የመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የስደት ዝግጅት
መካ ከሙስሊሞች ባዶ እስክትሆን ድረስ ወደ መዲና ሁሉም ነጎዱ። ቁረይሽም ኢስላም የሚጠበቅበት ጋሻ፣ የሚከላከልበት ምሽግ ሀገር እንዳገኘ ተሠማት። የመዲና ነዋሪዎች በፍቅርና በእንኳን ደህና መጣችሁልን መንፈስ ወንድሞቻቸውን ተቀበሉ። መልዕክተኛውም (ሰ.ዐ.ወ) ለመሰደድ አሰቡ። አላህ እስኪፈቅድላቸው ድረስ መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ለመሰደድ ዝግጅታቸውን ቀጠሉ። ዕቅዶችን ነደፉ፣ መሟላት ያለባቸውን ሰበቦች በሙሉ አደረሱ። መጠቀም የሚችሏቸውን ዘዴዎች በሙሉ ተጠቀሙ። ይህን ሁሉ ያደረጉት ከቁረይሾች ተንኮልና ሴራ ለመዳን ነበር።
ከነዚህ ዕቅዶች መሃል:-
- ለስደት የሚሆን የልብ ወዳጅና ጓደኛ መምረጥ የመጀመሪያው ነበር። እርሱም አቡበከር ሲዲቅ (ረ.ዐ) ነበሩ። አቡበከር (ረ.ዐ) መልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ለስደት ፍቃድ ለመጠየቅ ሲመጡ “አላህ የጉዞ ጓደኛ ሊያደርግልህ ይከጅላልና አትቸኩል” ብለዋቸው ነበር።
- መዲና እስኪደርሱ ከባልደረባቸው ጋር የሚጓዙባቸውን መጓጓዣዎች ማዘጋጀት።
- መንገድ ጠቋሚና አዋቂን ማዘጋጀት። ይህም እርሳቸውን ከባልደረባቸው ጋር መንገድ እየጠቆመ የሚጎዳኛቸው መሆኑ ነው። ለዚህም ከበኒ ዲይለም ቢን በክር ጎሳ ዓብደላህ ኢብኑ ኡረይቂጥን ቀጠሩት። የተዋጣለት መንገድ ጠቋሚ ነበር። በህዝቡ እምነት ላይ የነበረ ቢሆንም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አምነውት መጓጓዣቸውን አስረክበውት የሠውር ዋሻ ዘንድ ተቀጣጠሩ።
- መልእክተኛውና ባልደረባቸው ከመካ ሲወጡ ፍለጋና አሰሳው በረድ እስኪል ድረስ የሚደበቁበትን ቦታ አዘጋጁ። እሱም ጋሩ ሰውር ነበር።
- ሙሽሪኮችን ለማታለልና ራስን ለመጠበቅ ዓሊይን (ረ.ዐ) መኝታቸው ላይ እንዲተኙ አድርገው ነበር።
- ለመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የመካን ከተማ ነዋሪዎች የውሎ ወሬ የሚያመጣላቸው ሰው ማዘጋጀት ነበረባቸው። ለዚህ ተግባር የአቡበከር (ረ.ዐ) ወንድ ልጅ ዓብደላህ ተመረጠ።
- የምግብና መጠጥ አመላላሽና ወደ ዋሻው የሚመላለሱ ሰዎችን የእግር ፋና የሚያጠፋ ሰው ማዘጋጀት ነበር። ለዚህ ተግባር አስማ ቢንት አቡበከር (ረ.ዐ) ተመረጠች።
በመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የተጠነሠሠ ሴራ
መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በቁረይሽ እምነትና ክብር ላይ ሳይመጡ፤ ቁረይሽ በመሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እና ጥሪያቸው ላይ ከመካ ሳይወጡ ቀድማ ቁርጥ እርምጃ ለመውሰድ ፈለገች። የመካ ከሃዲያንና የጣዖት አምላኪያን ውሳኔ ለማሳለፍ በዳረ-ነድዋ ተሰባሰቡ።
“የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ። አላህም ከሓዲዎቹ ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን ገላጭ ነው።” (አስ-ሶፍ፤ 8)
