ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንደ ታላቅ የፖለቲካ መሪ

0
3988

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ነቢይም የአገር አስተዳዳሪም ነበሩ። አመራራቸውም ከየትኛውም መሪ በተሻለ መልኩ እጅግ ጠንካራ፣ የላቀና የመጠቀ ነበር። ነቢያችን በመልካም ሥራቸውም ሆነ በመንፈሣዊ ህይወታቸው ለዓለማት ሁሉ ህዝቦች ታላቅ ተምሣሌት የሚሆኑ ናቸው። እጅግ የተከበሩና በእዝነት የተሞሉ አስተማሪ፣

የታላቅ ስብእና ባለቤት፣ ፅኑ መሪና የለውጥ ቀያሽም ሲሆኑ በቤት ለቤተሠባቸው መልካም ባል፤ በውጭ ደግሞ ለህዝባቸው ታላቅ የፖለቲካ መሪ ነበሩ። በድንቅ ፖለቲካዊ አመራራቸው የዐረብን ባህረሠላጤ ከማዋሀዳቸውም በላይ እጅግ በተሣካ ወታደራዊ አመራራቸው ደግሞ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል በማድረግ መዲናን መቀመጫው ያደረገ ታላቅ መንግስትም መሥርተው ነበር። የፖለቲካ መሪነታቸው ሞራላዊና መንፈሣዊ አካሄድን ያጣመረ ሲሆን እንደማንኛውም የሰው ልጅ ሁሉ በህይወት ዘመናቸው በድክመትና በጥንካሬ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈዋል። በመካም ሆነ በመዲና የተከተሉት የአመራር ሂደት ትልቅ የሆነ የፖለቲካ አመራር ችሎታቸውን የሚያሣይ ነበር።

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሁሌም ቢሆን ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛና ዝግጁ ነበሩ። በሰዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችንና ውዝግቦችን ለመፍታት አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የተለየ ችሎታ ለግሦአቸዋል። ይህ ስጦታ ነቢይ ከመሆናቸውም በፊት ጀምሮ አብሮአቸው የነበረ ሲሆን ያኔ በወጣትነታቸው ዘመን በመካ ሰዎች መካከል ይከሠቱ የነበሩ ግጭቶችንና ውዝግቦችን ይፈቱ የነበረበት ሁኔታ ሁሌም ይጠቀሣል። በተደጋጋሚ የተነገረው የከዕባው ክስተትም ከነኚህ መካከል አንዱ ነው። በወቅቱ ለከዕባ እድሣት ይደረግ በነበረበት ወቅት የተከበረውን ሀጀረልአስወድን በቦታው ማለትም በደቡብ ምሥራቅ የካዕባ ማእዘን ላይ ማን ያስቀምጥ በሚለው ጉዳይ ላይ ሁሉም ጎሣዎች ይህን ክብር ይፈልጋሉና ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጠረ። ነቢዩም ሰላለሁ ዐለይህ ወሠለም በዚህ ጉዳይ ላይ በመካከላቸው እንዲፈርዱ ተጠይቀው ነገሩን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ፈትተውታል። የፈቱበትም ሁኔታ ጥበባቸውንና ከፍተኛ ብልሀታቸውን ያሣየ ነበር። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የራሣቸውን ካባ ከድንጋዩ ሥር በማንጠፍ በቦታው የነበረ ሰው ሁሉ የመጣበትን ጎሣ በመወከል የካባውን ጫፉ እንድይዝና ከፍ እንዲያደርግ ካደረጉ በኋላ ድንጋዩ ቀድሞ ከነበረበት የማስቀመጫ ቦታው ላይ ሲደርስ በተከበረ እጃቸው ደልድለው አስቀምጠውታል።

ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሁሌም በሰዎች መካከል ሰላምን ያወርዱ ዘንድ ይፈለጉ ነበር። በወጣትነታቸው ወቅት የመካ ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ ግጭቶችን የሚያረግብ ኮሚቴ ባቋቋሙበት ወቅት እርሣቸው ከትላልቅ የመካ ሰዎች ጋር ተመርጠው ይህንኑ ኮሚቴ ተቀላቅለው ነበር። ይህም ኮሚቴ “ሂልፍ አልፉዱል” የሚባል የመልካም ሥራ ቃለ መሃላ ፈፅሞ ይንቀሣቀስ ነበር። ኋላ ላይ በነቢይነታቸው ወቅት ይህንኑ ኮሚቴ በማስታወስ “ አሁን ላይ ሆኜ ለዚያ መልካም ሥራ ቃል ኪዳን ብጠራ ኖሮ በተገኘሁ ነበር”በማለት ክስተቱን በአድናቆት አስታውሰዋል።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የጥሩ ሀሣብ ባለቤት ብቻ ሣይሆኑ የተግባር ሰውም ጭምር ነበሩ። የተላኩበትን መለኮታዊ መልእክት ለሁሉም የሰው ዘር አድርሰዋል። ነገር ግን ይህ የሆነው እራሣቸውን ከሚኖሩበት ማህበረሰብ አግልለው አልነበረም። መልካም ባህሎችንና ልማዶችን ከማህበረሰባቸው በመውሰድ ከነሱ ተጠቅመዋል። ምንም እንኳ አጎታቸው አቡ ጧሊብ የተውሂድ መልእክታቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑም ወደ ኢስላም ጥሪ በሚያደርጉበት ሥራቸው ላይ ግን እርዳታቸውንና እገዛቸውን አልነፈጓቸውም ነበር። ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የአጎታቸውን እርዳታ ያደንቁና ከግምት ያስገቡ ነበር። ከአጎታቸው ሞት በኋላ በደዕዋ ሥራቸው ላይ አጋዠ ሰው ፍለጋ ወደ ጧኢፍ ሄደው እዚያ ከሚገኙት አንዳንድ ጎሣዎች ትብብር ቢጠይቁም ያሰቡት ሣይሣካላቸው ቀረ። እዚህ ጋ ማስተዋል ያለብን ነጥብ በሥራቸው ላይ የሚያግዛቸውን ፍለጋ ሙከራ ማድረጋቸውን ነው።

ወደ ሀበሻ የተደረገው ጉዞ ከሌሎች ጋር ህብረት በመፍጠር በኩል ሌላው የፖለቲካ አመራር ብቃታቸውን ያሣዩበት አጋጣሚ ነበር። በመካ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ እንግልቱና ስቃዩ በበዛና የተወሰኑ ተከታዮቻቸውም በዚያ ሁኔታ ላይ መኖሩ በከበዳቸው ጊዜ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ወደ ሀበሻ መሠደድንና ከክርስቲያኑ ንጉስ እርዳታ መፈለግን ፈቀዱላቸው። ሀባሻ በደረሱም ጊዜ ሙስሊሞች ሰላም አገኙ። በፀሎትም በመበርታት የንገሱንና የአጃቢዎቹን እገዛ ወደ ልዩ እንክብካቤ እስከመለወጥ ደረሱ። ሙስሊሞቹ ከንጉሠ ነገስቱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እጅግ ልዩና ያማረ ስለነበር ንጉሱ እስልምናን ሊወድ ቻለ፤ በመጨረሻም እስልምናን ተቀብሎ ሙስሊም ሆኖ ሞተ።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ጠንካራና ትልቅ ችሎታ ያላቸው የፖለቲካ መሪ ነበሩ። ጠላቶቻቸው እርሣቸውን ለማስፈራራት አቅምም ወኔም አልነበራቸውም። ለየትኛውም ዓይነት ሙከራ እጅ ሰጥተው አያውቁም። ያኔ ገና በእስልምና መባቻ አካባቢ የመካ ሰዎች ከተልእኮአቸው ይመለሱ ዘንድ በርካታ ገንዘቦችንና እርሣቸው የሚፈልጉትን ዓለማዊ ጥቅማ ጥቅም ሁሉ አቅርበውላቸው በምትኩ እስላማዊ ጥሪያቸውን እንዲያቆሙ ቢያባብሏቸውም እርሣቸው ግን ፅናትና ትህትናን በተላበሠ መንፈስ ሁሉንም ስጦታቸውን እንደማይቀበሉ ነግረው መለሷቸው።

