عَنْ ابْنِ مَسْعُودٍ رضي الله عنه قَال: قَال رَسُول اللهِ صلى الله عليه وسلم ‹‹لا يَحِل دَمُ امْرِئٍ مُسْلمٍ [يشهد أن لا إله إلا الله، وأني رسول الله] إلا بِإِحْدَى ثَلاثٍ: الثَّيِّبُ الزَّانِي، وَالنَّفْسُ بِالنَّفْسِ، وَالتَّارِكُ لدِينِهِ المُفَارِقُ للجَمَاعَةِ››.
رَوَاهُ البُخَارِيُّ وَمُسْلمٌ
ከኢብኑ መስዑድ ረ.ዐ. እንደተወራው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ‹‹ከሶስት ነገሮች አንዱን የፈፀመ እንደሆነ እንጂ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለና እኔም የአላህ መልእክተኛ መሆኔን የሚመሰክር የአንድን ሙስሊም ደም ማፍሰስ (መግደል) እርም ነው። አግብቶ የሚያውቅ ዝሙተኛ፣ ነፍስ ያጠፋ፣ እምነቱን የተወና ከጀመዓው ያፈነገጠ።›› (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።)
የሐዲሡ አስፈላጊነት
የአንድ ግለሰብ በህይወት መቆየቱ በማህበረሰቡ ህይወት ላይ የሚያስከትለው አደጋ ካሰጋ፣ ጤናው ተቃውሶ ከሰዎች ትክክለኛ ባህሪና አፈጣጠር ያፈነገጠ እንደሆነና የማህበረሰቡን ጤና የሚያውክ አደገኛ ተህዋስ፤ እምነታቸውን፣ መልካም ስነምግባራቸውንና ክብራቸውን የሚያበላሽ እንዲሁም አደገኛ ጥፋትንና ጥመትን የሚያስፋፋ ተባይ ከሆነ በዚህን ጊዜ የዚህ ሰው በህይወት የመኖር መብቱ ዋጋ ማጣት አለበት። በምድር ላይ መኖሩም አላስፈላጊ ይሆናል። ስለሆነም ኢስላማዊው ማህበረሰብ በሰላምና በደህንነት ይኖር ዘንድ እሱን ማስወገዱ ግድ ነው። በመሰረቱ የአንድ ሙስሊም ደም የተጠበቀ ቢሆንም ይህ ሐዲሥ እጅግ አሳሳቢ በሆነው ነገር ማለትም ከደም ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሐላል እና ሐላል ያልሆነውን የሚገልጽ በመሆኑ መሰረታዊና ከባድ ያደርገዋል።
የሐዲሡ ቃላት ትርጉም
- ‹‹የአንድም ደም ሐላል አይሆንም››፦ ሲባል ደም ማፍሰሱ አሊያም መግደሉ ማለት ነው
- ‹‹አግብቶ የሚያውቅ /ሠይብ/ ዝሙተኛ››፦ ሠይብ /አግብቶ የሚያውቅ/ ማለት ድንግል ያልሆነ ማለት ነው። ስያሜው ለወንድም ሆነ ለሴት ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ- አግብቶ የሚያውቅ /ድንግል ያልሆነ/ ወንድ፣ አግብታ የምታውቅ /ድንግል ያልሆነች/ ሴት ይባላል። ብዙን ጊዜ የሚባለው ግን ለሴቶች ነው።
- ዝሙተኛ፦ ማለት በቋንቋ ደረጃ ጋጠወጥ /አመፀኛ/ ማለት ሲሆን በሸሪዓ ድንጋጌ ደግሞ ወንድ ልጅ ያለ አንዳች ሸሪዓዊ ጋብቻ ከሴት ልጅ ጋር የሚፈጽመው የግብረስጋ ግንኙነት ነው።
- ‹‹ሃይማኖቱን የተወ››፦ ማለት እምነቱን ትቶ የወጣ ማለትም ከእስልምና ሃይማኖት ማለት ነው።
- ‹‹ከጀመዓው ያፈነገጠ››፦ ማለት እምነቱን በመለወጥ ከሙስሊም ጀመዓ ያፈነገጠ ማለት ነው።
የሐዲሡ አጠቃላይ ትርጉም
ከአላህ (ሱ.ወ) በስተቀር ሌላ አምላክ የሌለ መሆኑንና ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን የመሰከረና በአላህ መኖር አምኖ አንድ መሆኑንም የተቀበለ እንዲሁም የአላህ መልእክተኞች መቋጫ በሆኑት ነቢይ እውነተኛነት ያመነና መልእክታቸውንም የተቀበለ ማንኛውም ሰው ደሙ ተጠብቋል፣ ነፍሱም ድናለች፣ ህይወቱም ዋስትና ተሰጥቷታል። ህይወቱን ማጥፋትም ሆነ ደሙን ማፍሰስ ለአንድም ሰው አይፈቀድለትም። ከሚከተሉት ሶስት ወንጀሎች አንዱን እስካልፈፀመ ድረስም ይኸው ዋስትና ቀጣይ ሆኖ ይዘልቃል። እነርሱም
- ያለአግባብ ሆነ ብሎ ሰውን መግደል
- ካገቡ በኋላ ዝሙት መፈፀም እና
- ከእስልምና መውጣት ናቸው።
