ኢስላም የአላህና የመልዕክተኛው ፍቅር ማለት ነው። የአላህና የመልዕክተኛው ፍቅር በያንዳንዱ ሙስሊም ልቦና ውስጥ ሊሰርፅ ይገባል። ማንም ሰው ጥልቅ የሆነ የአላህና የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ፍቅር ሳይኖረው እውነተኛ ኢስላማዊ ህይወት ሊኖር አይችልም። ኢስላም እንዲሁ ብቻ እምነትና የቅዱሳን በዓላት ጥርቅም አይደልም።
ይልቅስ፤ በአላህና በመልዕክተኛው ፍቅር የተገነባ ግንኙነት ጭምርም እንጂ። ይህ ፍቅር የእምነታችን አካልና የእምነታችን ማሳያ ነው። እምነት ያለዚህ ፍቅር ጎዶሎ ነው። ይህ ፍቅር በጨመረ ቁጥር ደግሞ እምነታችን ይበልጥ አንጸባራቂ፣ ይበልጥ ውብና ምድርን በቆንጆ ሽታው የሚያጥናት ይሆናል።
الَّذِينَ يَتَّبِعُونَ الرَّسُولَ النَّبِيَّ الْأُمِّيَّ الَّذِي يَجِدُونَهُ مَكْتُوبًا عِندَهُمْ فِي التَّوْرَاةِ وَالْإِنجِيلِ يَأْمُرُهُم بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَاهُمْ عَنِ الْمُنكَرِ وَيُحِلُّ لَهُمُ الطَّيِّبَاتِ وَيُحَرِّمُ عَلَيْهِمُ الْخَبَائِثَ وَيَضَعُ عَنْهُمْ إِصْرَهُمْ وَالْأَغْلَالَ الَّتِي كَانَتْ عَلَيْهِمْ فَالَّذِينَ آمَنُوا بِهِ وَعَزَّرُوهُ وَنَصَرُوهُ وَاتَّبَعُوا النُّورَ الَّذِي أُنزِلَ مَعَهُ أُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ
“ለነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራት በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነብይ የኾነውን መልዕክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት (በርግጥ እጽፋታለሁ) በበጎ ሥራ ያዛቸዋል፤ ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል፤ መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል፤ መጥፎ ነገሮችንም በነሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል። ከነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያም በነሱ ላይ የነበሩትን ንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል። እነዚያም እነርሱ በርሱ ያመኑ ያከበሩትም የረዱትም ያንን ከርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ እነዚያ እነሱ የሚድኑ ናቸው።” (አል-አዕራፍ 7፤157)
قُلْ إِن كَانَ آبَاؤُكُمْ وَأَبْنَاؤُكُمْ وَإِخْوَانُكُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ وَعَشِيرَتُكُمْ وَأَمْوَالٌ اقْتَرَفْتُمُوهَا وَتِجَارَةٌ تَخْشَوْنَ كَسَادَهَا وَمَسَاكِنُ تَرْضَوْنَهَا أَحَبَّ إِلَيْكُم مِّنَ اللَّهِ وَرَسُولِهِ وَجِهَادٍ فِي سَبِيلِهِ فَتَرَبَّصُوا حَتَّىٰ يَأْتِيَ اللَّهُ بِأَمْرِهِ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ
“አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ወንድሞቻችሁም ሚስቶቻችሁም ዘመዶቻችሁም የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም መክሰሩዋን የምትፈሩዋት ንግድም የምትወዷቸው መኖሪያዎችም እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልዕክተኛው በርሱ መንገድ ከመታገልም ይበልጥ የተወደዱ እንደሆኑ አላህ ትዕዛዙን እስኪያመጣ ድረስ ተጠባበቁ በላቸው፤ አላህም አመጠኞች ሕዝቦችን አይመራም።” (አት-ተውባህ 9፤24)
ኢስላም የፍቅር ኃይማኖት ነው። ፍቅሩ የእውነት ፍቅር ነው። ባህሮችና ውቅያኖሶች ቀለም ፈጥረው ቃላት ቢመሰርቱ ይህን እውነተኛ ፍቅር መግለጽ ይሳናቸዋል። ኢስላማዊ ፍቅር የምር ፍቅር ነው። ልቦች የሚርበተበቱለት፣ ዓይኖች የሚያነቡለት፣ እጆችና እግሮች የሚዝሉለት፤ አዕምሮ ሙሉ ለሙሉ የሚንበረከክለት ልዩ ፍቅር። ይህ ፍቅር አላህን ቀጥሎም መልዕክተኛውን ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከማፍቀር ጀምሮ ለምድር ፍጥረታት ሁሉ የሚሰጥ ፍቅር ነው።
ፍቅር የኢስላም ምሰሶው ነው። እምነት ያለ ፍቅር ባዶ ነው። ፈፅሞ አይሞላም። ፍቅር የእምነታችን ጥንካሬ ማሳያ መነጽር ነው። ፍቅራችን ሲያብብና ውዴታችን ሲጎመራ እምነታችን ያንፀባርቃል፤ ያበራል፤ ሽታውም ለአለም ሁሉ ይደርሳል።
ግን መልዕክተኛውን ለምን እናፈቅራለን?
