ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብያችን (ክፍል 1)

0
5723

የሚጠበቀው ንጋት

ዓለም በድቅድቅ ጨለማ ተውጣለች። በውስጡ ብርሃን ባረገዘ የአዲስ ነብይ ብስራትን የያዘ ድምጽ በጨለማው መሐል ይሰማል። ይህ ድምጽ ብዙ ጆሮዎችንና ልቦናዎችን ማንኳኳት በመጀመሩ በርካታ የመካ ነዋሪዎች ስለሚጠበቀው ስለዚህ ነብይ መነጋገር ጀምረዋል። ከፊላቸው ከፊሉን፡- “ይህ ነቢይ ይፋ ሲሆን ፈጥናችሁ እመኑበት።” እያለ ይመክራል፣ ይዘክራል። (ሲረቱ ነበዊያህ- ኢብን ሂሻም 1/203-204)

ልቦናዎች ፈርተዋል። ተስፋዎች ሁሉ በዚህ ነብይ ላይ ተንጠልጥለዋል። ይህ ነብይ የአዳኞች መቋጫ ነው። ሁሉም ወላጆች ይህ ነብይ ከነርሱ ዝርያ እንዲሆን ጓጉተዋል። ከዚህ የተነሳ ብዙ አባቶች ልጆቻቸውን ሙሐመድ በሚል ስያሜ ይጠሩ ጀምረዋል። (ጦበቃተል ኩብራ- ቢን ሰእድ 1/69)

ግና ይህ የሚጠበቀው ነብይ የሚፈለቀቀው ከወርቃማ የዘር ሐረግ መሆን አለበት። ይህም የዘር ሐረግ በነቢ ኢብራሂምና በነቢ ኢስማኢል ጀምሮ በአብደል ሙጦሊብና በአብደላህ ይጠናቀቃል። ልቦናዎች ይህን ብርሃን በዚህ መንገድ በኩል ይጠባበቁ ነበር። መከሰቻ ዘመኑ መቃረቡን የሚጠቁሙ ምልክቶች ተበራክተዋል። የጽልመቱ ክብደት የንጋቱን መቅረብ ያበስራል።

የዚያ ዘመን ሰው ለሕይወቱ ትርጉም፣ ለመኖሩ ዓላማ የሚያጎናጽፍ እሴት አልነበረውም። ይልቁንም ተግባሩ በቁርአን አገላለጽ የሚከተለው ነበር።

“እነዚያም የካዱት ሰዎች ሥራዎቻቸው (መልካሞቹ) በበረሃ ሜዳ እንዳለ ሲሪብዱ የጠማው ሰው ውሃ ነው ብሎ እንደሚያስበው በመጣውም ጊዜ ምንም ነገር ኾኖ እንደማያገኘው ነው። (ከሓዲው) አላህንም እሠራው ዘንድ ያገኘዋል። ምርመራውንም (ቅጣቱን) ይሞላለታል። አላህም ምርመራው ፈጣን ነው።” (አል-ኑር 24፤ 39)

ስሜቶች፣ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ሁሉ ይህንኑ የሚያንጸባርቁ ነበሩ።

“ወይም (መጥፎ ሥራዎቻቸውን) ከበላዩ ደመና ያለበት ማዕበል በሚሸፈነው ጥልቅ ባህር ውስጥ እንዳሉ ጨለማዎች ነው። (እነዚያ) ከፊላቸው ከከፊሉ በላይ ድርብርብ የኾኑ ጨለማዎች ናቸው። (በዚህች) የተሞከረ (ሰው) እጁን ባወጣ ጊዜ ሊያያት አይቀርብም። አላህም ለእርሱ ብርሃንን ያላደረገለት ሰው ለእርሱ ምንም ብርሃን የለውም።” (አል-ኑር 24፤ 40)

የዚያ ዘመን ስያሜ ጃሂልያ ነበር። የድንቁርና ዘመን ማለት ነው። ጃሂልያ እዚህ ላይ ጽንሰ ሐሳቡ የእውቀት ተቃራኒ መሐይምነት ሳይሆን የእምነት ተቃራኒ የሆነውን ክህደት አመላካች ነው። በእርግጥ የዚያን ጽልመታማ ዘመን አሰቃቂ ገጽታዎች እዚህ ላይ በአጭሩም እንኳ ቢሆን መጥቀስ አልፈልግም ነበር። ምክንያቱም ለቅጽበትም እንኳ ከፊታችሁ ላይ አስቀያሚ ምስል እንድታዩ አልፈልግምና። ሐሰትን ማሰላሰል አእምሮን ይበክላል። ይህ ለኔ ወንጀል ሆኖ ነው የሚታየኝ። ሆኖም ግን የዚያን ዘመን ሁኔታ በትክክል በመረዳት አላህ የአለማትን ፈርጥና እዝነት በመላክ የዋለልንን ውለታ ግዝፈት ማጤን እንችል ዘንድ አንዳንድ ባህሎቹን መጠቃቀስ ግድ ይሆንብኛል። የነቢዩ ሙሐመድ መምጣት በእርግጥም ለዓለማት ወደር የማይገኝለት በረከት፣ አቻ የለሽ ውለታ ነው። ቁርአን ይህን እውነታ እንዲህ ሲል ያመለክታል፡-

