ሙስሊም መሆን

0
5434

ኢስላም የሚፈልገው አንጸባራቂ ስብእና አይነትና ባህሪ ይታወቃል። አንድ ሙስሊም ከአላህ ጋር ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙነት፣ በአእምሮው፣ በአካሉና በመንፈሱ መካከል ሚዛናዊነትን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት፣ ከወላጆቹ፣ ከባለቤቱ፣ ከልጆቹ፣ ከባልንጀሮቹና ከሌሎችም የሕብረተሰቡ ልዩ ልዩ አባላት ጋር ሊኖረው የሚገባውን ማሕበራዊ ግንኙነት የሚመለከቱ በርካታ ግልጽና ጉልህ የቁርአንና የሐዲስ መልእክቶች ሰፍረዋል።

ኢስላም የሚፈልገው ስብእና በስነ ምግባሩ፣ በግለሰባዊም ሆነ በማሕበረሰባዊ ግንኙነቶቹ እጅግ ድንቅና ውብ፣ እጅግ ማራኪ እንደሆነም ግልጽ ነው።

የሰው ልጅ በረዥሙ ታሪኩ እንዲህ ዓይነት የተሟላና ውብ ስብእና ያለው ግለሰብ የቁርአንና የሐዲስ ትምህርቶች በሰረጹት ሙስሊም ማንነት ውስጥ ካልሆነ በቀር እንዳልታደለም ግልጽ ሆኗል።

ኢስላም የሰውን ልጅ ልክ እንደ ግሪኮች አእምሮውን በፍልስፍና በመሙላት፣ ወይም እንደ ሕንዶች መንፈሳዊ ስልጠና በመስጠት ወይም እንደሮሞች አካሉን በማጎልበት ወይም እንደዘመኑ ምስራቃዊና ምእራባዊ ቁሳዊ ፍልስፍናዎች በአእምሮው ውስጥ ቁሳዊ አስተሳሰቦችን በማጨቅ ብቻ አልተወሰነም። ይልቁንም እጅግ ምሉእና ሚዛናዊ የሆነን የእነጻ ስልት ነው የተከተለው። አካሉንም፣ አእምሮውንም መንፈሱንም ሳይዘነጋ ለሁሉም የሚገባቸውን ስልጠና ይሰጣቸዋል። ይህ ሚዛናዊነት የሚመነጨው ስለ ሰው ልጅ ካለው አመለካከት ነው።

የሰው ልጅ በኢስላም እይታ አካልም መንፈስም አእምሮው ያለው ልዩ ፍጡር መሆኑ እውቅና ስለተሰጠው ኢስላማዊ ስብእና አንደኛው ማንነቱ ገኖ ሌላው ያልቀጨጨበት ሚዛናዊ ለመሆን ችሏል። የሰው ልጅ የተሳሳቱ አመለካከቶችንና ስሜቶችን መሠረት አድርጎ በሚቀርጻቸው ፈር የሳቱና ጎደሎ የእነጻ ስልቶች አማካይነት እንደሚቀረጸው ስብእና ሚዛን አልባነት አይስተዋልበትም።

ሙስሊም ግለሰብ በዚህ ጥናት እንደተመለከተው ለአላህ ታዛዥ፣ መመሪያውን የሚከተል፣ ወደርሱ የሚመለስ፣ ፍርዶቹንና ውሳኔዎቹን በጸጋ የሚቀበል፣ ምንጊዜም የአላህን ፍቅር ለማግኘት የሚሠራ ግለሰብ ነው።

ለአካሉ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጥ ስብእና ነው። ንጽህናውን ይጠብቅለታል። ላያዊ ገጽታውን ይከታተላል። አላህ ክብርን እንዲሰጠው፣ መላእክት እንዲሰግዱለት፣ በሰማያትም በምድርም ውስጥ ያሉ ነገሮችን ለርሱ እንዲገራለት ምክንያት የሆነውን ውስጣዊ ማንነቱንም አይዘነጋም። በሳል እና አዋቂ፣ ጥልቅ አሳቢና ነገሮችን መርማሪ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ የአስተሳሰብ ስልትን የሚከተል አእምሮ እንዲኖረው ይጥራል።