ከፊሉ ለከፊሉ እንዲህ ተባባሉ- “እንደምታዩት የዚህ ሠው ጉዳይ የምታዩት ደረጃ ላይ ደርሷል። እንመካከርና ማድረግ ያለብንን እንወስናለን” ተባባሉ። ከነርሱ ውስጥ አንዱ “አግቱትና በር ዘግታችሁ ከርሱ በፊት የነበሩት ገጣሚያን በእስር አንደሞቱት እርሱንም ተጠባበቁት” አለ። በዚህ ሐሳብ ላይ ህዝቡ ተወያይቶ ውድቅ አደረገው።
“በአላህ ይሁንብን እንዳላችሁት ካገታችሁት ጉዳዩ ከዘጋጅሁበት በር ውጭ ለባልደረቦቹ ደርሶ ከእጃችሁ በጉልበት አስወጥተውት፣ ቁጥራቸውም ተባራክቶ ተሸናፊ እንሆናለን። ሌላ ሐሳብ ካለ አምጡና እንወያይበት።” ተባባሉ።
ከነርሱ ውስጥ አንዱ “ከሐገር አባረን ዜግነት እንቀማው። ከኛ መሀል ከወጣ የትም ቢሄድ አያገባንም።” አለ። ህዝቡ ይህን ሐሳብ በፍፁም ብሎ አራቀው። “ምን ዓይነት ሐሳብ ነው? የንግግሩን ጥፍጥና፣ የቋንቋውን ምጥቀት ይዞት የተነሳው ጉዳይ ልቦናን እንዴት እንደሚያሸንፍ አታዩምን? በአላህ ይሁንብኝ ይህ ከተደረገ ሰዎች ተከታዮቹ ይሆናሉ። ከሐገራችን ሊያስወጡንም ይዟቸው ይመጣል። የናንተን ስልጣን በእጁ አድርጎ ያሻውን ይሰራችኋል።” አላቸው። አቡ ጀህል ኢብኑ ሒሻም “በአላህ ይሁንብኝ ከዚህ በፊት ለናንተ ውል ብሎ የማያውቅ ሐሳብ አለኝ” አለ። “ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
“ከእያንዳንዱ ጎሳ ጠንካራና ጎበዝ ወጣቶችን መርጠን ለእያንዳንዱ የሰላ ሠይፍ ሠጥተን ሁሉም በአንድ ጊዜ የአንድ ሰው ምት መትተው ይገድሉትና ከእርሱ እንገላገላለን። ደሙ በሁሉም ጎሳዎች ጫንቃ ላይ ስለሚሆን በኒ ዓብዲመናፎች ሁሉንም መዋጋት አይችሉም። ስለዚህ በደም ካሳ ይስማሙናል ማለት ነው” አላቸው።
ሁሉም በአንድ ላይ ያለተቃውሞ በሐሳቡ ተስማሙ። ከስብሰባው ከተበተኑ በኋላ መልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ለመግደል ዝግጅት ጀመሩ።
ይህ የክህደት ባህሪ ነው። እውነትን ነብይም ይሁን መልእክተኛ ወይም ወደ ቀጥተኛ መንገድ ተጣሪ ይሸከማት ሊገድላት ይከጅላል። ክህደት ይህን ባህሪውን በሁሉም ዘመናትና ቦታዎች አንፀባርቆታል። ነገር ግን
“አላህም በነገሩ ላይ አሸናፊ ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።” (ዩሡፍ፤ 21)
ቁርዓን ሴራቸውን ሲያጋልጥ
እውነተኛው አምላክ መልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) አጋሪዎቹ ምን እንዳሴሩባቸውና ትምክህተኞች ምን እንዳሰቡባቸው ሳያሳውቃቸው አልተዋቸውም።
“እነዚያም የካዱት ሊያስሩህ ወይም ሊገድሉህ ወይም (ከመካ) ሊያወጡህ ባንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ (አስታውስ)። ይመክራሉም አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል። አላህም ከመካሪዎቹ ሁሉ በላይ ነው።” (አንፋል፤ 30)