“አላህ በምእምናን ላይ ከጎሳቸው የኾነን፤ በእነርሱ ላይ አንቀጾቹን የሚያነብ፣ የሚጠራቸውም፣ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልእክተኛ በውስጣቸው በላከ ጊዜ፤ በእርግጥ ለገሰላቸው። እነርሱም ከዚያ በፊት በግልጽ ስህተት ውስጥ ነበሩ።” (አሊ-ዒምራን 3፤ 164)

የአላህ እዝነት ምን ያህል ሰፊና ጥልቅ እንደሆነ አስተውል። ለሰው ልጆች እንደነርሱው የሚያስብና ስሜታቸው የሚሰማው፣ ወደ አላህ የሚያደርሰውን ጎዳናም የሚያመላክታቸው ከራሳቸው የሆነ መልእክተኛ ላከላቸው። መሪ ሲፈልጉ ይህ መልእክተኛ መሪ ሆነላቸው። አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ ሲፈልጉ ሚንበር ላይ በመውጣት አፍ የሚያስከፍት ንግግር ያደርግለቸዋል። ንጉስ ሲፈልጉ ከንጉሳን ጋር መልእክት የሚጻጻፍ፣ ውሎችን የሚፈራረም ንጉስ ሆነላቸው። የጦር መሪ ሲሹ አንቱ የተሰኙ የጦር መሐንዲሶችን የሚያስከነዳ ክህሎት ያለው መሪ ሆነላቸው።

ክርስትያኖች አንድ የተሳሳተ እምነት አላቸው። ይህውም አላህ የሰው ልጆችን ከውርስ ሐጢአት ሊያጸዳ ዒሳን መስዋእት አደረገ ብለው ያምናሉ። ማለትም አላህ የሰውን ልጅ ሐጢአት ለመማር ሲል ልጁን እየሱስን እንዲሰቀል አደረገ- በዚህ የተሳሳተ እምነት መሠረት። እየሱስም በመስቀል ላይ ተሰቀለ። በአደም ተፈጽሞ ወደሌሎች ሰዎች በውርስ የተላለፈው ሐጢአትም በዚህ መልኩ ምህረት አገኘ። እያንዳንዱ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ ይህን ወንጀል ይሸከማል ይላሉ። በእርግጥ ይህ እምነት ስህተት ነው። አላህም እነርሱ ከሚሉት ሁሉ የጸዳ ነው። ይህ እምነት ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥመትም ጭምር ነው። ምክንያቱም በርካታ የተሳሳቱ መልእክቶችን በውስጡ ቋጥሯልና። ባይሆን አላህ የሰው ልጆችን ለማስተማር ሲል ነብያትን መላኩ፣ እነዚያም ነብያት ለስቃይ መዳረጋቸው፣ መስዋእትነትን መክፈላቸው እውነት ነው። ከነዚህ መሐል በላጩ ከርሱ ዘንድ ከሌሎች ነብያት ሁሉ በበለጠ ሁኔታ ተወዳጅ የሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ ይገኙበታል። ለከፍተኛ ስቃይና መከራ እንደሚዳረጉ እያወቀ ወደ ሰው ልጆች ላካቸው። ይህን ያደረገው የሰው ልጆችን ከጥምመት፣ መንገድ ከመሳት፣ ወሰን ከማለፍ ሊያጸዳቸው፣ በትክክለኛ ጎዳና እጦት ከመባከን ሊታደጋቸው፣ ብሎም ለምሉእ ሰብአዊ ፍጡር ተገቢ የሆነ ሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሊያስችላቸው በመሻት ነው። እውቁ ሱፊ ባለ ቅኔ ኢብራሂም ሐቂ እንደገለጸው፡- “አማኞች አምላካቸውን፣ በልቦናቸው ውስጥ እንደተቀመጠ ውድ ሐብት ሊያውቁት ይገባል።”

