መቼ ለመሞት አስበሃል?

0
9001

ምናልባት በዚህ ሰዓት የዩኒቨርስቲ ትምህርትህን አጠናቀህ ከተማሪነት ዓለም ወደ ሰራተኛው መደብ ልትቀላቀል የአንድ ሴሚስተር እድሜ ብቻ ቀርቶህ ይሆናል፤ አሊያ ደግሞ ከእጮኛህ ጋር ልትሞሸርና የአባወራነትን ማእረግ ከነሙሉ ጥቅሙና ክብሩ ልትጎናጸፍ ሁለት ሳምንታትን ብቻ እየጠበቅህ ይሆናል፤ ወይ ደግሞ ከዱባይ ያስጫንከው ውድ ዕቃ በወሳኝ ሰዓት ወደብ ደርሶ ገበያውን ልትቆጣጠረውና በሕይወት ዘመንህ አግኝተህ የማታውቀውን ትርፍ ልታጋብስና ተፎካካሪዎችህን ድባቅ ልትመታ ሁሉም ነገር ተሰካክቷል – ልክ እንደተቀባበለ ክላሽንኮቭ፤ . . . በዚህ ሁሉ መሃል ታዲያ አንተ መቼ ለመሞት አስበሃል?

ሚስትህ አይንህን ባይንህ ልታሳይህ ቀናትን እንድትጠብቅ ነግራሃለች፤ እቁብህ ሊወጣ ሰዓታት ቀርተውታል፤ ወይም ደግሞ ለዘመናት የደከምክለትን መጽሐፍ አጠናቀህ ለህትመት ልታበቃ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ያሉ ጥቂት ገጾች ብቻ ቀርተውታል፤ . . . እጅግ ሲበዛ የምትወደው የልጅነት ጓደኛህ፣ ክፉ ደግ አብራችሁ ያሳለፋችሁ፣ እንደውም ከበርካታ ችግሮች የታደገህ ከዘመናት በኋላ ከሚኖርበት አሜሪካን አገር አንተን ለመጠየቅ ከነ ቤተሰቡ አውሮፕላን ላይ መሳፈሩን “ሰርፕራይዝ“ ብሎ ነግሮሃል፤ . . . እኔ እምልህ . . . ታዲያ አንተ መቼ ለመሞት አስበሃል?

ያንተን ሃሳብ እንጃ እንጂ እኔ መቸም አሁኑኑ ሙት እልሃለሁ። ሙት! የምሬን ነው። አሁኑኑ ሙት – አሁኑኑ። ምንም እንኳ አስቸኳይ ጉዳይ ቢኖርህ፤ ምንም አንኳ አሳሳቢ ነገር ቢገጥምህ፤ ምንም እንኳ ጅምር ጉዳይህን ማሳካት ቢኖርብህም ሙት ግዴለህም።

መቼም የዘንድሮው አዝመራ ለጉድ ነው። ያንተ ደግሞ ለብቻው ነው። ሰው ሁሉ ጉድ ተሰኝቶበታል። አንተም አምላክህን በምን አስደስተህ ለዚህ ታላቅ ውለታ እንደበቃህ ማስታወስ ተስኖሃል። የሱ ችሮታ እንጂ የዚህ ዓይነት አዝመራ እንዴት ሆኖ ሊበቅል! እንዴት ሆኖስ ሊያፈራ? ለማንኛውም ይህን የመሰለ አዝመራ አሳጭደህ ወደ ጎተራህ ልታስገባ ቀን ቆርጠህ አጨዳው ላይ የሚሳተፉትን ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት ጓደኛ እድር፣ አገር ሽማግሌ ወዘተ… ነግረሃል፤ . . . የመጀመሪያ ሴት ልጅህን ድል ባለ ሰርግ ልትድርና ወግ ማዕረግህን ልታይ፣ ብድርህን ልትመልስ፣ ምን የመሰለ ሰርግ ሰርገሃል። አገር ሁሉ ጉድ የተሰኘበት ሰርግህ “ሰርግ ማለት የእገሌ ነው እንጂ” እየተባለ ገና እለቱ ሳይደርስ መተረት ጀምሯል፤ . . . ዋናው ነገር ታዲያ አንተ መቼ ለመሞት አስበሃል? የሚለው ነው።

