የወለድ ጉድፎች (ክፍል 2)

0
1947

ከአንድ ሐገር ከፍ ብለን በአለም ዓቀፍ ደረጃ ስናስብ ደግሞ ከዚህ የበለጠ አደገኛና አጥፊ ሁኔታዎችን እናስተውላለን። በሐገር ደረጃ ወለድ የሚያመጣው ችግር በክፍል አንድ ያየነውን ያህል ከሆነ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ የበለጠ የከፋ መሆኑን ማወቅ ቀላል አመክንዮ ነው። ድሃ ሐገራት ከገቢያቸው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ለብድር ክፍያ እያዋሉት የዜጎቻቸውን የምግብና የጤና ፍላጎት እስከመሠረዝ ይደርሳሉ።

ዛሬ በኋላ ቀር ሐገራት ውስጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናት ካፒታሊዝምና ካፒታሊዝም በፈጠረው መሳሪያ (ወለድ) ምክንያት ይሞታሉ። ይባስ ብሎ ብዙ የአፍሪካ ሐገራት መሪዎች ለጤናና ለትምህርት ከሚያውሉት ሐገራዊ ወጪ ይልቅ ወለዱ ተከምሮ ከዋናው ብድር የበለጠውን ዕዳ፤ የሚመልሱት ገንዘብ ይበልጣል።[1]

ከዚህ እውነታ በመነሳት እ.ኤ.አ በ1998 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እ.ኤ.አ ከ2000 በፊት የ20 ድሃ ሐገራት ዕዳ ሙሉ በሙሉ የሚሠረዝ ከሆነ 20 ሚሊዮን ሰዎችን ከሞት መታደግ ይቻላል የሚል ጥናት አውጥቶ ነበር። በሌላ አነጋገር ያልተሰረዘው እዳና ወለድ እ.ኤ.አ እስከ 2000 በየሳምንቱ ለ 130,000 ሕጻናት ሞት ቀጥተኛ ተጠያቂ ነው ማለት ነው።[2]

የለንደኑ ከንቲባ ኬን ሊቪንግስተን፣ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ዓለማቀፉ የካፒታሊዝም ስርዐት በየዓመቱ በአዶልፍ ሂትለር ከተገደሉ ሠዎች በላይ እንደሚገድል ተናግረው ነበር። ሠውየው ለሚሊዮኖች ሞት ተጠያቂ የሚያደርጉት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምን (የIMFን) እና የዓለም ባንክን በድሃ ሐገራት ላይ የቆለሉትን የዕዳ ጫና ትንሽ እንኳ ለማቅለል “አሻፈረን” ባይነታቸውን ነው። ወይዘሮ ሱዛን ጆርጅ በበኩላቸው “ከ1981 ጀምሮ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ የድሃ ሐገራት ዜጎች ያለጊዜያቸው ሕይወታቸው የሚቀጥፈው መንግስታቶቻቸው ለንጹህ ውሃ አቅርቦትና ለጤና ማውጣት የነበረባቸውን ገንዘብ ለብድር መመለሻ በማዋላቸው ነው” ሲሉ ይከሳሉ።[3]

በቁጥጥር ውስጥ

ብድር፣ በየጊዜው እየጨመረ ናላ ከሚያዞረው የወለድ መጠን ጋር ተደምሮ፤ ለአንድ ሐገር ሉዐላዊነት መከበር እጅግ አደገኛ ችግር መሆኑን ምሁራን ያስቀምጣሉ።[4] በተጨማሪም በድሃ ሐገራት ላይ ያለውን ሙሉ ብድር ባይሆን እንኳ ወለዱን እንኳ ማንሳት ቢቻል ኖሮ ድሃ ሐገራት ከጎበጡበት የድህነትና የችግር አዙሪት ደህና ቀና ማለት በቻሉ ነበር። እነዚህ ድሃ ሐገራት የሚከፍሉት የወለድ መጠን እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከዋናው ብድር የሚበልጥበት ጊዜ ብዙ ነው። ካውፊልድ የተባሉት ምሁር አጽንዖት ሰጥተው እንደሚገልጹት “እ.ኤ.አ በ1978 የነዳጅ ዘይት አምራች ሐገራት ማህበር (OPEC) አባል ያልሆኑ የ3ተኛው ዓለም ሐገራት ለአበዳሪዎቻቸው ከከፈሉት ገንዘብ ውስጥ ሩቡ ዋናውን ገንዘብ ሳይሆን ወለዱን ነው። ሁኔታው በተለይም እ.ኤ.አ በ1976 እና በ1982 መካከል እዳቸው እጥፍ በሆነባቸው የላቲን አሜሪካ ሐገራት ላይ እጅግ ከፋ። ልክ 1982 ላይማ አሳፋሪና ደረቅ ቀልድ ደረጃ ደረሰ። በዚህ ወቅት ሐገራቱ ብድራቸውን ሲመልሱ 70 ከመቶ የሚሆነው ወለዱን ብቻ ሆኖ ነበር። ላቲን አሜሪካ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ብታገኝም ብዙውን ግን ያለፉ ዓመታትን ዕዳ ለመክፈል ነው የምታውለው።”[5]

