አል-ወሰጢያ:- መገለጫዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች

0
6652

በመጀመሪያ አል-ወሰጢያ የሚለው ቃል የሚወክለውን ፅንሰ-ሀሳብ ከማብራረታችን በፊት ትንሽ ትርጉማዊ መንደርደሪያ ለማድረግ እንሞክር። አል-ወሰጢያ መካከለኛው መንገድ፣ ሚዛናዊ አካሄድ፣ ወርቃማ አማካይ (golden average) የሚሉት ቃላት የሚያስተላልፉትን ትርጉም ያስተላልፋል።

ወሰጢያ አስተሳሰብ ነው፤ ወሰጢያ አካሄድ ነው፤ ወሰጢያ ተግባራዊነት ያለው የህይወት ዘይቤ ነው። ወሰጢያ የኢስላም ሰማያዊ መልእክት መሬት ላይ ሊፈጥር የሚፈልገውን በተለያዩ ዘርፎች ሊገለፅ የሚችል የህይወት ዘይቤ ከየትኛውም ፅንፈኛ መገለጫ ነፃ የሚያደርገና መሀከለኛነትንና ሚዛናዊነትን የሚያላብስ ጥልቅ ፅንሰ-ሀሳብ ነው።

አል-ወሰጢያ የዚህ ኡማ ምልክቱ ነው። ከሌሎች ነቢያት አስተምህሮቶች ኢስላም ተለይቶ የሚታወቅበት ልዩ ባህሪው ነው። ታላቁ ዓሊም ሸይኽ ኢብኑ ተይሚያህ ይህን ጉዳይ እንዲህ ይገልጹታል፡-

قد خص الله تبارك وتعالى محمدًا صلى الله عليه سلم بخصائص ميّزه الله بها على جميع الأنبياء والمرسلين، وجعل لهشِرْعة ومنهاجًا أفضل شرعة، وأكمل منهاج مبين، كما جعل أمته خير أمة أخرجت للناس؛ فهم يوفون سبعينأمة هم خيرها، وأكرمها على الله من جميع الأجناس، هداهم الله بكتابه ورسوله لما اختلفوا فيه من الحق قبلهم،وجعلهم وسطًا عدلا خياراً ؛ فهم وسط في توحيد الله وأسمائه وصفاته، وفي الإيمان برسله وكتبه، وشرائع دينهمن الأمر والنهي والحلال والحرام

“አላህ ረሡልን (ሰ.ዐ.ወ) ከሌሎቹ ነቢያት የተለየ ያደረገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የተለየና የላቀ ሃይማኖታው ሥርዓትና አስተምህሮት መስጠት፣ የሁሉንም የህይወት ዘርፍ ያካተተ ምሉዕ መመሪያ ማጎናጸፍ፣ በተከታዮቻቸው ላይም የሰውን ልጅ የመምራትን ታላቅ ኃላፊነት መጣል የሚጠቀሱት ናቸው ።…. የሳቸውን ኡማ ሚዛናዊ፣ መካከለኛ፣ ፍትሃዊና ምርጥ አድርጎታል። ተከታዮቻቸው የእምነተታቸው መሰረት በሆነው በአላህ አንድነት (ተውሂድ)፣ በአላህ ስሞችና በባህሪያቱ፣ በመልዕክተኞቹና በመፃህፍቱ እንዲሁም በሌሎች ዲናዊ ድንጋጌዎች ላይ መካከለኛውን አቋም እንዲይዙ አድርጓል።”

ወሰጢያ የእስልምና ልዩ መገለጫ ቢሆንም ይህ መገለጫ በተጨባጭ በተገቢው መልኩና ክንውኑ ሲተገበር አናስተውልም። ከፊሎች ግትርነትን የተላበሰና ጽንፈኝነትን መሰረት ያደረገን መንገድን ሲመርጡ ይስተዋላል። ሌሎች ቁንፅል የሆነ አካሄድን ሲመርጡ ይታያል። እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ስያሜው ሽፋን በማድረግ ፅንሰ ሀሳቡ የማይወክለው ስህተት ሲሰራ፣ ሀቁ በሐሰት ሲሸፈን ያጋጥማል። ለግል ፍላጎትና ለተራ ምድራዊ ጥቅም ይህን መንገድ ሽፋን አድርጎ የሚጠቀምም አይጠፋም። ስለዚህ የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ይህን ልዩና ድንቅ ኢስላማዊ ፅንሰ-ሀሳብ ማብራራትና እንድምታዎቹን ማመላከት ይሆናል።

