የሐዘን ዓመት

0
498

በሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውና የተደረገው ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብና አጋሪዎች ከሙስሊሞች አንፃር የተስማሙበት ማኅበረሰባዊ እገዳ፤ በነቢያችንና ሰሐቦቻቸው ላይ ያደረሰው ግፍና መከራ እጅግ ከባድ ነበር። ይህ እገዳ በተነሳ ጊዜ እና የተወሰኑ አጋሪዎች ይህንን በደል የያዘውን የግፍ ስምምነት ማስታወቂያ ሲቀዳድዱ፣ ሙስሊሞች ከሸለቆው በመውጣት ወደ ድሮ እንቅስቃሴያቸው ተመለሱ። ይህ የሆነው እስልምና ለተከታታይ አስር ዓመታት መካ ውስጥ ከባባድ ክስተቶች፣ አስጨናቂ ህመሞችንና ተከታታይ ሀዘኖችን ካሳለፈ በኋላ ነበር። ይህ የእገዳና የመከራ ማዕቀብ ተነሳልን ብለው ብዙም ዘና ሳይሉ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) በሁለት ከባድ ሐዘኖች ተመቱ። አጎታቸውና አቡጣሊብ እና የሙእሚኖች እናት የሆኑትን ባለቤታቸው ኸዲጃን (ረ.ዐ) በሞት አጡ።

አቡጣሊብ ምንም እንኳ በወገኖቹ እምነት ውስጥ የነበረ ሰው ቢሆንም ኢስላማዊው ዳዕዋ ከአምባገነኖች እና ቂላቂሎች የተከለለበት ግንብ ነበር ማለት ይቻላል። አላህ(ሱ.ወ) ሃይማኖቱን መርዳት ሲፈልግ በጠማማ ሰውም ሆነ የመልካም ሥነምግባር ባለቤት ባልሆነ ግለሰብ ጭምር ሊረዳው ይችላል። አቡጣሊብም ለነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ከለላ በመሆንና ለርሳቸውም በመከላከል ነበር የኖሩት። ከርሳቸው ህልፈት በኋላ እንጂ ቁረይሾች ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ.) መዳፈር አልቻሉም ነበር። የሐዘናቱ መደራረብ እና በተመሳሳይ ዓመት ውስጥ መሆን፤ ዓመቱን የሐዘን ዓመት ተብሎ በታሪክ ሰዎች ዘንድ እንዲታወቅ ምክንያት ሆነው።

እናታችን ኸዲጃም (ረ.ዐ.) ከአቡጣሊብ ሞት ጥቂት ቀናት በኋላ ነበር የሞቱት። ከዚያ በኋላ በነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ላይ መከራው በዛ፤ በግልጽም ግፍን ያደርሱባቸው ጀመሩ። ሊገድሏቸው ጭምር ሞከሩ፣ አላህ ግን ጠበቃቸው።

