አንጸባራቂ ተምሳሌት

Prophet Muhammad, Best Example, Biography, Characteristics of Prophet Muhammad

0
6075
Prophet Muhammad

እያንዳንዷ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው በዝርዝር የተጻፈ ብቸኛው ስብእና ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ብቻ ናቸው። ሌሎች ነብያት በባህሪያቸው የሰውን ልጅ ወደ ሐቅ ጎዳና የሚመራ ተምሳሌታዊ ስብእና ይላበሳሉ። መልካም ድርጊታቸው እስካለንበት ዘመን ድረስ ከትውልድ ትውልድ በተወሰነ ደረጃ ሲሸጋገር ኖሯል። የመጨረሻው ዘመን ነብይ ግን የሕይወታቸውን እያንዳንዷን ቅጽበት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ እያንዳንዷን ንግግራቸውንና ተግባራቸውን ቁልጭ አድርጎ በሚያሳይ መልኩ ልቅም ተደርጎ ተመዝግቦ ለትውልድ ተላልፏል።

ሕይወታቸው ኢምንት ክፍሉ ሳይዘነጋ ተጽፏል። እርሳቸው ከኖሩበት ዘመን አንስቶ እስካለንበት ዘመን ድረስም ትውልዶች ተቀባብለውታል።፡ ቅብብሎሹ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሳይቋረጥ ይቀጥላል።

የሕይወትን ፈተናዎች ለመከላከልና ለመቋቋም የነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የ

ተላቁ ባህሪያት ልንላበስ ግድ ይላል። አመስጋኝነት (ሹክር)፣ በአላህ መመካት (ተወኩል)፣ የአላህን ውሳኔ በጸጋ መቀበል፣ መከራ ሲመጣ መታገስ፣ ቆራጥነት፣ ጀግንነት፣ መስዋእትነት፣ በእጅ ባለ ነገር መብቃቃት፣ የቀልብ ሐብታምነት፣ ለሌሎች ደህንነትና ደስታ መትጋት፣ ቸርነት፣ ተዋዱእ (መተናነስ)ና የመሳሰሉ ምጡቅ ስብዕናዎች በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙ ክስተቶችን በጽናት መዋጋትና መሰል ባህሪያትን መላበስ አስፈላጊ ነው።

በነዚህ ባህሪያት ሕያው ተምሳሌት እናገኝ ዘንድ አላህ ለሰው ልጆች አንድ ትልቅ ስጦታ አበርክቷል። አዋጅ፣ ይህ ስጦታ ድንቅና ንጹህ በሆነ ተምሳሌታዊ ሕይወታቸው ወደ ቅን ጎዳና የሚመሩት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ናቸው።

የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት ለመጭዎቹ ትውልዶች ሁሉ እስከ እለተ ቂያማ ድረስ ተምሳሌት ሆኖ ይቀጥላል። አላህ እንዲህ ብሏል፦

وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ

“አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።” (አል ቀለም፤ 4)

የመልእክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስብእናና የተባረከ መመሪያቸው ለሁሉም የሰው ልጅ ሕይወት መስኮች ተምሳሌት ነው። የሰው ልጅ ሊደርስባቸው የሚችሉ የስብእና የመጨረሻ ምጥቀቶችን ያመለክታሉ። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ራሳቸው ከሰዎች መሐል በሕይወት በመኖር በእያንዳንዱ የሕይወት ዘርፍ የመጠቀ ባህሪ ምሳሌ ሆነው አሳይተዋል።

አላህ የነቢዩን ስብእና -በቁርአን አገላለጽ- መልካም አርአያ (ቁድዋ ሐሰናህ) ይሆኑ ዘንድ አደራጅቶ ለሰው ልጆች አበርክቶታል። አላህ እንዲህ ብሏል፦

لَّقَدْ كَانَ لَكُمْ فِي رَسُولِ اللَّهِ أُسْوَةٌ حَسَنَةٌ لِّمَن كَانَ يَرْجُو اللَّهَ وَالْيَوْمَ الْآخِرَ وَذَكَرَ اللَّهَ كَثِيرًا

“ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ።” (አል አህዛብ፤ 21)

የነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እያንዳንዱ የሕይወት ገጽታ የምሉእነትን፣ የምጥቀትን እና የውበትን ዳርቻ የደረሰ ነው። ይህም በመሆኑ ሰዎች ከነቢዩ ሙሐመድ ሕይወት እንዲሁም ከአንጸባራቂ ሱናቸው የተሟላና ወደር የለሽ ትምህርት ያገኛሉ። ከስብእናቸው ገጽታዎች አንዱን በመምረጥ ለመከተል በጥቅል ወይም በዝርዝር ቀርቦላቸዋል።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሐይማኖት መሪነት አርአያ ናቸው። በርእሰ ብሔርነት አርአያ ናቸው። በመለኮታዊ ፍቅር አርአያ ናቸው። አንዳች ጸጋ ሲያገኙ አላህን በማመስገን እና በመተናነስ አርአያ ናቸው። በመከራ ጊዜና አጋጣሚዎች በመታገስ አርአያ ናቸው። በቸርነት እና ከአለማዊ ጸጋዎች በላይ በመሆን አርአያ ናቸው። ለቤተሰቦቻቸው፣ ለደካሞች፣ ለአገልጋዮችና ለሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች በማዘን አርአያ ናቸው። ጥፋተኞችን ይቅር በማለት አርአያ ናቸው።

ሐብታም ሰው ከሆንክ የርሳቸውን የትህትናና የቸርነት ባህሪ አስታውስ። መላ አረቢያን በፍቅር አስተሳስረዋል። ታላላቅ እና እውቅ ሰዎችን በፍቅር ወደርሳቸው መርተዋል።

የተራው የሕብረተሰብ ክፍል አባል ከሆንክም ከርሳቸው ሕይወት አርአያነትን ታገኛለህ። መካ ውስጥ በጣኦት አምላኪያን በግፍ የተሞላ አገዛዝ ስር ኖረዋል።

ድል አድራጊ የጦር መሪ ከሆንክም ጠላቶቻቸውን በጀግንነት ከተፋለሙትና በበድር፣ በሁነይንና በሌሎችም የጦር ግንባሮች አንጸባራቂ ድል ካስመዘገቡት ከነቢዩ ሙሐመድ  ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  ሕይወት አርአያነትን ታገኛለህ።

ሽንፈት ከገጠመህም በኡሁድ ዘመቻ የሞቱና የቆሰሉ ባልደረቦቻቸውን እየተዘዋወሩ ካጽናኑት፣ በፍጹም ጀግንነትም የጦርነቱን ሚዛን ከለወጡት ከነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት ውስጥ የትእግስትና የጀግንነት አርአያነትን ታገኛለህ።

መምህር ከሆንክም መለኮታዊ ትእዛዛትን ስላስተማሩት፣ በመስጊዳቸው ውስጥ የነበሩ “የአህሉ ሰፋ” ድሆችን በበረከት ስለሞላው ስስ ስሜትና አዛኝ ቀልባቸው አስብ።

ተማሪ ከሆንክም ወህይ ይዞላቸው ከሚመጣው ከጅብሪል ፊት በአደብና በጥንቃቄ ተቀምጠው ይማሩ የነበሩትን ነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አስብ።

ሰዎችን የሚመክርና የሚገስጥ ባለራእይ ከሆንክም በነቢያዊው መስጊድ ውስጥ ንግግሮችን ያደርጉ የነበሩትን ነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በእዝነ ሕሊናህ አድምጥ።

ሐቅን የያዝክና ለርሱ ተሟጋች ሆነህ ረዳት ካላገኘህም መካ ውስጥ ከግፈኞች ፊት ቆመው ወደ ሐቅ የጠሯቸውን እና ያለ አንዳች ረዳት ይህን ያደረጉትን የነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት አስብ።

ጠላትን ማሸነፍና ሐይሉን ማንኮታኮት፣ ሐሰትን መጣልና ሐቅን ማንገስ ከከጀልክም የነቢዩን ተምሳሌትነት አስተውል። መካን በድል በከፈቱ ጊዜ ድል አድራጊ መሪ ነበሩ። ይህም ሆኖ ግን በዚህ ቅጽበት አምላካቸውን አልረሱም። አመስጋኝ ባሪያው ነበሩ። እናም ከግመላቸው ጀርባ ላይ በትህትና ተቀምጠው፣ አንገታቸውን ደፍተው ወደ ተቀደሰው የሐረም መስጊድ ገቡ።

