የኢስላም ልዩ ባህሪያት (ክፍል 6) – ግልፅነት (አል-ውዱህ)

0
2739

ሌላው ኢስላም የሚለይበት ባህርይ በእመነትም ይሁን በህግጋቱ ግልጽና ቀላል መኆኑ ነው። የኢስላምን እምነት ነክ ጉዳዮችንም ይሁን ህግጋቶች ማንኛውም ሰው ሞኝም ይሁን ብልህ፣ ምሁርም ይሁን መሃይም በቀላሉ ሊረዳው ይችላል። በኢስላም ውስጥ ግልጽ ያልሆነና የተወሳሰበ ጉዳዮ የለም።

በሌሎች ዘንድ ያለው “አይንህን ጨፍነህ እመን” የሚለው አባባል በኢስላም አይሰራም። በኢስላም ሰው ማመን ያለበት አውቆና ተረድቶ ነው። ሙስሊም አምላኩ አንድ አላህ ብቻ መሆኑንና አምልኮትም ለርሱ ብቻ እንደሚገባ ያምናል፤ ጥቅምና ጉዳትም በርሱ እጅ ብቻ መሆኑን ይረዳል።

ኢስላማዊ እምነት ግልጽ መሆኑን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል አላህ (ሱ.ወ) የነገረን የአኺራ ጉዳዮች ለምሳሌ እንደ ጀነት፣ ገሐንም በነርሱ ውስጥ ያሉ ፀጋ ወይም ስቃይ፤ እንደዚሁም የአላህ ባህሪያትን የመሳሰሉት ገይብ (ሩቅ) ጉዳዮች ምንምን እንኳ ከስሜት ህዋሳት የራቁና በምናብ ህሊና ባንስላቸውም በጥቅሉ ሰው ሊረዳቸውና ሊገነዘባቸው የሚችሉ ነገሮች ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ
 

“የሚመስለው ምንም ነገር የለም። እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።” (አል-ሹራ 42፤11)

ሌላው ኢስላማዊ ህግ ግልጽ መሆኑን የሚያሳየው ጉዳይ በውስጡ ያሉት በአካልም ይሁን በገንዘብ የሚፈጸሙ አምልኮቶች ሁሉም ግልጽና በቀላሉ የሚታወቁ መሆናቸው ነው። ሶላቶች በቀንና ሌሊት ውስጥ አምስት ናቸው፤ ፆም በአመት አንድ ወር (ረመዳን)፤ ዘካ መነሻውና የክፍያ መጠኑ የታወቀና የተወሰነ ነው፤ ሐጅም ማእዘናቱና ግዴታዎቹን ሁሉ ማንም ሰወ ተምሮ ሊረዳቸው የሚችሉ ግልጽ ጉዳዮች ናቸው።

በመጨረሻም የዚህን ዲን ኢስላም ግለጽነትና ቀላልነት የሚያሳየው የዚህችን ኡማ መመሪያ የሆነው ቁርኣን ማንበብ፣ በቃል መሸምደድም ይሁን መልክቱን መረዳት ፍላጎት ላለው ሁሉ ቀላል መሆኑ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَلَقَدْ يَسَّرْنَا الْقُرْآنَ لِلذِّكْرِ فَهَلْ مِن مُّدَّكِرٍ 

“ቁርኣንንም ለመገንዘብ በእርግጥ አገራነው። ተገንዛቢም አልለን?” (አል-ቀመር 54፤17)

የነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) ተምሳሌትነት (ሱና)ም ሰንሰለቱን ጠብቆ እርሳቸው ዘንድ ይደርሳል፤ የህይወት ታሪካቸውም (ሲራቸው) ተጣርቶ ተጽፎ ተጠብቆ ይገኛል። የኢስላም ህግጋቶችና ሥርዓቶች ከነዚህ ከተጠበቁ ምንጮች ይወሰደዳሉ፤ ልዩነት በተፈጠረ ጊዜም ወደነዚህ ምንጮች መመለስ ይቻላል። ይህን ሁኔታ በሌሎች ሐይማኖቶች ዘንድ አናገኘውም።

* * * * *

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here