ኸዲጃ (ረ.ዐ) አላህ በነቢያችን ላይ ከዋለላቸው ታላላቅ ጸጋዎች ውስጥ አንዷ ናቸው። እጅግ አስቸጋሪ በነበሩ ጊዜያት ውስጥ ከጎናቸው የቆሙ፤ የተላኩበትን መልዕክት ያደርሱ ዘንድ ያገዟቸው፣ ሐዘንም ሆነ ደስታቸውን የተጋሩ፤ በገንዘባቸውና በራሣቸው ጭምር የረዷቸው ናቸው። ኸዲጃ (ረ.ዐ.) እጅግ እውነተኛ ሴት ነበሩ። ባላቸው ሀሳብና ጭንቀት ባገኛቸው ፍቅር ያሳዩ፣ በችግር ወቅት ከጎናቸው የቆሙ ናቸው። ሩብ ምዕተ ሙሉ የግፍ ጽዋን፣ የእቀባ ህመምን፣ የኢስላማዊ ጥሪ መከራን ከርሣቸው ጋር ተሸክመው ዘልቀዋል። ስለሆነም የኸዲጃ (ረ.ዐ.) ሞት ነቢያችንን (ሰ.ዐ.ወ.) ካጋጠሟቸው ጉዳቶች ሁሉ አጥንት ሰባሪው ነበር። በርሣቸው ሞት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እጅጉን አዘኑ። ሕይወታቸውንም በሙሉ በመልካም ሲያወሷቸው ነበር የኖሩት። ብልጫዋንና መልካምነቷንም ለሰዎች ይገልጹ ነበር። ዓኢሻ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይላሉ፦ “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ኸዲጃን  እጅጉን በማረ ሁኔታ ያወሷት ነበር። አንድ ቀን ቅናት ያዘኝና እንዲህ አልኳቸው። ከርሷ የተሻለ አላህ ተክቶልዎት ሳለ ምንድነው እንዲህ ወዘናዋ የረገፈን ሴት አብዝተው ማውሳትዎ?” አልኳቸው። እርሣቸውም እንዲህ አሉኝ “ኃያሉና የተከበረው አላህ ከርሷ የተሻለ አልተካልኝም፤ እርሷ እኮ ሰዎች በካዱኝ ወቅት ያመነችብኝ፤ ሰዎች ባስዋሹኝ ጊዜ እውነተኝነቴን የመሠከረች፤ ሰዎች ገንዘባቸውን ሲከለክሉኝ በገንዘቧ የደገፈችኝ ነች። ከሌሎች ሴቶች ልጅ ሳይሰጠኝ አላህ ከርሷ ልጅ ለገሰኝ።” (አሕመድ ዘግበውታል)

ከሁለቱ ከባባድ ሐዘኖች በኋላ የቁረይሾች መከራና ግፍ እየጨመረ መጣ። ዐብደላህ ኢብኑ ዐምር ኢብን አልዓስ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይላል፦ “ሒጅር ላይ (ከዕባ በዙሪያ ያለ የመስገጃ ስፍራ፤ ሒጅሩ ኢብራሂም በመባል ይታወቃል። የቁረይሽ ባላባቶች ተሰብስበው ሳሉ መጣሁኝ። የአላህን መልዕክተኛ በማንሳት እንዲህ ይሉ ነበር፦ “እርሱን እንደታገስን ማንንም አልታገስንም፤ ህልማችንን መና አስቀረ፤ አባቶቻችንን ሰደበ፣ ህብረታችንን በተነ” በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) መጡ። የከዕባን ማዕዘን ሳሙ። በአጠገባቸው ሲያልፉም ተጠቃቀሱ።

በሌላ ዘገባ ላይ ነቢያችን “በእርግጥ ልፋለማችሁ መጥቻለሁ!! አሏቸው። እነርሱም “የቃሲም አባት ሆይ! (አላዋቂ) መሃይም አልነበርክም።” እንዳሏቸውና እርሳቸውም በሰላም እንደተመለሱ ተዘግቧል።

በነጋታው በተመሳሳይ ሁኔታ ተሰብስበው “የምትጠሉትን ነገር ሲናገራችሁ ጭምር ዝም አላችሁት” ተባባሉ። በዚሁ ሁኔታ ላይ እያሉ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ብቅ አሉ። “ተነሱና እንደ አንድ ሰው ሆናችሁ ተረባረቡበት” ተባባሉ። ዑቅባ ኢብኑ አቡ ሙዐይጥ ተነሳና ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ.) በኩታቸው ሸምቅቆ ያዛቸው። አቡበክርም ከኋላቸው ደረሱና እያለቀሱ “ጌታዬ አላህ ነው ያለን ሰው ትገድላላችሁን?” አሏቸው። አስማእ (ረ.ዐ.) ባወራችው ሌላ ዘገባ ደግሞ “በቤታችን እያለን አንድ ሰው እየጮኸ መጣና ለአቡበክር (ረ.ዐ) “ጓደኛህን ድረስለት!” አላቸው። አቡበክር (ረ.ዐ.) ትልቅ ኩታቸውን እንደለበሱ “ወዮላችሁ! ጌታዬ አላህ ነው ያለን ሰው ትገድላላችሁን?” እያሉ ወጡ። ይሄኔ ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ትተው አቡበክር ላይ ዘመቱ። ከመደብደባቸው የተነሳ ከሳቸው ጋር ያልተቀደደ ኩታ አልተመለሰም ነበር።” ብላለች።

