የወለድ ጉድፎች (ክፍል 1)

0
3101

የስነ-ኢኮኖሚ (የኢኮኖሚክስ) ባለሙያዎች ወለድን መሠረት ያደረገ ኢኮኖሚ አስፈላጊነቱን ለማስረዳት ብዙ ርቀት ሊጓዙና ማስረጃም ለማግኘት ይሞክሩ ይሆናል፤ ዋናው ፈተና ግን የወለድ ተጽዕኖ በግልጽ ማጥናቱ ላይ ነው። መታወቅ ያለበት ነገርም አላህ(ሱ.ወ) አንድን ነገር ሐራም ሲያደርግ (ሲከለክል) የተከለከለው ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥቅም የለውም ማለት እንዳልሆነም ጭምር ነው።

በርግጥ፤ አንዳንዴ ሐራም በተደረጉ ነገሮች ውስጥ እንኳ ጥቅሞች ይገኙ ይሆናል። ለአብነት ያህል፡- አልኮልን በተመለከተ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْخَمْرِ وَالْمَيْسِرِ قُلْ فِيهِمَا إِثْمٌ كَبِيرٌ وَمَنَافِعُ لِلنَّاسِ وَإِثْمُهُمَا أَكْبَرُ مِن نَّفْعِهِمَا

“አእምሮን ከሚቃወም መጠጥና ከቁማር ይጠይቁሃል። ‘በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢኣትና ለሰዎች ጥቅሞች አሉባቸው። ግን ኃጢኣታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው’ በላቸው።” (አል-በቀራ .2፤ 219)

ስለዚህ፤ ዋነኛው አጀንዳ ሐራም የተደረገው ነገር “ጥቅም አለው ወይስ የለውም?” የሚለው ሳይሆን “ከጥቅሙና ከጉዳቱ የትኛው ይበልጣል?” የሚለው ነው። እናም… ኢኮኖሚስቶቹ ከወለድ የሚገኝ መጠነኛ ጥቅምና አስፈላጊነት የሚያሳይ ነገር ሊያመጡ ይችሉ ይሆናል። ይሄ “ተገኘ” የሚባለው አንዳች ጥቅም ግን በጭራሽ ከጉዳቱ ሊበልጥ አይችልም፤ ከታች እንደምናየው ወለድ ጉዳቱ ከጥቅሙ እጅግ በጣም ይልቃል።

ሚዛናዊ ያልሆነ የገቢ ክፍፍል

ምንም እንኳ ወለድ ከምርት ላይ የሚከፈል ድርሻ (payment to a factor of production) ተብሎ ቢታሰብም ከምርት ከሚከፈል ድርሻነት የሚያወጡት ልዩ ባሕሪያት አሉት። በነዚህ ልዩ ተፈጥሮዎቹ ምክንያት አንዳንድ በጣም የሚረብሹ ውጤቶችን ያስከትላል።

አንደኛ ወለድ እኩልነት የሌለው የገቢ ክፍፍልን ይፈጥራል። ይሄ አሳሳቢ ተፈጥሮውን ለማየት ሶስት ሠዎችን ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። እነዚህ ሶስት ሰዎች ገቢያቸውን በሙሉ ለፍጆታ ወጪነት የሚያውሉ (consume የሚያደርጉ) ናቸው ብለን እንውሰድ።

