ከሰባቱ ባህሪያት የትኛውን ተላብሰናል?

2
11025

ነዚህ ሰባት ድንቅ ባህሪያት ቀጥለን ከምናየው የአቡ ሁረይራ ሀዲስ ውስጥ ይገኛሉ። አቡ ሁረይራ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ ይለናል፡-

سبعة يظلهم الله في ظله يوم لا ظل إلا ظله: إمام عادل، وشاب نشأ في عبادة الله، ورجل قلبه معلق بالمساجد، ورجلان تحابا في الله اجتمعا عليه وتفرقا عليه، ورجل دعته امرأة ذات منصب وجمال فقال إني أخاف الله، ورجل تصدق بصدقة فأخفاها حتى لا تعلم شماله ما تنفق يمينه، ورجل ذكر الله خاليًا ففاضت عيناه

“በዚያ ከአርሹ ጥላ በስተቀር ምንም ጥላ በሌለበት ቀን (የፍርዱ ቀን)፤ አላህ ሰባት ሰዎችን በአርሽ ጥላ ስር ያኖራቸዋል። እነሱም፡- ፍትሃዊ መሪን፣ አላህን በመገዛት ወጣትነቱን ያሳለፈ፣ ልቡ ከመስጅድ ጋር የተቆራኘን ሰው፣ ለአላህ ብቻ ብለው በአላህ መንገድ ላይ የተዋደዱንና በርሱም መንገድ ላይ የተለያዩ (ሲለያይም ለአላህ ብለው)፣ አንዲት ቆንጆ ሴት ራሷን ለዝሙት አዘጋጅታለት ‘አላህን እፈራለሁ’ በማለት እምቢ ያለ፣ በድብቅ ምጽዋት የሚሠጥ ሰው፣ ብቻውን ሆኖ አላህን ሲያስታውስ አላህን ፈርቶ አይኖቹ በእንባ የሚሞላና ጉንጮቹ የሚርሱ ሰው” (አል-ቡኻሪ 620)

በእርግጥ በዚያ ቀን ጥላ ያሻናል። የማንም ሳይሆን የአላህ ጥበቃ ያስፈልገናል፤ ከዚያን ያህል ርቀት በቃጠሎዋ የምናውቃት ፀሐይ በአንድ ስንዝር ልዩነት ስትቀርበን ሁላችን በላባችን ስንጠመቅ ሞልቶም እስከ አንገታችን ሲደርስ ያኔ በእርግጥ ጥላ ያስፈልገናል። ምንስ ጥላ ይኖራል ከአላህ ሁሉን ከሚችለው ጌታ ጥላ በስተቀር። በዚያን ወቅት ከነዚህ ሰባት ሰዎች መካከል ከሆንን የአላህን ጥበቃና ጥላ እናገኛለን። ኢንሻአላህ! እስቲ ስለ ሰባቱ ሰዎች ባህሪ ጥቂት እንበል።