ገበሬ ከሆንክና ስራህን በአግባቡ ለማከናወን ከከጀልክ የነቢዩን የግብርና ሕይወት ገጽታ አስተውል። በኒ ነድር፣ ፈድክና ኸይበር በተሰኙ ቦታዎች መሬት ነበራቸው። ለቦታው ብቁ የሆኑ ሰዎችን በመቅጠር መሬታቸውን በወጉ አልምተዋል።

ረዳት አልባ ብቸኛና ባይተዋር ከሆንክም የአሚናና የአብደላህ የዓይን ማሪፊያ የነበረውን የቲም ሕጻን (ሙሐመድን) አስብ።

ወጣት ከሆንክም ለአጎታቸው አቡ ጧሊብ በመካ ፍየል ይጠብቁ የነበሩትን ንጹህና መልካም ወጣት ሙሐመድን አስተውል። ነጋዴም ከሆንክ ወደ ሻምና ወደ የመን ከሚያቀኑ ቅፍለቶች ጋር ለንግድ የወጣውን የብርቅዬ ስብእና ባለቤት በልቦናህ አስብ።

ዳኛም ከሆንክ የነቢዩን ፍትሃዊና ብልህ ስብእና አስብ። በተለይም የመካ መሪዎች ሐጀረል አስወድን ከካእባ ላይ ማን ነው የሚያስቀምጠው በሚለው ሐሳብ ዙሪያ በተወዛገቡ ጊዜ የሰጡትን፣ ታላቅነታቸውንና በጥበብ የከበረ ስብእናቸውን የሚያጎላውን ፍርድ አስብ። ከነቢያዊው መስጊድ ውስጥ ተቀምጠው ሃብታም ከድሃ ሳያበላልጡ ይሰጧቸው የነበሩ ፍትሃዊ ብይኖችን አስታውስ።

ባልም ከሆንክ በዚህ ረገድ ያስተላለፏቸውን የተባረኩ መመሪያዎች አጢን። ለባለቤቶቻቸው የነበራቸውን የጥንቃቄ ስሜትና እዝነት መርምር።

አባት ከሆንክም የፋጡማ አባት፣ የሐሰንና የሑሰይን አያት እንደመሆናቸው በዚህ መስክ ከነበራቸው ድንቅ የአባትነት ስብእና ትምህርት ቅሰም።

ምንም ሁን ምን ከነቢዩ ስብእና መልካም አርአያነትን፣ የተሟላ መመሪያን፣ አንጸባራቂ ተምሳሌትነትን ለራስህ ታገኛለህ።

እርሳቸው መሪህ ስለሆኑ ድርጊትህን በድርጊታቸው መዝንና ስህተትህን አርም። ሱንናቸውን በመከተል ተግባሮችህን ሁሉ አስተካክል። በርሳቸው ብርሃንና አመራር ጥላ ስር የሕይወትን እንቅፋቶች ሁሉ ታልፋለህ። እውነተኛ ደስታም ታገኛለህ።

የሕሊናና የቀልብ አጸዳቸው የተለያዩ ቀለማት ባላቸውና ሽታቸው በሚያውዱ ልዩ ልዩ አበቦች እንደተሞላ አጸድ ማለት ነው። የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት በተለያየ የማሕበረሰብ እርከን ላይ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ተምሳሌት እንደሆነ አይተናል። በአንጻሩ በሌሎች ሰዎች ስብእና ውስጥ ይህ አይስተዋልም። ለምሳሌ የገዥዎች ሕይወት ለተገዥዎች፣ በድሎት የተከበበ ሐብታም ሕይወት በድህነት ለሚሰቃይ እና የእለተ ጉርስ ለማግኘት አሳሩን ለሚያይ ባተሌ አርአያ ሊሆን አይችልም።

የነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት ግን ከተቃራኒ ጫፍ ላሉ ወገኖች ሁሉ አርአያ ይሆናል። ምክንያቱም አላህ ሕይወታቸውን በየቲምነት አስጀምሮታል። የቲምነት በሰው ልጅ ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ የደካማነት ጥግ ነው። በመቀጠልም የሕይወትን የተለያዩ እርከኖች ደረጃ በደረጃ እየረገጡ ከላይኛው ጫፍ ላይ እንዲደርሱ አደረጋቸው። እርሱም የመንግስት ርእሰ ብሄርነት እና ነብይነት ነው። ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ያሳለፏቸው የሕይወት እርከኖች ለእያንዳንዱ የሕይወት ውጣ ውረድ አርአያ በሚሆኑ ተምሳሌታዊ የባህሪያት የከበሩ ናቸው። ስለዚህም አንድ ግለሰብ ማሕበራዊ ደረጃውና ቦታው ምንም ይሁን ምን ከነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት ይማራል። ሰዎች እንደየ አቅማቸው ሊከተሉት እና ሊተገብሩት የሚችሉት የተሟላ መልካም አርአያ በነቢዩ ሕይወት ውስጥ ያገኛል።