ሙስሊም ዑለማኦች እንዳሉት አንድ አግብቶ የሚያውቅ ሰው ዝሙት የፈጸመ እንደሆነ ተወግሮ ይገደላል። ለምን የተባለ እንደሆነ የሌሎችን ክብር የተጋፋ በመሆኑ ነው። አላህ (ሱ.ወ) በሐላል መንገድ በጋብቻ ሚስት ሰጥቶት እያለ ከጥሩ ነገር ወደ መጥፎ በማዘንበሉና በሰው መብት ላይ ወንጀል በመፈፀሙ እንዲሁም ዘርንና ትውልድን ለማበላሸት በማሰብ አስፀያፊ የሆነውን የዝሙት ድርጊት በመፈፀሙ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
‹‹ዝሙትንም አትቅረቡ። እሱ በርግጥ መጥፎ ሥራ ነው። መንገድነቱም ከፋ።›› (አል-ኢስራእ፤ 32)
-
አል ቂሳስ /ማመሳሰል/
አንድን ሙስሊም ሆነብሎ የገደለ ሰው መገደል እንዳለበት ሙስሊሞች ተስማምተውበታል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏልና፦ ‹‹በነርሱም ላይ በውስጧ ‹‹ነፍስ በነፍስ፣ ዐይንም በዐይን፣ አፍንጫም በአፍንጫ፣ ጆሮም በጆሮ፣ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)። ቁስሎችም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ፃፍን …›› (አል-ማኢደህ፤ 45)
ይህም የሆነው ሰዎች በሰላም እንዲኖሩ ታስቦ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦ ‹‹ባለ አዕምሮዎች ሆይ! በማመሳሰል ውስጥ ለናንተም ህይወት አለላችሁ።…›› (አል-በቀረህ፤ 179)
ሆኖም ግን የሟች ቤተሰቦች ይቅር ያሉ እንደሆነ ብቻ ገዳይን አለመግደል ሊቀር ይችላል።
-
ከእስልምና የመውጣት ድንጋጌ
አንድ ሰው ከእምነቱ የወጣ እንደሆነና በክህደቱም ከቀጠለና በተውባ /ንስሀ ገብቶ/ ወደ እስልምና እስካልተመለሰ ድረስ እንደሚገደል በሙስሊሞች መካከል ስምምነት አለ። ቡኻሪ እና ሌሎችም የሐዲሥ ዘጋቢዎች ኢብኑ ዐባስን ረ.ዐ በመጥቀስ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ሃይማኖቱን የለወጠን ሰው ግደሉ።›› ብለዋል።
-
ሶላትን የተወ
ሙስሊሞች እንደተስማሙበት አቋም ሶላትን ሆነ ብሎ የተወና ግዴታነቷንም ያልተቀበለ ሰው እንደካደና ከእምነቱ እንደወጣ ነው የሚቆጠረው። ግዴታ መሆኑን እያወቀ በተወ ሰው ጉዳይ ላይ ግን ዑለማኦች በአቋም ተለያይተውበታል። አብዛኞቹ ዑለማኦች ያሉት ግን ከድርጊቱ ተጽጽቶ ወደ አላህ እንዲመለስ ይደረጋል ካልሆነ በከሐዲነት ይገደላል። ኢማም አሕመድና አንዳንድ የማሊኪ መዝሀብ ተከታዮች ደግሞ በከሐዲነት ይገደላል። ብለዋል። ሐነፊያዎች ደግሞ እስኪሰግድ አሊያም በሞት እስኪለይለት ድረስ ይታሰራል ያሉ ሲሆን እስራቱንም በድብደባና በሌላም ነገር ማጠናከር ይቻላል ብለዋል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
‹‹ሰላትን በትክክል ስገዱ። ከአጋሪዎችም አትሁኑ።›› (አርሩም፤ 31) በሌላ የቁርኣን አንቀጽ ደግሞ
‹‹ቢፀፀቱ፣ ሶላትንም በትክክል ቢሰግዱ፣ ዘካንም ቢሰጡ በእምነት ወንድሞቻችሁ ናቸው።…›› (አትተውበህ፤ 11) ብሏል።
የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ደግሞ ‹‹በአንድ ሰውና በክህደት መካከል ያለው ሰላትን መተው ነው።›› ብለዋል። (ኢማም አሕመድ እና ሙስሊም ዘግበውታል።)
ከሐዲሡ የምናናገኛቸው ጠቃሚ ትምህርቶች
- ዲን ሲባል ብዙሃኑ ሙስሊም ጀመዓዎች/ሰብስብ/ ያሉበት መንገድ ነው።
- ከሙስሊም ሰብስብ ጋር በፅኑ መተሳሰርና ከነርሱ አለማፈንገጥ እንዳለብን
- ከነኚህ ሶስት ወንጀሎች ማለትም ከዝሙት፣ ከነፍስ ግድያና ከእምነት መውጣት መራቅና በዚህም ውስጥ ላለመውደቅ ማስጠንቀቅ
- ማህበረሰቡን በአላህ (ሱ.ወ) ፍራቻ ላይ ማሳደግ፤ በግልጽ ይሁን በስውር ድንበር ከማለፍ በፊት እሱ ያየኛል ይቆጣጠረኛል ብሎ ማሰብ
- በኢስላም ውስጥ የተደነገጉ ህግጋቶች ድንበሮች ናቸው። ከነሱ መጠንቀቅና እነሱንም መጠበቅ ያስፈልጋል።