የአል-ወሰጢያ (መካከለኛው መንገድ) እንድምታዎች

ወሰጢያ ኢስላም ሊፈጥረው የሚፈልገው ህብረተሰብ መካከለኛና ሚዛናዊ እንደሆኑ ያመላክታል። አላህ ይህን በተመለከተ በቁርዓኑ እንዲህ ይገልፃል ፡-

وَكَذَٰلِكَ جَعَلْنَاكُمْ أُمَّةً وَسَطًا لِّتَكُونُوا شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ وَيَكُونَ الرَّسُولُ عَلَيْكُمْ شَهِيدًا

“እንደዚሁም (እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ምርጥ (መካከለኛ) ሕዝቦች አደረግናችሁ።” (አል-በቀራ 2፤143)።

ወሰጢያ ማንኛውም ሰው ኢስላማዊውን አስተምህሮ በጠራና ብስለት ባለው መንገድ እንዲተገብር የሚያስችል ድንቅ ፅንሰ-ሀሳብ ነው። እንዲሁም ወሰጢያ የጠራውን የኢስላማዊ አስተምህሮ ምንጭ መሰረት በማድረግ ተከታዮቹ በሰዎች መካከል ፍትህን እንዲያሰፍኑ፣ መልካምነትን እንዲያስፋፉ፣ የአላህን አንድነት መሰረት በማድረግ ምድርን ለሰው ልጅ መኖሪያነት ለማሳመር እንዲጥሩና፣ በሠዎች መካከል ወንድማማችነትን ሰብዓዊነትን ለማበልፀግ ይቆሙ ዘንድ መሰረታዊ መርሆዎችን ያስቀምጣል። ቁርአን

وَكَذَٰلِكَ جَعَلْنَاكُمْ أُمَّةً وَسَطًا لِّتَكُونُوا شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ وَيَكُونَ الرَّسُولُ عَلَيْكُمْ شَهِيدًا
 

“እንደዚሁም (እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ምርጥ (መካከለኛ) ሕዝቦች አደረግናችሁ።” ይላል። (አል-በቀራ 2፣143)

በሌላ አንቀፅም

قَالَ أَوْسَطُهُمْ أَلَمْ أَقُل لَّكُمْ لَوْلَا تُسَبِّحُونَ

“ትክክለኛቸው (መካከለኛው) ‘ለእናንተ አላህን ለምን አታጠሩም አላልኳችሁምን?’ አላቸው።” (አል-ቀለም 68፣28)።

በሁለተኛው የቁርኣን አንቀፅ አገባብ የወሰጢያን መንገድ የያዙ ማለት፣ በጣም ፍትሃዊውና የበሰለ አስተሳሰብ ያላቸው ማለት ነው።

ወሰጢያ ማለት ተግባራዊ ክንዋኔን ሚዛናዊውና መሃከለኛነት መሰረት ባደረገ መልኩ መፈፀም ማለት ነው። ለዚህም ሦስት ሰዎች የረሡልን ስራዎች-ኢባዳዎች ከባለቤቶቻቸው ጠይቀው ኢባዳዎቹን አሳንሰው ተመልክተው በተለያዩ የአምልኮ ተግባራት ራሳቸውን ከልክ በላይ ለማሳተፍ መወሰናቸውን በመስማት ረሡል (ሰ.ዐ.ወ) የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡-

 أما والله إني لأخشاكم لله وأتقاكم له، ولكني أصوم وأفطر، وأصلي وأرقد، وأتزوج النساء،.فمن رغب عن سنتي فليس مني