ነቢዩ አላህ ለሰው ልጆች ያበረከታቸው ታላቅ ጸጋ፣ ወደር የለሽ ስጦታ፣ አስደናቂ ተአምር ናቸው። ከዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ድረስ ለእያንዳንዱ የሕይወት እርከንና ዘመን ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ አንጸባራቂ ስብእና ናቸው። ልዩ የሆነ ስብእናቸውን በአርአያነት ለሚከተሉ ሙእሚኖችም የስራዎቻቸው መለኪያ ሚዛን ናቸው።

ለሰው ልጅ የሐሴትን አቅጣጫ እናመለክታለን የሚሉ፣ ራሳቸውንም ለሰው ልጅ በተምሳሌትነት ያቀረቡ ወገኖች ሁሉ፣ በተለይም ሁሉንም ነገር በደካማ አእምሯቸው ለማብራራት የሞከሩ ፈላስፎች በዚህ ረገድ በጣም ደካማ ናቸው። ነብያትና የነርሱን ፈለግ የተከተሉ ደጋግ ሰዎች ሲቀሩ። ምክንያቱም ነብያት መነሻቸው መለኮታዊ መልእክት ነውና። አምላካዊ መመሪያ ይዘው መጥተዋል። ይህም መመሪያ እውነተኝነታቸውን ያረጋግጣል። አምላካዊውን ትእዛዝና ድንጋጌ አድርሰዋል። ሁሌም የሚሉት፦ “አምላክ ይህን አዟል” ነው። በአንጻሩ ፈላስፎች ዓላማቸው የሰውን ልጅ ወደተሻለ አቅጣጫ መምራት ቢሆንም አምላካዊ እገዛ በሚጎድለውና የስሜታቸው ተከታይ በሆነ ደካማ አእምሯቸው ብቻ ስለሚወሰኑ እይታቸው የግለሰብ አስተያየት ከመሆን አያልፍም። “እኔ እንዲህ አስባለሁ፣ ለኔ እንዲህ ይታየኛል።” ከማለት ሌላ አማራጭ የላቸውም። ከዚህም የተነሳ በመካከላቸው እጅግ የተራራቀ የሐሳብ ልዩነት ይስተዋላል። አንዱ የገነባውን እሳቤና ምልከታ ሌላው ሲያፈርሰው፣ አንዱ ያጸደቀውን ሌላው ሲያስተባብለው ማየት የተለመደ ነው። ከዚህ የተነሳ ራሳቸውንም ሆነ ሕብረተሰቡን ወደ ቅን ጎዳና መምራት አልቻሉም።

ለምሳሌ አርስቶትል በሞራልና በሌሎች መስኮች በርካታ የፍልስፍና መሠረቶችን የጣለ ቢሆንም አምላካዊ መገለጥን የተነፈገ በመሆኑ በፍልስፍናው የሚያምንለት፣ ፍልስፍናውን ወደ ተግባር ለውጦ ደስታን የተጎናጸፈ አንድም ግለሰብ አላገኘም። የዚህ ምክንያት ፈላስፎች ቀልባቸውን አላጸዱም። ነፍሳቸውን አልገሩም። አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው በወህይ እገዛ ሊበስልና ሊጎለብት አልቻለም።

ስለዚህም የሰው ልጅ በወህይ ያልተገሩ አእምሮዎችና ልቦናዎች ከሚያመጧቸው ሙከራዎች ሊወጣ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ የተከበረው ቁርአን ነው። ቁርአን አላህ ለሰው ልጆች ከመጨረሻው ነብይ ጋር የሰጠው እማይበጠስ ፍጹም ጠንካራ ገመድ ነው።፡