ሌላው ቀርቶ አበዳሪ ሐገራትና ድርጅቶች “የዕዳ ማቅለያ” ሲሰጡ እንኳ ዋናውን እንጂ ወለዱን አይምሩም። ስለዚህ ወለዱ እየወለደ እየተራባ ይከመራል። እንደ ግዋይን ገለጻ “ባንኮች እንደ ፖላንድ ላሉ ሐገራት የዕዳ መክፈያ ግዜ ሲያራዝሙላቸው (ማለትም በ10 ዓመት መክፈል ያለባቸው በ20 ዓመት ሲያደርጉላቸውም) ወለዱ መራባቱን አያቆምም። 10 ጊዜ መውለድ የነበረበት 20 ጊዜ ይዋለዳል ማለት ነው። በዚህ ዓይነት ዘዴ ነው የዓለም አቀፍ ባንኮች የትርፍና ኪሳራ መዝገብ ‘እንዳማረበት’ የሚቀጥለው።”[6]

ይህንን የመሳሰሉ ወለድ አመጣሽ ችግሮችን፣ “ተበዳሪ ሐገራት እ.ኤ.አ ከ1974 ወዲህ በደንብ አድርገው እየተረዱት ነው” ቢባልም ምንም የማስተካከያ እርምጅ ግን እስካሁን አልታየም። በነገራችን ላይ፤ እንዲህ አይነቱ ሐገርንም ጭምር አደጋ ላይ የሚጥል ነገር የሚከሰተው ድንገት ሳይታሰብ አይደለም። ድሃና ኋላ ቀር ሃገራት ይህን መሰል የዕዳ ክምር እንዲጫንባቸው በማድረግ ረገድ የየሃገራቱ ብልሹ መሪዎችና “ምሁራኖቻቸው” ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም። ዳሩ ምን ያደርጋል? “ብድር አንወስድም” ቢሉ ከያቅጣጫው የሚመጣው ጫናም እንዲሁ በቀላሉ የሚያልፉት አይደለም፤ እናም ይበደራሉ።

ዓለም ባንክም የሚሠጠውን ብድር በጠቅላላ ባንዴ ከመልቀቅ ይልቅ ቀስ በቀስ፣ ትንሽ በትንሽ ወደ መልቀቅ ተሸጋግሯል። ውጤቱም የተበዳሪዎች እዳ ከሚገባው በላይ ተከማችቶ ሉአላዊነትን ማጣት ደረጃ ይደርሳል። ማንኛውም አበዳሪ ደግሞ በተበዳሪው እንቅስቃሴ ላይ የሆነ የመቆጣጠር ስልጣን እስካላገኘ ድረስ ብድሩን እየለቀቀ ለመቆየት ፍቃደኛ አይደለም። በቀደሙት ዘመናት ኃያላን ሐገራት ለፍላጎታቸው የማያጎበድዱትን ተበዳሪዎች ለማንበርከክ ወታደራዊ ኃይል እስከመጠቀም ይሄዱ ነበር። ታላቁ የኢኮኖሚክስ ሠው ሄነሪ ካርተር አዳምስ እ.ኤ.አ በ1887 ባሳተመውና “Public Debts” በተሰኘው መጽሃፉ እንዲህ ይላል፡-

“የውጭ ብድር መስጠት ጸብ-ጫሪ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለመተግበር የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ከብድሩ ጋር በተያያዙ አንዳንድ ምክንያቶችም ወደ ወረራና ሐገራትን ወደ መቆጣጠር ሊኬድ ይችላል።”