  1. ፍትሃዊ መሪ፡- ይህ የትልቅ ስልጣን ባለቤትን ብቻ አይመለከትም። ማንኛውም የትንሽም ሆነ ትልቅ ስልጣን ባለቤት ኃላፊነት የሚሰማው መሪ መሆን አለበት። አላህ ሁሉንም የሰው ልጅ ፍትሃዊ ይሆኑ ዘንድ ያዛል። ፍትሃዊነት የስልጣን ባለቤትነት ሲረጋገጥ ከባድ ይሆናል። ይሄኔ ነው የፍትሃዊነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው። በጣም ከባዱ ደግሞ ከሚጠሉህ ሰዎች ጋር የአንተን መውደቅ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር በፍትሃዊነት መኖር ነው። ምንም እንኳ ስልጣንና ኃይል በእጅህ ቢሆን እንኳን! ይህ በእርግጥ ታላቅ ትዕግስተኝነትንና ታማኝነትን ይሻል። ጉዳዩ ግለሰባዊ ሳይሆን ማህበረሰባዊ ነው። ለዚህም ይመስላል ከሰባቱ ሰዎች የመጀመሪያ በመሆን የተጠቀሰው።
  2. አላህን በማምለክ ላይ ወጣትነቱን ያሳለፈ፡- አላህን መገዛት በሁሉም ሰብዐዊ ፍጡር ላይ ግዴታ ነው። ጉዳዩ ግን ወጣትነት ስሜታዊነት የሚንፀባረቅበት እድሜ በመሆኑ ነው። ዓለም ያረገዘችውን ሁሉ የምትወልድበት ወቅት በወጣትነት አይን የተመለከትናት ወቅት ነው። ተቃራኒ ፆታ፣ ገንዘብና ስሜት በወጣት ላይ ያበረታሉ። እነዚህን መጋፈጥ ደግሞ በእርግጥ ትልቅ ችሎታን፣ ትዕግስተኝነትንና ቆራጥነትን ይጠይቃል። ለእነዚህ ሁሉ ስሜቶች ከተሸነፉ በኋላ በእርጅና ወቅት ለኢስላማዊው መንፈስ ራስን መስጠት የሚገርም አይሆንም። የሚገርመው የሚደንቀውም በፍርዱ ቀን የአላህን ጥላ የሚያጋነውም እነዚህን ፈተናዎች በሚገባ ተቋቁሞ አላህ በመገዛት ያሳለፈ ወጣት ነው።
  3. ልቡ ከመስጅድ የተቆራኘ ሰው፡- በዚህ ገለፃ ወቅት ነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ የተጠቀሙት የአረብኛ ቃል (ሙአለቅ) የሚለውን ነው። በቀጥታ ሲተረጎምም የተንጠለጠለ ማለት ነው። ይህን ኢማም ማሊክ የተባሉ የኢስላም አዋቂ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ:- “ይህ ሰው ወደ መስጅድ ይመጣል፤ ከመስጅድ ሲወጣ ግን በፍጥነት የሚመለስበትን ጊዜ እየናፈቀ ነው።” በእርግጥ የሰዎች ልብ ከስራቸው፤ ከቤተሰቦቻቸውና ከንግዳቸው ላይ የተንጠለጠለ ነው። መስጅድ የቅድሚያ ፍላጎታቸው አይደለም። ነገር ግን አላህን በእውነት ለሚወዱ ሰዎች በምድር ካለ ቦታ ሁሉ መስጅድ ለነርሱ ተወዳጅ ስፍራ ነው። የቅድሚያ ፍላጎታቸውም የአላህን ቤት መጠበቅና በውስጡም ዘውታሪ መሆን ነው። ታዲያ ለነዚህስ የአላህን ጥላ አይገባቸውምን? አላህም በእርግጥ በነገሮች ሁሉ ውስጥ አዋቂ ነው።
  4. ለአላህ ብለው የተዋደዱ ሁለት ሰዎች፡- ፍቅር የማህበረሰባችን ቋሚ ነው። ያለውዴታ የተሟላ ማህበረሰብን መገንባት የማይታሰብ ነው። ኢስላም ከሁሉም ሰዎች ጋር በፍቅርና በርህራሄ እንድንኗኗር ያዛል። ነገር ግን ውዴታው የአላህን ውዴታ በመሻት ለአላህ ብቻ ተብሎ ሲሆን ደግሞ የልቅናን ማማ ይቆናጠጣል። ውዴታውም የተባረከ ይሆናል። ጉዳያቸው ሁሉ አላህን በማስደሰት ላይ ስለሚገነባም ለራሳቸውም ሆነ በዙሪያቸው ላሉት ሁሉ መልካምን ይለግሳል። ይህን አይነቱ ውዴታ እውነትን፣ ታማኝነትን፣ የተላበሰ ውዴታም በመሆኑ የአላህን በረከት ይቸራል፣ ዘለዓለምም የእዝነት መሠረት ይሆናል። እነኚህስ አይገቡምን? የአላህ ጥበብ በእርግጥ ሰፊ ናት!!
