ኢስላም የህይወታችን ምሉዕ ገፅታ የሚዳስስ የተሟላ የህይወት መመሪያ ነው። በዚህም የተነሳ ቤተሰብን እንደ አንድ የማሕበረሰቡ የማእዘን ድንጋይ አድርጎ ይመለከታል። ፍቅር፣ መስዋእትነት፣ ታማኝነትና መተሳሰብ መገለጫዎች ናቸው።
እዚህ ላይ ቤተሰብ የሚለውን ቃል ብንጠቀም ጠበብ ባለ መልኩ ባል፤ ሚስትና ልጆችን ማለታችን ነው። በእርግጥ አያት፤ አክስትና አጎትም የሰፊው ኢስላማዊ ቤተሰብ አካል ናቸው።
እዚህ ጋር የሚነሳ መሰረታዊ ጥያቄ አለ፡- ኢስላም አንዴት አድርጎ ነው ይህንን ቤተሰባዊ ቁርኝነት (ጥምረት) የሚያዋቅረው? የባልና የሚስት ጥምረት በተመለከተ ኢስላማዊ አስተምህሮች በቁርአን እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡-
“ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደእነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉ።” (አልሩም 30፤21)
ይህነን ቁርአናዊ አስተምህሮች ታማኙ የአላህ ነብይ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ በማለት ያጠናክሩታል።
“ከመሀከላችሁ በላጫችሁ ለቤተሰቡ መልካም የሆነ ነው፤ እኔ ለቤተሰቤ መልካም ነኝ”
በሌላ አጋጣሚ እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል፡-
“ለሴቶች መጥፎ የሚውልላቸው መጥፎ የሆነ ነው፤ የሚያከብራቸው የተከበረ ነው”
በአንድ ወቅት አንድ ሰው ወደ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) መጣና “በጓደኛነት ቅርብ አድርጌ ልይዘው የሚገባ ከሁሉም በላጩ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው። እሳቸውም “እናትህን” አሉት። በድጋሚ ጠየቃቸው “እናትህን” አሉት ለሶስተኛ ጊዜ በድጋሜ ጠየቃቸው። “እናትህን” አሉት። በአራተኛ “አባትህን” አሉት።
ይህ ክብር ደግሞ እናትን ጀነት ከእግሮቿ ስር እንደሆነ አድርጎታል እንደ ሀዲስ ዘገባ።
የአላህን ቃል ቁርአንን አስተንትነንና በጥልቅ ካነበብን የወላጆቻችን የልጆቻችን ግንኙነት በአራት የተለያዬ ቦታዎች በሚገባ ጠቅሶታል። ልጆች ለወላጆቻቸው በጎ የሚውሉና ታዛዥ እንዲሆኑ ከማዘዙ በፊት ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት መኮትኮት እንዳለባቸው ያሳስባል። በሌላ አገላለፅ ወላጆች መብቶቻቸውን ከመጠየቃቸው በፊት ግዴታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል። እስኪ ቀጥሎ ያለውን የቁርአን አንቀፅ በሚገባ እናስተውለው
“ለሉቅማንም ጥበብን በእርግጥ ሰጠነው። (አልነውም)፡-‘አላህን አመስግን።’ ያመሰገነም ሰው የሚያመሰግነው ለራሱ ብቻ ነው። የካደም ሰው (በራሱ ላይ ነው)። አላህ ተብቃቂ ምስጉን ነውና። ሉቅማንም ለልጁ እርሱ የሚገሥጸው ሲኾን ‘ልጄ ሆይ! በአላህ (ጣዖትን) አታጋራ። ማጋራት ታላቅ በደል ነውና’ ያለውን (አስታውስ)። ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ) በጥብቅ አዘዝነው። እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው። ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)። መመለሻው ወደኔ ነው። ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው። በቅርቢቱም ዓለም፤ በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው። ወደእኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል። ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው። ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ (አልነው)።”