በቁርአን ውስጥ የተካተቱ የእውቀትና የተግባር እውነታዎች በነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት ውስጥ በጉልህ ሰፍረዋል። እናም የሰው ልጅ የተፈጠረለትን ዓላማ ለማሳካት የሚያስፈልገው ቁርአንንና ሱንናን ተከትሎ መንቀሳቀስ ብቻ ነው። የአላህ መልእክተኛ ሁለት መመሪያዎችንና ምንጮችን ትተውልናል። ቁርአንና ሱንናን። እነዚህ ሁለት ምንጮች ለሁለቱም ዓለማት ስኬት ቁልፎች ናቸው።

ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መልእክት ከሰማይ ሳይወርድላቸው በፊት እንኳ ከወገኖቻቸው ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ። ሰዎች አልሲዲቅ (እውነተኛ)፣ አልአሚን (ታማኝ) በማለት እንዲጠሯቸው ማድረግ የጀመሩት የፍጹም እውነተኛነት እና ታማኝነት ባህሪ በስብእናቸው ውስጥ ከነገሰ በኋላ ነው።

ሰዎች መልካም ባህሪያቸውን፣ ጥሩ ስነ ምግባራቸውን፣ ቀጥተኛነታቸውንና ታማኝነታቸውን ከነብይነታቸው በፊት አውቀው ወደዋቸዋል። “አል አሚን” የሚል ማእረግም ሰጥተዋቸዋል። በካእባ ግንባታ ወቅት ለተከሰተው ውዝግብ ፍርዳቸውን ያለተቃውሞ ተቀብለዋል።

የነቢዩን እውነተኛነት ከሚያረጋግጡ ምስክሮች መሐል የሮማው ንጉስ ሂረቅል የነቢዩ ዋነኛ ጠላት የነበረውን አቡ ሱፍያንን ከመስለሙ በፊት እንዲህ በማለት ጠየቀው፦ “ነብይ ነኝ ከማለቱ በፊት ዋሽቶ ያውቃልን?” አቡ ሱፍያን፦ “በፍጹም” ከማለት ውጭ መልስ አልነበረውም። “ሸፍጥ ፈጽሞ ያውቃልን?” ሲልም ጠየቀው። “አያውቅም። በእርግጥ ከኛ ለተወሰነ ጊዜ ርቋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የፈጸመው ነገር መኖሩን አላውቅም።” አለ። “ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር ለመጨመር አልተቻለኝም።” ሲል አቡ ሱፍያን አስተያየቱን አክሏል።

የመካ ሰዎች የነቢዩን ቃል ሙሉ በሙሉ ያምኑ ነበር። ምክንያቱም ከርሳቸው ታማኝነትን እንጅ ሌላን አያውቁምና። አንድ ቀን አቡ ጀህልና ባልንጀሮቹ የነቢዩ ቀንደኛ ጠላቶች ቢሆኑም እንዲህ ብለዋቸዋል። “ሙሐመድ ሆይ፣ እኛ ሐሰተኛ ነህ አንልም። ከኛ ዘንደ አንተ እውነተኛ ነህ። ግና ያመጣህውን መልእክት እናስተባብላለን።” ይህን ክስተት አስመልክቶ ተከታዩ የቁርአን አንቀጽ ወረደ፦

قَدْ نَعْلَمُ إِنَّهُ لَيَحْزُنُكَ الَّذِي يَقُولُونَ ۖ فَإِنَّهُمْ لَا يُكَذِّبُونَكَ وَلَٰكِنَّ الظَّالِمِينَ بِآيَاتِ اللَّهِ يَجْحَدُونَ

“እነሆ ያ የሚሉህ ነገር እንደሚያሳዝንህ በእርግጥ እናውቃለን። እነርሱም (በልቦቻቸው) አያስተባብሉህም። ግን በዳዮቹ በአላህ አንቀጾች ይክዳሉ።” (አል አንዓም፤ 33)

ነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰዎች -ጣኦታውያንን ሳይቀሩ- “ታማኙ ሙሐመድ” በሚል ቅጽል እንዲጠሯቸው ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ከታሪክ መጽሐፍት እንዲህ ተጠቅሷል፦