የሰው ልጅ ማለት አካልና አእምሮ ብቻ ነው ብሎም አያስብም። በበጎነት መሰላሎች ወደላይ መዝለቅ፣ ወደሰማየ ሰማያት መምጠቅ፣ የሚያስችለው ቀልብና መንፈስ እንዳለውም ያምናል። እናም ለአእምሮና ለአካሉ ትኩረት እንደሚሰጠው ሁሉ ለመንፈሱም ትኩረት ይሰጣል። ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ያንጻቸዋል። ለአንዱ የተጋነነ ትኩረት ሰጥቶ ሌላውን ችላ የሚልበት ሁኔታ የለም።

ሙስሊም ከወላጆቹም ጋር ድንቅ ግንኙነትን ይፈጥራል። ይንከባከባቸዋል። ያዝንላቸዋል። ውለታቸውን ይመልሳል። ተገቢውን ክብርና ትኩረት ይቸራቸዋል። የበጎነት ምሳሌ ነው።

ከባለቤቱም ጋር የመልካም ግንኙነት ተምሳሌት ነው። ፍቅርና እንክብካቤ ይለግሳታል። እንስታዊ ተፈጥሮዋን በጥልቅ ይረዳላታል። መጠጊያ፣ ተገን፣ ከለላ ይሆንላታል። ልጆቹን በተመለከተ ያለበትን የከበደ ሐላፊነት ይረዳል። ፍቅሩን ይሰጣቸዋል። ያዝንላቸዋል። ስብእናቸውን በጥንቃቄ ይቀርጻል። ሚዛናዊ ሰዎች እንዲሆኑ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ጊዜውን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን ለዚሁ ተግባር ያለመሰሰት ይጠቀማል።

ከቅርብ ዘመዶቹም ጋር ባለውም ግንኙነት ዝምድናን ይቀጥላል። ኢስላማዊ ሸሪዓ ለዝምድና ግንኙነት የሰጠውን ክብደት ይረዳል። ለዚህ ግንኙነት ይጠነቀቃል። መጥፎ ሁኔታዎች ቢኖሩ እንኳ እነርሱን ተቋቁሞ ይንከባከባቸዋል።

ከጎረቤቶችም ጋር የጥሩ ጉርብትና ተምሳሌት ነው። በጎ ግንኙነት ይፈጥራል። ስሜታቸውን ይረዳል። ክፋታቸውን ይታገሣል። ስህተታቸውን ያልፋል። እንዳያስከፋቸው ይጠነቀቃል። ግንኙነቱ ኢስላማዊ ነው። ኢስላም ለጉርብትና ግንኙነት የሰጠውን ክብደት ይረዳል። በጅብሪል አማካይነት ነው ኑዛዜ ያስተላለፈው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የውርስ መብት ሊሰጠው ነው በማለት እስኪያስቡ ድረስ ጅብሪል ኑዛዜውን አጽንቷል። ከዚህም የተነሳ የጉርብትና ጉዳይ ለሙስሊም ከባድ ነው።

ሊያስቀይማቸው አይሻም። ሊያስከፋቸው አይፈቅድም። ቢቻለው በጎ ያደርግላቸዋል። ለውለታው ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይፈልግ። ከወንድሞቹ ጋር ያለው ግንኘነትም ግሩም ነው። እጅግ የጸዳና የመጠቀ ግንኙነት። ለአላህ ሲሉ መዋደድ። እውነተኛውና ንጹሁ ወንድማዊ ግንኙነትም ይህው ነው።፡ ከጠራው መለኮታዊ ምንጭ የመነጨ እና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አቻ የማይገኝለት አንጸባራቂና ጠንካራ ትስስር።

ከዚህ ድንቅ ግንኙነትና የፍቅር ስሜት ሙስሊምን ከሌሎች ሰዎች ልዩ የሚያደርጉት ማራኪ ባህሪያት ይፈልቃሉ። የኢስላም ስነ ምግባርና እሴቶች በነኝህ ባህሪያት ውስጥ ይንጸባረቃሉ። ሙስሊም ወንድሞቹን ይወዳል – አይንቅም። ለነርሱ ታማኝ ነው፣ አይክዳቸውም። ጥሩ መካሪ ነው – አያታልላቸውም። የማይከረድድ – ጓደኛ፣ ጥላቻና ጎሜ የሌለበትና ይቅርባይ ነው። ቸር ነው – ያለውን ለወንድሞቹ ይለግሳል። እነርሱን ከራሱ ያስቀድማል። ሲርቁ ለነርሱ ዱዓ ያደርጋል።

ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለዉ ግንኙነትም ድንቅ ነው። የመጠቀ ስነ ምግባር ባለቤት ነው። ኢስላም ባስተማረው ባህሪያት ይዋባል። በጎ የሚሆነው ለማስመሰል ብሎ አይደለም። ወይም ይህ ባህሪው ጊዜያዊ አይደለም። ከአንጀቱ ነው። የማይነጥፍና ዘልዓለማዊም ነው። መልካም ባህሪያት ከቀርአንና ከሐዲስ የመነጨ እና መሠረታዊ የሐይማኖቱ አካሎች ናቸውና።

ከሁሉም ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት እውነተኛና ታማኝ ነው። አያታልልም። ሸፍጥ አይፈጽምም። ምቀኛ አይደለም። ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል። ትሁት ነው። ይቅርባይና ማሐሪ ነው። ብሩህ ገጽታ አለው። አይከብድም፣ አይከረድድም። ታጋሽ ነው። ብልግና ወይም ስድብ ከአንደበቱ አይወጣም። ጸያፍ ቃላት አይናገርም። ሰዎችን ያለ አግባብ ካፊር ወይም ወንጀለኛ እያለ አይዘልፍም። የሰውን ነውር ይሸፍናል። በማይመለከተው ጉዳይ አይገባም። ከሐሜት እና ነገር ከማሳበቅ የራቀ ነው። አይዋሽም። በክፉ አይጠረጥርም። ሚስጥር ይጠብቃል። ትሁት ነው። አይኮራም። በሰው አያፌዝም። ትልቆችን ያከብራል። አዋቂዎችን ያልቃል። ከበጎ ሰዎች ጋር ይውላል። ሰዎች እንዲጠቀሙና፣ ጉዳትን ከነርሱ ለመከላከል ይጥራል። ሙስሊሞችን ለማስታረቅ ይሰራል። ወደጌታው መንገድ በጥበብና በመልካም ግሳጼ ይጠራል። በሽተኛን ይጠይቃል። የሞተን ይቀብራል። በጎ የዋለለትን ያመሰግናል። ውለታውንም ይመልሳል። ክፋቱን ይታገሳል። በቻለ መልኩ እንዲደሰቱ ይጥራል። ወደ በጎ ያመላክታል። ገርነትን ይወዳል። ማካበድንና ማጥበቅን ይጠላል። በሁሉም ጉዳዮች። ፍጹም ፍትሐዊ ነው። አይበድልም። ግፍ አይሰራም። አያስመልስልም። አይልመጠመጥም። በተግባሩና በውጤቱ አይኮራም። ቀጥ ያለና ጽኑ ነው። ምንም ይፈጠር ምን እንደ እስስት አይቀያየርም። ታላላቅ ጉዳዮችን ይወዳል። እንቶ ፈንቶ ነገሮችን ይጠላል። ንግግር አያወሳስብም። አይራቀቅም። ሰዎችን አይንቅም። ቸር ነው። በስጦታው አይመጻደቅም። ለውለታው ምላሽ አይጠብቅም። እንግዳ ተቀባይ ነው። በሚገባ ያስተናግዳል። የተቸገረን ይረዳል። የሰው እጅ በምንም መልኩ አያይም። ሰጭ ከተቀባይ እንደሚበልጥ ያምናል። በቀላሉ ይግባባል። ይላመዳል። ልምዶቹን በኢስላም መስፈርት ይመዝናል። የሚበጁትን ይይዛል። የማይበጁትን ይጥላል። በአመጋገቡ፣ ሲጠጣ፣ ሰላምታ አቀራረቡ፣ ሰዎችን ሲጠይቅ፣ ሰዎች ወደተሰበሰቡበት ቦታ ሲገባ እና በሌሎችም የእለት ከእለት ክንውኖች የኢስላምን አደብ ይከተላል።