ቁርአን በመቀጠል:-
“(ሉቅማንም አለ) ‘ልጄ ሆይ! እርሷ የሰናፍጭ ቅንጣት ክብደት ያህል ብትሆንና በቋጥኝ ውስጥ ወይም በሰማያት ውስጥ ወይም በምድር ውስጥ ብትሆን አላህ ያመጣታል። አላህ ሩኅሩኅ ውስጥ ዐዋቂ ነውና። ልጄ ሆይ! ሶላትን አስተካክለህ ስገድ። በበጎ ነገርም እዘዝ። ከሚጠላም ሁሉ ከልክል። በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገስ። ይህ በምር ከሚያዙ ነገሮች ነው። ጉንጭህንም (በኩራት) ከሰዎች አታዙር። በምድርም ላይ ተንበጥርረህ አትሂድ። አላህ ተንበጥራሪን ጉረኛን ሁሉ አይወድምና። በአካኼድህም መካከለኛ ኹን። ከድምጽህም ዝቅ አድርግ። ከድምጾች ሁሉ አስከፊው የአህዮች ድምጽ ነውና’።” (ሉቅማን 31፤ 12-19)
ይህ የቁርአን አንቀፅ ለወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ባለሁኔታ ማነፅና መኮትኮት እንዳለባቸው በሚጣፍጥ ቋንቋ ገልፆታል። ይህን ማድረግ ያልቻለ ወላጅ ከልጁ አመፀኝነትን እንጂ ሌላን አይጠብቅ። ነገር ግን፤ ይህንን ወላጆች ካሟሉ ቀጣዩ የልጆች ተራ ነው። አላህም እንዲህ ሲል ይገልፃል።
“ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ። በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው። አትገላምጣቸውም። ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው። ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው። ‘ጌታዬ ሆይ! በሕፃንነቴ (በርኅራኄ) እንዳሳደጉኝ እዘንልላቸውም’ በል። ጌታችሁ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ሁሉ አዋቂ ነው። ታዛዦችም ብትኾኑ (በመሳሳትም ብታጠፉ) እርሱ ለተመላሾች መሓሪ ነው።” (ኢስራእ 17፤23-25)
እነዚህን ሁለት ዋና ዋና ምዕራፎች ስለ ወላጅና ልጅ ግንኙነት በሚገባ ያብራሩ ሲሆን ኢስላማዊ ስርዓት ምን መምሰል እንዳለበት በግልፅ አስቀምጠዋል። ይህ የወላጅና የልጅ መስተጋብር መሰረቱን ያደረገው በመጀመሪያ በአላህ ላይ ማመን ሲሆን ሲቀጥል አላህ የምናድርገውን ነገር ሁሉ በጥልቀት የሚከታተል መሆኑን እንድናስብ በማድረግ ነው። በንዴት ሰአት እንኳን ሳይቀር የምናሰማት የ ‘ኡፍ’ ትንፋሽ ይከታተላል። ይህንን ሳይቀር መቆጣጠር እንዳለብን ያዘናል።
ነገር ግን፤ አንድ ነገር መዘንጋት የለብንም። ይኸውም፤ ይህንን የወላጅነት ክብር ሊያገኝ የሚችለው ግዴታውን የተወጣ ወላጅ ብቻ መሆኑን። ለዚህም ነው አንድ ሰው መጥቶ የአላህን መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ልጁ ለሱ ያለውን መጥፎ አመለካከትና የሚያሳየውን አላስፈላጊ ባህሪ ስሞታ ሲያቀርብ ልጅየውን አስጠርተው ጠየቁት ልጁም “አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ እንዲህ ላደርግ የቻልኩት አባቴ ለኔ በሚያሳየኝ መጥፎ ስነምግባር ነው” ብሎ መለሰላቸው። የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ልጁን ሳይሆን ድርጊቱን በመኮነን የዚህ ሁሉ ጥፋት መንስኤ የአባቱ ልጁን በሚገባ አለመያዝ መሆኑን አስገነዘቡት። ይህ መልዕክት ለሁሉም ወላጆች ነው።
