ከስር የምናነበው የኣሊ-ዒምራን ምዕራፍን የመጨረሻ አንቀፆች ነው። ይህች አንቀፅ ማስተዋል ለሚችሉ ሁሉ ድንቅ ትምህርትን ትለግሳለች።
አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በአንቀፆቹ ውስጥ በአላህና በመልዕክተኛው የከዱትን ሰዎች ከጠቀሰ በኋላ ስለአስተዋዮች ይናገራል።
“ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀን በመተካካት ለባለ አዕምሮዎች በርግጥ ምልክቶች አሉ። (እነርሱም) እነዚያ ቆመው ተቀምጠውም በጎኖቻቸው ተጋድመውም አላህን የሚያወሱ በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ ጌታችን ሆይ ይኽንን በከንቱ አልፈጠርከውም። ጥራት ይገባህ ከእሳትም ጠብቀን የሚሉ ናቸው። ጌታችን ሆይ! እኛ በጌታችሁ እመኑ በማለት ወደ እምነት የሚጠራን ጠሪ አመንንም፤ ጌታችን ሆይ! ኃጢያቶቻችንንም ለኛ ማር ክፉ ሥራዎቻችንንም ከኛ አብስ፤ ከንጹህ ሰዎችም ጋር ግደለን። ጌታችን ሆይ! በመልዕክተኞችህም ላይ የተስፋ ቃል ያደረግልንን ስጠን በትንሳዔ ቀንም አታዋርደን ቀጠሮን አታፈርስምና (የሚሉ ናቸው)።” (ኣሊ-ዒምራን 3፤ 190-194)
አስተዋይ በዚህ ፍጥረተ-ዓለም (ዩኒቨርስ) ያሉትን ድንቅ የአላህ ፍጥረታት በመመልከትና በማስተንተን የአላህን (የፈጣሪን) መኖር የሚረዳ ማለት እንደሆነም ያስረዳል። አስተዋዮች አላህን ከማስታወስ አልፈው በችሎታው ተማርከው እንደሚገዙትና እንደሚያመሰግኑትም ያትታል። በዙሪያቸው ያሉት ፍጥረታት ላይ ያለውን ድንቅ ተዓምርም በማጤን ይህች ምድርና ሰማይ በውስጡም ያሉት ፍጥረታት በሙሉ ያለ ምክንያት፣ ለጨዋታና ዛዛታ ያልተፈጠሩ መሆናቸውን ይገነዘባሉ። ሁሉም ነገር የተገኘበት ምክንያትና ዓላማ አለው። ይህ ድንቅ አስተሳሰብና አስተዋይነት የዚህ ፍጥረተ-ዓለም (ዩኒቨርስ) ፈጣሪ ምንኛ ጠቢብ መሆኑን እንዲያምኑና እንዲመሰክሩ ያደርጋቸዋል።
ስለ ድንቅ ፍጥረተ-ዓለሙና ስለአስገኚው ያላቸው እሳቤ ወደ ራሳቸው በመመለስ እንዲመለከቱ ይጋብዛቸዋል። የህይወታቸውን ውጣ ውረድ ይመለከታሉ። መልካሙንና መጥፎውን፣ ፍትሁንና ጭቆናውን፣ ጽድቅና ኩነኔውን ሁሉ ሲመለከቱ ይህ ጥበበኛ ፈጣሪ ይህንን ሁሉ አለመስተካከል ኢ-ፍትሃዊነትና በደል በዝምታ እንደማያልፈው ይረዳሉ። አላህን ከዚህ ጥፋት ይጠብቃቸው ዘንድ ይለምናሉ። ከቅጣቱ ያድናቸውም ዘንድ እርዳታውን ይሻሉ። ወደ አላህ ፊታቸውን ያዞራሉ፣ እምነታቸውን በነቢያት መንገድ ያንፃሉ። ይህ የኣሊ-ዒምራን የመጨረሻ አንቀፆች ምሉዕ መንፈስ ነው።
