ቤተሰብ በኢስላም

1
4853
وَقَضَىٰ رَبُّكَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا إِمَّا يَبْلُغَنَّ عِندَكَ الْكِبَرَ أَحَدُهُمَا أَوْ كِلَاهُمَا فَلَا تَقُل لَّهُمَا أُفٍّ وَلَا تَنْهَرْهُمَا وَقُل لَّهُمَا قَوْلًا كَرِيمًا ﴿٢٣﴾ وَاخْفِضْ لَهُمَا جَنَاحَ الذُّلِّ مِنَ الرَّحْمَةِ وَقُل رَّبِّ ارْحَمْهُمَا كَمَا رَبَّيَانِي صَغِيرًا ﴿٢٤﴾ … وَآتِ ذَا الْقُرْبَىٰ حَقَّهُ وَالْمِسْكِينَ وَابْنَ السَّبِيلِ وَلَا تُبَذِّرْ تَبْذِيرًا … وَلَا تَقْتُلُوا أَوْلَادَكُمْ خَشْيَةَ إِمْلَاقٍ  نَّحْنُ نَرْزُقُهُمْ وَإِيَّاكُمْ  إِنَّ قَتْلَهُمْ كَانَ خِطْئًا كَبِيرًا   

“ጌታህም (እንዲህ ሲል አዘዘ) እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ። በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ‘ኡፍ’ አትበላቸው። አትገላምጣቸውም። ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው። ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው። ጌታዬ ሆይ! በህፃንነቴ (በርህራሄ) እንዳሳደጉኝ እዘንላቸውም በል …. ለዝምድና ባለቤትም መብቱን ሥጥ ለምስኪንና ለመንገደኛም (ስጥ) ማባከንንም አታባክን …. ልጆቻችሁንም ድህነትን በመፍራት አትግደሉ። እኛ እንመግባቸዋለን። እናንተም እንመግባለን። እነርሱን መግደል ታላቅ ሃጢያት ነውና።” (አል-ኢስራዕ፤ 23-31)

ቤተሰብ አላህ የፈጠረው የሰው ልጆች የፍቅር፣ የርህራሄ፣ የእዝነትና የእንክብካቤ ተቋም ነው። ቤተሰብ ብልፅግናን፣ ዕድገትን፣ ሰላምና መረጋጋትን ይፈጥራል። ህብረተሰብን የሚያሰለጥነውና የሚያፋፋውም ቤተሰብ ነው። ይህን የማህበራዊ እሴቶች መፍለቂያ ተቋም ለመፍጠር አንድ ወንድ እና አንድ ሴት በህጋዊ ውል ይጋባሉ። ያን ውል ከገቡበት ዕለት አንስቶ ቤተሰብ የተባለው ተቋም ይፈጠራል። አዲስ ትውልድ ያቆጠቁጣል። የቤተሰብ መመስረት ዝምድናን ያጠነክራል። ህብረተሰብን ይፈጥራል። የቤተሰቡ (የተቋሙ) አባላትም የሚቀጥለው ትውልድ ከነሱ የተሻለ እንዲሆን ይመኛሉ። በግልፅ እንደሚታየው ወላጆች ልጆቻቸውን ከነሱ የበለጠ ደስተኛ፣ ከነሱ የበለጠ የተማሩ፣ በአጠቃላይ ከነሱ የላቀ ደረጃ እንዲደርሱ ይተጋሉ። ስለሆነም ኢስላምም ለቤተሰብ ከፍተኛ ቦታ ሰጥቷል።

