የኢስላም ልዩ ባህሪያት (ክፍል 1) – መለኮታዊነት (አር-ረባኒያ)

0
3550

አበይት የኢስላም መለያ ባህሪያት

ኢስላም ከሌሎች ሀይማኖቶችና አስተሳሰቦች ከሚለይባቸው አበይት ባህርያት (ኸሷኢስ አል-ዓም) ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. መለኮታዊነት (አር-ረባኒያ)
  2. ሰብዓዊነት (አል-ኢንሳኒያ)
  3. ሁለንተናዊነት (አሽ-ሽሙል)
  4. መካከለኛነት (አል-ወሰጢያ)
  5. ተጨባጭነት (አል-ዋቂዒያ)
  6. ግልጽነት (አል-ውዱህ)

መለኮታዊነት (አር-ረባኒያ)

ኢስላም መለኮታዊ ነው ስንል የኢስላም ምንጩ፣ መነሻውና መድረሻው ሁሉ ከአላህ (ሱ.ወ) ነው ማለት ነው።

የኢስላም ህግጋቶች በሁለት በኩል መለልኮታዊ ሆነው እናገኛቸዋለን፡-

  • 1ኛ የኢስላም ምንጩና መመሪያው መለኮታዊ ስለመሆኑ፡-

ኢስላም ወደሚፈልገው አላማ ለመድረስ ያስቀመጠው አቅጣጫ ጥርት ያለ መለኮታዊ መንገድ ነው፤ ምክኒያቱም የኢስላም ምንጩና መነሻው ከአላህ (ሱ.ወ) ወደ መጨረሻው ነበይ ሙሃመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላለፈወው መልእክት የአላህ ወህይ ስለሆነ ነው።

ይህ ኢስላማዊ የህይዎት መመሪያ በግለሰብ፣ ቤተሰብና ቡድን አለያም በህዝብ ፍላጎት የተገኘ አይደለም፤ ይልቁንም አላህ (ሱ.ወ) ራሱ ለሰዎች መመሪያና ብርሃን፣ እዝነትና ርህራሄ እንዲሆን ስለፈለገው የተገኘ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَكُم بُرْهَانٌ مِّن رَّبِّكُمْ وَأَنزَلْنَا إِلَيْكُمْ نُورًا مُّبِينًا 

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ዘንድ በእርግጥ አስረጅ መጣላችሁ፤ ወደእናንተም ገላጭ የኾነን ብርሃን (ቁርኣንን) አወረድን።” (አን-ኒሳእ 4፤174)

በሌላ የቁርኣን አንቀጽም እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَتْكُم مَّوْعِظَةٌ مِّن رَّبِّكُمْ وَشِفَاءٌ لِّمَا فِي الصُّدُورِ وَهُدًى وَرَحْمَةٌ لِّلْمُؤْمِنِينَ

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ግሳጼ በደረቶች ውስጥም ላለው (የመጠራጠር በሽታ) መድኃኒት ለምእምናንም ብርሃንና እዝነት በእርግጥ መጣችላችሁ።” (ዩኑስ 10፤57)

  • 2ኛ የአላማና የግብ መለኮታዊነት፡-

ኢስላም የመጨረሻ አላማና ግቡ የሚያደርገው የሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው አላህ (ሱ.ወ) ጋር ያለቸውን ግንኙነት ማሳመርና የርሱንም ውደታ ማግኘት እንዲችሉ ማድረግን ነው፤ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ሊለፋለትና ሊታገልለት የሚገባ ትክክለኛው አላማና የስኬት አቅጣጫ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الْإِنسَانُ إِنَّكَ كَادِحٌ إِلَىٰ رَبِّكَ كَدْحًا فَمُلَاقِيهِ
 

“አንተ ሰው ሆይ! አንተ ጌታህን (በሞት) እስከምትገናኝ ድረስ ልፋትን ለፊ ነህ፤ ተገናኚውም ነህ።” (አል-ኢንሺቃቅ 84፤6)

በሌላም የቁርኣን አንቀጽ እንዲህ ብሏል፡-

وَأَنَّ إِلَىٰ رَبِّكَ الْمُنتَهَىٰ
 

“መጨረሻውም ወደ ጌታህ ብቻ ነው።” (አን-ነጅም 53፤42)

በኢስላም ውስጥ የሚገኙ ማንኛቸውም ድንጋጌዎችና መመሪያዎች የሚያልሙት የሰው ልጅ ከማንም ባርነት ነፃ ሆኖ ትክክለኛ የፈጣሪው አላህ (ሱ.ወ) ባሪያ እንዲሆን ለማዘጋጀት ነው፤ ስለዚህም ነው የኢስላም ዋነኛ መንፈሱና ውስጠ ሚስጥሩ የኣላህን ብቸኛ አምላክነት ማረጋገጥ (ተውሂድ ) የሆነው።

ይህን እውነታ አላህ (ሱ.ወ) ለነብያችን ሙሃመድ (ሶ.ዐ.ወ) ያስረዳቸው ሲሆን ለሰው ልጆችም እንዲያሳውቁና እንዲያደርሱ አዟቸዋል፤ ታላቁ ጌታ እንድህ ብሏል፡-