ይህ የምርጡ አርኣያችን ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መንገድ ነው። የህይወታችንን አላማ በግልፅም የሚያሳይ ምዕራፍ ነው። ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሌሊት ሶላታቸው እነዚህን አንቀፆች ማንበብ ያዘወትሩ ነበር።
አብዱላህ ኢብን አባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና፡-
“አንድ ቀን ከነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቤት አደርኩኝ” ይላል። “ነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሌሊቱ ክፍል ሲነሱ ተመለከትኩኝ። ጥርሳቸውን ፋቁና ውዱእ አደረጉ። ከዚያም ‘አስተውሉ በምድርና ሰማይ መፈጠር በቀንና ሌሊት መፈራረቅ ለልብ ባለቤቶች በእርግጥ ምልክት አለ።’ የሚለውን የኣሊ-ኢምራን የመጨረሻ አንቀፅ እስከ ምዕራፍ መጨረሻ አነበቡ። ተነስተውም ሁለት ረከዓ ሰገዱ። ረጃጅም ሩኩዕና ሱጁድም አደረጉ። ወደ አልጋቸውም ተመለሱና ተኙ። ይህንንም ሦስት ጊዜ ፈፀሙ። ለእያንዳንዱ ጥርሳቸውን ይፍቁና አዲስም ውዱእ ያደርጉ ነበር። የኣሊ-ዒምራን ምዕራፍ የመጨረሻ ክፍልም ያነቡ ነበር። በዚህ ሁኔታ ስድስት ረከዓን ከሰገዱ በኋላ ሶስት ረከዓ ዊትር ሰገዱ። ከዚያም በኋላ የሱብሂ ሶላት አዛን ተሰማና ለሰላት ወጡ። በዚህም ወቅት ‘የአላህ ለልቤ ብርሃንን ለግሰኝ ለምላሴም ብርሃንን፣ ለጆሮኤም ብርሃንን፣ ለአይኔም ብርሃንን ለግሰኝ፣ ከፊቴም ከበስተጀርባዬም ብርሃንን ለግሰኝ፣ ከበላዬም ከስራዬም ብርሃን ለግሰኝ። የአላህ ብርሃንን ለግሰኝ’ በማለት አላህን ይለምኑ ነበር።” (ሙስሊም ዘግበውታል)
ዛሬ የሰው ልጅ ከታላቅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ይገኛል። ጨረቃን ከረገጥን ዘመናት ተቆጠሩ፣ ዛሬ ደግሞ ወደ ማርስ ለመድረስ እየለፋን እንገኛለን። የአላህን ታላላቅ ፍጥረታት እየተገነዘብን እንገኛለን። በእርግጥ ይህ እመርታ አላህን ወደ ማስታወስና ወደ አስተዋይነት አሸጋግሮልናልን? አመለካከታችንን አርቋልን? ፈጣሪያችን ወደ ማምለክ ለትዕዛዙ እጅ ወደመስጠት መልሶናልን? የተሻሉ ህዝቦች ሆነናልን? ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ሰላማዊ ዓለምን መገንባት ችለናልን? በእርግጥ የዚህ ፍጥረተ-ዓለም (ዩኒቨርስ) ፈጣሪ ምድርንና ሰማይን በውስጧ ያሉትንም ያለ ምክንያት ያለ ዓላማ አልፈጠረም። ይህንን ዓላማስ ተረድተናልን? ምክንያታዊ ህይወት መኖርስ ጀምረናልን?