ዓለም ባንክ ከተበዳሪዎቹ ጋር ያለው ግንኙነትም ያልተገራ እንደሆነ ይታወቃል። ለመተባበርና እግዛ ለመስጠት ከመዘጋጀት ይልቅ የተበደሩት ሐገራት ፋይናንሳቸውን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው፣ ህጋቸው ምን መምሰል እንዳለበት፣ ለዜጎቻቸው ምን አይነት አገልግሎት ማቅረብ እንዳለባቸው እና ዓለም አቀፍ ንግዳቸው ምን መምሰል እንዳለበት ሊገልጽላቸው ይቃጣዋል። የማሳመኛ ጉልበቱም (ሃያላኑ አበዳሪዎች የባንኩን አቋም ስለሚደግፉና እነሱም ስለሚከተሉት) ከፍተኛ ነው። በዚህና መሠል ዘዴዎችም በመጠቀም (ከተቋቋመበት ዓላማ ጋር ቢጋጭም ቅሉ) አለቅጥ በማበደር በሚያገኘው ጉልበት በመጠቀም ተበዳሪዎቹን የራሱ ምርኮዎች አድርጓቸዋል።[7]

ጆን ፐርኪን አሁን አሁን ይበልጥ ተወዳጅነትን እያተረፈለት ባለው Confessions of an Economic Hit Man[8] በተሰኘው መጽሃፉ የኢኮኖሚ ስርዐቱን ውስብስብና ድብቅ ጉዳዮች በጥልቅ ይዳስሳል። የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሠራቸውን የግምገማ ሥራዎች አስመልክቶ የራሱን የሥራ ልምድ ሲገልጽ፡-

“በተሳተፍኩባቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ያስተዋልኩት ያልተነገረ ሐቅ ቢኖር፤ የነዚህ ፕሮጀክቶች ዋነኛ ዓላማ ለኮንትራክተሮቹ ከፍተኛ ትርፍን ማስገኘት፣ በተበዳሪዎቹ ሀገራት የሚገኙ ጥቂት ሐብታምና ተደማጭነት ያላቸውን ሠዎች በማስደሰት ሃገሬውንና ሐገሪቱን ግን በፋይናንስና ጥገኝነት እና በፖለቲካ ታማኝነት ውስጥ መክተት ነው። ብድሩ ብዙ ከሆነ ደግሞ እሰየው ነው። በሐገራት ላይ ተከምሮ ያለው የብድር ጫና ድህነት አላላውስ ባለው ምስኪን ዜጋ ላይ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎት ከማግኘት ለአስርት ዓመታት እያገደው ቢሆንም ለነዚህ ወገኖች ደንታቸው አይደለም።”[9] ይላል።

ከዚህ የፐርኪን ሥራ ተከትሎ ለህትመት የበቃውና በስቴቨን ሃይት አርትኦት የተደረገለት፤ A Game as Old as Empire: The Secret World of Economic Hit Men and the Web of Global Corruption መጽሃፍም ተመሳሳይ ክሶችን ያሰማል። ስቴቨን ሃይት እንደሚለው፡-

“እዳ ሶስተኛውን ዓለም በቁጥጥር ሥር አውሎ ለማቆየት ሁነኛ ዘዴ ነው። ሐገራቱ በዓለም ካርታ ላይ ለመቆየት እርዳታና ብድር ያስፈልጋቸዋል። አበዳሪዎቹ ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ደግሞ ሐገራቱ ኢኮኖሚያቸውንና ሕግጋቶቻቸውን እነሱ በሚሉትና በሚፈልጉት መልኩ እንዲቀይሩ ያስገድዷቸዋል።”[10]

የብድር ሥጋቶች

በአሁኑ ሰዓት ያለው የብድር ሁኔታ (በዋናነት ወለድ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወትበት የብድር ስርዐት) ለጠቅላላው ዓለም አደጋ ነው። የአሜሪካ የስለላ ተቋም (ሲ አይ ኤ) ከዓመታት በፊት 2015ን ሲተነብይ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