“እኔማ በአላህ ይሁንብኝ! ከሁላችሁም እጅግ በጣም የበለጥኩ አላህ ፈሪ እና ጥንቁቅ ነኝ። ቢሆንም ግን እጾማለሁ፤ አፈጥራለሁ፤ እሰግዳለሁ፤ እተኛለሁ፤ ሚስትም እገባለሁ። ከኔ ሱና ያፈነገጠ የኔ (እውነተኛ) ተከታይ አይደለም።” (ሙስነድ አህመድ)።

በእምልኮ ተግባራት እንኳን ሚዛናዊነትን ወሰጢያ ይሰብካል። ሰሓቦችና ቀጣዩ ትውልድ፣ መካከለኛውን መንገድ በዚህ ሁኔታ ነው የተገነዘቡት። ኢማሙ ዓሊይ፡-

عليكم بالنمط الأوسط، فإليه ينزل العالي، واليه يرتفع النازل

“መካከለኛውን መንገድ አደራችሁን! ከፍ ያለውም ዝቅ፤ ዝቅ ያለውም ከፍ ይልበታል (ለጠንካራውም ለደካማውም-ለሁሉም አማካኝ ነው)” ብለዋል። በሌላ ዘገባ ደግሞ፡-

يلحق بهم التالي، ويرجع إليهم الغالي

“እታች (ተከታዩ-ከስር) ያለው የሚያገኘው እና እላይ የወጣው ደግሞ የሚመለስበት ነው” ብለዋል (አቡ ዑበይድ የዘገቡት)።

ዑመር ኢብኑ ዐብዱል ዐዚዝ ደግሞ፡-

إنّ من أحب الأمور إلى الله القصد في الجدة، والعفو في المقدرة، والرفق في الولاية، وما رفق عبدٌ بعبد في الدنياإلا رفق الله به يوم القيامة

“አላህ በጣም ከሚወዳቸው ነገሮች መካከል በብርታት ወቅት መካከለኛ መሆንን፤ መበቀል እየቻሉ ይቅርታ ማለትን፤ ባለሥልጣን ሲሆኑ ሩህሩህ መሆንን ነው። አንድ ሠው በዱንያ ሩህሩህ ከሆነ፣ አላህ በዕለተ-ቂያማ ይራራለታል” ብለዋል (ኢብኑ አቢ ሸይባና ኢብኑ ሲሪይን)።

ረሡል (ሰ.ዐ.ወ) መካከለኛውን መንገድ ሙስሊሞች የሙጥኝ እንዲሉ አደራ ብለዋል። ከጽንፈኝነት፣ ጠርዘኝነትና፣ ድንበር ከማለፍ እንዲርቁም መክረዋል። ረሡል ይህን አስመልክተው በተናገሩት መልዕክታቸውም፡-

 واياكم والغلو في الدين، فإنما هلك من كان قبلكم بالغلو في الدين

 “ከጽንፈኝነት አደራችሁን (ራቁ)! ከእናንተ በፊት የነበሩት ህዝቦች ያጠፋቸው በሀይማኖት ጽንፈኛ መሆን ነው” ብለዋል (አህመድና ነሳኢ)።

በሌላ ሐዲስም፡-

يسروا ولا تعسروا، وبشروا ولا تنفروا، إنما بعثتم ميسرين ولم تبعثوا معسرين

“አግራሩ (አቅልሉ)፣ አታጠባብቁ፤ አብስሩ፣ አታስደንብሩ። እናንተ የተለካችሁት ለሠዎች ልታግራሩ እንጅ፣ ልታጠባብቁ አይደለም” ብለዋል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

በአሁኑ ዘመን ያሉ የኢስላም ሊቃውንትም ህዝበ-ሙስሊሙ ወሰጢያን እንዲኖርና እንዲተገብር ጥሪ አድርገዋል። የኢስላም የዘመኑ ሊቅ የሆኑት ሸይኽ ዩሡፍ አል-ቀርዷዊና ዶ/ር ሙሐመድ ዐማራ “ወሰጥያን” ሲገልፁት፡- “ወሰጥያ ማለት በሁሉም ነገር ሚዛናዊ መሆን ነው” ይላሉ።