በእርግጥ ዓለማችን የህይወታቸውን ዓላማ ባልተረዱ ሚሊዮን ደርዘን ሰዎች የተሞላች ከረጢት ናት። ህይወታቸው ማሰብና ማስተዋል ከማይችሉት እንስሳት በማይለዩ ሰዎች ተጥለቅልቃለች። ቁሳዊያን የሕይወታቸው ዓላማ ሀብትን ማካበት፣ ህይወትን ማጣፈጥ፣ በብርና ወርቅ ማጌጥ ብቻ ነው። ዓለማውያን የህይወት ዓላማቸው በዚህች ጠፊ ምድር መደሰትና ማለፍ ብቻ ነው። “ከዚያስ ምን?” ብለን ብንጠይቃቸው ሚሊዮኖች ለጥያቄያችን መልሳቸው ዝምታና ግራ መጋባት ነው። “በእርግጥ የህይወቴ አላማ ምንድን ነው?” በማለት ራሳቸውን መጠየቅ ይጀምራሉ። ይህ ጥያቄ ይበልጡኑ የሚገዝፍባቸው የህይወታቸው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ሲቀመጡ፣ ሞት ከፊታቸው ሲታያቸው ነው። “ከዚያ ሁሉ ደስታ በኋላ ይህ ምን የሚሉት ነው?” በማለት ግራ ይጋባሉ። አሁን ግን የቁጥራቸው መብዛትና የነርሱን አመለካከት ተከታዮች መበርከት እውነቱን ሸፍኖባቸዋል።
ቁርዓን እንደሚያስተምረን እንዲህ አይነት ሰዎች በሞት አፋፍ ላይ ሲቆሙ ሲሰሩት ስለነበረው ስራ ያስታውሳሉ፣ ምንኛ መጥፎ እንደነበሩም ይረዳሉ። ተራና የማይረባ ህይወትም ማሳለፋቸውን ይገነዘባሉ። ያኔ ግን በእርግጥ ረፍዷል። ፀሀይም ጠልቃለች። መንገዱም ተዘግቷል።
“የሞትም መከራ እውነቱን ነገር ታመጣለች፤ (ሰው ሆይ)፡- ከርሱ ትሸሸው የነበርከው ነው (ይባላል)። በቀንዱም ውስጥ ይነፋል፤ ያ (ቀን) የዛቻው (መፈጸሚያ) ቀን ነው። ነፍስም ሁሉ ከርሷ ጋር ነጂና መስካሪ ያለባት ኾና ትመጣለች። ከዚህ ነገር በርግጥ በዝንጋቴ ውስጥ ነበርክ። ሽፋንህንም ካንተ ላይ ገለጥንልህ፤ ስለዚህ ዛሬ ዐይንህ ስለታም (በደንብ የሚያይ) ነው (ይባላል)።” (ቃፍ 50÷19-22)
የፍጥረተ-ዓለሙ ዓላማ ምንድን ነው? ይህንን መልስ ሊሰጥ የሚችለው አካል ራሱ የፍጥረተ-ዓለሙ ፈጣሪ ብቻ ነው። ለመልሱ የሚገባው እርሱ ብቻ ነው። ምክንያቱም ያስገኘው እንጂ ማንስ አስበልጦ የመገኘቱን ምክንያት ሊረዳ ይችላል? አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ፈጣሪያችን ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? እርሱ ከኛ የሚሻው ሁሌም እንድናመልከው፣ ምስጋናን እንድናቀርብለት፣ ዘወትር እንድናጠራው ነው። ለምን? አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እኛን በእጅጉ ይወደናል። ዘልአለማዊና ጣፋጭ ህይወትም ሊለግሰን ይፈልጋልና ነው። ሁሌም ከርሱ ጋር እንድንሆን ይሻልና ነው። በእርሱም የልቅና ጥላ ስር ሊያኖረን፣ የፍቅሩን ካባ ሊደርብልን ይወዳልና ነው።
የአላህን ዘልአለማዊ ተጓዳኝት (አል-ረፊቁል አዕላ) ማግኘት ምንኛ መታደል ነው? ምንኛስ መከበር ነው? ግና ይህ ታላቅ ስጦታ በፈተና እንጂ አይገኝም። የህይወትን ፈተና ላለፈ ብቻ የምትሰጥ ድንቅ ሽልማት ነች። አላህን በታማኝነት ለተገዙ ብቻ የምትደፋ የአልማዝ አክሊልም ነች።
አላህ በቁርዓኑ እንዲህ ይላል፡-
“ጋኔንንና ሰውንም ሊገዙኝ እንጂ አልፈጠርኳቸውም። ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፤ ሊመግቡኝም አልሻም። አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው።” (አዝ-ዛሪያት 51÷56-58)
አላህን መገዛት ማለት ለእርሱና በመልዕክተኛው ማመን ማለት ነው። ለትእዛዙ ማደር ማለት ነው። ለሸርፍራፊ ሰኮንዶች እንኳን ከምህዋሩ አለመውጣት ማለት ነው። በፍጥረታት መሀከል ፍትህንና ፍቅርን ማስፈን ማለት ነው። የመልዕክተኛውን ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መንገድ መከተል ማለት ነው። ይህ በእርግጥ የጀነት መንገድ ነው-ትክክለኛው ኢስላማዊ ሕይወትና ስኬት።
ማሻ አላህ አላህ ስራችሁን ይባርክላችሁ
Comment: love it