ወደ መዲና የገቡት በስደት ቢሆንም ኋላ ላይ ግን ሁሉም ሰዎች በእኩል ዐይን የሚታዩበትን ጠንካራ መንግስት መሠረቱ። በአስተዳደራቸውም ወቅት ነገሮች ሁሉ ውሣኔ የሚያገኙት በምክክር ነበር። ሁሉም ሰዎች ተመሣሣይ ህግ ይከተላሉ። የርሣቸው መንግስት ለአንድ ቤተሰብ አሊያም ቡድን ያልቆመ፤ ሁሉንም ሰው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የሚመለከት የህግ የበላይነት የሠፈነበት መንግስት ነበር። ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች እንኳ በዚህ መንግስት ውስጥ እኩል መብት ነበራቸው። የጡእማ ኢብኑ ዐብረቅን ታሪክ እዚህ ላይ ማንሣት እንችላለን። ጡዕማህ የአንድን የመዲና ሰው ጥሩር በሰረቀና በክስተቱም አይሁዶችን በወነጀለ ጊዜ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሰዎች ከዚህ ዓይነቱ ኢፍትሃዊነት ይታቀቡ ዘንድ የቁርኣን አንቀፅ አወረደ ።(ሱረቱ ኒሣእ ቁ 110 – 112 ያለውን የቁርኣን አንቀፅ ይመልከቱ)። በመዲና የሚኖሩ የአይሁድ ማህበረሰቦችንም ነፃነት አወጀ። ሙስሊም የነበረው ጡእማም ወንጀለኛነቱ ተረጋግጦ ተገቢውን ፍርድ አገኘ።

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም የህዝባቸውን ሃይማኖታዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት በሚገባ መልኩ ጠብቀዋል። ለህዝባቸው ደዕዋ ማድረግ ብቻ ሣይሆን ስለ ኢኮኖሚ ደህንነታቸውም ጭምር ያስቡ ነበር። ከበርካታ ጎሣዎች ጋርም የትብብርና የቃልኪዳን ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። ነቢያችን ትልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ችሎታም ነበራቸው። ለቃላቸው ተገዠ ሲሆኑ ከሌሎች ጋር ያደረጓቸውን ውሎችና ስምምነቶች ያፈረሱበት አጋጣሚ አልነበረም። ህዝቦቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን አሣልፈው ሰጥተው አያውቁም። በዙሪያቸውና በአካባቢያቸው እየተካሄደ ስላለው ነገር ጠልቀው የሚያነቡ ሲሆን ተከታዮቻቸውንም መልስ ለመስጠት ባስፈለገ ጊዜ ያመች ዘንድ ዝግጁና ንቁ እንዲሆኑ ያደርጉ ነበሩ። ጠንካራና ከጠላቶቻቸው በተሻለ ሁኔታና አቅም ላይ የሚገኙ ቢሆንም እንኳ አንድም ጊዜ ቀድመው ጦርነት ጭረው አሊያም ቀስቅሰው አያውቁም። ሁሌም ሰለ ሰላምና ሠላማዊ ግንኙነቶች ያስተምሩ ነበር።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የታላቅ ትእግስትና የቁርጥ ውሣኔ ባለቤትም ነበሩ። ከህይወት ታሪካቸው የምንማራቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ። ከመሪነታቸው ገፅታ እጅጉን ጎልቶ የሚወጣው የሁልጊዜም ታማኝነታቸውና የእውነት ተናጋሪነት ባህሪያቸው ነው። ለዚህም እጅግ ጥሩ ምሣሌ ሊሆን የሚችለው በአንድ ወቅት የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ቀንደኛ ጠላት የነበረ የመካው ባለሟል አቡሱፍያን ከቢዛንታይኑ ንጉስ ሂረቅል ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ነው። ይህ ቃለምልልስ የተካሄደው በ628 ሲሆን ሂረቅል ወደ ኢየሩሣሌም መንፈሣዊ ጉዞ ባደረገበት ወቅት ከነቢዩ የተላከለት ደብዳቤ እዚያው እያለ ደረሰው። ደብዳቤውን ተቀብሎም ስለዚህ ነቢይ ነኝ ስለሚለው ሰው የሚያውቅ የሀገሩና የጎሣው የሆነ የቅርብ ሰው እንዲያፈላልግለት የፖሊስ ሀላፊውን አዘዘ። በወቅቱ የመካ መሪ የነበረው አቡሱፍያን ለንግድ የመካ ሰዎችን አስከትሎ ወደ አካባቢው መጥቶ ስለነበር የፖሊስ አዛዡ ያሠማራቸው ሰዎች አግኝተውት ወዲያው ወደ ኢየሩሣሌም ወሠዱት።