መልዕክተኛው ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ልዩ ናቸው። የምርጥነት ተምሳሌት የአላህ የመጨረሻ ነቢይ። የፍቅር መፅሀፍ ናቸው። የገለጡት የሚንበረከኩለት፤ ያነበቡት የሚወዱት የውዴታ ድርሳን ነው። መልዕክተኛው የፍቅር ፅጌረዳ ናቸው። ሽታው ያውዳል፤ ሳይፈልጉትም “ውደዱኝ አፍቅሩኝ” እያለ ይጣራል። መልዕክተኛው ሙሐመድ የተሟላ የሚያደርጋቸውን ባህሪያት ሁሉ ከፈጣሪያቸው የተቸሩ ድንቅ ፍጡር ናቸው። ቃላቸውና ተግባራቸው የተጣጣሙላቸው ድንቅ በድንቅነት ብቸኛ ሰው! ያዩዋቸው ሁሉ መስክረውላቸዋል። ያደመጡት ሁሉ ልባቸውን ሰጥተዋቸዋል። ታሪካቸውን ያነበቡ ሁሉ አንብተውላቸዋል።
አራተኛው ኸሊፋ የአጎታቸው ልጅ ዐሊይ እንዲህ ይላል፡- “በድንገት ረሱልን ያያቸው ሰው በማንነታቸው ይመሰጣል፤ የሚያውቃቸው ሰው ሲያያቸው ደግሞ ያፈቅራቸዋል”። ለነገሩ ረሱልን ከማንም በላይ አላህና መላኢካዎች ያፈቅሩዋቸዋል።
ነቢዩ ሙሀመድ ለዓለማት እዝነት የተላኩ ሰው ናቸው (ራህመቱን ሊል ዐለሚን)። ከምሳሌዎች ሁሉ የላቁ ምርጥ ምሳሌ ናቸው (ኡስዋቱል ሀሰና)። የአላህን ውዴታ ድንቅ መንገድም እሳቸው ብቻ ናቸው። የኢስላም ትክክለኛ መንገድ ነቢዩ ሙሐመድን ማፍቀር ነው። እሳቸውን ማፍቀር የስኬትና የጀነት ቁልፍ ነው። ይህች ዓለም ስንት የለውጥ ሀይሎችን አሳልፋለች።ቢሆንም ግን፤ እንደ ነቢዩ ሙሐመድ ሁለገብ ሰው ሆኖ፣ ስሙ ሁሌም ለዘላለም በሁሉም አፍ የሚወሳ ማግኘት ይሳናል።
እንዴት ነቢዩ ሙሐመድን ማፍቀር እንችላለን?
ይህ ወሳኝ ጥያቄ ነው። ከባድ መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው። ፍቅር ማለት በቃላት ውርጅብኝ የሚገለፅ የስሜት ዱላ አይደለም። ነገር ግን ፍቅር እውነትን ያዘለ፣ ቁርጠኝነት የታከለበት፣ ወደ ጥሩ ስራ የሚመራ መንገድ ነው። የእውነት ፍቅር ልብን ያርበደብዳል፤ አያስቀምጥም ለመልካም ስራ ያተጋል፤ ለእውነትና ለፍትህ ዘብ ያቆማል። በጥሩ ስራም ይገለፃል። በልብ የተቃኘው እና በምላስ የተላወሰው እንዲሁም በአካላት መልካም እንቅስቃሴ የታጀበው ፍቅር፤ እውነትኛ ፍቅር ይሰኛል።
ነቢያችን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “እናንተ ዘንድ እኔ ከወላጆቻችሁ፣ ከልጆቻችሁና፣ ከሰው ልጆች ሁሉ በላይ ተወዳጅ እስካልሆንኩኝ ድረስ የአንዳችሁም እምነት አልሞላም” (ቡኻሪ)።
የነቢዩ ፍቅር ደስታን ይለግሳል፣ በሀሴት ይሞላል። የምር ያዝናናል ወደ ቀጥተኛውም መንገድ ይመራል። እስቲ እነዚህን ቀጥሎ የተጠቀሱትን አምስት ነጥቦች ልብ እንበላቸው።
1. የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የህይወት ታሪክንና ፈለግ (ሱና) እንማር። ህይወታቸውን ስናውቀው ይበልጥ እናፈቅራቸዋለን። ፈለጋቸውን ስናነብ ብሎም ተግባራዊም ስናደርግ ይበልጥ እንወዳቸዋለን። የነቢዩ ሙሐመድ ፈለግ እንዲሁ የአንድና የሁለት መፅሀፎች ጥርቅም ሳይሆን የህይወት መስመር ነው። ረሱል የፍቅር መምህር ነበሩ። ሳር ቅጠሉን፣ ጠላት ወዳጃቸውን፣ ዘመድ አዝማዱን፣ የሚያፈቅሩ ድንቅ መምህር ናቸው። ይህን አይነት ስብዕና መላበስ የሚቻለው ደግሞ ስናውቀው ብቻ ነው።
قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ اللَّهَ فَاتَّبِعُونِي يُحْبِبْكُمُ اللَّهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ قُلْ أَطِيعُوا اللَّهَ وَالرَّسُولَ فَإِن تَوَلَّوْا فَإِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْكَافِرِينَ
“በላቸው፡ አላህን የምትወዱ ከሆናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና፤ ኃጢያታችሁንም ለናንተ ይምራልና አላህ መሃሪና አዛኝ ነው።” (አሊ ኢምራን 3፤ 31-32)
2. የፍቅራችን ማጠናከሪያ ድንቅ መሳሪያ ነውና ሁሌም ስማቸውን ስናወሳና ሲወሳ፣ የአላህ ሰላምና ሶላት ብሎም እዝነት (ሰለዋት) በርሳቸው ላይ ይሆን ዘንድ መለመን አለብን። ቁርኣን፡-
“አላህና መላዕክቱ በነብዩ ላይ የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ፤ እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በርሱ ላይ የአክብሮት እዝነትን አውርዱ የማክበርንም ሰላምታ ሰላም በሉ” (አል-አህዛብ 33፣56)።
3. ፍቅራችን ሙሉ ሊሆን ይገባዋል። እነዚያ አብረዋቸው የነብይነትን የአብዬት እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ የመከራውን ቀንበር አብረዋቸው ተሸክመው ከግብ ያደረሱትን ቤተሰቦቻቸውን (አህለልበይት)፣ ድንቅ ሶሃባዎች (ባልደረባዎቻቸውን) ልንወዳቸውና ልናከብራቸው ይገባል። እንዲሁም አርአያቸውን መከተል የግድ ይላል።
4. ነብዩን መውደድ ማለት ሕዝባቸውን (ኡማቸውን) መውደድ ማለትም ጭምር ነው። ለኡማቸው አባላት ጥንቃቄ ልናደርግና ለነርሱም አንድነትና ህብረት ልንሠራ ይገባል። በማንም ሠው ላይ (በተለይም በሙስሊም ላይ) መጥፎ ነገር ልናስብ ወይም ቂም ልንይዝ አይገባም። ረሱልን የወደደ፣ እርሳቸው ያፈቀሩትን ሁሉ ያፈቅራል፤ ያከበሩትን ሁሉ ያከብራል። ነቢዩ ፍጡርን ሁሉ ይወዱና ለነሱም ይሳሱ ነበር። እኛም ለፍጡራን ሁሉ ልንሳሳና ልናዝን ይገባናል። ለአንዳቸውም የጥላቻ መንፈስ በውስጣችን ልናሳድር አይገባም። ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ያፈቅሩትን እኛ ጠልተን እንዴት የሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ወዳጅ መሆን እንችላለን? አነስ ኢብኑ ማሊክ ነቢዩ እንዲህ በማለት መከሩኝ ይላል፡- “ልጄ ሆይ! ቀንንና ምሽትህን ለማንም የጥላቻ መንፈስ ሳይኖርህ ማሳለፍን አትዘንጋ!” ከዚያም እንዲህ አሉኝ “ልጄ ሆይ! ይሄ የኔ ፈለግ ነው፣ ፈለጌን የወደደ በእርግጥ እኔን ወደደ፣ በእርግጥ እኔን የወደደ ከኔ ጋር በጀነት ይሆናል” (ቲርሚዚ)።
5. የፍጥረታት መሪው ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የተላኩት ለዓለማት እዝነት ነው። በአለም ላሉ ፍጥረታት ሁሉ እዝነት። በዚህ ቃል የታነፀ የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ወዳጅ በእርግጥ ለሰው ልጅና ለፍጥረታት ሁሉ ያዝናል። ከዚህች ዓለም ላይ ድህነትን፣ ችግርን፣ ሰቆቃንና ረሀብን ለማጥፋት ይጥራል። ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ኢ-ፍትሀዊነትን ለማጥፋት ተልከዋል። ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የሚወድ ሁሉ ለሰላምና ፍትህ፣ ለነፃነትና መረጋጋት ዘብ ይቆማል። ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የሰውን ልጅ ከዚያ ከባድ የእሳት ቅጣት ለመታደግ ተልከዋል። የነቢዩ አፍቃሪ ሁሌም ለሰው ልጆች የእውነትንና የስኬትን መንገድ ይሰብካል። በትህትናና በርህራሄ ወደ አላህ ይጠራል- ድንቅ ምሳሌ፣ ድንቅ እዝነት፣ ድንቅ ትህትና፣ ድንቅ ሰው፣ ከታላቅ መልዕክት ጋር!!!
SAW
‘ኢስላም እንዲሁ ብቻ እምነትና የቅዱሳን በዓላት ጥርቅም አይደልም’ what does this statement meaning? what is the importance?
ወደነዋል አላህ ይውደድላችሁ