አል-ኢስራዕ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከመካ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረጉትን የሌሊት ጉዞ ተከትላ የወረደች የቁርአን ምዕራፍ ናት። በዚህች ምዕራፍ ውስጥ አላህ (ሱ.ወ) መሰረታዊ ግዴታዎች በጥልቀት እንዲዳሰሱ አድርጓል። እነዚህ ግዴታዎች አንድ ህዝብ ከሚያልመው የስኬት ጣራ ላይ የሚያቆናጥጡ ድንቅ መርሆዎች ናቸው።
መርሆዎቹ ዘር፣ ቀለምና ቦታ የማይገድባቸው በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ ውስጥ የሚሰርፁ ድንቅ ትምህርቶችን አዝለዋል።
“ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ። እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምንም ሥሩ። በአንተ ዘንድ ሆነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸውም እርጅናን ቢደርሱ ‘ኡፍ’ አትበላቸው፤ አትገላምጣቸውም፤ ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው።
ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው፤ ጌታዬ ሆይ! በሕጻንነቴ (በርህራሄ) እንዳሳደጉኝ እዘንላቸው በል።
ጌታችሁ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው። ታዛዦም ብትሆኑ (በመሳሳትም ብታጠፉ) እርሱ ለተመላሾች መሓሪ ነው።
ለዝምድና ባለቤትም መብቱን ስጥ፤ ለምስኪንና ለመንገደኛም (ስጥ)፤ ማባከንንም አታባክን። አባካኞች የሰይጣናት ወንድሞች ናቸውና፤ ሰይጣንም ለጌታው ብርቱ ከሃዲ ነው። ከጌታህም የምትከጅላትን ጸጋ ለማጣት ከነርሱ ብትዞር ለነሱ ልዝብን ቃል ተናገራቸው።
እጅህንም ወደ አንገትህ የታሰረች አታድርግ መዘርጋትንም ሁሉ አትዘርጋት፤ የተወቀስክ የተቆጨህ ትኾናለህና። ጌታህ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ያሰፋል፤ ያጠባልም፤ እርሱ በባሮቹ ኹኔታ ውስጠ ዐዋቂ ተመልካች ነውና። ልጆቻችሁንም ድህነትን በመፍራት አትግደሉ፤ እኛ እንመግባቸዋለን፤ እናንተንም (እንመግባለን)፤ እነሱን መግደል ታላቅ ኃጢያት ነውና።
ዝሙትንም አትቅረቡ፤ እርሱ በርግጥ መጥፎ ሥራ ነውና፤ መንገድነቱም ከፋ!
ያችንም አላህ ያወገዛትን ነፍስ ያለ ህግ አትግደሉ፤ የተበደለም ኾኖ የተገደለ ሰው ለዘመዱ (በገዳዩ ላይ) በርግጥ ሥልጣንን አድርገናል፤ በመግደል ወሰንን አትለፍ፤ እርሱ የተረዳ ነውና።
የየቲምንም ገንዘብ የብርቱነቱን ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በኾነች ኹኔታ እንጂ አትቅረቡ፤ በኪዳናችሁም ሙሉ፤ ኪዳን የሚጠየቁበት ነውና።
በሰፈራችሁም ጊዜ ስፍርን ሙሉ፤ በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ፤ ይህ መልካም ነገር ነው፤ መጨረሻውም ያማረ ነው።
ለአንተም በእርሱ እውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፤ መስሚያ ማያም ልብም እነዚህ ሁሉ (ባለቤታቸው) ከነሱ ተጠያቂ ነውና።
በምድርም ላይ የተንበጣረርክ ሆነህ አትኺድ፤ አንተ ፈፅሞ ምድርን አትሰረጉድምና በርዝመትም ፈጽሞ ጋራዎችን አትደርስምና።
ይህ ሁሉ መጥፎው ጌታህ ዘንድ የተጠላ ነው።