ለዘመናት የለፋህበት የምርምርና የጥናት ውጤትህ (አዲሱ ግኝትህ) ለህዝብ ሊቀርብ በዚያም ሐገርና ህዝብን ልትጠቅም ያንተም ስምና ዝና በዓለም ላይ ሊናኝ ሰዓታት ቀርተውታል፤ . . . ከዘመናት ጥረት ግረት በኋላ ባፈራኸው ጥሪት ቤተ መንግስትን የሚያስንቅ ማለፊያ ቤት ገንብተሃል። የእልፍኙ ስፋት፣ የመኝታ ቤቱ ግርማ፣ የመስኩ ውበት (በግቢው ውሥጥ ያለው)፣ መዋኛ ገንዳው ሁሉ ሳይቀር ልዩ ነው። ግንባታው የተከናወነው በውድ ቁሳቁሶች ሲሆን ባለሙያዎቹ ደግሞ በመስኩ አንቱ የተባሉ ናቸው። በውድ ቁሳቁስና በጥሩ ባለ ሙያ የተሰራ ቤት ማማር ሲያንሰው ነው። ጥንካሬም ጌጡ ነው። ታዲያ ይህን የመሰለ ቤት አስመርቀህ ልትገባበት ምን ቀረህ? ምንም! . . . ታዲያ አንተስ! መቼ ለመሞት አስበሃል?

የእህል ውሃ ነገር አያስገባው የለ፤ ራስህን ችለህ ቤተሰብህን ከችግር ለመታደግ ስደት ጀምረሃል። መቼም የስደት ነገር መሃሉ አይነገርምና የሰማኸውና አንተን የገጠመህ አይገናኝም። ’’ሰው ሁሉ ይህን መሰል ከባድ ፈተናና ችግር ተቋቁሞ ነው ያለፈለት ወይስ የኔ የብቻው ነው?’’ ብለህ መቆዘምህ አልቀረም። ቁርና ሀሩር ተፈራርቀውብሃል። በተለይ በተለይ በበረሃ ላይ ያደረከውን ጉዞ ያክል አስቸጋሪና ፈታኝ ነገር ገጥሞህ እንደማያውቅ ልብ ብለሃል። የዉሃ ጥሙ ኃይለኝነት የሰዓታት ሳይሆን ከተፈጠርክ ጀምሮ የተጠራቀመ የውሃ ፍላጎት ውጤት መስሎሃል። የሰውነትህ ፈሳሽ ሁሉ ተሟጦ አልቆ ግንባርህ የጨው ግግር ማምረት ጀምሯል። ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ አልፈህ ደስ የሚል ጥላ ያለው ዛፍ ስር ደርሰሃል። አየሩ ብቻ ምግብ ነው። ከስሩ ኩልል ያለ የምንጭ ውሃ ሲኖር ድምጹ መንፈስን ይማርካል። አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያ ሁሉ ድካምና ስቃይ ብን ብሎ ጠፍቶ በምትኩ ትልቅ እፎይታና እርካታ ተጎናጽፈሃል። . . . ታዲያ መቼ ለመሞት አስበሃል?

የፊታችን እሁድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የሙሐደራ ፕሮግራም በከተማይቱ እምብርት ላይ በሚገኘው ሰፊ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ላይ ይከናወናል። በዚያ ፕሮግራም ላይ ብቻ ከሃምሳ ሽህ ሰዎች በላይ በአካል እንደሚገኙበት ተተንብዮአል። ፕሮግራሙ በከተማይቱ በሚገኙ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ላይ በተሰቀሉት ታላላቅ ዲስፕሌዮች ከመታየቱ በተጨማሪ በተለያዩ የቴሌቪዢን ጣቢያዎች ጭምር በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል። የዚህ ፕሮግራም ቁልፍ ሰው ደግሞ አንተ ነህ። ህብረተሰቡ ያንተን ንግግር ለማድመጥ ካለው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ከሩቅ የክፍለ ሃገር ከተሞች ሳይቀር ከፕሮግራሙ መጀመር ሳምንታት አስቀድሞ ወደ ከተማው ተምሟል። ታላላቅ ሰዎች ሳይቀሩ ፕሮግራሞቻቸውንና የውጭ ጉዟቸውን ጭምር በመሰረዝ ያንተ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ወስነዋል። አንተም ብትሆን የዋዛ አይደለህምና ፕሮግራሙን ለማድመቅና ህብረተሰቡ ከጠበቀው በላይ ተጠቃሚ እንዲሆን ለወራት በከባዱ ተዘጋጅተሃል። ይሁንና ታዲያ አንተ መቼ ለመሞት አስበሃል?

