የአካባቢ ጥበቃና ኢስላም

1
3517

በቁርአንም ሆነ በሃዲስ ለቁጥር የሚታክቱ ቦታዎች ላይ አካባቢንና የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን በሠፊው ይገለፃል። ሁሉም አይነት እፅዋት እና እንስሳት እንዲሁም የመልከዓ ምድር አፈጣጠር የአላህ ውብና እንከን አልባ አፈጣጠር መገለጫና የዚህ ፍጥረተ-ዓለም አካላት መሆናቸውን ይገልፃል።

በመሆኑም፤ ተፈጥሮንና የተፈጥሮ ህግን ማክበር በሁሉም ለአላህ እጃቸውን በሠጡ ወይም “ሙስሊሞች” የመባልን ማዕረግ ያገኙ ሠዎች ሁሉ ግዴታ ነው።

የአካባቢ ጥበቃ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብና ሁሉም የልማት እንቅስቃሴዎች የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረጉ መሆን አለባቸው የሚለው አነጋገር የተፀነሠው እ.ኤ.አ በ2002 በተካሄደው የጆሃንስበርግ ሰሚት (Johannesburg Summit) ላይ ነበር። በዚህ ሰሚት ትንታኔ መሠረት የአካባቢ ጥበቃ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው።

በዚህ ጽሁፍ ኢስላም እነዚህን ሦስት አጀንዳዎችን በተመለከተ ትኩረት መስጠት አለመስጠቱን እንቃኛለን። ይህች ዩኒቨርስ (ፍጥረተ-ዓለም) ሁሌም በእንቅስቃሴ ላይ ብትሆንም ሚዛንዋን ግን አትስትም። አላህም

وَالسَّمَاءَ رَفَعَهَا وَوَضَعَ الْمِيزَانَ
 

“ሰማይንም ከፍ አድረገ፤ ሚዛኑንም አስቀመጠ” (አረህማን 7፤55) ሲል ይናገራል። ይህ ሚዛን በቁሳዊ ዓለም ብቻ ሳይሆን ቁሳዊ ዓለሙን በሚቆጣጠሩት ስርዓቶችም ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ጋሊሊዮ፣ ሜንዴሌቭ፣ ኒውተን፣ ዋትሠንና አንስታይን አንድ ክፍል ገብተው ስለአለም ያላቸውን ዕይታ ተነጋግረው በአንድ ምስል እንዲገልፁ እንደማስቻል ነው። እነዚህ ሁሉ ሠዎች በተለያየ ዘመን የተለያየ ሥራ የሠሩ ቢሆኑም ቅሉ የተወሰነ ነገር አግኝተዋል። የሁሉም ድምር ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል በማሠብ በኩል ግን እርግጠኞች አይደሉም። የዚህ ፍጥረተ-ዓለም ፈጣሪ ግን ሁሉንም በዝርዝር የሚያውቀው እውነተኛ አምላክ ነው። ሚዛናችንንም የሚጠብቀው እርሱ ነው። በዚህ መሠረት ከላይ ያየናቸው ሦስት ነገሮች በኢስላማዊ አስተሳሰብ ውስጥ ዳብረዋል።

1. ማኅበራዊ ልማት

ማህበራዊ ፍትህ በኢስላም ለድርድር የማይቀርብ አጀንዳ ነው። ማንኛውም ሙስሊም የሚሠጠው ክብር የሚወሰነው በህብረተሰቡ መካከል በሚኖረው ውጤታማ ተሣታፊነት ነው። ሙስሊሞች ህብረተሰቡን እንዲገነቡ (እስቲዕማር) ታዘዋል። ሙስሊሞች በየአመቱ ዘካን በማውጣት የማህበረሰቡ የሀብት ክፍፍል ሚዛን እንዳይዛባ እንዲተጉ ታዘዋል። የዘካ ገንዘብ ወደ በይተል ማል ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎን በህገ-ወጥ መንገድ ሃብት ማጋበስንም ይከላከላል። ሁለተኛው የኢስላም ኸሊፋም ዑመር ኢብኑልኸጣብ /ረ.ዐ/ “ይህን ከየት አመጣኸው? (ሚን አይነ ለከ ሃዛ)” የሚለውን መርህ እንደጀመረ ይታወቃል።