የፊዚላል አል-ቁርአን ፀሐፊና አዘጋጅ ሰይድ ቁጥብ ደግሞ የሙስሊሙ ኡማ ወሰጢያን በመተግበር ለሰው ልጅ አርአያ መሆን እንዳለበት ያመላክታሉ። በእምነት፣ በአመለካከት፣ በርዕዮተ-ዓለም፣ የህይወት ስርኣትን በመዘርጋትና ውጫዊና የእርስ በርስ ግንኙነቶች በመመስረት ሁሉ ሚዛናዊነትና መሃከለኛነትን እንዲይዝ የታዘዘ ኡማ ነው ይላሉ (ፊ ዚላል አል-ቁረኣን ቅ 1፣199-200)። ሸይኽ አቡበክር አል-ጀዛኢሪይና ሸይኽ ኢብራሂም ሰዕዲይ ደግሞ፣ ይህ ኡማ ሚዛናዊ /ፍትሃዊ/ ነው ይላሉ (አይሰሩ አት-ተፋሲር)። የመካከለኛው መንገድ ተቃራኒ የሆነው ጽንፈኝነት በኢስላማዊው አስተምህሮ ቦታ የሌለውና በሸሪዓው በጽኑ የተወገዘ ተግባር ነው።

መገለጫዎች

የወሰጢያ መንገድ መገለጫዎች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. የዕውቀት ምንጮች መስተጋብር፡- ይህም ማለት ከሰማይ የወረደውን ወሕይ (ራዕይ)ንና ሰብአዊ መሰረት ያለውን አዕምሮኣዊ እውቀትን (አቅል) በአንድ ላይና በተጣጣመ መልኩ መጠቀምን (harmony between revelation and reason/ ተውሂድ መሷዲር አል-ማዕሪፋ) ያመላክታል። ማለትም “ወህይ” የሸሪዓው የህግጋት ምንጭ ሲሆን፣ አዕምሮ ደግሞ ይህን “ወህይ” በመገንዘብና በመረዳት እንዲሁም የተጨባጩ ዓለም እውቀት ምንጭ በመሆን መስተጋብር ያደርጋሉ። ይህ የወሰጢያ መገለጫ የሃይማኖቱ ሸሪዓዊ እውቀቶችንና ሰብአዊ የእውቀትን አድማሶች አጣምሮና አስማምቶ የመጠቀም ስርአትን ያመላክታል። የወህይን ዉጤት ከትክክለኛ ምንጩ መወሰዱን በማረጋገጥና የአእምሮ ውጤትን ደግሞ ትክክለኛነት በማረጋገጥ ላይ ይመሰረታል።
  2. የውስጣዊና የውጫዊ ገፅታዎች ተጣምሮነት፡- የወሰጢያ መንገድ በእስልምና ህግጋት ለሚጠቃለሉ ስራዎች መንፈሳዊና ውስጣዊ ገጽታዎችና (ባጢን) ስራዎቹ ላላቸው ውጫዊ መገለጫዎችም (ዟሂር) ትኩረት ይሰጣል (አተላዙም በይነ ዟሂር ወልባጢን)። አንድ ስራ ከልብ በሚመነጩ መንፈሳዊ ግፊቶችና በአካል በሚገለፁ እንቅስሲዎች መስተጋብር ምሉዕ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። (ዒሷም በሺር፣ አል-ሒዋር መፍሁሙሁ ወዶሩራቱሁ ወአንዋኡሁ፣ 15)
  3. መቀበልና መፍጠር (ኢቲባዕ ፊዲን ወልኢብቲዳዕ ፊኡሙር አድ-ዱንያ) ፡- የሃይማኖቱ መገለጫ የሆኑ ጥርት ያሉ እንደ ፆም፣ ሰላት፣ ሀጅ ያሉ የአምልኮ ተግባራትና የሃይማኖት ክፍሎች ላይ ያለ ምንም ሰብኣዊ ጣልቃ ገብነት ተቀብሎ መተግበርን (ኢቲባዕን) መሰረት ሲያደርግ የህይወት መገለጫ በሆኑት ዘርፎች (ኡሙር አድ-ዱንያ) ደግሞ መመራመርን አዳዲስ ፈጠራዎች ማስገኘትን (ኢብቲዳዕ) መሰረት ያደርጋል።
  4. ኢስላማዊ መረጃን በተገቢው ከምንጩ መውሰድና ብሩህ አዕምሮን መጠቀም (ሲሃታል ነቅል ወሶራሃታል አቅል)፡- ኢስላማዊ መረጃዎችን ከመተንተንና መረዳት አኳያ ሁለት ኢስላማዊ የትምህርት ተቋማት (መድረሳ) ይስተዋላሉ። አንደኛው ተቋም መረጃዎችን ከምንጩ በጥንቃቄና በጥሬው ወስዶ የሚጠቀም ሲሆን (መድረሳ አል-አሰር)፣ ሌላኛው ደግሞ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ በራሳቸው አተያየት የሚተነትኑ (መድረሳ አል-ራዕይ) ናቸው። አል-ወሰጢያ የነዚህን ሁለት ኢስላማዊ የትምህርት ተቋማትን ሸሪዓዊ አመለካከታቸውን አጣምሮ በሚዛናዊነት ያራምዳል።