ቀልብ የነገሮች መቀመጫ ነው። ሰማያትና ምድር የማይችሉት አምላክ በዚህ ልቦና ውስጥ ይገለጻል። መጽሐፍትም፣ አእምሮም፣ ሐሳቦችም፣ ፍልስፍናዎችም፣ የቋንቋ ክህሎትም፣ የንግግር ምጥቀትም፣ ሰማያትና ምድርም ይህን አምላክ በተሟላ መልኩ መግለጽና መሸከም ሲሳናቸው ቀልብ ብቻ በመጠኑም ቢሆን ሊረዳው ችሏል። ሊገልጸው ሞክሯል። አዎ፣ ቀልብ አንደበት አለው። በዚህ አንደበቱ ጆሮዎች ሰምተውት የማያውቁትን እጅግ ድንቅና ውብ፣ እጅግ ማራኪ መልእክት ያስተላልፋል። ስለሆነም የሰው ልጅ በቀልቡ ውስጥ ብዙ ርቀት ተጉዞ መፈለግ የሚገባውን ነገር ማሰብ፣ ወደ አምላኩ መድረስ፣ በፍቅሩ መጠመቅ አለበት። አላህ ነቢዩ ሙሐመድን ወደኛ የላካቸው ለዚሁ ዓላማ ነው።

አዎ፣ ነቢዩ ወደ ሰው ልጆች የአምላክን ቃል ሊያነቡለት፣ ተአምራቱን ከፊት ለፊቱ ሊያቀርቡለት፣ እውነተኛ ማንነቱን ሊያብራሩለት ተላኩ። በርሳቸው ጥረትና በረከት የሰው ልጅ ከርክሰት መጽዳትና ንጽህናን መጎናጸፍ፣ ከዚህች ዓለም ዝቅተኛ የአካል ሕይወት ወደ ቀልብ ዓለም፣ ወደ መንፈስ ሕይወት ሊመጥቅ ቻለ። በእርግጥም ወደ ላይ ዘለቀ። ወደሰማዬ ሰማያት መጠቀ።

አዎ፣ ነቢዩ ለሰው ልጅ መጽሐፍትንና ጥበብን አስተምረዋል። በዚህ መጽሐፍና ጥበብ ብርሃን የሰው ልጅ ራሱን ያገኛል። ትኩረቱም ወደ መጭው ዓለም ይሳባል። ወደ ዘልዓለማዊው ሕይወት የሚያደርሰውን ጉዞ ይጀምራል። አዎ፣ በእርግጥም በዚህ ጎዳና መጓዝ ጀምሯል።

እኛ እጅግ የተባረኩ፣ የተላቁና እጅግ አስፈላጊ ቀናት አሳልፈናል። ከነዚህ ቀናት መካከል ከፊሎቹ ከአማኞች ዘንድ እንደ በዓል የሚቆጠሩ ናቸው። ዘወትር በየሳምንቱ አንድ ሙእሚን የጁሙዓን ቀን በደስታ ያሳልፋል። በዒደል አድሐ እና በኢደል ፊጥር ይህ ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል። በኢደል አድሐ ቀናት የነቢዩ ኢብራሂምን መስዋእትነት በጉጉት እናስታውሳለን። አላህንም ወንጀላችንን ይምር ዘንድ እንለምናለን። ከፊሎቻችን ወደ ካእባ በመጓዝ ከሐጅ በረከት እንቋደሳለን። ዓረፋ ላይ ቀልቦቻችን ወደ አላህ ይዞራሉ። ምህረቱን ለማግኘትም በሙሐመዳዊው ስልት ሲማጸኑት ይውላሉ።

ዒደል ፊጥርም በብዙ መልእክቶች የተሞላ ብሩክ የባእል ቀን ነው። ሙእሚን ከአንድ ወር የጾም ጊዜ በኋላ የአላህን ፍቅር በማግኘት ስሜት ልቦናው ደምቆ የሚያሳልፈው እለት ነውና። ግና ለሰው ልጆች ባጠቃላይ፣ ከዚያም አልፎ ለፍጡራን ሁሉ እጅግ አስደሳች የሆነ እለት አለ። እርሱም አላህ ይህችን ዓለም ነቢዩ ሙሐመድን ወደርሷ በመምጣት ያላቀበት እለት ነው። የዓለማት ፈርጥ የተወለዱበት ቀን። ይህ ቀን አላህ የሙሐመዳዊውን ብርሃን በሰው ልጅ አድማስ ላይ የፈነጠቀበት ቀን ነው። አዎ፣ በዚህ ብርሃን የመሐይምነት ጽልመት ተገፈፈ። ዓለም በደማቅ ብርሃን ተሞላች። አላህ ለሰው ልጆች እና ለአጋንንት ከዋላቸው ውለታዎች ሁሉ በላጩ ያለ ጥርጥር ይህ ነው።

________________

ምንጭ፡- ፈትሁላህ ጉለን- “ኑሩል ኻሊድ” /ዘልዓለማዊው ብርሃን/፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here