የወለድ ጉድፎች:- እስላማዊ ምላሽ (ክፍል 3)

0
2929

ወለድን በተመለከተ ለሚፈጠረው ችግር ኢስላማዊው መፍትሄ በሁለት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

አንደኛ፡- አንድ ሠው ሌላን ሠው ገንዘብ ሊያበድረው ከፈለገ ብድሩ መመስረት ያለበት በ “ወንድማዊነት መርህ” ላይ ነው። በዚህ ዓይነት የብድር ስርዐት ወለድን የብድሩ አካል ማድረግ ክልክል ነው።

አንድ ግለሰብን ለመርዳት በሚል ሰበብ ከተበደረው ገንዘብ በላይ ተዋልዶና ተከምሮ የብድር ክፍያ አዙሪት ውስጥ መክተት ሰውየውን የሚረዳና የሚጠቅም አይደለም።

ይህ “እስላማዊ” መርህ በግለሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህ ማሠሪያም ጭምር ነው። ዛሬ ይሄ መርህ የእውነት ቢተገበር ኖሮ ሐገራት ለሌሎች ሐገራት የእውነት እርዳታ በለገሱ ነበር። አሁን የሚታየው ግን ብድር እየሰጡ የማይወጡበት የዕዳ ማጥ ውስጥ በመክተት ጥገኞች ማድረግ ነው።

ሁለተኛ፡- አንድ ሰው ገንዘቡን አውጥቶ በመሥራት ትርፍ ለማግኘት ከፈለገ ኪሳራ ሊገጥመው ይችላልና ገንዘቡን የመክሰር አደጋ ውስጥ ከትቶ ነው። በሌላ አገላለጽ ማንም ሠው ገንዘቡ የፈለገው አይነት “ቆንጆ” ኢንቨስትመንት ላይ ይዋል፣ አስቀድሞ ይህን ያህል አተርፋለሁ ብሎ (ለዚያውም በየአመቱ የሚራባና የሚዋለድ) መናገር ግን አይችልም። ስለዚህ፤ ገንዘቡን የመክሰር አደጋ ውስጥ የከተተ ሠው ትርፍ ሲገኝም ከትርፉ የመካፈል፣ ኪሳራ ከመጣም ከኪሳራው የድርሻውን መካፈል አለበት። ይሄ አይነቱ ስርዐት ፍትሕ ላይ የተመሰረተ ነው። ብዙ ትርፍ ያለው ስርዐትም ይኸው አይነት ስርዐት ነው።

ኢንቨስት የሚያደርግ ሠው የኢንቨስትመንቱን ውጤታማነት ቢከታተል አይደንቅም። ኢንቨስት ሲያደርግም (ሲያበድርም) ምን ውጤት እንደሚያስከትል አስቦ ነው። ከኢንቨስትመንቱ ሁሌ የማያቋርጥ ትርፍ (ወለድ) መጠየቅ ኢ-ፍትሃዊነት ነው።

ኢስላማዊ የባንክ አሠራር

ኢስላማዊው መፍትሄ ለግለሰቦች እንዲሁም ለማህበረሰቡም በጠቅላላ ያገለግላል። ባንኮችም በሰዎችና በተቋማት መካከል ያለውን የፋይናንስ ልውውጥ አገናኝ ድልድዮች ናቸው። ባንኮች፣ ከሚጠቀመው በላይ ገንዘብ ያለውና መቆጠብ ከሚፈልግ ሰው ገንዘብ ተቀብለው ለኢንቨስትመት ገንዘብ ለሚያስፈልገው በብድር መልክ ይሰጡታል። በዚህ መልክ ለሚደረግ ሥራ ደግሞ የግድ ወለድ መኖር አለበት አይባልም። በኢስላማዊ የባንክ ስርዐት፤ ባንኩ እና ባለ ድርሻዎቹ (ገንዘብ አስቀማጮቹ) እንዲሁ ከማበደር ይልቅ ኢንቨስት ያደርጋሉ። የሚያበድሩት ገንዘብ የመክሠር አደጋ ሊያገጥመው ይችላል። እንዲሁም፤ ትርፍ ሊኖርም ይችላል። ስለዚህ፤ አስቀማጮቹም በሚገባቸው የድርሻ መጠን ልክ ትርፍና ኪሳራውን ይጋራሉ።

በተለመደው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ፣ ባንኩ ትልቅ አቅም ያለውና የሰበሰበውንም ገንዘብ በብዙ መልክ ካሰራጨው ከጠቅላላው ኢንቨስትመንቱ የሚያገኘው ድምር ውጤት አዎንታዊ ይሆናል (ትርፍ ያገኛል)። ስለዚህ፤ እንዲህ ካለ ባንክ ጋር ገንዘባቸውን ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎችም ሆኑ ተቋማት (ከጊዜው አስቀድሞ ዋስትና ባይሠጠው አሊያም ይህን ያህል ተብሎ በቅድሚያ ባይተነበይለትም) አዎንታዊ ውጤት ያገኛሉ።

ዛሬ በጣም ብዙ “እስላማዊ” የፋይናንስ ተቋማት በመላው ዓለም ተሠራጭተው ይገኛሉ። እነዚህ ተቋማት የተመሠረቱበት መርህ ከወለድ ነጻ በሆነ ስርዐት የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት ነው። ብዙዎቹም እየፋፉና የተቋቋሙለትን ዓላማ (ከወለድ ነጻ በሆነ ስርዐት የፋይናንስ አገልግሎት የመስጠት ዓላማ) እያሳኩ እንደሆነ እየታየ ነው።