  5. ምድራዊ ልማትና መንፈሳዊ ምጥቀት ማጣመር፡- ይህ ማለት በቁሳዊና በመንፈሳዊ ጉዳዮች በኩል ሚዛናዊ መሆንን የሚገልፅ ነው። ዱንያ (የምድሪቱ ዓለም) ዘላለማዊውን የአኺራን ህይወት ለማሳመር የስራ ተጨባጭ እንደሆነች ይሰብካል። ምድራዊ ልማትና መንፈሳዊ ምጥቀት በዚህች ዓለም ውስጥ በአንድ ላይ ተግባራዊ መሆን እደሚችሉና እንደሚገባቸው ያውጃል።
  6. በተገቢው ሰውና በተገቢው ቦታ ኢጅቲሃድ ማድረግን ይደግፋል
  7. የዓላማ መሰረታዊነትና የማስፈፀሚያ መንገዶች መለያየት፡- የሸሪዓው ዓላማ እስከተጠበቀ ድረስ የማሳኪያው ዘዴዎች እንደጊዜውና እንደቦታው የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ ያስገባል (አሰባት ፊልአህዳፍ ወል ሙሩና ፊልወሳኢል)።
  8. በቅርስ (ቱራስ) ላይ ሚዛናዊ አቋም መያዝ፡- የቀደምት ሙስሊም ምሁራን የእውቀት ውጤቶችን (ቱራስ) ሙሉ በሙሉ በመቀበልና ሙሉ በሙሉ በመቃወም ማካከል ሚዛናዊነትን ያማከለ አቋምን መሰረት ያደርጋል።
  9. ምሉዕ ሰብዕና ግንባታ፡- የሠው ልጅ አዕምሮኣዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ገፅታ ያለው ፍጡር ነው። በመሆኑም ለሰው ልጅ እድገት በእነዚህ መካከል ሚዛናዊነት የጠበቅ እነጻ /ግንባታ/ መኖር እንዳለበት ያምናል። ምሉዕ ስብእና የእነኢህ ገፅታዎች በጥምር መዳበርና መስተካከል እንደሆነ አፅንኦት ይሰጣል።
  10. መልካምን ነገርን ባማረ ሁኔታና በሚገባ መልኩ ማቅረብ፡- ስንት መልካም ነገሮችን በማስተላለፊያ /በማቅረቢያ/ ስልታቸው አለማማር ማስተላለፍ የሚገባቸውን ጠቃሚ መልዕክት በቅጡ ሳያስተላልፉ እንዲሁ ቀርተዋል። ሌሎች ደግሞ ሰንካላና እርባና-ቢስ ጉዳይ ይዘው፣ በአቀራረባቸው ማማርና መስተካከል ምክንያት ስንቶችን አታለዋል፤ አማለዋል። ስለሆነም መካከለኛው አቋም ሀቅን ባማረ ሁኔታና ለዘመኑ ሰው በሚገባ መልኩ ማስተላለፍን ይቀበላል።
  11. ትምህርታዊ ምክር /እነጻ/ እና ህጋዊ እርምጃን ያጣመረ፡- የጎበጠውን ለማረቅና የተጣመመውን ስርዓት ለማስያዝ ሀይማኖታዊ እነጻ (ተህዚብ) እና ህጋዊ የማረም እርምጃን (ተእዲብ) በአግባቡ ይጠቀማል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ማወርዲ እንደሚሉት ዱንያ በስድስት ነገር ትክክለኛ መንገድን ይዛ ትሄዳለች፣ ከነዚህም መካከል “ሠዎች የሚከተሉት ዲን መኖርና ስርዓትና ህግ አስከባሪ መሪ መገኘት” ተጠቃሽ ናቸው። (አደብ አድ-ዱንያ ወድ-ዲን ሊልማወርዲይ፣ 67-68)
  12. ሴቶችን ከባህል ማነቆና ከዘመናዊ ለቅነት ሚዛንዊ በሆነ መልኩ ነፃ ማውጣት፡- የሴቶችን ጉዳይ ሁለት ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ይጔተቱታል። አንደኛው ጽንፈኛ ወገን ሴቶችን ከተፈጥሯዊ መልካም ስነ-ምግባር ተራቁተው እርቃናቸውን እንዲቀሩ የሚሻ ሲሆን ሌላው ጽንፈኛ ወገን ደግሞ ከሸሪዓው ጋር የማይስማማ በሆነው በአጉል ባህል አስገድዶ ሊያስራቸው የሚፈልገው ነው። ወሰጢያ ግን ሴትና ወንድ ከሸሪዓው ጋር በሚስማማ መልኩ ሚዛናዊነትን በተላበሰ መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው ያምናል።