በኸይበር ዘመቻ ጊዜ አንድ የአይሁድ እረኛ ወደ አላህ መልእክተኛ መጣ። ከርሳቸው ጋር ተነጋገረ። መስለምና ከሙስሊሞች ጋር መቀላቀል እንደሚፈልግም ነገራቸው። የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይጠብቃቸው የነበሩ የፍየል መንጋዎችን ለባለቤቶቻቸው እንደዲመልስና ከዚያ በኋላ መጥቶ ከሙስሊሞች ጋር መቀላቀል እንደሚችል ነገሩት። ይህ የሆነው ከአይሁድ ጠላቶቻቸው ጋር እየተፋለሙ ባሉበት ጊዜ ነው። የፍየል መንጋው የጠላቶቻቸው ሐብት ነው።  በዚያ ላይ ሙስሊሞች አስከፊ የስንቅ እጥረት ነበረባቸው። ይህ የነቢዩ ድርጊት እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይሰማቸው የነበረውን የሐላፊነትና የአደራ ጠባቂነት ስሜት ያጎላል።

ባልንጀራቸው አቡበክር በዚህ የነቢዩ ባህሪ ተመስጠዋል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ታማኝ እንደሆኑ ከልብ አምነዋል። ከዚህም የተነሳ የሚእራጅ እለት ዝንተ ዓለም ሲዘከር የሚኖር ምስክርነታቸውን ሰጡ። ይህውም ነቢዩ ከሰማይ ደርሰው እንደተመለሱ መናገራቸው ሲወሳላቸው እንዲህ አሉ፦

“በእርግጥ ይህን ተናግሮ ከሆነ እውነቱን ነው።”

“ቃሉ ከነቢዩ አንደበት መውጣቱን አረጋግጡልኝ” ነው ነገሩ። “እርሱን ካረጋገጣችሁልኝ እኔ ደግሞ እውነት መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ።”

በነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሕይወት ውስጥ የተስተዋሉ ለቁጥር የሚታክቱ የፍትህና የእዝነት ክስተቶች ለዚህች ዓለም እስከ እለተ ቂያማ ድረስ አንጸባራቂ ምሳሌ ሆነው ይቀጥላሉ።

ቅን ሕሊና ያለው ሰው ከብቸኛው ምንጭ ፈንጥቆ ዓለምን ያበራውን አንጸባራቂ ብርሃን ቢያንስ በውስጡ ሊያስተባብል አይችልም። ሙስሊም ያልሆኑ ባለ ቅን ልቦና ምሁራን የነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ታላቅነት እና ስኬት መስክረዋል። ቶማስ ካርላይል ስለርሳቸው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦

“የርሳቸው አነሳስ ከጽልመት ተፈልቅቆ የወጣ ብርሃን ዓይነት ነበር።”

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ላይ ስለነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ የሚል ተጽፏል፦

“ነቢዩ ሙሐመድ ያስመዘገበውን ዓይነት ስኬት ያስመዘገበ የተሐድሶ አራማጅ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አይገኝም።”

ስሚዝ እንዲህ ብሏል፦

“ሙሐመድ የተሐድሶ አራማጆች ሁሉ አውራ መሆኑን የሚጠራጠር ማንም የለም፡”

እውቁ ጸሐፊ ስታንሊ ሊበል እንዲህ ሲል ጽፏል፦

“ሙሐመድ በጠላቶቹ ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ባስመዘገበበት በዚያው ቅጽበት እጅግ አንጸባራቂ የሞራል ድል ተቀዳጅቷል። ይህውም ለዘመናት ያሰቃዩትን ቁረይሾች ማለትም የዚያን ዘመን የመካ ነዋሪዎች ሁሉ ይቅር ብሏል።”

አርሰር ጀልማን እንዲህ ብሏል፦

“የሙሐመድን ታላቅነት መካን በድል በከፈተ ጊዜ ተመልክተናል። ጠላቶቹ ባለፉት ዘመናት የፈጸሙትን ግፍ ሁሉ ይቅር አለ። ድርጊታቸው እነርሱን በሚገባ ለመበቀል በቂ ምክንያት ነበር። ግና ሙሐመድ ለሰራዊቱ አንዲት ጠብታ ደም እንዳያፈሱ ጥብቅ ትእዛዝ አስተላለፈ። እጅግ የላቀ እዝነትም አሳየ። ለዚህ ድርጊቱም አላህን አመሰገነ።”