ይህ ጌታህ ከጥበቡ ወደ አንተ ካወረደው ነገር ነው፤ ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ፤ የተወቀስክ የተባረርክ ኾነህ በገሃነም ውስጥ ትጣላለህና።” (አል-ኢስራዕ 17፡23-39)
እስቲ ከነዚህ አንቀጾች የጥበብ መርሆዎችን ከልባችን እንመልከት፡-
- አላህን በብቸኝነት መገዛት፡- ይህ ታላቅ መርሆ አላህን ከማወቅ ይጀምራል። አላህ (ሱ.ወ) የዚህ ፍትረተ-ዓለም /ዪኒቨርስ/ (ከውን) ፈጣሪ መሆኑን መገንዘብና በብቸኝነት መገዛትንም ያካትታል። የአንድ ሙስሊም ህይወት ተውሂድ (አላህን በብቸኝነት ነጥሎ መገዛት) ከሌለው ባዶ ነው። አላህን በመገዛት ሂደት ውስጥ ህይወትንና ሞትን ብሎም ሁሉንም ተግባራትን በአጠቃላይ ለአላህ (ሱ.ወ) ማስገዛት ግድ ይላል። እኛ የተውሂድ ህዝቦች ብቻ አይደለንም ተውሂድን መሰረትና ግብ ያደረግን ህዝቦች እንጂ የህይወታችን፣ የመገኘታችን ምስጢር አላህ ነው። ዋነኛ ግባችንም አላህን ማስደሰት ነው።
- ለወላጆችህ ታዛዥና መልካም ሁን፡- ቤተሰባዊ ፍቅርና ርህራሄ ሁለተኛው ድንቅ መርህ ነው። ወላጆችህን በእዝነትና ርህራሄ ትመለከታቸው ዘንድ ኢስላም ያዛል። የመተናነስንም ክንፍ እንድትዘረጋላቸው ኢስላም በፅኑ ያስተምራል። ቤተሰብ የምርጥ ህብረተሰብ መሠረት ነውና። ይህንን ማህበረሰብ የፈጠሩ አንተንም የተንከባከቡህ ወላጆች ደግሞ የምትሰጣቸው ርህራሄና እዝነት፣ ክብርና ትህትና ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይሆንም።
- ለዘመዶችህ፣ ለመንገደኞችና ለድሆች አዛኝ ሁን፡- የዚህች ዓለም ህይወት በጋራ መስተጋብር ላይ የተመሰረተ ነው። የአንድ ሙስሊም ኃላፊነትም በራሱና በቤተሰቦቹ የተገደበ መሆን አይገባውም። ይልቁንስ መስጠት (መለገስ) የሚችል ሊሆን ይገባዋል። በዚህ ዓለም ስንኖር ብቻችንን በአንድ በረሃ ላይ እንደመጣል ነው። በመንገዳችን ላይ አንዳችን አንዳችንን በጥብቅ እንሻለን። አይኖቻችን የወንድሞቻችን ችግሮች መመልከቻና መደገፊያ ልናደርጋቸው ይገባል። ህይወታችን በኅብረተሰባዊ ማንነት ሊታጀብ ዘንድ ኢስላም ያስተምራል።
- በእጅህ ያሉትን ንብረቶች በአግባቡ ተጠቀምባቸው፡- አባካኝ አትሁን፣ ከአላህ የተሰጠህን ችሮታ አግባብ ባለው መንገድ ፈልግ፣ ሐላልን እንጂ አትመገብ፣ ያገኘኸውን ንብረት ደግሞ በሐላል መንገድ ላይ እንጂ በአልባሌ ቦታዎች አትበትነው። ከሙስሊም አባካኝነት እንደማይፈልገው ሁሉ ንፉግነትም አይገባውም። እጁ የማይፈታ (ንፉግ) አትሁን። የሙስሊም ህይወት በእነዚህ ሁለት አስፈላጊ ነገሮች መካከል የተገነባና የተደላደለ ህይወት ነው – በመለገስና ንብረቶችን በመንከባከብ። መሀከለኛ ህይወት!
- ልጆችህን በመልካም አሳድጋቸው፡- አስቀድመን የወላጆችህን ደረጃ እንዳወራነው ሁሉ ልጆችህም ባንተ ላይ መብትን አላቸው። ልጆቻችን የወደፊት ተስፋዎቻችን ናቸው። ጤናማ፣ ጎበዝና ኃላፊነት የሚሰማቸው ልጆችን ማፍራት ግዴታችን ነው። ኃላፊነታችንም ልጆቻችንን ጤናማና ንፁህ በሆነ አካባቢ ማሳደግ ነው። ቃላችንም የልጆቻችንን መንፈስ፣ አዕምሮ፣ አስተሳሰብና አመለካከት ብሎም ህይወት ከክፉ ሁሉ መጠበቅ ነው።
- ከአፀያፊ ተግባራት ራስህን ጠብቅ፡- ልቅ ፆታዊ ግንኙነት ማህበረሰብ ማፍረስ የሚችል ትልቅ አካል ነው። ስርዓትን የጠበቀ ፆታዊ ግንኙነቶችን ጤናማ፣ ደስተኛና የመልካም ስነ-ምግባር ባለቤት የሆነን ማህበረሰብ ማፍራት ያስችላሉ። እያንዳንዱ ሙስሊም ከነዚህ ተግባራት መታቀብ ብቻ ሳይሆን ወደ መንገድ የሚያስገቡ ነገሮችን መከልከል እንዳለበት ኢስላም አፅንኦት ሰጥቶ ያስተምራል። ይህም ማለት መልካምና ተቃራኒ ፆታን ወደ አስፈላጊ ተግባር የማይመራ የአለባበስ ስርዓት፣ የፆታዎች መቀላቀልን በተገቢው መልኩ ማካሄድና አላስፈላጊ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶችና መዝናኛዎችን መታቀብ ይካተቱበታል።