ዳሩ ግን ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ ዛሬ ከፍተኛ የቤተሰብ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ከሚወለዱት ህፃናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከቤተሰብ ውጪ የሚወለዱ ናቸው። ይህ በየትኛውም የሥልጣኔ ዘመን ታይቶ አይታወቅም። የቤተሰብ ግጭትም ማንም መገመት ከሚችለው በላይ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ብዙ ምዕራባውያን ጉዳዩ ስላስጨነቃቸው በየሀገራቸው የቤተሰብን ቦታ ለመመለስ የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ይህ ቀውስ በሞኞችና በተራ ሰባኪዎች ሊሻሻል አይችልም። ቤተሰባዊ ሥርዓት ሊመለስ የሚችለው በህብረተሰቡ ሞራል፣ ሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ እሴት በአዕምሮው ሲሰርጽና ህብረተሰቡም በልቡ ማሳደር ሲችል ብቻ ነው። በዚህም ተገቢና ቅንነት ያልጎደላቸው ህፃናትን ማፍራት ሲቻል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቤተሰባዊ ተቋም ወደ ተፈለገው ደረጃ እንዲደርስና ስራውን በአግባቡ እንዲከውን መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ከሁሉ በፊት ኢ-ሰብዓዊ ወሢባዊነትን የሚፈጥረውን እርቃናዊነት፣ ልቅ ቅልቅል፣ አልኮለኝነት፣ የዝሙት ፊልሞችና ምስሎች እንዲሁም ፅሁፎች፣ ወዘተ በሙሉ መወገድ አለባቸው። ቤተሰብ በአግባቡ ትውልድ የመቅረፅ ሥራውን እንዲሰራ፣ የእነዚህ እኩይ ነገሮች መወገድ “ሐሳብን በመግለፅ መብት” ና “በባህልን በመጠበቅ” ሥም መደናቀፍ የለበትም። ከዚህ በተጨማሪም ፍፁም መረሣት የሌለበት ጉዳይ ደግሞ ሰዎች ጊዜያቸውን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ መልመድ አለባቸው። አሁን አሁን “ቤት” ማለት ሰዎች ለመኝታ ብቻ የሚጠቀሙበት ሆቴል ሆኗል። ከቤት ይልቅ በዓላትና በትርፍ ጊዜም ጭምር ከውጭ መመገብ፣ በልጅና በወላጅ መካከል ያለውን የመግባባት ችግር ከማስፋቱም በላይ የቤተሰብን ህልውናም አፍራሽ ነው።

ሰፊ ቤተሰብ መፍጠር የራሱ የሆነ ከፍተኛ ጥቅም አለው። በዛሬው ጊዜ ቤተሰብ ማለት ወላጆችና ልቻቸው ብቻ ወይም ወላጅና ልጅ ብቻ ነው። ይህ በራሱ አደጋ ነው። ብቸኝነት ይፈጥራል። በህመም፣ በሃዘንና በኢኮኖሚ ችግር ጊዜ የሚፈጥረው ውጥረት ቀላል አይደለም። አንዳንዴም በቤተሰቡ መካከል ግጭት ከተፈጠረ ከባድ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ከነዚህም መካከል ጭንቀት እና የአዕምሮ ውጥረት ይከሰታል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቅርቡ ነገሮችን የሚያክም ሰው አለመኖሩ ነው። ስለዚህ ከቅርብ ዘመዶች ጋር ቀረብ ብሎና ተግባብቶ መኖር ያስፈልጋል።

“ከናንተ ውስጥ ምርጡ ሰው፣ ለቤተሰቡ ምርጥ የሆነው ነው። እኔ ለቤተሰቦቼ ከናንተ የላቅሁ ምርጥ ነኝ።”

