የኢስላም ልዩ ባህሪያት (ክፍል 5) – ተጨባጭነት /ወቅታዊነት/ (አል-ዋቂዒያ)

0
2626

ይህ ማለት ኢስላማዊ ድንጋጌዎች ምንግዜም ቢሆን በሰዎች ኑሮ ውሰጥ ያለውን ተጨባጭ (practical) ሁኔታ ያገናዝባሉ ናቸው ማለት ነው። በኢስላም ውስጥ ያሉት ህግጋቶችና መመሪያዎች ሁሉ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚስማሙና የሚሄዱ ናቸው፤ ለዚህም ነው ኢስላም በማንኛውም ጊዜና ቦታ እንደሚተገበር የምንናገረው።

በኢስላም ውስጥ ያሉ ህግጋቶች በሙሉ ተጨባጭነት፣ ተአማኝነትና እውነተኝነትን የተላበሱ ናቸው።

በኢስላም ተጨባጭነት የሌለው አመለካከት (እምነት) የለም። በኢስላም የሚታመነው በአንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ይህም የሰው ልጅ ስሜት በሙሉ በአንድ መንፈስ ወደ አንዱ አምላክ አላህ (ሱ.ወ) ብቻ እንዞር ያደርጋል።

በኢሰላም የሚታመነው ተጨባጭ በሆነ ጉዳይ ነው። ኢስላም ውስጥ እምነት በልብ ብቻ ነው የሚለው አባባል አይሰራም፤ በኢሰላም ኢማን (እምንት) የሚሰጠው ትርጓሜ በልብ ማመን፤ በቃል መናገርና በተግባር መፈፀምን ያጠቃልላል። ስለዚህ አንድ ሰው ሀይማኖቱ የሚያዘውን ተግባራት እሰካልፈጸመ ድረስ እምነቱ የተሟላ ነው ሊባል አይችልም።

የኢስላም ነብይና መልከተኛ ሙሀመድ (ሶ.ዐ.ወ) ከሰው ዘር የሆኑና ከሰዎቸ ጋር በስራና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚሳተፉ፤ የሚበሉና የሚጠጡ ናቸው፡፡ የኢስላም መጽሐፍ ቁርኣንም ከሰው ልጅ በሆኑት መልክተኛው ሙሃመድ (ሶ.ዐ.ወ) ላይ የወረደና በማንበብ ብቻ አምልኮ የሚፈጸምበት ቅዱስ የአላህ ቃል ነው፤ ፊደላቱም ቃላቱም ከአላህ የመጡ ናቸው። በኢስላም ሸሪዐ (ህግ) ለማመንም ይሁን ለመተግበር የሚከብዱ፣ ለሰው ልጅ ተፈጥሮ እንግዳ የሆኑና ከሰዎች ተጨባጭ ህይዎት ጋር የሚቃረኑ ነገሮች የሉም።

በአንጻሩ ሰው ሰራሽ እምነቶችና ፍልስፍዎች እንዲሁም የተበረዙ ሐይማኖቶችን ስንመለከት ህጎቻቸውና መመሪያዎቻቸው ተጨባጭነት ርቋቸው እናገኛቸዋለን። በዚህም የተነሳ ለሰዎች ፍላጎት የተሟላ መልስ መስጠት አይችሉም። ይህ ጉዳይ የአለማችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያረጋግጠው ሐቅ ነው።

ኢስላም ግን የሰዎች ፍላጎት መንፈሳዊም ይሁነ ሥጋዊ በተሟላ መልኩ መልስ እንዲያገኝ ለሰዎች ተስማሚና በተጨባጭ ሊፈጸሙ የሚችሉ የአምልኮት ሥነ-ሥርዓቶችን ደንግጓል። ይህም የሆነበት ምክኒያት የሁሉም ፈጣሪ የሆነው አላህ (ሱ.ወ) በሰው ልጅ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ ጥማትና የአምልኮት ፍላጎት ስለሚያቅ ነው። ይህ ጥማትና ፍላጎት ሊረካ የሚችለው ደግሞ ሰው ከፈጣሪው ጋር ሲገናኝ ብቻ በመሆኑ አላህ (ሱ.ወ) በሰዎች ላይ ከአፈጣጠራቸው ጋር የሚሄድ የተለያዩ ኢባዳዎችን ደንግጓል፤

أَلَا يَعْلَمُ مَنْ خَلَقَ وَهُوَ اللَّطِيفُ الْخَبِيرُ
 

“የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀት ረቂቁ፣ ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን?” (አል-ሙልክ 67፤14)