የወሰጢያ መንገድ መስኮች

ወሰጢያ የሚከሰትባቸው አበይት መስኮች የሚከተሉት ናቸው፡-

  • ዐቂዳ (እምነት)፡- ይህ ነጥብ ቁርአንን ሱናን እንዲሁም የሰለፎችን መንገድ መሰረት ያደረገ የእምነት አስተምህሮት ነው። በተቃራኒውም ቴክኒካዊ ከሆኑ ሙያዊ የቋንቋ ብያኔዎች ምጉትና ክርክር በመራቅ ኢማን በነፍስ ላይ ያለውን ጉልህ ሚና በተገቢው መንገድ ተጽዕኖ እንዲኖረው ትኩረት ማድረግ። ከአላህ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ዐቂዳዊ መረጃዎችን በቀጥታ ከምንጫቸው መውሰድ እንዳለብን ሁሉ አዕምሯዊ ጥረትን መጠቀም የሚፈቅድ መንገድ ነው።
  • የአምልኮ ተግባራት፡- ሀይማኖታዊ ስርዓቶችና ክንውኖች የዱንያ ህይወትን /ኑሮን/ ለማሸነፍና ያማረ ህይወትንም ለመኖር ብሎም መሬትን ለማበልጸግ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት አይደሉም። እንዲያውም ኢስላማዊ የሀይማኖት ስርዓቶች ለስራና ለምርታማነት ምቹና ገር ከመሆናቸውም ባሻገር አበራታች ናቸው።
  • ተሃድሶና ኢጅቲሃድ፡- መሰረታዊውን የእስልምናን አስተምህሮ መነሻ በማድረግ ለዘመኑ ጉዳዮችና ለጊዜው ጥያቄዎች መልስ መስጠትና በተለያዩ የህይወት ዘርፎችና ሐይማኖታዊ ክንውኖች ተሀድሶ ማድረግ ነው።
  • በፊቂህ ጉዳዮች፡- ወሰጢያ ጽንፈኛ የመዝሀብ አካሄድን (ተዐሱብን) አይቀበልም። በአንፃሩ ማስረጃን መሰረት በማድረግ የተወሰነ የአዋቂዎች አቋምን መያዝን (መዝሃብን መከተልን) ግን አይቃወምም። ወሰጢያ ኢጅቲሃድን፣ ኢትባዕንና ተቅሊድን ሚዛናዊና ተደጋጋፊ በሆኑ መልክ የሚራምድ የአስተሳሰብ ዘይቤ ነው።
  • በፈትዋ ዘርፍ፡- ወሰጢያ መሰረታዊና ጥቅል (ኩልይ) እና ዝርዝር (ጁዝኢይ)፣ የሸሪዓውን ዋና ዓላማ (መቃሲድ)ና ቅርንጫፍ (ፍሩዕ) ጉዳዬችን፣ የሸሪዓውን ቀዳሚ ማስረጃዎች (ቁርአንና ሱና)ና ግለሰባዊ ምሁራዊ አስተያየቶችን (ረዒ) ሁሉ የሚያቀናጅና እነዚህን ነገሮችም ግምት ውስጥ አስገብቶ ፈትዋ እንዲሰጥ የሚጋብዝ ነው። በፈትዋ ጽንፈኝነትንና የግል አቋምን ማንጸባረቅ የዚህ መንገድ አቋሙ አይደለም። በአጠቃላይ ሽይኸ ዐብደሏህ ኢብኑ በያህ እንደሚሉት፣ ፈትዋ አራት ነገሮችን መሰረት አድርጎ ይከናወናል። እነሡም፡-
  1. የፈታዋ በጊዜና በቦታ የመለዋወጥ ባህሪን
  2. የልምድና የባህል (ዑርፍ) ተጨባጭን
  3. የፈትዋ ማስፈፀሚያ ስልቶችን እና
  4. ግለሰቦችንና የነገሮችን አይነትና ሁንታ መሰረት ያደርጋል።