.  .  .  .  .  .  .  .  .  .

ያንተን ሃሳብ እንጃ እንጂ እኔ መቸም አሁኑኑ ሙት እልሃለሁ። ሙት! የምሬን ነው። አሁኑኑ ሙት – አሁኑኑ። ምንም እንኳ አስቸኳይ ጉዳይ ቢኖርህ፤ ምንም አንኳ አሳሳቢ ነገር ቢገጥምህ፤ ምንም እንኳ ጅምር ጉዳይህን ማሳካት ቢኖርብህም ሙት ግዴለህም። የሚሻለው እሱ ነው – ለሞት ቀጠሮ መስጠት ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? ከስንት ልፋትና መከራ በኋላ ያፈራኸውን ሀብትና ንብረት ተረጋግተህ በሰከነ አኗኗር ማጣጣም አልጀመርክ ይሆናል። ይሁና! ሙት ከተባልክ መሞት ነው። በስንት ጾምና ጸሎት የተወለደውን ልጅህን አቅፈህ መሳም አምሮህም ይሆናል፤ ቢሆንም ሞት ነውና ሙት። . . . ወንድሜ ሆይ ምነው ግራ የተጋባህ ትመስላለህ። ነገሩ ጠናህ እንዴ? . . . “አይዞህ ሊገባህ ነው” አሉ ሸኽዬ።

እስቲ አንዳንድ ጉዳዮችን እንጨዋወት። መቼም የነጋዴ ዓላማ ነግዶ ማትረፍ ነው። ጠቀም ያለ ትርፍ ያለውን ነገር አነፍንፎ በጥሩ ዋጋ መሸጥ ደግሞ ከጉብዝና ይቆጠራል። ትርፍን የእጥፍ እጥፍ የሚያሳድግ አጋጣሚ ሲገኝ ደግሞ “ዋው” ያስብላል። ስለዚህ ከትርፋማው እቃ ላይ አንዳንድ ነገሮች ቢታከሉበት ትርፉ ትርፍርፍ ይላል። ተጠቃሚም “ጥሩ” ዕቃ በተመጣጣኝ ዋጋ ያገኛል። ከነገዱ አይቀር በደንብ ማትረፍ ነው እንጂ ቁጥ ቁጥ ምን ያደርጋል። አንዴ ዘጋ አድርጎ ራስን መለወጥ እያለ የምን መትነፍነፍ ነው። የገበያውን ሁኔታ አጢኖ ከዚህ ቀደም ተወዳጅ የሆነችውን ዕቃ በሆነ ነገር ቀይጦ ብቻ ጉዳት የማያስከትል ይሁን እንጂ (ቢያስከትልስ አበሻን መች ጀርም ይገድለውና) ቸብ ቸብ አድርጎ ዘወር ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ሌላ የተሻለ ዝግ ያለውን ፈልጎ መሰማራት። ያኔ ደንበኞች በዚህኛው የስራ መስክ በደንብ ይካሳሉ። አሪፍ አይደል ታዲያ! በጣም እንጂ!! . . . ግን የቅድሙን ምክሬን አስታውስ – ሙት ያልኩህን። አሁኑኑ ሙት ያልኩህን። ስራውን ጀምረኸውም ሊሆን ይችላል ወይም መሀል ላይ ብቻ መሞትህን አትዘንጋ – ሙት። . . .