ማህበራዊ ልማትና ድሆችን መጠበቅ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ግዴታ ነው። በይተልማልም የገንዘብ ሚኒስቴርነትን ብቻ ሣይሆን የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርነትን ሥራም ደርቦ ይሠራል። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ተካፋይ (የሁሉንም ጣጣ በጋራ መሸከም) እንዲችል ተደርጎ ይቀርፃል። በዚህ ሁኔታ የተቀረጸው ህብረተሰብ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚካሄድን የትኛውም አይነት ውንብድና መከላከል አያቅተውም ተብሎ ይታመናል። በወራጅ ውሃ ወይም በባህር ላይ ወዱዕ የሚያድርግ ሠው እንኳ ጠብታ ውሃ እንዳያባክን የሚከለክለው ሐዲስ በዚህ ረገድ ሊነሣ የሚችል ድንቅ ምሣሌ ነው። ይህ አስተምህሮ ሙስሊሞችን በሁሉም ነገራቸው ሚዛን እንዳይስቱ ያስጠነቅቃል።

2. ኢኮኖሚያዊ ልማት

ኢኮኖሚያዊ ልማት ማምጣት የኢስላማዊ ሃገር አንዱ ግዴታ ነው። ነብዩም ህይወታቸውን የጀመሩት በንግድ ነው። ነጋዴዎችም ሚዛን እንዳይሰርቁ አበዳሪም አራጣ (ወለድ) እንዳይበላ ይከራከራል።

ኹለፋኡ ራሺዲን አዲስ ግዛት ወደ ኢስላም ሲቀላቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በማካሄድና እድገት በማምጣት ይታወቃሉ። ለምሳሌ፡- በኢራቅ ደቡባዊ ክፍል ለኢኮኖሚ ሲሉ አንዴ በብዛት ይዞሩ እንደነበረ ታሪክ ያስታውሳል። እነዚህ ኸሊፋዎች ኢኮኖሚያዊ እድገትን የኢስላህ (የመልካም እድገት) አንዱ መገለጫ አድርገውት ነበር።

ኢስላማዊ ባንክ በየአለም ክፍል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በማሣየት ላይ የሚገኝ መሆኑ የታወቀ እውነታ ነው። የነዚህ ባንኮች እድገት የኢስላም ኢኮኖሚያዊ አስተምህሮ ስኬታማነት ህያው መገለጫ ናቸው።

3. አካባቢያዊ ጥበቃ

በኢስላም “ላ ዶር ወላ ዲራር” የሚባል አስተምህሮ አለ። ማለትም “አለመጎዳት አለመጉዳት” ማለት ነው። ይህን ህግ መከተል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከሠተ ያለውን የደን ጥፋት በውጤታማነት ይታደጋል። በመሠረቱ “ላ ዶር ወላ ዲራር” ለኢኮኖሚውም ሊተረጎም ይችላል።

በቁርአን “ሁሉም ፍጥረታት አላህን ይገዛሉ፤ እርሱንም ያመልካሉ” ተብሎ ተጠቅሷል። በዚህ ምክንያት አላህን እያመለከ ያለን ተፈጥሮ እንዴት እናወድማለን? ከሚያስፈልገን በላይም እንበዘብዛለን? ምክንያቱ ይህን የቁርአን አስተምህሮ አለማወቅ ወይም አለመተግበር ነው። በኢስላም አደን የማይካሄድባቸው ወራት ሸሁሩል ሁሩም (የተከበሩ ወራት) አሉ። በነዚህ ወራት የዱር እንስሳት ከመታደን ይድናሉ። ይህ እንግዲህ ሌላኛው የመከላከያ ስርአት ነው።

ከኢስላም በፊት ዐረቦች ለረጅም ክፍለ ዘመናት በግጦሽና በውሃ ምክንያት ሲዋጉ ኖረዋል። ኢስላም ግን ይህንን ፅንሠ-ሃሳብ በመተግበሩ ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ ተቀርፏል። ከ12 ወራት ሹሁሩል ሁሩም የተባሉት 3 ወራትም ሠዎች ጦርነትም ሆነ ሌላ ተፈጥሮ ላይ አደጋ የሚያስከትል ተግባር የሚያቆሙበት ወራት በመሆናቸው ሠው ከተፈጥሮ ጋር የሚታረቅባቸው ወራት ልንላቸው እንችላለን። በዘመናዊው ዓለምም “Giving nature a chance” የሚል ለተፈጥሮ የተወሠነ የማገገሚያ /Reviving/ ጊዜ መስጠት የሚል አባባል እየተለመደ መጥቷል። ይህ እንግዲህ “ሹሁሩል ሁሩም” በሌላ መንገድ መሆኑ ነው።