ሶስተኛው በቤተሰብ (በወላጅ-ልጅ) ግንኙነት ላይ የሚያተኩረው የቁርአን አንቀፅ የሚገኘው ሱረቱል አህቃፍ ላይ ነው።
“ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው። እናቱ በችግር ላይ ኾና አረገዘችው። በችግርም ወለደችው። እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሰላሳ ወር ነው። ጥንካሬውንም ወቅት በደረሰ ጊዜ (ከዚያ አልፎ) አርባ ዓመትንም በደረሰ ጊዜ ‘ጌታዬ ሆይ! ያችን በእኔ ላይና በወላጆቼ ላይ የለገስካትን ጸጋህን እንዳመሰግን የምትወደውንም መልካም ሥራ እንድሠራ ምራኝ። ዘሮቼንም ለእኔ አብጅልኝ። እኔ ወዳንተ ተመለስኩ። እኔም ከሙስሊሞ ነኝ’ አለ።” (አል-አህቃፍ 46፤ 15)
በተቃራኒው ልጆችን በተመለከተ ቁርአን በመቀጠል እንዲህ ሲል ይገልፃል:-
“እነዚህ (ይህንን ባዮች) በገነት ጓዶች ውስጥ ሲኾኑ እነዚያ ከሠሩት ሥራ መልካሙን ከነሱ የምንቀበላቸውና ከኀጢአቶቻቸውም የምናልፋቸው ናቸው። ያንን ተስፋ ይስሰጡት የነበሩትን እውነተኛ ቀጠሮ (እንሞላላቸዋለን)።” (አል- አህቃፍ፤ 46፡16)
በተቃራኒው አመፀኛና ወላጆቹን የሚያንኳስስ ሰው አላህ ምን አይነት መጨረሻ ሊኖረው እንደሚችል እንዲህ ሲል በማለት ያብራራል።
“ያንንም ለወላጆቹ ‘ፎህ ለእናንተ ከእኔ በፊት የክፍል ዘመናት ሰዎች (ሳይወጡ) በእርግጥ ያለፉ ሲኾኑ (ከመቃብር) እንድወጥጣ ታስፈራሩኛላችሁን?’ ያለውን ሁለቱም (ወላጆቹ) አላህን የሚለምኑ ሲኾኑ (ባታምን) ‘ወዮልህ። እመን። የአላህ ቀጠሮ እርግጠኛ ነው።’ (ሲሉት) ‘ይህ የፊተኞቹ ሰዎች ጽሑፍ ተረቶች እንጅ ሌላ አይደለም’ የሚለውንም ሰው (አስታውስ)። እነዚህ እነዚያ ከጋኔንም ከሰውም ከእነርሱ በፊት ካለፉት ሕዝቦች ጋር ቃሉ በእነርሱ ላይ የተረጋገጠባቸው ናቸው። እነርሱ ከሳሪዎች ነበሩና። ለሁሉም ከሠሩት ሥራ ደረጃዎች አልሏቸው። ሥራዎቻቸውንም ይሞላላቸው ዘንድ (ይህንን መነዳቸው) እነርሱም አይበደሉም።” (አል- አህቃፍ 46፡17-19)
አራተኛውና የመጨረሻው የወላጅን የልጅ ግንኙነት ምን መምስል እንዳለበት የሚያብራራው አንቀፅ እንዲህ ይላል።
“ሰውንም በወላጆቹ መልካም አድራጎትን አዘዝነው። ላንተም በእርሱ ዕውቀት የሌለህን (ጣዖት) በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህ አትታዘዛቸው። መመለሻችሁ ወደኔ ነው። ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ።” (አል- አንከቡት፤ 29፡8)
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ይህ አንቀፅ የሚያወራው ኢ-አማንያን በሆነ ወላጆችና አማኝ በሆኑ ልጆች ጉዳይ ሲሆን እነዚህ ወላጆች አንኳ ምን ያህል መብት እንዳላቸው መረዳት እንችላለን። ምንም አንኳ ይህ መብት ከአላህ (ሱ.ወ) መብት ጋር የማይጋፋ መሆን ቢኖርበትም በአላህ ሀቅ ላይ ማንም ጣልቃ ሊገባ አይችልም። በተቀረው ግን በመልካም ልንኗኗር ታዘናል።
ለማጠቃለል ያህል ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ቤተሰብ የማህበረሰብ የማእዘን ድንጋይ፤ የደስታ ምንጭ፤ የእድገት መሠረት ሊሆን የሚችል በወላጅ-ልጅ ግንኙነት ዙርያ ቁርአን ያስቀመጠላቸውን ዘመን አይሽሬ መመሪያዎች ስንተገብርና ሁሉም ወገን ከመብቱ በፊት ግዴታውን መውጣት እንዳለበት ሲረዳ ነው።