ሂረቅልም የሮም የተከበሩ ታለላቅ ሰዎች ዙሪያው ተሰብስበው ባሉበት ሁኔታ አቡሱፍያንንና የሀገሩን ሰዎች ወደ እልፍኙ አስገባ። የሚጠይቀውንም እንዲተረጉምለት አስተርጓሚውን አስጠራ።

“ከናንተ መካከል በዝምድና ለዚህ ነቢይ ነኝ ለሚለው ግለሰብ ቅርብ የሆነ ሰው ማነው” አላቸው።

አቡሱፍያን “እኔ ነኝ” አለ (ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ጋር በአምስተኛው አያት ላይ ይገናኛሉ።) ሂረቅል “እሱን ወደኔ አቅርቡ የሱ ሰዎች ከኋላው ይሁኑ።” በማለት አዘዘ ።

አቡ ሱፍያን ከሰዎቹ ፊት እንዲቀመጥ ተደረገ። ሒራቅል ለሰዎቹ “ይህንን ሰው እኔ እጠይቀዋለሁ በንግግሩ የሚዋሽ ከሆነ እናንተ ትይዙታላችሁ” አላቸው። አቡ ሱፍያን ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ይላል “ብዋሽ እንኳ በነሱ ዘንድ ያለኝን ደረጃና ክብር ሰለሚያውቁ ሰዎቼ አይዩዙኝም ነበር። ነገር ግን እኔ ከመካ ባለሟሎች አንዱ ሆኜ ሣለሁ እንዴት እዋሻለሁ? ውሸት ከኔ ዓይነቱ አያምርም” የቢዛንታይኑ ንጉስ ሰለነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መጠየቅ ያዘ ።

ሒራቅል– በናንተ ውስጥ ዘሩ (የቤተሠቡ የክብር ደረጃ) እንዴት ነዉ?

አቡ ሱፍያን– እሱ ከኛ ዘንድ ከተከበረ ቤተሠብ ነው።

ሒራቅል– ከሱ በፊት ከናንተ ዉስጥ ነቢይ ነኝ ብሎ የተነሣ ሰው ነበር?

አቡሱፍያን– አይ አልነበረም።

ሒራቅል – ከቀደምት አባቶቹ ንግስና የነበራቸው ነበሩ (የንጉሣውያን ዘር ነው)?

አቡ ሱፍያን – አይ የሉም/ አይደለም።

ሒራቅል – ትላልቅ /የተከበሩ/ ሰዎች ናቸው የሚከተሉት ወይንስ ደካሞቹ?

አቡ ሱፍያን – ደካሞቹ ናቸው የሚከተሉት።

ሒራቅል – ከእለት ወደ እለት በቁጥራቸው ይጨምራሉ ወይንስ ይቀንሣሉ?

አቡ ሱፍያን – ይጨምራሉ።

ሒራቅል – ወደ አዲሱ ሃይማኖት ከገቡ በኃላ ሃይማኖቱን ጠልተው የሚወጡ አሉን?

አቡ ሱፍያን – የሉም።

ሒራቅል – ነቢይ ነኝ ብሎ ከመነሣቱ በፊት ባለው ህይወቱ በውሸት ይታማ /ይዋሽ ነበር?

አቡ ሱፍያን – አይታማም/ አይዋሽም ።

ሒራቅል – ይክዳል /ቃል ኪዳን ያፈርሣል?

አቡ ሱፍያን – አይ አያፈርስም …. አሁን ለነገሩ ለተወሠኑ ጊዜያት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት አለን። በዚህ ዙሪያ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አላውቅም ።

ሒራቅል – ተዋግታችሁት ነበር?

አቡ ሱፍያን – አዎን

ሒራቅል – የጦርነት ውሎአችሁ እንዴት ነበር?

አቡ ሱፍያን – ተራ በተራ ነው የምንሸናነፍው፤ ድል ያደርገናል ድል እናደርገዋለን።

ሒራቅል – በምንድን ነው የሚያዛችሁ?