  • ተፈጥሮን ማክበር

በአንድ ሐዲስ ላይ እንደተገለጸው ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ዑሁድ የተባለው ተራራ ላይ ሲወጡ “ይህ የምንወደውና የሚወድን ዑሁድ ተራራ ነው።” ማለታቸው ተዘግቧል። ይህ እንግዲህ ኢስላም ህይወት ያላቸውን ብቻ ሣይሆን ህይወት የሌላቸውን የተፈጥሮ አካላት እንድናከብርና እንድንወድ ያለውን አስተምህሮ ያሣያል።

በቁርአንም ተራሮች አማና (የኢስላም አደራ) እንደተሠጣቸውና አንቀበልም እንዳሉ ይገልፃል። የሠው ልጅ ግን ይህን አደራ በድፍረት ተቀብሏል። እዚህ ጋርም ተራሮች ልክ ህይወት እንዳለው አካል መቆጠራቸውን እናያለን። በዚህ መሠረት ህይወት የሌለው የፍጥረተ ዓለሙ አካልም ክብር ተሰጥቶታል። ውሃው አየሩና ሌላው ሁሉ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። ቁርኣን ለተፈጥሮ ከሠጣቸው ትኩረቶች ውስጥ አንዱ መገለጫ በላም፣ በጉንዳንና በንቦች ስም የቁርአን ምዕራፎች መኖራቸው ነው።

  • ሚዛንን መጠበቅ

ቁርኣን ተፈጥሮ ሚዛኗን መጠበቋን በተመለከተ ውሃን ምሳሌ በማድረግ ያስረዳል። ሱረቱ አል-ረህማን ምዕራፍ 55 ቁጥር 19-20 ላይ፡-

مَرَجَ الْبَحْرَيْنِ يَلْتَقِيَانِ بَيْنَهُمَا بَرْزَخٌ لَّا يَبْغِيَانِ
 

“ሁለቱን ባሕሮች የሚገናኙ ሲኾኑ ለቀቃቸው። (እንዳይዋሐዱ) በመካከላቸው ጋራጅ አልለ። (አንዱ ባንዱ ላይ) ወሰን አያልፉም።” በማለት የሚገናኙ ነገር ግን ሚዛናቸውን የማይስቱ እንደተደረጉ ያትታል።

  • ተፈጥሮን ማድነቅ

أَفَلَمْ يَنظُرُوا إِلَى السَّمَاءِ فَوْقَهُمْ كَيْفَ بَنَيْنَاهَا وَزَيَّنَّاهَا وَمَا لَهَا مِن فُرُوجٍ وَالْأَرْضَ مَدَدْنَاهَا وَأَلْقَيْنَا فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنبَتْنَا فِيهَا مِن كُلِّ زَوْجٍ بَهِيجٍ تَبْصِرَةً وَذِكْرَىٰ لِكُلِّ عَبْدٍ مُّنِيبٍ
 

“ወደ ሰማይም ከበላያቸው ስትኾን ለእርሷ ምንም ቀዳዳዎች የሌሏት ኾና እንዴት እንደ ገነባናትና (በከዋክብት) እንዳጌጥናት አልተመለከቱምን? ምድርንም ዘረጋናት። በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት። በውስጧም ከሚያስደስት ዓይነት ሁሉ አበቀልን። (ይህንን ያደረግነው) ተመላሽ ለኾነ ባሪያ ሁሉ ለማሳየትና ለማስገንዘብ ነው።” (ሱረቱ ቃፍ 50፤ 6-7)

ሠዎች ተፈጥሮን የሚያወድሙት ለተፈጥሮ ደንታ-ቢስ ሲሆኑ ወይም ውበቷን ሳያስተውሉ መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ፤ ቁርአን ለቁጥር አታካች በሆኑ ቦታዎች ተፈጥሮን እንድናደንቅ ውበትንም እንድናጣጥም ያስተምራል።

  • የአካባቢ ጤና ጥበቃ

ኢስላም በሙስሊሙም ሙስሊም ባልሆነውም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ንፅህና ነው። ስለንፅህና የተወሩ ሐዲሶችና የነብዩ ትውፊቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም። ንፅህና ከትንሿ መፋቂያ አንስቶ የሚጀመር ነው። የውሃን ብክለት መቋቋምና መከላከልም የንፅህና አንዱ አካልና የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ነው። ከመንገድ ላይ ቆሻሻንና እንቅፋትን ማስወገድም የኢማን አንዱ ዘርፍ መሆኑ በግልፅ የተቀመጠ ሐዲስ ያስረዳል።

1 COMMENT

  1. Comment: ይህ መልዕክት ለተፈጥሮ ሚዛን ወሳኝ በመሆኑ ተግብረን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here