የሙስሊም ስብእና አንጸባራቂ ማንነት ቁርአንና ሐዲስ እንደቀረጹት። አእምሮው በኢስላማዊ አስተሳሰብ ሲሞላ፣ ቀልቡ የእምነት ብርሃን ሲሰርጽበት ይህን ይመስላል። እንዲህ ዓይነት ድንቅና አንጸባራቂ ስብእና ያለው ግለሰብ መቅረጽና በሕይወት ውስጥም በተግባር ማሣየት የትኛውም አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና፣ አይዲዮሎጂና ስርዓት እውን ሊያደርጉት የሚመኙት ታላቅ ስልጣኔያዊ ስኬት ነው። በዘመናችን ዓለምን ካጥለቀለቁት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ስኬቶች ሁሉ የላቀ ስኬት ነው። ምክንያቱም በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ትልቁ ፍጡር የሰው ልጅ ነውና። እርሱን ለማስደሰት እና ለማምጠቅ፣ እንዲሁም ሰብአዊ ፍጡር ያሰኘውን ጎኑን ለማጎበልጸግና ለማፋፋት ለምእተ ዓመታት ጥረት ተደርጓል።

ስለዚህም በሰው ልጅ ቁሳዊ ጎን ላይ ብቻ በማተኮር ሰው ያሰኘውን ጎኑን የዘነጋ፣ መንፈሱን ለማበልጸግና የበጎነት ምንጭ ለማድረግ ተገቢውን ጥረት የማያሳይ ስልጣኔ ጎደሎ ስልጣኔ ነው። የሰብአዊውን ስልጣኔ አብይ መስፈርት አያሟላም። ምክንያቱም የሰውን ልጅ አንኳር ማንነት ዘንግቷልና። ሰው የሚያሰኘውን ጎኑን ረስቷልና።

የሰው ልጅ የደረሰባቸው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሚሳየሎች፣ ሣተላይቶች፣ ቴሌቪዢኖች፣ ቪዲዮ፣ ኢንተርኔት፣ ኮምቲዩተር፣ ወዘተ ሰብአዊነቱን ለማጎልበትና ውስጣዊ እርካታን ለማጎናጸፍ ተግባር እስካልዋሉ ድረስ ፋይዳ የላቸውም።

وَنَفْسٍ وَمَا سَوَّاهَا فَأَلْهَمَهَا فُجُورَهَا وَتَقْوَاهَا قَدْ أَفْلَحَ مَن زَكَّاهَا وَقَدْ خَابَ مَن دَسَّاهَا

“በነፍስም ባስተካከላትም፤ አመጽዋንና ፍርሃትዋንም ባሳወቃት (አምላክ እምላለሁ)። (ከኀጢኣት) ያጠራት ሰው ፍላጎቱን በእርግጥ አገኘ። (በኀጢኣት) የሸፈናትም ሰው በእውነት አፈረ።” (አሽ ሸምስ፤ 7-10)

የሰው ልጅ እድገት የሚለካው ባስመዘገበው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤት ብቻ ሣይሆን በይበልጥ መሠረታዊ በሆነ መመዘኛ ነው። እርሱም ፍቅር፣ መተባበር፣ መተሳሰብ፣ ሌሎችን ከራስ ማስቀደም፣ መስዋእትነት፣ ጽናትና ቀጥተኛነት፣ በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ጻእድነትና በሌሎችም ሰብአዊ እሴቶች ማበብ እና መጎልበት ነው።

የሕብረተሰቡ መሠረትና የየትኛውም ማሕበራዊ ተሐድሶ አስኳል ግለሰቦች በመሆናቸው ትክክለኛ ሰብአዊ ማሕበረሰቦች ግለሰቦችን ለመቅረጽና ለማነጽ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። በጎ ጎናቸውን ለማጎልበትና የክፋት ዝንባሌያቸውን ለማክሰም ይጥራሉ። ብቁና መልካም ዜጎች ይሆኑ ዘንድ። የመልካም ዜጎች ድምር ጠንካራ፣ ንጹህና የሰለጠነ ሕብረተሰብ ይፈጥራል።

ኢስላማዊ ሕብረተሰብ የተሟላና ያደገ ሕብረተሰብ ነው። የሰለጠነ ሕብረተሰብ ነው። ሙስሊም ግለሰብ ኢስላም ባስተማረው ማሕበራዊ ግንኙነቶችና ስነ ምግባሮች አማካይነት ጥሩ ማሕበራዊ ስብእና ያለው ዜጋ ይሆናል።