ስለዚህም አላህ ስለ ሴራው ነገራቸው። ኢብኑ ኢስሐቅ አንዲህ ይላሉ “አላህ በዚያ ዕለት የተስማሙበትን አጋልጦ ካወረዳቸው አንቀፆች ውስጥ ከላይ የተቀመጠው የአንፋል ሰላሳኛ አንቀፅና እና
“ይልቁንም የሞትን አደጋ በእርሱ የምንጠባበቅበት የኾነ ባለ ቅኔ ነው ይላሉን?” (ጡር፤ 30) የሚሉት ይገኙበታል።
የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስደት አፈፃፀም
አጋሪዎቹ ሊገድሏቸው ውሳኔ ካሳለፉ በኋላ መካ ውስጥ የመልዕክተኛው ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሚሆን በቀላሉ የሚገመት ነው። የሚጠብቁት የግድያውን ዕቅድና ተግባር የማሳካት ቀጠሮ ብቻ ነበር። መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ከዚህች ጥሪያቸውን አልቀበል ካለች ደረቅና ልታስገድላቸው ካሴራችባቸው መሬት በደስታ ወደ ተቀበለቻቸውና በተለይ ባልደረቦቻቸው ቀድመው ወደ ከተሙባት መዲና ከተማ ሊሰደዱ የአላህን ፍቃድ ብቻ ነበር የሚጠባበቁት። የየስሪብ ነዋሪዎችም በናፍቆት እየጠበቋቸው ወደነርሱ መሠደዳቸውን እየጠበቁ ነበር።
አላህ እንዲሠደዱ ፈቀደላቸው። መዳረሻ ሐገራቸውንም በህልም አሳያቸው አስቀድመን እንዳየነውም በቂ የሆነ ዝግጅት አደረጉ። ወደ አቡበከር (ረ.ዐ) ቤት በመሄድ አላህ እንዲሰደዱ እንደፈቀደላቸው ነገሯቸው። አብሮ መሰደድን አቡበከር ጠየቁ። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተስማሙ። ጓዛቸውን በፍጥነት አዘጋጁ። አስማ አገልግላቸውን ቋጠረችላቸው፤ ማሰሪያ ስላጣች መቀነቷን ሰንጥቃ አገልግሉን አሰረችው። ለዐብደላህ ኢብኑ ኡረይቂጥ መጓጓዣቸውን ሰጥተውት ከ 3 ቀናት በኋላ የሰውር ዋሻ ጋር ቀጠሩት። አቡበከርን ከመካ ውጭ ለሊት እንገኛኝ ብለው ተለያዩ።
ይህች ለሊት አጋሪዎቹ ቁረይሾች ውሳኔያቸውን ሊፈፅሙ የወሰኑባት ነበረች። ወደ መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ቤት በመምጣት ተሠባሰቡ። ለሊት የሚወጡበት ሰዓት ሲቃረብ የአጎታቸውን ልጅ ዓሊይን (ረ.ዐ) ፍራሻቸው ላይ እንዲተኙ አዘዟቸው። ይህን ያደረጉት አጋርያኑ ቤት ውስጥ ስለመኖራቸው እንዳይጠረጥሩ ነበር። በእርግጥ በቤታቸው በር ቀዳዳ በተደጋጋሚ አጮልቀው እያዩ መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
“ከስተፊታቸውም ግርዶን ከስተኋላቸውም ግርዶን አደረግን። ሸፈንናቸውም። ስለዚህ እነሱ አያዩም።” (ያሲን፤ 9) የሚለውን እየቀሩ ከቤት ወጥተው ሄዱ።
አላህ እንቅልፍ ለቀቀባቸውና መልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) አንዳቸውም ሳያዩዋቸው ወጥተው ሔዱ። ከአቡበከር (ረ.ዐ) ጋር ተገናኙ። የሠውር ዋሻ ውስጥም ተሸሸጉ።
አጋርያኑ ሴራቸው መክሸፉንና ዓሊይን አንጂ መልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) እየጠበቁ እንዳልነበሩ ሲረዱ ስሜታቸው ክፉኛ ተሰበረ። በሁሉም አቅጣጫ ያገኘው ወይም የጠቆመ ሽልማት አለው በማለት ፈላጊ አሰማሩ። ፍለጋቸው እስከተደበቁበት ዋሻም ደርሷል። አቡበከር በስጋት ለመልዕክተኛው “አንዳቸው እኮ ወደ እግሩ ቢመለከት ያየናል” ሲሉ
