራዕይ) ከሌለ ሠሃቦች የራሳቸውን የመናገርና የማሠብ ነፃነታቸው የተጠበቀ ነበር።

5. የመሠብሠብ ነፃነት

በኢስላም፤ የፈለጉት አይነት ዓላማ ያለው ነገር ሥነ-ምግባራዊ እይታው ኢ-ሰብዓዊ ያልሆነ ማንኛውም አይነት ስብስብ የተፈቀደ ነው።

6. የህሊና ነፃነት

ቁርአን “በኃይማኖት ማስገደድ የለም።” ይላል። በተለያየ አጋጣሚ የምናስተውለው ግን በተለያዩ ሰበብ አስባቦች ሠዎች ህሊናቸው ለባርነት ሲዳረግ ነው። ከሸሪዓ አላማዎች አንዱ “ሒፍዘል ዐቅል” (አዕምሮን መጠበቅ) ነው። አዕምሮን (ህሊናን) መጫን በራሱ ባርነት ነው።

7. የሃይማኖት ነጻነት

የሃይማኖት ነፃነት ከህሊና ነፃነት ጋር ጥልቅ ቁርኝነት አለው። ይህን በተመለከተም ኢስላም ሠዎች በኃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ መብት እንዳላቸውና ምርጫው የራሣቸው እንደሆነ ያስገነዝባል።

أَلَّا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ

“(እርሱም ኃጢያት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢኣት አትሸከምም።” (አነጅም 53፤38)

8. በህግ ፊት አኩል ስለመሆን

ኢስላም ሁሉም ሠዎች በህግ ፊት ፍፁም እኩል መሆናቸውን ያስተምራል። ይህን በተመለከተ “መሪዎች ከተራው ዜጋ የተለየ ክብር ሊሠጣቸው አይገባም” ሲልም አጥብቆ ይሞግታል። እንደ ኃይማኖታችን የፍትህ ግንዛቤ ማንም ሰው ህግ ፊት ከማንም አይበልጥም፤ ከማንም አያንስምም። ይህን ለማብራራት ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ህይወት አንድ ታሪክ እንምዘዝ፤

አንድ ወቅት የተከበሩ ቤተሠቦች አባል የሆነች አንዲት ሴት በስርቆት ወንጀል ተጠርጥራ ቀረበች። ወንጀለኛነቷም በህግ ተረጋገጠ። በዚህም ምክንያት ህጉ ተፈፃሚ ሊሆንባት ሆነ። ይሄኔ ግን ቤተ-ዘመዶቿ ነብዩን ለማግባባት ሞከሩ፤ አልተሣካላቸውም። እነሱም ተስፋ ባለመቁረጥ ነብዩን በሚቀርቡ ሠዎች ሽምግልና ላኩ። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ግን፤ እንዲህ በማለት ታሪካዊ ንግግር አደረጉ።

“ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ። የሰረቀችው ልጄ ፋጢማ ቢንት ሙሐመድ ብትሆን ኖሮ እንኳ እጇን በመቁረጥ ህጉን ከመፈፀም ወደ ኋላ አልልም ነበር።”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here