በአሁኑ ሰአት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙስሊሞች መካከል የሚስተዋለው መከፋፈልና መናቆር ሙስሊሞች ከኢስላም አስተምህሮ መራቃቸውን፣ ከአላህ ጋር ያላቸው ግንኙነት መላላቱን፣ የእምነት ትስስራቸው መዳከሙን፣ ትክክለኛ ወንድማማችነት ማጣታቸውን የሚያመላክት ነው። በዚህም የተነሳ በገዛ አገራቸው ውስጥ የድንቁርና አስተሳሰቦች ተስፋፉ። ባእድ መርሆዎች በነርሱ ላይ ሰየጠኑ። በመስሊሞች ሰማይ ላይ ብዙ ፍልስፍናዎች ነገሱ። መርዞች ወደ ሕብረተሰቡ ሰረጹ። በሽታዎች ተስፋፉ። እናም በዓለም መድረክ ከገለባ የቀለሉና ዋጋ ያጡ አደረጓቸው።

ለሙስሊም ግለሰብ ትክክለኛ መንፈሳዊና አስተሳሰባዊ እነጻ ቢሰጠውና ስብእናው ቢቀረጽ ኖሮ ይህ ሁሉ ጥፋት ባልተከሰተ ነበር። በሙስሊሞች ላይ የተከፈተው ዘመቻ ይበልጡነ ያነጣጠረው በሙስሊም ግለሰብ ላይ ነው። አስተሳሰቡን በመቀየርና መንፈሱን በማላሸቅ ላይ ነው። ወራሪዎች በሙስሊሞች ላይ የዘመቱት በሁለት አቅጣጫ ነበር። የመጀመሪያው አቅጣጫ የሙስሊም ግለሰብን ኢስላማዊ ስብእና ማናጋት ነበር። ሁለተኛው አቅጣጫ ደግሞ አስተሳሰባዊና መንፈሳዊ ድባቡን መበከል ነበር። ወይም ደግሞ እንግዳ የሆኑ አስተሳሰቦችን መጋት ነበር።

በበርካታ ሙስሊም ሐገሮች ያሰቡትን ማድረግ ችለዋል። ኢስላማዊ ስብእናን አናግተዋል። ከመሠረታዊ ማንነቱ ነጥለውታል። በአስተሳሰብም፣ በስሜትም፣ በተግበርም እነርሱን እንዲከተል አድርገዋል። ከሐይማኖታዊና ስነ ምግባራዊ እሴቶቹ ሁሉ አራቁተውታል። ወደ ታሪክ መድረክ እንዲገባ እና የምድር ላይ ዋጋ ያለው ፍጡር እንዲሆን ያስቻለውን መለኮታዊ ማንነቱን አጥፍተውበታል።

በጃሂልያ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በመደናበር ላይ ያለው ሕዝባችን ወደ አላህ መንገድ ሲመለስ የቀድሞ ማንነቱን መልሶ ይጎናጸፋል። የሚዋደድ፣ የሚተዛዘን፣ የሚተሳሰብ፣ ነጻና ጠንካራ የሆነ አንድ ሕዝብ ይሆናል። ያኔ ከፊት ለፊቱ የሚቆም ምድራዊ ሐይል አይኖርም። ያኔ በእርግጥም የእምነት ሕዝብ ይሆናል። አላህ አማኝን ሕዝብ እንደሚረዳ በቁርአኑ በግልጽ ቃል ገብቷል፦

وَلَقَدْ أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ رُسُلًا إِلَىٰ قَوْمِهِمْ فَجَاءُوهُم بِالْبَيِّنَاتِ فَانتَقَمْنَا مِنَ الَّذِينَ أَجْرَمُوا ۖ وَكَانَ حَقًّا عَلَيْنَا نَصْرُ الْمُؤْمِنِينَ

“ከአንተ በፊትም መልክተኞችን ወደየሕዝቦቻቸው በእርግጥ ላክን። በግልጽ ማስረጃዎችም መጡባቸው። ከእነዚያ ካመጹትም ተበቀልን። ምእመኖቹንም መርዳት በእኛ ላይ ተገቢ ሆነ።” (አል ሩም 30፤ 47)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here