ኢስላም ከሰዎች አቅም በላይ የሆኑ አምልኮትን አልደነገገም፤ እንዲያውም ኢባዳዎችን ገርና ቀላል አድርጓቸዋል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል:-

وَجَاهِدُوا فِي اللَّهِ حَقَّ جِهَادِهِ هُوَ اجْتَبَاكُمْ وَمَا جَعَلَ عَلَيْكُمْ فِي الدِّينِ مِنْ حَرَجٍ مِّلَّةَ أَبِيكُمْ إِبْرَاهِيمَ هُوَ سَمَّاكُمُ الْمُسْلِمِينَ مِن قَبْلُ وَفِي هَٰذَا لِيَكُونَ الرَّسُولُ شَهِيدًا عَلَيْكُمْ وَتَكُونُوا شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ فَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَآتُوا الزَّكَاةَ وَاعْتَصِمُوا بِاللَّهِ هُوَ مَوْلَاكُمْ فَنِعْمَ الْمَوْلَىٰ وَنِعْمَ النَّصِيرُ
 

“በአላህም ሃይማኖት ተገቢውን ትግል ታገሉ፡፡ እርሱ መርጧችኋል፡፡ በናንተም ላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ምንም ችግር አላደረገባችሁም፡፡ የአባታችሁን የኢብራሂምን ሃይማኖት ተከተሉ፡፡ እርሱ ከዚህ በፊት ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል፡፡ በዚህም (ቁርኣን)፤ መልክተኛው በእናንተ ላይ መስካሪ እንዲሆን እናንተም በሰዎቹ ላይ መስካሪዎች እንድትኾኑ (ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል)፡፡ ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፣ ዘካንም ስጡ፣ በአላህም ተጠበቁ፣ እርሱ ረዳታችሁ ነው፡፡ (እርሱ) ምን ያምር ጠባቂ! ምን ያምርም ረዳት!” (አል-ሐጅ 22፤78)

ሌላው የኢስላምን ተጨባጭነት የሚያሳየው ጉዳይ ለጥሩ ሥራዎች ማበረታቻና ማጠናከሪያ፣ ከመጥፎ ሥራዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያዎችንና ማስፈራሪያዎችን ማድረጉ ነው። ይህም የሆነበት ምክኒያት ሰው በተፈጥሮው ጥሩ ለመስራት የሚንቀሳቀሰው ወደዚያ ጉዳይ የሚገፋፋውና የሚያበረታታው ነገር ሲኖር ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ መጥፎ ነገር ከመስራት የሚቆጠበው የሚፈራውና የሚከለክለው ነገር ሲኖር ነው። በመሆኑም ኢስላም የአላህን ምንዳ ማግኘት፣ ጀነትን መውረስና የተከበረውን የአላህን ፊት ማየት ለጥሩ ሰሪዎች ማበረታቻ አድርጓል። በአንጻሩም መጥፎ ሠሪዎች እንዲገሰጡና እንዲቆጠቡ የአላህን ቁጣና ገሀነምን ማስፈራሪያ አድርጓል።

የኢስላም ህግ ተጨባጭ ከመሆኑ አንጻር ለሰዎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አልከለከለመ፤ እንዲሁም ሰውን የሚጎዳ ነገርንም አልፈቀደም። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

يَا بَنِي آدَمَ خُذُوا زِينَتَكُمْ عِندَ كُلِّ مَسْجِدٍ وَكُلُوا وَاشْرَبُوا وَلَا تُسْرِفُوا إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الْمُسْرِفِينَ قُلْ مَنْ حَرَّمَ زِينَةَ اللَّهِ الَّتِي أَخْرَجَ لِعِبَادِهِ وَالطَّيِّبَاتِ مِنَ الرِّزْقِ قُلْ هِيَ لِلَّذِينَ آمَنُوا فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا خَالِصَةً يَوْمَ الْقِيَامَةِ كَذَٰلِكَ نُفَصِّلُ الْآيَاتِ لِقَوْمٍ يَعْلَمُونَ قُلْ إِنَّمَا حَرَّمَ رَبِّيَ الْفَوَاحِشَ مَا ظَهَرَ مِنْهَا وَمَا بَطَنَ وَالْإِثْمَ وَالْبَغْيَ بِغَيْرِ الْحَقِّ وَأَن تُشْرِكُوا بِاللَّهِ مَا لَمْ يُنَزِّلْ بِهِ سُلْطَانًا وَأَن تَقُولُوا عَلَى اللَّهِ مَا لَا تَعْلَمُونَ
 