قُلْ إِنَّنِي هَدَانِي رَبِّي إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ دِينًا قِيَمًا مِّلَّةَ إِبْرَاهِيمَ حَنِيفًا وَمَا كَانَ مِنَ الْمُشْرِكِينَ قُلْ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ لَا شَرِيكَ لَهُ وَبِذَٰلِكَ أُمِرْتُ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُسْلِمِينَ
 

“እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትክክለኛን ሃይማኖት ወደ እውነት አዘንባይ ሲኾን የአብርሃምን መንገድ መራኝ። እርሱም ከአጋሪዎቹ አልነበረም” በል። “ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው” በል። “ለእርሱ ተጋሪ የለውም። በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ። እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ” (በል) (አል-አንዓም 6፤161-163)

እርግጥ ነው በኢስላም ውስጥ የተለያዩ ድንጋጌዎችና የማህበራዊ ግንኙነት ሥርዓቶች ተቀምጠዋል፤ ነገር ግን የነዚህ ድንጋጌዎች ዋና ግብና አላማ የሰዎችን ሕይዎት ሥርዓት በማስያዝና የቅርቢቷን አለም ፀጋዎች ለመቆራመት ከሚያደርጉት ያላግባብ ግበግብ ነጻ ወጥተው ወደ ተከበረው ታላቁ አላማ አላህን መታዘዝና መገዛት እንዲዞሩ ማድረግ ነው።

በኢስላም ትግልና ጦርነት አለ፤ ዋናው አላማና ግቡ ግን አለማዊ ጥቅምና የበላይነት ማምጣት አይደለም። ይልቁኑ አላህ (ሱ.ወ) እንዳለው

وَقَاتِلُوهُمْ حَتَّىٰ لَا تَكُونَ فِتْنَةٌ وَيَكُونَ الدِّينُ كُلُّهُ لِلَّهِ فَإِنِ انتَهَوْا فَإِنَّ اللَّهَ بِمَا يَعْمَلُونَ بَصِيرٌ
 

“ሁከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሏቸው። ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው።” (አል-አንፋል 8፤39)

ኢስላም ሰዎች በመሬት ላይ በመንቀሳቀስ ጥሩ ሲሳይን በመፈለግ እንዲመገቡና እንዲጠጡ ያዛል፤ ቢሆንም የዚህ አላማው እንሰሳዊ ስሜትን ለማርካት ብቻ ሳይሆን የአላህን ፀጋ ለማመስገንና ሐቁንም ለማድረስ ነው።

كُلُوا مِن رِّزْقِ رَبِّكُمْ وَاشْكُرُوا لَهُ
 

“ከጌታችሁ ሲሳይ ብሉ። ለእርሱም አመስግኑ።” (ሰበእ 34፤15)

አላህ (ሱ.ወ) ጅንና የሰውን ልጅ የፈጠረበት ዋናው አላማ ሰፋ ባለው የኢባዳ ትርጓሜ መሰረት አላህን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ነው፤ እንዲህም ይላል፡-

وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ مَا أُرِيدُ مِنْهُم مِّن رِّزْقٍ وَمَا أُرِيدُ أَن يُطْعِمُونِ إِنَّ اللَّهَ هُوَ الرَّزَّاقُ ذُو الْقُوَّةِ الْمَتِينُ
 

“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም። ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም። ሊመግቡኝም አልሻም። አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኀይል ባለቤት ነው።” (አዝ-ዛሪያት 51፤56-58)

ኢስላም ከሰዎች ብረዛ፣ መቀነስና መጨመር የፀዳ መለኮታዊ የሆነ የህይዎት መመሪያ ነው። ሌሎች ሐይማኖቶች ግን ከፊሎቹ ከመጀመሪያው በሰው ልጆች የተመሰረቱ ሲሆኑ የሰው ልጆችን ህይዎት ሊያስተካክሉና ዘላቂ ደስታ ሊያመጡ አይችሉም፤ ምክኒያቱም እነዚህ እምነቶች ሰው ሰራሽ ስለሆኑ በሰው ልጅ ላይ ያሉት እንደ አለማወቅና ስሜትን መከተል የመሳሰሉ ድክመቶች ስለሚንፀባረቅባቸው ነው፤ ሌሎች ሐይማኖቶች ደግሞ መሠረታቸው መለኮታዊ ሆነው ነገር ግን በተለያየ ጊዜ በሰው ልጆች መበረዝና መቀያየር ደርሶባቸዋል፤ በዚህም ምክኒያት ቅዱስነታቸውና መለኮታዊነታቸው ጠፍቷል፤ ለምሳሌ የአይሁድና የክርስትና ሐይማኖቶችን መጥቀስ ይቻላል። አላህ (ሱ.ወ) እንድህ ይላል፡-

إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ
 

“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው። እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።” (አል-ሒጅር 15፤9)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here