  5. ቁርጠኝነት የተላበሰ የመልካም ባህሪ ባለቤት፡- ነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ስለዚህ ሰው ድንቅ ባህሪ ሲያወሱ የተጠቀሙት የአረብኛ ቃል “መንሰብ” የሚለውን ሲሆን ይህ ማለት ሁሉንም ያሟላች ሴት (ቁንጅና፣ ሀብት፣ ጥሩ ዘርና የተከበረ ቤተሰብ) ማለት ነው። ይህን ሁሉ ያላት ሴት ማንም ሰው በሌለበት ይህንን ከባድ የስሜት ጥያቄ ስታቀርብ እምቢ፣ አሻፈረኝ ማለት ድንቅ የአላህን ፍራቻ ያመላክታል። ታላቁ የኢስላም አዋቂ ኢብን ሀጀር አል አስቀላኒ ሐዲሱ በተከበረ፣ መልከ መልካምና ሀብታም ወንድ ጥያቄ ያልተሸነፈችን ሴትንም ያመላክታል ይላሉ። በእርግጥም ይህንን ጥያቄ አሻፈረኝ ማለት ጠንካራ ስብዕናን ይሻል። በአላህ ፍራቻ ልባቸው የተሞላ ግን ይህን አማላይ ጥያቄ አሻፈረኝ ለማለት አያንገራግሩም። ታዲያ የአላህ ጥላ አይገባቸውምን? የአላህ ራህመት ምንኛ ሰፋች!
  6. ለዝና ብሎ የማይለግስ ቸር፡- የዚህ ሰው ባለቤት የራሱ ግራ እጅ በማይመለከትበት ሁኔታ ቀኝ እጁ ይሰጣል ማለት ለመስጠቱ ምላሽን ከሰዎችም ሆነ ከራሱ አይሻም። ይልቁንም የሥራውን ምስጋና ከአላህ ብቻ ይጠብቃል። የሰዎች ምስጋና ፍላጎት ፈፅሞ አይቀይረውም። ፍላጎቱ አላህን ማስደሰት ብቻ ነው። ይህ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀው አሰጣጥ ነው ሽልማቱም አርሽ ጥላ ስር መቀመጥ ነው።
  7. አላህን ብቻውን ባስታወሰው ጊዜ ጉንጮቹ በእንባ የሚርሱ ሰው፡- አላህን ብቻ በማሰብ፣ ድንቅ ባህሪያትን እና ስሞቹን በማስታወስ፣ እርሱንም በማመስገንና በማወደስ የምታልፍ ሰዓት ከሰዓቶች ሁሉ እጅግ የተዋበችዋ ሰዓት ነች። አላህን ማስታወስ በማንኛውም ወቅት የሚተገበር የአምልኮ አይነት ሲሆን ስሙም “ዚክር” ይባላል። ማንም በማይመለከትህ ሰዓት፣ ልብህ ከአላህ ጋር ሲገናኝ፣ ውለታዎች ስታስታውስና አይኖችህ በእንባ ጎርፍ ሲሞሉ ጉንጮችህ በዚህ የተቅዋ (አላህን ፍራቻና ጠንቃቃነት) ዶፍ ሲናጡ በእርግጥም ለአላህ ያለህን ውዴታና ተቅዋ ያመላክታል። የአላህን ፊት መሻትህን ያስገነዝባል። አላህን በእውነት የወደዱ ደግሞ በእርግጥ ስኬትን ይጎናፀፋሉ። በዚያች የጭንቅ ቀንም የአርሽ ጥላ ስር ይጠለላሉ።

እነዚህ ሰባት ድንቅ ባህሪያት እውነተኛ እምነትን፣ ቁርጠኛ አቋምን መለኪያ ሚዛን ናቸው። ስሜት፣ መንፈስን፣ አስተሳሰብንና ተግባርን ባማከለ ሁኔታ ለአላህ ያለንን ውዴታ ያሳያሉ። እነዚህ የምርጥ አማኞች ባህሪያት ናቸው። አላህ እነዚህን ባህሪያት በእውነት ከሚጎናፀፉት ሰዎች ያድርገን። ሁላችንንም በጭንቁ ቀን በእርሱ አርሽ ጥላ ስር ያኑረን።    አሚን!!!

2 COMMENTS

  1. አሰላሙአለይኩም። ወራህመቱላህ። ወረካቱሁ። የአላህ። ጥበቃ። አይለያችሁ። እዚህ ደረገፅ። የገባ ሰው። ምንም። ለመዉጣት። አያስፈልግም። አላህ እዉቀቱን። እጥፍ። ድርብ። ያድርግላችሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here