የኢስላማዊው ዳዕዋ ብርሓን መካ ውስጥ ፈነጠቀ። በእውነትና ክህደት መኃል ውጥረት እንዲነግስ የአላህ ፍላጎት ሆነ። ይህን ትግል መካ በአፈሯ ማስተናገድ ጀመረች። ይህ በህይወትም ይሁን በሌሎች ተመሣሣይ ጥሪዎች የነበረ የአላህ ፍጥረት ህግ ነው።
“ለእነዚያ ለጌታቸው ለታዘዙት መልካም ነገር (ገነት) አልላቸው። እነዚያም ለእርሱ ያልታዘዙት ለእነሱ በምድር ያለው ሁሉ ከእርሱም ጋር ብጤው ቢኖራቸው ኖሮ በእርሱ በተበዡበት ነበር። እነዚያ ለእነሱ ክፉ ምርመራ አለባቸው። መኖሪያቸውም ገሀነም ናት። ፍራሻቸውም ከፋች!” (አር-ራዕድ፤ 17)
ከዚህ በፊት መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ጉዳያቸውን ለወረቃ ኢብኑ ነውፈል ሲነግሩት ምን እንደመለሰላቸው እናስታውሳለን። “የዛኔ ህዝቦችህ ከሃገር ሲያስወጡህ በወቅቱ ወጣትና ህያው ብሆን ምን ነበር! አንተ ይዘኸው የመጣኸውን ዓይነት ይዞ የመጣ ሁሉ ጠላትን አፍርቷል። ያን ጊዜ በህይወት ካለሁ ከጎንህ ሆኜ እረዳሃለሁ።” ብሏቸው ነበር ።
በተገለለው እውነትና፣ ደጋፊ እንዲሁም ጠንካራ መሳሪያ በነበረው ውሸት መኃል የነገሠው ውጥረት ተጠናከረ። አላህ መውጫ እስኪያዘጋጅላቸው ድረስ ሙስሊሞች የጀግና ትዕግስትን ታገሱ። ዓመታት ነጎዱ፣ ቀናት ተቀያየሩ። ቁረይሽ አማኞችን ለመፈተን ጭካኔዋና ማስጨነቋ ጨመረ። ከሙስሊሞች ውስጥ በእምነቱ የተፈተነ፣ ከእጃቸው ቅጣትን የቀመሰ እንዲሁም እምነቱን ለመጠበቅ ሲል በረዘመና ጥቅጥቅ ጨለማ ወደ ሐበሻ ምድር የተሰደደም ነበር። ለአማኞች የአላህ እዝነትና ብልጭታ ግልፅ ወጣ። ለሠራተኞቹ እርዳታውን አመጣ።
“መልክተኞቹም ተስፋ በቆረጡና እነርሱ በእርግጥ የተዋሹ መኾናቸውን በተጠራጠሩ ጊዜ እርዳታችን መጣላቸው። (እኛ) የምንሻውም ሰው እንዲድን ተደረገ። ቅጣታችንም ከአጋሪዎቹ ሕዝቦች ላይ አይመለስም።” (ዩሱፍ፤ 110)
የስሪብ (መዲና አል-ሙነወራ) ለአማኞችና ታጋይ የአላህ ሰራተኞች ሰላም በሠፈነበት ምድር አዲስ ማህበረሰብ ይቋቋም ዘንድ እቅፏን ከፍታ ተቀበለቻቸው…
መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ለባልደረቦቻቸው እንዲሠደዱ መፍቀዳቸው
የየስሪብ ነዋሪች ልቦና በኢስላም ሲከፈት፣ እምነት እነርሱ ዘንድ እጅግ ሲወደድ፣ ኢስላም በደም ስራቸው ሲዘዋወር፣ ሁለተኛው የአቀባ ቃልኪዳን ላይ ለመልዕክተኛው እና ለተከታዮቻቸው የእርዳታን ቃል ሲገቡላቸው የሙስሊሞች ልብ ወደ መዲና መሠደድን ናፈቀች። ዑርዋህና ዓኢሻ (ረ.ዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) “የስደት ቀያችሁን በርግጥ አየኋት። የተምር ዛፍ የበዛባት በሁለት ተራሮቸ መሓል የምትገኝ ሃገር ናት” ብለዋል።
መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦቻቸውንና መካ ውስጥ የነበሩ አማኞችን ወደ መዲና መሠደድንና ከአንሷር ወንድሞቻቸው ጋር እንዲገናኙ አዘዙ። እንዲህ ሲሉም ተናገሩ “አላህ (ሱ.ወ) በርግጥ ለናንተ ወንድሞችንና በርሷም ውስጥ ሰላም የምታገኙባትን ሐገር ሰጥቷችኋል።”
የአላህን እንዲሁም የመልዕክተኛውን ትዕዛዝ በማክበር፣ የእውነትን ወታደሮች ለመርዳትና ኢስላማዊ ማህበረሰብና ሐገርን ለማቋቋም ሲሉ ተከታትለው ወጡ…
የሶሐቦች ወደ መዲና መሠደድ
ሙስሊሞች በቡድንም በግልም እየሆኑ ወደ መዲና ተሠደዱ። ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች ወደ መዲና መጀመሪያ የተሰደደው አቡ ሠለማህ ከባለቤቱ ለይላ ቢንት ሐስማ ጋር በመሆን ነበር። በመቀጠል ዓብደላህ ኢብኑ ጀህሽ፣ ከእርሱ ቀጥሎም ዑመር ኢብኑል ኸጣብ ነበሩ። ከዑመር በኋላ ወንድማቸው ዘይድ ኢብኑል ኸጧብ ተሰደዱ። በታሪክ የዘመን ጉዞ ልዩ የተባለውን የጀግንነትና እምነት ትዕይንቶች በያዘው ስደት ሁሉም ተከታትለው መዲና ከተሙ።


