ኢስላም፣ ቤተሰብ ከመተሣሰብና ከፍቅር በተጨማሪ ስርዓትና ሃላፊነት የተጠበቀበት ተቋም እንዲሆን ይሻል። የቤቱ አባውራም ስርዓትና ዲሲፒሊን በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት ተጥሎበታል። በምንም መልኩ ቢሆን ኢስላም ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠርን ችላ መባባልንና ከመልካም ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ ነፃነትን አይፈቅድም። ይህ ማለት ግን ባል በቤተሰብ ህይወት ላይ አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ ነው ማለት አይደለም። አባውራ ሥልጣኑን በፍቅርና በእንክብካቤ መንገድ መጠቀም አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ማዘንንና ማማከርንም መርሳት የለበትም። ነብያችን /ሰ.ዐ.ወ/ እንዳሉትም “ከናንተ ውስጥ ምርጡ ሰው፣ ለቤተሰቡ ምርጥ የሆነው ነው። እኔ ለቤተሰቦቼ ከናንተ የላቅሁ ምርጥ ነኝ።” ነብዩ ቤተሰባቸው ውስጥ ፈፅሞ አምባገነን አልነበሩም። የርሳቸው ሥልጣን በርህራሄና በፍቅር የተሞላ ነበር። ቤተሰብ እዝነት ከሌለበት ወይም የእልህ ቤት ከሆነ በአግባቡ ይቆማል ማለት ዘበት ነው። ሚስት ባሏን መታዘዝ ሲኖርባት ባል ደግሞ በቤቱ ጉዳይ ሚስቱን ማማከር አለበት። ልጆችም ወላጆቻቸውን መታዘዝና ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ወላጆችም ልጆቻቸውን ማፍቀር፣ ስሜታቸውን መረዳት፣ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ መርዳት ይገባቸዋል። በልጆቻቸውም መካከል ማዳላት፣ ሴቶችን ከወንዶች ማሳነስ አይገባም። ሁሉንም እኩል ማየት ያስፈልጋል። ልጆች ያፈቀራቸውንና ያከበራቸውን ወላጅ ያፈቅራሉ። እኛም ልጆች፣ የወደፊቱ ልጆቻችን እንዲያክበሩን ዛሬ ወላጆቻችንን ማክበር ይገባናል።

ኢስላም ፍቺን አያበረታታም ። ነብዩም /ሰ.ዐ.ወ/ እንዳሉት፡- “አላህ እየጠላ የፈቀደው ነገር ፍቺን ነው።” ፍቺ የተፈቀደው እጅግ ከባድና በቀላሉ ሊፈታ የማይችል ችግር ሲያጋጥም ብቻ ነው። ሁሉም ቤተሰብ ውስጥ የማያስማማው ችግር አለበት። “ፍቺ” የሚባለው ቃል መነሣት ያለበት መሰረታዊ መፍትሄ ለመሻት ሲታሰብ ብቻ ነው። ተመሳሳይ ስህተት ላለመፈጸምም ሲባል፣ ፍቺ ከመፈጸሙ በፊት፣ የሚከሰተውን አወንታዊና አሉታዊ ነገር ቀድሞ ጠንቅቆ ማወቅና መገንዘብ የግድ ነው።

ጥንዶች ከምንም በፊት ጋብቻ ማለት ቋሚ ጉድኝት እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል። ፍቺ የሚባል ነገር ከማሰባቸው በፊት ለችግሮች ሁሉ ትክክለኛውን መፍትሄ ማፈላለግና ባለሙያ ማማከር ሊለምዱ ይገባቸዋል። የተራዘመ ንትርክና አለመግባባት በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት በስተቀር የማይሻር ጠባሳ ይፈጥራል። ለችግራቸውም መፍትሄ ከተገኘለት በኋላ ከሁለቱ ማናቸውም ቢሆኑ ያለፈውን ችግር ማንሳትና ማስታወስ የለባቸውም። በብዛት እንደምናስተውለው የፍቺ መንስኤዎች፣ ራስ ወዳድነት፣ ጨለምተኝነት፣ ለሌላው መስዋዕት ለመሆን ፈቃደኛ አለመሆን፣ አለመከባበር ወይም ኢስላማዊው ቅንነትና ታዛዥነት አለመኖር ናቸው። በትክክል አላህን የሚፈሩ ሰዎች ምርጡን ቤተሰብ ይመሰርታሉ።

1 COMMENT

  1. o
    አሰላሙአለይኩም።
    ወራህመቱላህ። ወረካቱሁ።
    የአላህ። ጥበቃ። አይለያችሁ።
    እዚህ ደረገፅ። የገባ ሰው።
    ምንም። ለመዉጣት።
    አያስፈልግም። አላህ
    እዉቀቱን። እጥፍ። ድርብ።
    ያድርግላችሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here