“እያደገ የሚመጣው የዓለም ኢኮኖሚ ብዙ ተጠቃሚዎችን ያፍራ እንጂ ማዕበሉ ግራና ቀኝ የሚያላትመውን ጀልባ ሁሉ ከአደጋ አያተርፍም። እንዲያውም ሐገር ውስጥም ከሐገር ውጭም ግጭትና ሁከትን ይወልዳል። ውጤቱም ድሮም ያላማረበትን የኑሮ ልዩነት (gap) የበለጠ ይለጥጠዋል። የግሎባላይዜሽን ዝግመተ-ለውጥ (evolution) መጓተቱ፣ ለተቃወሰ የፋይናንስ ቀውስ መጋለጡና የኢኮኖሚ ክፍተቱም የሚጠበቅ ነው። ትኩረት ያልተቸራቸው ወይም በውድድሩ ኋላ የቀሩ የዓለም አካባቢዎች፣ ሐገራት እና ቡድኖች ከባድ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የባህል መጋጨት ይገጥማቸዋል። በዚህ ሳይቆሙ የፖለቲካ፣ የዘር፣ የአይዲዮሎጂ እና የሃይማኖት አክራሪነት ከነሙሉ የሁከት አቅማቸው ጋር ይላተሟቸዋል።”[11]

ኑሪና ኸርትዝ በታዋቂው መጽሃፏ The Debt Threat ውስጥ አንድ የሚደነቅ ምዕራፍ አለ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ብድር (በተለይም ወለድ የታከለበት ብድር) ታዳጊ ሐገራትን እንዴት እየጎዳ እንደሆነና መላውን ዓለም እንዴት አደጋ እንደጋረጠበት በጥሩ ሁኔታ ታስረዳለች። ከዚህ የወለድ አደጋ ጋር እያያዘች ከምታወራቸው ነጥቦች ውስጥ ጽንፈኝነት፣ ሽብርተኝነት፣ የተፈጥሮ ሐብት መመናመን፣ ወዘተ ይካተታሉ። ከምዕራፉ አንዱን አንቀጽ ብቻ መዘን እንመልከት።

“ይባስ ተብሎ የብድር አስቀያሚ ውልዶችን (ድህነት፣ የእኩልነት መታጣት እና ኢ-ፍትሀዊነት፣ ወዘተ) ምክንያት እየተፈለገላቸው ብሎም እውቅና እየተሰጣቸው ነው። የመስከረም 11ዱ ጥቃት በተፈጸመ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ዝነኛው አፍሪካዊው ጸሃፊ ሚካኤል ፎርቲን ‘ይሄን የመሠለ ዘግናኝና ተቀባይነት የሌለው ጸብጫሪ ድርጊት ሙሉ በሙሉ አይደለም ቢባል እንኳ በከፊል በምዕራቡ የኢኮኖሚ ጭቆና ከሠው ተራ እንዲወጡ የተደረጉ ጭቁኖች የበቀል ድርጊት መሆኑን መቀበል አለብን።’ የሚል ሐተታ አስነብቦ ነበር። የፎርቲን ‘ጭቆና’፣ ‘በቀል’፣ ወዘተ የሚሉት ቃላት ሆን ተብለው የገቡት ለነዚህ ቃላት ስሱና ድንጉጥ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩን በማሰብ ነው።”[12]

በተግባር ሲታይ ወለድ ከላይ ከገለጽናቸው ችግሮች በላይ ብዙ ሊነገሩ የሚችሉ ብዙ ህጸጾች ቢኖሩበትም ለአሁኑ በዚህ እናብቃ።[1] Cf., Noreena Hertz. The Debt Threat (New York: Harper Business, 2004)፣ ገጽ 3

[2] Ali Mohammed and Muhammad Ahsan, Globalization or Recolonisation? The Muslim World in the 21st Century (London: Ta-Ha Publishers, Ltd. 2002)፣ ገጽ 38

[3] Ali Mohammed and Muhammad Ahsan፣ ገጽ 43

[4] (ለበለጠ መረጃ፤ Cheryl Payer, The Debt Trap: The International Monetary Fund and the Third World (New York: Monthly Review Press, 1974)፣ ገጽ 46ን ይመልከቱ፡፡

[5] ካትሪን ካውፊልድ፣ Masters of Illusion: The World Bank and the Poverty of Nations (London, England: Pan Books, 1996)፣ ገጽ 137

[6] S. C. Gwynne, “Selling Money-and Dependency: Setting the Debt Trap,” in Steven Hiatt, ed. A Game as Old as Empire: The Secret World of Economic Hit Men and the Web of Global Corruption (San Francisco: Berrett-Koehler Publishers, Inc., 2007), ገጽ. 35.

[7] Caufield ገጽ 336

[8] John Perkins, Confessions of an Economic Hit Man (San Francisco: Berrett-Koehler Publishers Inc., 2004)

[9] Perkins, ገጽ. 15.

[10] Hiatt, ገጽ. 23.

[11] Hertz, ገጽ. 156.

[12] Hertz, ገጽ. 161.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here