  • በልዩነት (ኺላፍ) ጉዳዮች:- ልዩነት ሁለት አይነት ሲሆን፣ የመጀመሪያው መሰረታዊና አጠቃላይ (ኡሱል ወል-ኩሊያት) በሆኑ ዐቂዳዊና ሸሪዓዊ ጉዳዬች ላይ ሲሆን ይህ አይነቱ ኺላፍ በኢስላም የተወገዘ ነው። ሌላው ኺላፍ ደግሞ መሰረታዊ ባልሆነው (ፉሩዕ) ጉዳዮች የሸሪዓውነ ማስረጃ መሰረት ባደረገ መልኩ የሚኖረው ልዩነት ነው። ይህን መሰረት አድርገው የሚከሰቱ ልዩነቶች ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። በዚህ አይነቱ ሁኔታ የውይይት ተገቢ ስልቶችን በመጠቀም ልዩነትን ማስወገድ ወይም ማጥበብ ይቻላል።
  • ከሌሎች ጋር በሚኖር ግንኙነት:- ይህ መንገድ ሙስሊም ካልሆኑ ወገኖች ጋር በሚኖር ግንኙነት ውይይትን መሰረታዊ ድልድይ ያደርጋል። ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች ሀይማኖታዊ ስርዓታቸውን የመከወን ነጻነትን አይነፍግም። ስለሆነም በጋራ ተባብሮ መኖርን እንጂ ሀይማኖታዊ ልዩነትን የጥላቻ መሳሪያ ማድረግን አይቀበልም። ከዚህ ይልቅ በአንድ ሀገር ላይ አብሮ መኖር መቀራረብንና የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን ለማሳካት ባንድነት መስራት ትልቅ መፍትሄ ነው ብሎ ያምናል ።
  • በሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች (አህካም):- ይህም መሰረታዊ ህጎችን (ኡሱል) ከፍተኛ ቦታ መስጠትና ቅርንጫፎችን (ፉሩእ) ደግሞ በማቅለልና በማግራራትን (ተይሲር) የሚመለከት ነው። ኢስላምን የሚወክለው ወሰጢያ ሃይማኖቱ የቆመባቸውን መሰረታዊ ቁም ነገሮችን በማላቅና ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ያምናል። ቀደም ባሉት ሀይማኖቶች ላይ የተከሰተው እንዳይከሰት፣ መሰረታዊ የሸሪዓውን ህጎች ሰርጎ-ገብ አጥፊ እጆች እንደፈለጉ እንዳይጠመዙዟቸው ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋል። ጎን ለጎንም የነኚህን መሰረታዊ ሸሪዓ ህጎች መሰረታዊ ትርጓሜያቸውንና የሚያስተላልፉትን መልዕክት ለማዛባት የሚደረግ ሙከራንም ይከላከላል። ወሰጢያ ለመሰረታዊ የሸሪዓ ህጎች ጥበቃ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ለቅርንጫፍ ሸሪዓዊ ጉዳዮችም የተግራራ መንገድን ይከተላል። ይህን የሚያደርገው ችግርን ለመከላከል፣ ጭንቅና መከራን ለማስወገድ ነው። ይህ ደግሞ የረሡል (ሰ.ዐ.ወ) የማይቀየር መሰረታዊ አቋም ነው። ረሡል (ሰ.ዐ.ወ)