በሌላ ጊዜም ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) በከዕባ ዙሪያ እየሰገዱ ሳለ የቁረይሽ ሹማምንት እያዩት ከመካከላቸው አንደኛው ብቅ አለና የታረደ የግመል ፈርስ በጀርባቸው ላይ አስቀመጠባቸው። በርግጥ እነዚህ ሰዎች የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ.) እውነተኛነትና ታማኝነት ብሎም ይዘው የመጡት ሁሉ እውነት መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ግና ነገሩ ሁሉ አላህ (ሱ.ወ) እንደተናገረው ነው፦

‹‹ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) (ከወሕይ) የጀመራቸው መልካም ሕልሞችን በእንቅልፋቸው መመልከት ነው፡፡ ልክ እንደ ንጋት ጎህ ሆና የምትከሰት ብትሆን እንጂ ሕልም አያዩም ነበር፡፡ መገለልን ወደዱ፡፡ በሒራእ ዋሻ ውስጥ ብቻቸውን ለዚህ የሚሆን ስንቅን ለመሰነቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሳይመለሱ ብዙ ሌሊቶችን ያሳልፉ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ኸዲጃ (ረ.ዐ) ይመለሱና ስንቅ ይሰንቃሉ፡፡በሒራእ ዋሻ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከጌታቸው የሆነው እውነት እስከመጣላቸው ድረስ ቀጥለው ነበር፡፡››

﴿فَإِنَّهُمْ لَا يُكَذِّبُونَكَ وَلَٰكِنَّ الظَّالِمِينَ بِآيَاتِ اللَّهِ يَجْحَدُونَ﴾

“እነርሱም (በልቦቻቸው) አያስተባብሉህም። ግን በዳዮቹ በአላህ አንቀጾች ይክዳሉ።” (አል-አንዓም፡ 33)

ዘህሪይ የተሰኙት ዓሊም እንዲህ ይሉናል። አባጀህልና ከርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች አኽነስ ኢብን ሹረይቅን ጨምሮ በአንድ ወቅት በለሊት የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ.) ቂርኣት (የቁርኣን ንባብ) ያደምጡ ነበር። አኽነስ ኢብኑ ሹረይቅም ለአቡጀህል “አቡልሐከም ሆይ! ከሙሐመድ በሰማኸው ነገር ላይ ምን ትላለህ? በማለት ጠየቀው። አቡ ጀህልም “እኛና የዐብድ መናፍ ልጆች በክብር ጉዳይ ንትርክ ውስጥ ገባን። ሰዎችን አበሉ እኛም አበላን፤ ተሸከሙ እኛም ተሸከምን፣ ለገሱ እኛም ለገስን፣ በግልቢያ ጭምር ተወዳደርንና እኛ አሸነፍናቸው። እነርሱም “እኛ ከሰማይ ወሕይ (መለኮታዊ ራዕይ) የሚወርድለት ነቢይ አለን አሉ። ይህን ብናውቅ እንኳን በፍጹም አንሰማቸውም። በፍጹም አናምንላቸውም” አለ።

በሌላ ዘገባም “የሚለው ነገር እውነት እንደሆነ በርግጥ አውቃለሁ፤ ነገር ግን በኒ ቁሰይ ነድዋ የኛ ነው ሲሉ እኛም እሺ ብለን ተቀበልን። የመካ ኃላፊነት ተገቢነቱ ለኛ ነው ሲሉን ተቀበልን ፤ ሐጃጆችን ውሃ የምናጠጣው እኛ ነን ሲሉ እኛም እሺ ብለን ተቀበልን” በማለት ሌላም ተመሳሳይ ነገር አወሳ። (ታዲያ ይህ እስከመቼ እንደማለት ነው)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here