ወደ አምላካዊው መመሪያ መመለስ

በብዙዎቹ የዓለማችን ክፍሎች እየታዘብናቸው ካሉ እውነታዎች አንዱ “ዘመናዊው ስልጣኔ” (በተለይም የምዕራቡ ዓለም) ጀርባቸውን ለአምላካዊ መመሪያዎች መስጠቱ ነው። በኢ-አምላካዊ መመሪያዎች የኢኮኖሚ ስርዐታቸውን፣ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን፣ ዓለም አቀፍ የግንኙነት መስመራቸውን፣ ወዘተ ሁሉ ገንብተዋል።

ይህን አቅጣጫና አስተሳሰብ ሲተገብሩ ግን የሚሞክሩት ነገር እጃቸው ላይ የሌለ ነገር መሆኑን ማመን አለባቸው። ምክንያቱም፤ ማሕበራዊ ሳይንስ (social science) እና የተፈጥሮ ሳይንስ (physical science) እጅግ በጣም የተለያዩ ናቸው። የሠው ልጅ በምን ዓይነት ሁኔታዎች፣ ምን ዓይነት ስርዐት እንደሚጠቅመው ለማወቅ ላብራቶሪ ውስጥ ገብቶ ሙከራ የሚደረግበት ፍጡር አይደለም። ይኼውም፤ ሠው ሁሉ ለአንድ አይነት ክስተት አንድ አይነት ምላሽ ይሰጣል ብለን ገምተን ነው።

ምናልባትም፤ ስለ ስነ-ኢኮኖሚ ስናስብ በቅድሚያ ወደ ጭንቅላታችን የሚመጣው የሶሻሊዝምና የኮሚኒዝም መፈራረስ ይሆናል። ሆኖም፤ ስለ ካፒታሊዝምም ስናስብ ይሄ የካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ስርዐትም “አለ” ከሚባልበት ቦታ ምን ያህል ርቆ መቀመጡን በጥልቀትና በቅርበት ማስተዋል ያስፈልጋል።

የመጀመሪያዎቹ የካፒታሊዝም ቲዎሪ ቀራጺና አቀንቃኝ ምሁራን “ካፒታሊዝም በሁሉም ሁኔታዎችና ክስተቶች ሁሉ ምርጡ የኢኮኖሚ ንድፈ-ሃሳብ ይሆናል” የሚል ሕልም ነበራቸው። ዳሩ ግን፤ ህልማቸው ሁሉ ባልሆነና ሊሆን በማይችል መላ ምት ላይ የተመሠረተ ነበር። እነሱ ካፒታሊዝም ከተገነባ “ምርጡ የኢኮኖሚ ንድፈ-ሃሳብ ይሆናል” ያሉት እንከን አልባ የውድድር መድረክ፣ እንከን አልባ (ምሉዕ) ዕውቀት፣ ከመንግስት ተጽዕኖ የነጻ ንግድና ወዘተ፣ ወዘተ ሲሟሉ ነው። ከነዚህ መላ ምቶች አንዱ ከፈረሰ (ተከብረውም አያውቁም) ቲዎሪው እንኳንስና “በሁሉም ሁኔታዎችና ክስተቶች ሁሉ ምርጡ” ሊሆን ቀርቶ ሚዛኑን ሳይስት መቆም እንኳ አይችልም።

ከላይ የተጠቀሱት የካፒታሊዝም ስኬት ይገነባባቸዋል የተባሉት ቅድመ-ሁኔታዎች ከፈረሱ (ዛሬ ላይ እንደምንታዘበው) ዓለማችን ሐብታሞች ይበልጥ ሐብታም እየሆኑ በሄዱ ቁጥር ድሆች ያለማቋረጥ የችግርንና የድህነትን ቁልቁለት የሚወርዱባት ትልቅ የብዝበዛ መድረክ ሆና ታርፋዋለች። የብዝበዛ መድረኩ ጸሃፌ-ተውኔት እና አዘጋጆች፣ መጋቢና ቀላቢዎቹ ደግሞ የወለድ ተቋማትና ደላሎቹ ናቸው።

አላህ (ሱ.ወ) አምላካችን ለሠው ልጅ ቁርኣን በማውረድና መመሪያውን በመስጠት ባርኮታል። ቁርኣን ደግሞ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በራዕይነት ከተገለጠበት ወቅት ጀምሮ ፍጹም በአላህ (ሱ.ወ) ጥበቃ ውስጥ ያለ ንጹህ የአላህ ቃል ነው። በዚህም ምክንያት፤ የሰው ልጅ “ልመራበት” ካለ ዛሬም በረከቱን ከማግኘት ምንም አያግደውም። ይህ መጽሃፍ በውስጡ የሰው ልጅ ቢከተለው ሙሉ የሕይወት መመሪያና የመዳን ምስጢር ሞልቶታል።

እናም ወለድን ከላይ ባየናቸው (ባላየናቸውም ጭምር) እንከኖቹ እና ችግሮቹ ምክንያት ቁርኣን ክልክል ቢያደርገው ምን ይደንቃል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here