 ما خُير بين أمرين إلا اختار أيسرهما، ما لم يكن إثمًا

“ከሁለት ነገሮች አንዱን እንዲመርጡ ሲጠየቁ፣ ወንጀል እስካልሆነ ድረስ ቀለል /ገር የሆነውን/ ያለውን ይመርጡ ነበር”

  • ኢስላምና ሌሎች ስልጣኔዎች፡- ወሰጢያ በዓለም ላይ ካሉ ሌሎች ስልጣኔዎች ጋር መነጠል ወይም ጥግ መያዝን ሳይሆን ሰጥቶ መቀበልን፤ ባዶ ኩራት የሌለበት በራስ መተማመንን፤ መዋረድን የማያስተናግድ መቻቻልን ይቀበላል፣ ያበረታታል እንደ መርህም ይወስዳል። ሙስሊሞች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙና የራሳቸው መለያ ባህሪይ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ረሡልም እንዲህ ገልፀዋቸዋል፡-

 المؤمنون تتكافأ دماؤهم، ويسعى بذمتهم أدناهم، وهم يد على من سواهم…

“ሙእሚኖች ህይወታቸው አንዱ ለአንዱ ዋቢ ሲሆን፣ ከነሱ ውጪ በሆነው (ጠላታቸው) ላይ ደግሞ በአንድነት ብርቱ ሀይል (እጅ) ናቸው” (ነሳኢ)።

ማጠቃለያ

አል-ወሰጢያ መገለጫና ትርጔሜ የሌለው ምናባዊ ትረካ አይደለም። አዕምሮን ለማርካት ብቻ የሚውል አካዳሚያዊ ዕውቀትም ብቻ አይደለም። ወሰጢያ ሁለገብ የሆነ የአስተሳሰብ ስርዓትና የህይወትን መንገድ ነው። ግለሰብንና ማህበረሰብን እንደሚመለከት ሁሉ ሀገራዊ ጉዳዮችንም በሚዛናዊ እይታው ይዳስሳል።

ይህ መንገድ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሙስሊሞች በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ሊከውኑትና ሊያራምዱት የሚገባውን ኢስላማዊ አስተምህሮት የሚያመላክትና የሚመራ ዕሳቤም ነው። ወሰጢያ ሙስሊሞች በዳዕዋ እንቅስቃሴ፣ በዕውቀት፣ በባህል፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በልማት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ ወዘተ… ሁለገብ እንቅስቃሴ ሊኖራቸው የሚገባውን ኢስላማዊ የአስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ የሚገልፅ ፅንሰ ሀሳብና የህይወት መንገድ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here