ይገርማል ያ ሁሉ ልጃገረድ ባንተ ሃብትና ዝና ሲነሆልል ያቺ “ኬቲ” ብቻ ጥብርር ማለቷ ይገርማል። አትጠቀሚ ቢላት ነው እንጂ አንተን የመሰለ ሸበላ፣ መለሎ፣ ዲታ፣ ተጨዋች ጠይቋት እምቢ ማለቷ ካሰገራሚ ነገሮች ውስጥ እጅግ በጣም አስገራሚው ነው – ለበርካቶች። ሴቱ ሁሉ ያንተን ቀላል ሰላምታ ለማግኘት ስንት እንዳልተራኮተ እሷ ግን በስንት ምልጃና ልመና ልትነካ አልቻለችም። በርግጥ ውብ ነች – ውብ የሚለው ቃል ከገለጻት። ቁመናዋ ሌላ ነው። ጨዋታ አዋቂ ናት። ሳቅና ፈገግታዋ ልብን ይንጣል። እንደዘመኑ ሴቶች መልክ ብቻ ሳትሆን ቁም ነገረኛም ነች። አስተሳሰቧ ለነገሮች ያላት ምልከታና ትንታኔ አጃኢብ ያሰኛል። አንተንስ የማረከህ ምን ሆነና። የሷን ይሁንታ ለማግኘት ያልከፈልከው መስዋዕትነት መች አለና። ህይወትህን ገብር ብትባልስ ወደ ኋላ የምትል ይመስልሃል? እርግጠኛ አይደለህም። ዛሬ ግን ልዩ ቀን ነው ላንተ። “ኬቲ”ን የመሰለች ሸጋ ልጅ የግልህ አድርገሃል። ከስንት ስቃይና ልፋት በኋላ ከቅፍህ ገብታለች። ውበቷ ደግሞ ከወትሮው ተለየብህ። ይበልጥ ውብ ይበልጥ ትሁትና አስተዋይነቷ ተገለጠልህ። ከዚህ በኋላ ምን የቀረ ነገር አለ? ምንም! ወደ ገደለው . . . ነዋ! . . . ምክሬን ግን አትዘንጋ! ሙት ብያሃለሁ ሙት – ከዚና በፊትም ቢሆን!

ከተማው መሐል ላይ የሚገነባው ባለ ሀምሳ ምናምን ሰማይ ጠቀስ ፎቅ የሰው መነጋገሪያ ከሆነ ቆዬ። ስምህና ዝናህም የዛኑ ያክል በየ ጋዜጣው፣ በየ መጽሄቱ፣ በራዲዮና ቴሌቭዥን ሁሉ ተወራልህ። ያንተን ፎቶ ሳይዝ የወጣ ጋዜጣ፣ ያንተን ስም ያልጠቀሰ መጽሄት ምን ያማረ ስራ ይዞ ቢወጣ ዞሮ የሚያየው ገዥ የለም። አንተ በምታልፍበት ጎዳና ሁሉ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባልተናነሰ መልኩ መንገድ ይዘጋልሃል፤ አጃቢ ይመደብልሃል። ምክንያቱም የሀገሪቱ ዋልታና መከታ ሆነሃል። ያንተ ቢዝነስ ማትረፉ የሀገሪቱ ማትረፍ ነው። ኪሳራህም እንደዛው። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ታላላቅ ፕሮጅክቶች በሙሉ ያንተ አሊያም ያንተ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው። ተፅዕኖህ ከሀገር ውስጥ አልፎ አለማቀፍ ይዘትን መጎናጸፍ ጀምሯል። በቅርቡ በተከናወነው የዓለም መሪዎች ጉባዔ ላይ የክብር እንግዳ በመሆን ተጋብዘሃል። በዚያ ስብሰባ ላይም የነበረው አቀባበልና ከበሬታ ከጠበከው በላይ ነበረ። እነዚህና መሰል ጉዳዮች ተደማምረው አንተ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም። ከዚህ የተነሳም በሀገሪቱ ለሚከናወኑ የልማት ተግባራት ጠቀም ያለ ድጎማ አድርገሃል። ከውጭ ሀገር በመግባት ላይ ያሉት ውድ እቃዎች ወደብ ቢደርሱም ባንዳንድ ያሰራር ሂደቶች በታሰቡበት ሰዓት ወደ ገበያ ሊገቡ አልቻሉም። ይህና ሌሎች መሰል ክስተቶች የስራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆነዋል። ስራዎች መጓተት የለባቸውም። በተለይ ደግሞ የህብረተሰቡ ዓይን ያረፈበትና የሀገሪቱ መለያ ይሆናል ተብሎ የታሰበው ህንጻ በምንም መልኩ ስራው ዝንፍ ማለት የለበትም። ጭራሽ በገንዘብ እጥረት ነው የቆመው ተብሎ እንዲወራማ በፍጹም አትፈልግም። እንዲህ ተወርቶ ሰውስ ምን ይላል? ለክብርህ አይመጥንም። ባይሆን አማራጮችን መጠቀም ጥሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ዓይነተኛው አማራጭ ባንክ ነው። ምንም እንኳ የሚፈለገው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ቢሆንም አንተ ጠይቀህ መከልከል ቀርቶ ማቅማማት አይታሰብም። እንደውም የመበደርህ ወሬ ከደረሳቸው ራሳቸው መጥተው ምን ያህል እንፍቀድልህ ብለው ባለ በሌለ አቅማቸው ይሽቀዳደማሉ። መቼም አራጣ ክፉ መሆኑን ብታውቅም ከዚህ አጣብቂኝ መውጣትህ ግድ ነውና . . . ለማንኛውም ምክሬን ደግመህ ደጋግመህ ስማ – ሙት!       መቼ?         አሁኑኑ!!!