“የአዳም ልጆች ሆይ! (ኀፍረተ ገላችሁን የሚሸፍኑትን) ጌጦቻችሁን በመስገጃው ሁሉ ዘንድ ያዙ፡፡ ብሉም፤ ጠጡም፤ አታባክኑም፡፡ እርሱ አባካኞችን አይወድምና፡፡

‘የአላህን ጌጥ ያችን ለባሮቹ የፈጠራትን ከሲሳይም ጥሩዎቹን እርም ያደረገ ማን ነው?’ በላቸው፡፡ ‘እርሷ በትንሣኤ ቀን ለእነዚያ ላመኑት ብቻ ስትኾን በቅርቢቱ ሕይወት ተገቢያቸው ናት’ በላቸው፡፡ እንደዚሁ ለሚያውቁ ሕዝቦች አንቀጾችን እናብራራለን፡፡

‘ጌታዬ እርም ያደረገው መጥፎ ሥራዎችን፣ ከርሷ የተገለጸውንና የተደበቀውን ኃጢኣትንም፣ ያላግባብ መበደልንም፣ በርሱም ማስረጃ ያላወረደበትን (ጣዖት) በአላህ ማጋራታችሁን፣ በአላህም ላይ የማታውቁትን መናገራችሁን ብቻ ነው’ በላቸው፡፡” (አል-አዕራፍ 7፤31-33)

ኢስላማዊ ህግ ከሰው ልጆቸ ተፈጥሮና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ስለሆነ የሰው ልጅ ያለውን የመጫዎት፣ የመዝናናትና የመደሰት ተፈጥሯዊ ዝንባሌና ፍላጎት ይቀበላል፡፡ ኢስላም በነዚህ ነገሮች ላይ ያደረገው ጉዳይ ቢኖር ሥርዓት እንዲኖራቸውና ድንበር እንዳያልፉ ማድረግ ነው፤ ነገር ግን ከናካቴው አልገደባቸውም ወይም አልከለከላቸውም፡፡ ቀልዶችና ጨዋታዎች ሐራም ያልሆኑ፣ አላህን የማያስረሱና ከኢባዳ የማይከለክሉ እስከሆኑ ድረስ በኢስላም የተፈቀዱ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ግን ከላይ የተጠቀሱትን ሐራም ነገሮች የሚያጠቃልል ጨዋታም ይሁን መዝናናን ኢስላም ይከለክላል፡፡ ለምሳሌ የሙዚቃ መሳሪያዎችን እየተጠቀሙ መጨፈር አጸያፊና አሳፋሪ ቃላቶችን በመናገር መዝፈን የተረከለከሉ ናቸው። ነገር ግን ጥሩ ቃላትን ተጠቅሞ ግጥም በመግጠም ከበሮ እየመቱ መዘመርን ኢስላም ይፈቅዳል።

ለዚህ ማስረጃ መጥቀስ ካስፈለገ አንድ ጊዜ ነብያን (ሶ.አወ) ቤት ውስጥ እርሳቸው ባሉበት ከበሮ እየመቱ ሁለት ሴት ልጆች ይዘፍኑ ነበር፤ አቡ በክር (ረ.ዐ) ይህን ሲያዩ እንዴት በነበያችን ቤትና በእርሳቸው ፊት ትዘፍናላችሁ ሲሉ ልጆቹን ወረፏቸው፤ ነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) ግን እንዲህ ሲሉ የልጆቹን ጨዋታ አጽድቀውታል፡-

دَعْهُمَا يَا أَبَا بَكْرٍ فَإِنَّهَا أَيَّامُ عِيد

“አቡበክር ተዋቸው አትከልክላቸው፤ ጊዜው የበዓል ቀናት ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

በተጨማሪም ይህንኑ በተመለከተ ነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

لِتَعْلَمَ يَهُودُ أَنَّ فِي دِينِنَا فُسْحَةً إِنِّي أُرْسِلْتُ بِحَنِيفِيَّةٍ سَمْحَة

“በሐይማኖታችን መጫዎትና መዝናናት አለ፤ እኔም በሐቅና ቀላል መንገድ ነው የተላኩት፤ ይህን ጉዳይ አይሁዶች ይወቁት።” (አህመድ ዘግበውታል)

በሌላ ግዜም ነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) ሐበሻዎች በመስጅድ ውስጥ እንዲዘፍኑ ፈቅደዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here