“አትዘን አላህ ከእኛ ጋር ነውና” (ተውባ፤ 4) ብለው መልሰውላቸዋል።
አላህ የአጋርያኑን ዓይን ወደ ዋሻው አንዳያይ ጋረደው። መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ዋሻው ውስጥ ከባልደረባቸው ጋር ፍለጋና አሰሳው እስኪቆም ለሶስት ቀናት ቆዩ። ፈጣንና ንቁ የነበረው ዓብደላህ ኢብኑ አቡበከር አብሯቸው ያድራል። ወደ መካ ከተማ በማለዳ ይወጣል። መካ ስለ መልዕክተኛው የዶለተቻቸውን እያንዳንዳንዷን ወሬ ለቅሞ በምሽት ወደ ዋሻው ይመለሳል። አሚር ኢብኑ ፋሃይራም ፍየሎችን ይዞ ወደዛው አካባቢ ቀን ላይ ያግዳል። ምሽቱን ዓብደላህ ኮቴ ያጠፋል።
ሱራቃ ኢብኑ ማሊክን ለማግኘት ወደርሱ ጎሳ የሚጓዝ ሠው በመንገድ ላይ መልዕክተኛውንና (ሰ.ዐ.ወ) አቡበከርን አይቶ ነበር። ሱራቃ ከጎሳው ሰዎች ጋር ቁጭ ባለበት መጣና “ሱራቃ ሆይ! በባህር ዳርቻው ላይ ሁለት ሰዎችን አይቻለሁ። ሙሐመድና ባልደረባው አንደሆኑ ጠርጥሬያለሁ።” አለ። ሱራቃም እነርሱ እንደሆኑ አወቀ። በተቀመጠበት ትንሽ ቆየት ብሎ ፈረሱን ጋልቦ በፍጥነት ደረሰባቸው። ሲቀርባቸው ፈረሱ ከላይ ጣለችው። ዳግመኛ ጋልቦ የመልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ቁርዓን ሲቀሩ ድምፃቸውን መስማት እሚችልበት ርቀት ድረስ ቀረባቸው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዙረው አላዩትም። አቡበከር (ረ.ዐ) ግን ለመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ስላሰቡ መዟዟር ያበዙ ነበር። የሱራቃ ፈረስ እግር እስከ ጉልበቷ ድረስ መሬት ውስጥ ሠመጠች። እርሱንም ጣለችው። ፈረሱን ጮኸባት። እግሯን ለማውጣት ስትታገል ሰማዩን በአቧራ ጉም ሞላችው።
ሱራቃም እየሰራው ያለው ስራ ከንቱ እንደሆነ አወቀ። ልቦናው በፍርሃት ራደ። ከሩቅ ጠራቸውና ቆሙለት። “ህዝቦችህ በአንተ ላይ የግድያ ካሳን አስቀምጠዋል” ሲል ነገራቸው። ስንቅና አንዳንድ መጠቃቀሚያዎችን ሊሰጣቸው ቢፈልግም ግን አልተቀበሉትም።
“ስለኛ ጉዳይ አታውራ። ሚስጥራችንን ጠብቅ” አሉት። ሱራቃ ከመልእክተኛው የሰላም ስምምነት ደብዳቤ እንዲፅፉለት ጠየቃቸው። አቡበከር እንዲፅፉለት አዘው ይህ እንቅፋት በዚህ መልኩ ሊፈታ ችሏል። የመዲና ሰዎች የመልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ከመካ መውጣትና ወደነርሱ አቅጣጫ መምጣት ከሠሙ ጊዜ ጀምሮ በዛፎች ጥላ ስር ሆነው መድረሳቸውን ይጠባበቁ ነበር። ከዚህ ሁኔታ የቀኑ ሐሩር ነበር ወደ ቤት የሚያስገባቸው። አንድ ቀን ለረዥም ሰዓት ከጠበቁ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ሊገቡ ሲሉ ካብ ላይ የተቀመጠ አንድ አይሁድ ”አረቦች ሆይ! ስትጠብቁት የነበረው ድርሻችሁ ይኸው መጣላችሁ” ብሎ በከፍተኛ ድምፅ ተጣራ። በጠራራው ፀሃይ ተመልሠው መልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ተቀበሏቸው።


