አሁን ላይ የምትሰራውን ስራ አሁኑኑ እንደምትሞት ሆነህ ካልሰራኸው ልታበላሸው፣ ወይም ልትተወው፣ ወይም ሌላን በሚጎዳ መልኩ ልታጣምመው ትችላለህ። ይህችን የሰከንድ ሽርፍራፊ እንዴት ካለብክነት ልትጠቀምባት እንደምትችል ለመጠበብ ከፈለግህ ሞትህን አሁን አድርገው።

ወንድሜ ሆይ! የሚሻለው ይኼ ነው – መሞት – አሁኑኑ። አለበለዚያማ መቼም ላትሞት ትችላለህ – በሃሳብህ ማለቴ ነው እንጂ በዟሂርማ ምን ጥያቄ አለው። አሁን ላይ የምትሰራውን ስራ አሁኑኑ እንደምትሞት ሆነህ ካልሰራኸው ልታበላሸው፣ ወይም ልትተወው፣ ወይም ሌላን በሚጎዳ መልኩ ልታጣምመው ትችላለህ። ይህችን የሰከንድ ሽርፍራፊ እንዴት ካለብክነት ልትጠቀምባት እንደምትችል ለመጠበብ ከፈለግህ ሞትህን አሁን አድርገው። አሁን ልትሞት ነውና ባለችህ ጥቂት ሰከንድ ወይም ደቂቃ ለሞትህ ምን ማድረግ እንዳለብህ በደንብ ትገልጽልሃለች። ዋጋዋ ምን ያህል እንደሆነና እሷን ማባከን ምን ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በደንብ ትገነዘብበታለህ። ከወንጀል ራስህን ማስገዛት ካማረህ አሁኑኑ ከመሞት የተሻለ አማራጭ ከየት ታገኛለህ። የሚሞት ሰው ወንጀል ለምን ይሰራል? ጌታውን ሊያስደስት አትለኝም መቼም። ለመልካም ነገር ተሸቀዳደሙ ተብሎ የለ እስቲ ሞትህን አሁን አድርገው . . . የትኛውን መልካም ስራ ጠበቅ ታደርግ ነበር? የትኛውን ክፉ አመል እርግፍ አርገህ ትተው ነበር?

መሞትህ እርግጥ ሆኖ ሳለ ሞትህን እሩቅ አድርገኸው የማትሞት እየመሰለህ ተታለሃል። ሞትህን አሁን አድርገው። ያኔ ጊዜና ንብረትህን ባግባቡ ትጠቀምበታለህ፤ መልካም ስራ ላይ ትዘወትራለህ፤ እኩይ ባህሪዎችህን ትተዋለህ፤ የራስህን፣ የወላጆችህን፣ የቤተሰብህን፣ ባጠቃላይ የህብረተሰቡን ሀቅ ጠባቂ ትሆናለህ። ይህን ሁሉ ማድረግ ከቻልክ ምን ያላደረከው ነገር አለህ? “ምንም” አትለኝም። ስለዚህ ሙታ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here