- የሰውን ህይወት አክብር፣ በፍትህ ካልሆነ የማንንም ህይወት አትቅጠፍ፡- ህይወት ክቡር የአላህ /ሱ.ወ/ ስጦታ ናት። ማንም ባሻው ሰዓት ሊቀጥፋት አይገባም። አንድ ሙስሊም ከባድ ቁጣንና ግጭትን ብሎም ማን አለብኝነትን ከህይወቱ ሊያስወግድ ይገባል። ህይወትን ወደ ማጥፋት ይመራሉና። ኢስላም በሰላም ላይ የተመሰረተ ስለሰላም የሚሰብክ የሰላም ሀይማኖት ነው። ሙስሊሞችም የዚህ ሰላም ጋሻ ጃግሬዎች ናቸው። ከዚህ ሁሉ ጋር የፍትህ ቦታ ሊጓደል አይገባውም። ማንም ጥፋተኛ ፍትሃዊ ቅጣትን መቀበል ግድ ይለዋል።
- ወላጅ አጥ ህፃናት የሁላችንም ልጆች ናቸው፡- ወላጅ አጥ ህፃናትን መንከባከብና ለትልቅ ደረጃ ማብቃት የእያንዳንዱ ሙስሊም ኃላፊነት ነው። መብታቸውን መለገስና ከመጥፎም መጠበቅ መርሆአችን ነው። እነዚህ ልጆች የማህበረሰቡ ልጆች ናቸው። ኢስላም የተገነባው ተዝቆ በማያልቀው የእዝነትና የፍቅር መሰረት ላይ ነው። እዝነቱ ሁሉም የሰው ልጅ ብሎም እንስሳትንና እፅዋትን ጭምር ይካልላል።
- ቃላችንን እንጠብቅ፣ አደራችንን በአግባቡ እንወጣ፡- አብዛኛው የሰው ልጅ ህይወት ቃልን በመስጠትና በመቀበል መካከል ይገኛል። ቃል የመልካም መስተጋብር ምሰሶ ነው። ቃል ሲታጠፍ መተማመን ይከስማል፣ ማህበረሰቡም ይደክማል። ሙስሊም ለቃሉ ታማኝ ሊሆን ይገባዋል። ቃላችን እውነትን መናገር፣ ታማኝ መሆንና ቃል ከገባን በአግባቡ መወጣት ነውና።
- በንግድህና በስራህ ላይ ታማኝ ሁን፡- አታጭበርብር፣ ሚዛን አታጉድል። ታማኝነት የስኬትና ብልፅግና መሰረት ነው። በማጭበርበር ላይ የተመሰረተ ማንነት ንፋስ በመጣ ሰዓት አይቆምም፤ ይፈርሳል። ለሥራህ ክብርን ስጥ። ሰዎች የሚኮሩብህ ሠራተኛ ለመሆን ጣር። ሙስሊም ነጋዴ በእውነት የሚሰራ ታማኝ ነው። ሙስሊም ሰራተኛ የታመነና የተከበረ ሰራተኛ ነው። ሙስሊም ባለበት መስክ ሁሉ ምሳሌ ነው።
- መንገድህ ሁሉ እውቀትን መሰረት ያደረገ ይሁን፡- ጥርጣሬን ጥራዝ ነጠቅነትን ከህይወትህ አስወግድ። እውቀት የሁሉም መሠረት ነው። ለኢንፎርሜሽን ቅርብ ሁን። የኢ-ፍትሃዊነት መሰረቱ የተሳሳተ መረጃና መረጃን በአግባቡ አለመጠቀም ናቸው። ሙስሊም ከሁለቱም መታቀብ ይገባዋል። በእውነት ላይ የተመሠረተ ኃሳብን መለገስና እውቀቱንም በአግባቡ መጠቀም ይገባዋል። ያለ ዕውቀት ከመናገር ራሳችንን እንቆጥብ። የውድቀት መሰረት ነውና። ለዓለም የእውነትና የእውቀት ህዝቦች መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል።
- ለሰዎች ተናነስ፣ ማንአለብኝነት አይሰማህ፡- ራስህን ዝቅ አድርገህ አትመልከት። ለሰዎች መተናነስ በሰዎች ዘንድ ያለህን ቦታ ከፍ ያደርገዋል። ተሰሚነት ይኖርሃል። ፈፅሞ ማንአለብኝነት፣ ኩራትና ንቀት አይኑርብህ። ህይወትህን ያሰናክሏታል። ሙስሊም ሁሌም በአላህ ስጦታ ይደሰታል። የኩራትና የክብር ባለቤት ለሆነው ጌታውም ይሰግዳል፤ ይታዘዛል።
ከላይ ያወሳናቸው የጥበብ መርሆዎች የሙስሊም ዓለም ስልጣኔ መሰረት ነበሩ። የማይነቃነቁ ችካል ሆነውም አልፈዋል። በእነዚህ ሚዛኖች የተለካ ኅብረተሰብ የሰላም፣ የነፃነትና የፍትህን ፍሬ የማይመለከትበት ብሎም በቀጣዩ ዓለም የአላህ ስጦታ የማይቸርበት ምንም ምክንያት አይኖርም።