አንደኛው 1,000 ሌላኛው 100 ሶስተኛው ደግሞ ከዜሮ ብር መቆጠብ ጀመሩ እንበል። ወለዱ ደግሞ በዓመት 10 ከመቶ ነው። በዓመቱ መጨረሻ ላይ እነዚህ ሶስት ሠዎች በባንክ ሂሳባቸው ላይ፤ የመጀመሪያው 1,100 ብር ሁለተኛው 110 የመጨረሻው ደግሞ ዜሮ ብር ይኖራቸዋል። በዚሁ የወለድ መጠን ከቀጠሉ በሚቀጥለው ዓመት 1,210 ሁለተኛው 121 እና የመጨረሻው ዜሮ ብር ይኖራቸዋል። ከዚህ ቀላል ትንታኔ የነዚህ ሠዎች ድርሻ ዓመት ላመት የራሳቸውን ገንዘብ በቆጠቡት ሠዎች መካከል እንኳ እንዴት እንደሚያድግ አይተናል። በገንዘብ አቅሙ ትንሽ ሻል ያለው ሰዉዬ የበለጠ ገንዘብ ሊቆጥብ ቢነሳ ይህ ክስተት የበለጠ የከፋ ውጤት ያሳያል። እንግዲህ በቀላሉ በየዓመቱ መጨረሻ 1,000 ብር እንኳ ቢጨምር በመጀመሪያው አመት መጨረሻ ወለዱን ጨምሮ 1,100 በሁለተኛው ዓመት መጨረሻ 2,310 ብር፣ በሶስተኛው ዓመት መጨረሻ ደግሞ ከነወለዱ 3,640 ብር፣ ወዘተ ይሠበስባል።

ይሄ የገንዘብ መጠን በትክክል የሚከፈለው አዎንታዊ ከሆነ የምርት ድርሻ ላይ ቢሆን አንድ ነገር ነበር። መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን እንዲያ ብሎ ለመከራከርም የሚያመች አይደለም። ሰዎች ከወለድ የሚያገኙት ገንዘብ በተበዳሪዎች የባከነ፣ የጠፋ ወይም የተሰረቀ ሁሉ ሊሆን ይችላል። ሆኖም፤ ተበዳሪዎቹ እንዴትም ይሁኑ እንዴት፣ ወለድ መክፈል ግዴታ ስለሆነባቸው ከፍለውታል። አንዳንዴ፤ የነዚህ ቆጣቢዎችን ገንዘብ የተበደሩት ፕሮጀክቶች የከሰሩና ምንም ዓይነት ምርት ያላስገኙ ወይም ትርፍ ያልነበራቸው ይሆናሉ። የፈለገውን ቢሆኑም ግን “የምርት ድርሻ” የሚባልለትን ወለድ የመክፈል ግዴታ አለባቸው። ምርት በሌለበት የምርት ድርሻ ክፍያ ማለት ነው። የገንዘብ (ለገንዘብ ገንዘብ የመክፈል) ንግድ አንዱ ልዩ ባሕሪም ይኸው ነው። ማንም ሰውም ተነስቶ “ይሄ አሰራር ፍትሃዊ ነው” ብሎ ሊከራከረን አይችልም። የአሰራሩ ውጤት የተዛባ የገንዘብ ስርጭትና ኢ-ፍትሃዊ የገንዘብ ክፍፍል ነው፡፡

ከላይ ያየነው ኢ-ፍትሃዊ የገንዘብ ክፍፍል እንዳለ ሆኖ የገቢ ክፍፍሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበትና እየተወሳሰበ ይሄዳል። የጊዜው መጨመር እና የበለጠ ኢ-ፍትሃዊነቱ ላይ ደግሞ ገንዘብ ቆጣቢዎች የሚያስቀምጡት የገንዘብ መጠን ልዩነት በሚሊዮኖች እና በመቶ ቤት ያለ ሲሆን የሚያገኙት የወለድ መጠንም እንዲሁ በየዓመቱ እየሰፋ፣ እየሰፋ የተራራቀ ደረጃ ላይ ይደርሳል። በሌላ አነጋገር ሐብታሞች ይበልጥ እየናጠጡ ድሆቹ ደግሞ የድህነትን ቁልቁለት በፍጥነት እየወረዱበት ይበልጡኑ ድሃ ይሆናሉ። ምንም ተጨማሪ ምርት ሳያመርቱ፣ ብድር ስለወሰዱ ብቻ ወለድ የሚከፍሉትን ብናካትት ደግሞ ውጤቱ ከዚህም የከፋ ሆኖ እናገኘው ነበር። ምክንያቱም፤ እነዚህ ሠዎች ከሐብትና ምርታቸው ላይ ምንም አይነት ጭማሪ ሳያሳዩ በየጊዜው የሚከፍሉት ወለድ፤ የገቢ ክፍፍሉን ኢ-ፍትሃዊነት ይበልጥ በሚያጋልጥ ሁኔታ፤ ያላቸውን ጥሪት ሊያሟጥጥ አልፎም ተርፎ ጨርሶ ሊወስድ የሚችልበት እድል ሁሉ አለውና ነው።