ለ1789 የፈረንሳዮች አብዮት፣ የአስተሳሰብ መሠረት ከጣሉ ፈላስፎች መካከል አንዱ የሆነው ላውፊት የተሰኘ ፈላስፋም፣ ሰብአዊ መብቶች ከመደንገጋቸው በፊት የዓለምን የህግ ስርዓቶች ከመረመረ በኋላ የእስልምና ሕግ ከሁሉም የላቀ መሆኑን በተረዳ ጊዜ እንዲህ ሲል ተናዟል፦

“ሙሐመድ ሆይ፣ ታላቅ ሰው ነበርክ። እስከ ዛሬ ድረስ ማንም ያልደረሰበትንና ወደፊትም ማንም ሊደርስበት የማይችልን የፍትህ የመጨረሻ ጫፍ አንተ ደርሰህበታል።”

ጠላት እንኳ ሊያስተባብለው ያልቻለና የመሰከረለት የነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ታላቅነት ይህ ነው። በነቢዩ የሚያምኑ ሁሉ ታላቅነታቸውን አምነዋል። ብልህነታቸውን መስክረዋል። የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ልዩ የሕይወት ታሪክ በውስጡ ያካተተው የተሟላ ሞራላዊ ሕይወት፣ ብርሃን ለሚሹ አጥኝዎች ሁሉ ብርሃን የለገሰ ነው። በምድር ላይ የሚገኙ የሰው ልጆችን ሁሉ ለማስተማርም መሠረት ሆኗል።

የነቢዩ ትግል ከማንም የተሰወረ አይደለም። ለአጥኝዎች ትክክለኛውን መንገድ አመላክቷል። በእርግጥ አቻ የማይገኝላቸው የሰው ልጅ መምህር ናቸው።

የአላህ መልእክተኛ  ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ትምህርት ከሚሰጡባቸው ቦታዎች ላይ የተለያየ ቋንቋ፣ ዘርና ማሕበራዊ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ይገኙ ነበር። የነቢዩ ትምህርቶች እነዚህን ሁሉ በአንድ አስተናግደዋል።፡ ከርሳቸው የትምህርት ማእድ ለመቋደስ ምንም ዓይነት የተለየ መስፈርት አልነበረም። ሁሉም የሰው ዓይነት መሳተፍ ይችላል። በሰው ልጅ ላይ የሚያተኩሩ የትምህርት ማእከላት ነበሩ። እናም ደካማው ከጠንካራው ሳይነጠል ሁሉም ከበረከታቸው ይቋደሱ ነበር።

የነቢዩን ሶሐቦች ስናጠና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ግለሰቦችን እናገኛለን። ለምሳሌ የሐበሻው ንጉስ ነጃሺ፣ የዑመይር ጎሳ አለቃ ዙል ኩልየህ፣ ፌሩዝ ደይለሚ፣ ፋርወት አዚም መዑን፣ የአማን ገዥ አቢድ ቢን ጃእፈር፣ የየመን ገዥ መርከቡድ ይገኙባቸዋል። ከነዚህ የሕዝቦች መሪዎች በተጓዳኝ ደግሞ ቢላል፣ ያሲር፣ ሱሐይብ፣ ኸባብ፣ አማርና ሌሎችም የዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል አባላት፣ እንዲሁም እንደ ሱመያህ፣ ለቢነህ፣ ዘኒረህ፣ ነህድያህና ኡም ኡበይስ ያሉ ባሮችን እና ባል አልባ እንስቶችን እናገኛለን።

ከነቢዩ የእውቀት ማእድ ላይ ባለሰፊ እውቀተ እና ጥበበኛ ሰዎች፣ ሃገር ለማስተዳደር የሚበቁ ታላላቅ ስብእናዎች ይገኙ ነበር።

ከነቢዩ ተከታዮች መካከል ሃገር የሚያስተዳደሩ መሪዎች ፈልቀዋል። እነዚህ ሰዎች በሕዝቡ መሐል ሰላምን አስፍነዋል። መረጋጋትን አንግሰዋል። ከሚገዙት ሕዝብ ጋር ልክ እንደ ወንድማማች ተጣጥመው ኖረዋል። በነርሱ ጥላ ስር የሰው ልጅ ደስታን አግኝቷል። በአስተዳደራቸው የፍትህን ለዛ አጣጥሟል።

የአላህ መልእክተኛ አቻ የለሽ ተምሳሌት የአላህ ሰላም እና እዝነት በርሳቸው ላይ ይሁን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here