አቡ ሱፍያን – አላህን ብቻ እንድናመልክና በሱ እንዳናጋራ፣ ለጣዖታት እንዳንገዛ፣ አያቶቻችን ሲሉ የነበሩትን ሁሉ እንድንክድ፣ በሰላት፣ በምፅዋት፣ እውነትን እንድንናገር፣ ቁጥብነት/ ትህትና እንዲኖረን፣ ዝምድናን እንድንቀጥል እና በሣሠሉት ያዘናል።

ከዚህ ቃለ ምልልስ በኋላ ሂረቅል ለአስተርጓሚዉ ለአቡ ሱፍያን አንዲህ በለው ሲል ተናገረ –

“ሰለዘሩ ሁኔታ ጠይቄህ ከተከበረ ቤተሠብ መሆኑን ነገርከኝ፤ እርግጥ ነው መልዕክተኞች የሚላኩት ከህዝቡ ውስጥ የተከበረ ከሚባል ቤተሠብ ነው። ከናንተ ውስጥ ‘ይህን ዛሬ እሱ ነኝ ያለውን የነቢይነት ቃል የተናገረ ሰው አለ ወይ’ ብዬ ብልህ ‘የለም’ አልከኝ። አለ ብለሀኝ ቢሆን ኖሮ ‘ይህ ሰው ከዚህ በፊት የተባለን ነገር የሚደግም ሰው ነው’ ባልኩህ ነበር። ቀደምት አባቶቹ የንጉሣውያን ዘር የነበሩ በሆነ ኖሮ ‘ይህ ሰዉ የቤተሰቡን ንግስና ለማስመለስ የሚታገል ነው’ ባልኩህ ነበር። ነቢይ ነኝ ከማለቱም በፊት የመዋሸት ባህሪ እንደሌለበት ስትነግረኝ ‘ሰውን ያልዋሸ ሰው በአምላኩ ላይ ሊዋሽ እንደማይችልና ድፍረቱም እንደሌለዉ ተረዳሁኝ።’ ‘የሚከተሉት ሰዎች (ተከታዩቹ) ተራና ደካሞች መሆናቸው ደግሞ አይገርምም እነሱ ናቸውና የነቢያት ተከታዮች።’ ‘ይጨምራሉ ወይንስ ይቀንሣሉ’ ብዬ ብጠይቅህ እንደሚጨምሩ ነገርከኝ፤ እስኪሟላ ድረስ የኢማን ጉዳይ ይሀው ነው እየጨመረ ይሔዳል እንጂ አይቀንስም። ‘ወደ አዲሱ ሀይማኖት ከገባ በኃላ ጠልቶ የሚመለስ ሰው አለ ወይ’ ብዬ ስልህ እንደሌለ ነገርከኝ ‘ከቀልብ ውስጥ ማረፊያን እስካገኘ ድረስ የኢማን ነገር ይሀው ነው ሰውን ያፀናል።’ ‘ይክዳል/ ቃል ያፈርሣል ወይ’ ስልህ እንደማይክድ/ ቃሉን እንደማያፈርስ ነገርከኝ፤ ‘እርግጥ ነው መልዕክተኞቸ አይክዱም በቃላቸዉም ታማኝ ናቸው’። በምን እንዲሚያዛችሁ ስጠይቅህ አላህን እንድታመልኩ በሱም አንዳችን ነገር እንዳታጋሩ፣ ባዕድ አምልኮን እንድትርቁ፣ ዝምድናን በመቀጠል፣ በሰላትና በምፅዋት፣ እውነትን በመናገር፣ በቁጥብነት አልከኝ።

በመጨረሻም ሒራቅል እንዲሀ ሲል መሰከረ

“በርግጥ ያልከው ሁሉ እውነት ከሆነ ይህን የኔን ቦታ እጅግ ቅርብ በሆነ ጊዜ ውስጥ መውረስ የሚችል ሰው ቢኖር ይህ ሰው ብቻ ነው። ከናንተ አካባቢ ነቢይ እንደሚወጣ አውቅ ነበር ነገር ግን ከውስጣችሁ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም። ወደዚህ ሰው መድረስ የሚችል ብሆን ኖሮ በፍጥነት ላገኘው ጉጉቱ ነበረኝ። እሱ ዘንድ ሆኜ በሆን የእግሩ አጣቢ መሆንንም በወደድኩ ነበር።”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here