የተገፉ ድሆች

አንዳንድ ሠው እኩልነት የማይታይበት “የገቢ ክፍፍል ያን ያህል አጀንዳችን ሆኖ ልንጨነቅበት የሚገባን አይነት ጉዳይ ነው እንዴ?” ሲል ያስብ ይሆናል። የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ምርቶችን እያስተዋወቁና የተጠቃሚነትን (consumer የመሆንን) “አሪፍነት” ለጉድ ሲነዙ፤ ድሆች አቅም ማጣቸውን በማሰብ ከሚመጣባቸው የስነ-ልቦና ጫና በተጨማሪ በገበያ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖም በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ገበያ መር በሆነ ኢኮኖሚ (market economy) ምርት፤ ሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ ይበልጥ አስፈላጊ ሆነው ቢገኙ እንኳ፤ የሚዘጋጀውም የሚተዋወቀውም የመክፈል አቅም ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ነው። ሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ ይበልጥ አስፈላጊ ሆነው ቢገኙም ቅሉ የአምራቾችን ቀልብ ስለማይስቡ ይተዋሉ። ሃብታሞች ግን የሚፈልጉት ኤስ. ዩ. ቪን (SUV-sport utility vehicle) የመሳሰሉ እና መርዛማ ጭስ የሚረጩ ተሽከርካሪዎች ቢሆኑእንኳ ለኅብረተሰቡ እጅግ አንገብጋቢ በሆነ ሁኔታ የሚፈለጉት ምርቶች ቀርተው እነዚህ ይመረታሉ።

የገቢ ክፍፍሉ ይበልጥ ኢ-ፍትሃዊነት እየተስተዋለበት በሄደ ቁጥር የሕዝቡ አንጡራ ሐብትም የሃብታሙን ፍላጎት ለማርካት መዋል ይጀምራል። አንጡራ ኃብቶችም መጠናቸው የተወሰነ በመሆኑ እያነሱ ይሄዳሉ። ለድሃው ፍላጎት የሚውለው የአንጡራ ኃብት መጠንም ቀስ በቀስ እያነሰ፤ እየመነመነ ይሄዳል። ስለዚህ፤ የድሆችን ፍላጎት ለማሟላት የሚመረተው ምርት (አቅርቦት) ያንሳል። ይሄን ተከትሎ ድሆች የሚፈልጓቸውን ምርትና አገልግሎች በበቂ መጠን ከገበያ ለማግኘት ይቸገራሉ። የአቅርቦት ማነስም በበኩሉ የዋጋ ውድነትን ስለሚያስከትል የነዚህ ድሆች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል። ለምሳሌ፡- በብዙ የዓለማችን አካባቢዎች ውስጥ ለሃብታሞች (ኮስሞቲክ ሰርጀሪ[1] የመሳሰለ) የተቀናጣ አገልግሎት የሚሰጡ ብዙ ክሊኒኮችን ማየት እየተለመደ ነው።

በተቃራኒው ድሆች መሰረታዊ የህክምና ፍላጎታቸውን የሚመልሱ ክሊኒኮች ቁጥር አናሳ እየሆነ ሲሄድ ይታያል። እነዚህ በኢኮኖሚው የተደቆሱ ሰዎች አቅማቸው ችሎ ለሚፈልጓቸው የሕክምና አገልግሎቶች የሚሆን ከፍተኛ ክፍያ መክፈል ቢችሉ ኖሮ ሕክምናውን ከገበያው ፈልጎ ለማግኘት ባልተቸገሩ ነበር። (እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ሌላኛው ነጥብ የገቢ ክፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት የዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን የጤናማነት መጠን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጠንካራ አቅም አለው። ይህን አጀንዳ በዚህ መጠነኛ መጣጥፍ የማካተት እቅድ ስለሌለኝ በዚሁ አልፈዋለሁ።)

ዕዳ እንኳንስና ወለድ ተጭምሮበት እንዲሁ ብቻውንም ለማንኛውም ግለሰብ ከባድ ሆኖ ሳለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እዳው ላይ ወለድ ሲጨመርበት ለተበዳሪው ከባድ አዙሪት ነው። ባለዕዳው ድሃ ሲሆን ደግሞ ታሪኩ ሌላ ይሆናል። እዳ ያለባቸው ድሆች በወለድ ጣጣ ምክንያት ማቆሚያው በማይታወቅ የድህነት አዘቅት ውስጥ በመግባት ከዚህ ችግር በቀላሉ የማያገግሙበት ማሕበራዊና ኢኮኖሚያው ቀውስ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ይኸው ቀውስ ተመልሶ በድሆችና በሀብታሞች መካከል ያለውን የገቢ ክፍተትና የኢኮኖሚ መራራቅ ያሰፋዋል። በቀላሉ ወለድ “የምርት ድርሻ ክፍያ” የሚባል የዳቦ ስም ቢሰጠውም ሀብታሞችን ይበልጥ ሃብታም እያደረገ ጉም ውስጥ ሲያስገባቸው ድሆችን ግን የማይወጡበት የዕዳና የችግር ማጥ ውስጥ ይዶላቸዋል።

ዕዳ ያለበት ማኅበረሰብ

ይህን መጣጥፍ የሚያነብ ሁሉ እንደሚረዳው ሐገራችን ኢትዮጵያ ምን ያህል ዕዳ እና ብድር እንዳለባት እንደሚረዳ ግልጽ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ሀገሪቱ በልማትና በተለያዩ ምክንያቶች በሚል የተበደረችው ገንዘብ ላይ የድርሻውን ተካፋይ ነው። ወለድን መሠረት ባደረገ የኢኮኖሚ ስርዐት የአሜሪካንን ያህል ከፍተኛ እድገት ያሳየ ባለመኖሩ አሜሪካንን በጥቂቱ እንይ። የዚህች ልዕለ-ኃያል ሀገር ሕዝብ ባለዕዳነት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሣያሉ። ባለ ዕዳው ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋም የዚሁ ተጠቂ ሆኗል። በርግጥ የዕዳው ጫናና የወለዱ መከማቸት የበለጠ ዱላው የሚጠነክረው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ መሆኑ ግልጽ ነው።

የኢኮኖሚ ስርዐቱ እንደ መዥገር እነሱው ጫንቃ ላይ የተጣበቀ በመሆኑ ድሆች እንደግለሰብ ሲታዩ የከፋ የዕዳ ጫና ያለባቸው ሆነው የሚከፍሉት የወለድ ድርሻ (ratio) ግን ከፍተኛ ነው። የሚርዛ ሻህጃሃን Income, Debt and the Quest for Rich America: The Economic Tale of Small and Mid-Sized US Cities የተሠኘው የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው አብዛሃኛው መካከለኛ ገቢ ያለው አሜሪካዊ በዕዳ ብዛት የሚዋትት ነው።

በሐገራችንም ሆነ በብዙ የዓለማችን አካባቢዎች አነስተኛ ገበሬዎች በምርት ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት ለመበደር እንደሚገደዱ በደንብ የታወቀ ነው። ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ የተበደሩትን ገንዘብ ወለድ መክፈል ባለመቻላቸው ምክንያት ለዘመናት ከልጅ ልጅ ሲተላለፍ የነበረውን የእርሻ መሬትና ውድ አንጡራ ንብረቶች ሲነጠቁ ማየትም የተለመደ ክስተት ሆኗል። በሻህጃሃን ጥናት መሰረት የዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው አሜሪካዊ ገበሬዎች ዋናውን ዕዳ ሳያካትት ለወለድ ብቻ ከአመታዊ ገቢና ምርታቸው ውስጥ 15 ከመቶ ያህሉን ይከፍላሉ። እንግዲህ እዚህ ጋር እነዚህ ምስኪኖች ከአበዳሪዎቻቸው የሚደርስባቸውን እንግልትና ዛቻ ከግምት ሳናስገባ መሆኑ ነው። ሻህጃሃን ጥናቱን ሲያጠናቅቅ እንዲህ በማለት ነው፡-

“እልፍ አዕላፍ ተበዳሪዎች፣ እዳ በሚያመጣው የገንዘብ እና ሌሎች ሸክሞች ምክንያት እድሜያቸውን ሙሉ ብድር ከነወለዱ ሲከፍሉ ይኖራሉ። እ.ኤ.አ ከ1990-1993 የተበዳሪ ቤተሠቦች አማካይ የዕዳ መጠን 32 ሺህ 493 ዶላር ነበር። ይህ የዕዳ መጠን ከቤተሰቦቹ ዓመታዊ ገቢ እኩል ነው። ከ1990-93 ባለው ዓመታት የአንድ አሜሪካዊ ዓመታዊ ገቢ 12 ሺ 571 ዶላር ነበር። የአንድ ቤተሰብ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ ደግሞ 32 ሺ ዶላር አካባቢ ነበር። ቋሚ ያልሆነ የሥራ እድል እና ዝቅተኛ ገቢ ላይ ይህን ያህል የዕዳ መጠን ላይ ሲጨመርበት የሚፈጥረው የድብርትና የጭንቀት መጠን ከፍተኛ ነው።”

ሻህጃሃን እንደተነበየውም ባለፉት አምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ቀውሱ በፈጠረው ቀውስ ብዙዎች የራሳቸውንና የሌሎችንም ሕይወት ሲያጠፉ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠዎችም የአዕምሮ ሕክምና ሆስፒታሎችን ሲያጨናንቁ ቆይተዋል።

ለአንድ ቤተሠብ ዋናውን ብድር ሳያካትት ወለድ ብቻ 15 ከመቶ ገቢን መክፈል ማለት የቤተሠቡን ገቢ ሁሉ ጠርጎ መውሰድ ማለት ነው። ገበሬዎቻችንን ጨምሮ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የሐገራችን ዜጎች ከባንኮችና ከብድር ተቋማት የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ አቅቷቸው፣ ወለዱም እየተከመረ ከዋናው ብድር በልጦ ይታያል። እነሱም መቼስ ብድር ነውና የበሉትንም ያልበሉትም ያህል በመመለስ ተጠምደው ቀን ተሌት ይባክናሉ። በዚህ ምክንያት ስንቱ ቤተሰብ ለልጆቹ ጥሩ ትምህርት መስጠት አቅቶታል? ልጆቻቸውም በዕዳ መሐል ተወልደው በዕዳ መሐል ይሞታሉ። እንደ ሰው ሙሉ ሳይሆን ግማሽ ሕይወት ነው የምንኖረው ቢሉስ ይፈረድባቸዋል?

የባሰው ነገር ደግሞ እነዚህ ባለዕዳ ቤተሰቦች ከዚህ የዕዳ አዙሪት በፍጥነት ሊወጡ የሚችሉበትን መንገድ እንዳያገኙ ተቋማዊ የሆነ ብልሹ አሰራር እና የወለድ ሥርዐት አግቷቸዋል። ሙያ ማወቅ ወይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልጆችን ማስተማር ከብድር የመላቀቅ ዘላቂ መፍትሄ ቢሆንም የብዙዎቹ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍያን የመክፈል አቅም ማግኘት በራሱ ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው። ስለዚህ፤ ዓለማችን ከዚህ የወለድ አዙሪት ለማላቀቅ መውጫ መፍትሄ ያስፈልጋታል።


[1] የውበት ማስተካከያ ቀዶ ጥገና፣ የተፈጥሮ መልክ መቀየሪያ የህክምና ጥበብ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here