የኢማን መሟላት ምልክት (አስራ ሶስተኛ ሐዲሥ)

0
413

عَنْ أَبِي حَمْزَةَ أَنَسِ بْنِ مَالكٍ رضي الله عنه خَادِمِ رَسُول اللهِ صلى الله عليه وسلم عَنْ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَال: “لا يُؤْمِنُ أَحَدُكُمْ حَتَّى يُحِبَّ لأَخِيهِ مَا يُحِبُّ لنَفْسِهِ”.

رَوَاهُ البُخَارِيُّ وَمُسْلمٌ

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አገልጋይ ከነበሩት አቢ ሐምዛ አነስ ኢብኑ ማሊክ ረ.ዐ. እንደተወራው የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ዉ. “አንዳችሁም አላመናችሁም ለራሱ የሚወደውን ነገር ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ።” ብለዋል።

የሐዲሡ ቃላቶች ትርጉም

  • ‹‹አላመናችሁም››፦ የተሟላ ኢማን ማለት ነው።
  • ‹‹አንዳችሁም››፦ እምነት አለኝ አሊያም ሙስሊም ነኝ የምትሉ
  • ‹‹ለወንድሙ››፦ ለሙስሊም ወንድሙና እህቱ። ወንድሙ ለሆነው ለሰው ልጅ በሙሉም ሊሆን ይችላል።
  • ‹‹ለራሱ የሚወደውን ነገር››፦ ለራሱ የሚወደውን ማንኛውንም መልካም ነገር ሁሉ

የሐዲሡ አጠቃላይ ትርጉም

  1. ሙስሊሙ ማህበረሰብ በኢስላም ዙሪያ መዋደድና መተሳሰሰር እንዳለበት

እስልምና የሰው ልጆች በሙሉ ተዋደውና ተከባብረው እንዲኖሩና እያንዳንዱ ሰውም ለሁሉም የጋራ ጥቅምና ደስተኛ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚተጋ እንዲሆን ይፈልጋል። ይህ ሲሆን ፍትህ ይነግሳል። በነፍሶች ውስጥም እርጋታ ይስፋፋል። በመካከላቸውም መተጋጋዝና አብሮነት ይሰፍናል። ይህ ሁሉ ሊረጋገጥ የሚችለው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ የሚመኘውን ደስታ፣ መልካም ነገርና ፀጋ ለሌሎችም የተመኘ እንደሆነ ነው። ለዚህም ነው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ጉዳይ ከኢማን ጋር ያያዙትና የኢማን መገለጫ ምልክትም ያደረጉት።

  1. የተሟላ ኢማን

ኢማን በመሰረቱ ሊረጋገጥ የሚችለው እውነተኛ በሆነ ቁርጠኛ ቀልብ ሲረጋገጥና የሀያሉንና የተከበረውን አላህን ጌትነት ሌሎችንም የእስልምናና የኢማን ማእዘናት ማለትም በመላእክት ማመን፣ በመፃህፍት ማመን፣ በመልእክተኞች ማመን፣ በመጨረሻው ቀን ማመንና በአላህ የቀደመ ፍርድና ውሳኔ ማመንን (ቀዷና ቀደር) ሲቀበል ነው። ኢማን ሊቆም የሚችለው በነኚህ ማዕዘናት ላይ ነው። በዚህ ሐዲሥ ውስጥ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የኢማን ስሩ በነፍስ ውስጥ ሊሰርጽ የሚችለው፤ በቀልብ ውስጥም ቦታ የሚያገኘውና በሙስሊም ልብ ውስጥም ሊሟላ የሚችለው ሰውዬው የመልካም ስራ ባለቤት በመሆን ከራስ ወዳድነት፣ ከምቀኝነትና ከጥላቻ ሲርቅ እንደሆነ ገልፀውልናል። በአንድ ሙስሊም ውስጥ ይህን ምሉእነት ሊያረጋግጡ ከሚችሉ ነገሮች መካከል፦

  • ለራሱ የሚወዳቸውን መልካምና የተፈቀዱ ነገሮችን እንዲሁም የአምልኮ ተግባራትን ለሌሎችም ሲወድ፤ ለራሱ የሚጠላቸውን መጥፎና ሀጢኣት የሆኑ ነገሮችን ለሌሎችም በመጥላት
  • ግዴታ በተደረጉበት ነገሮች ላይ ጉድለት አሊያም በሃይማኖቱ ጉዳይ እንከን ያገኘበት እንደሆነ ሙስሊም ወንድሙ ይስተካከል ዘንድ በመጣር ይገኙበታል።

ሙስሊም እንደዘገቡት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ከእሳት እንዲርቅ እንዲደረግና ጀነት መግባት የፈለገ ሰው በአላህና በመጨረሻው ቀን አማኝ ሆኖ ሳለ ሞቱ ይምጣበት። ሰዎች እንዲያደርጉለት የሚወደውን ነገርም ለሰዎች ያድርግ።››

የአንድ ሙስሊም ኢማን የተሟላ ስለመሆኑ ከሚያመላክቱ ነገሮች መካከል አንድ ሰው ለሌላው ሰው መልካም ከመውደድ አለመቆጠብና በተለይ ትልቁን ነገር እምነትን ሌላው ቀርቶ ሙስሊም ያልሆነ ሰው እንዲሰልምና እንዲያምን መመኘት እንዲሁም ክህደትንና አመፀኝነትን ለሱ መጥላት ነው። የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ዉ. እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹ለራስህ የምትወደውን ነገር ለሰዎች ውደድ ሙስሊም ትሆናለህ።›› (ቲርሚዚይ ዘግበውታል።)

ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ) ከሀዲያንን ቀናውን ይመራቸው ዘንድ ዱዓእ ማድረግ ተወዳጅ ድርጊት ነው የሚባለው።

በዚህ ሐዲሥ ላይ እንዳየነው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እያንዳንዱ ሙስሊም ለሰዎች መልካምን ነገር ይወድ ዘንድ አነሳስተዋል። ይህም ኢማኑ የእውነት ስለመሆኑና እስልምናውም ለመስተካከሉ ማሳያ ከሱ የሚታይ ማስረጃ ነው። በዚህ መልኩ ውዴታ በሰው ልጆች መካከል ይስፋፋል፤ መልካም ነገርም በመካከላቸው ይሰራጫል።

ከሐዲሡ የምናገኛቸው ጠቃሚ ትምህርቶች

  • የሰዎችን ቀልብ ለመያዝ ማነሳሳት፤ ሁኔታቸውን ለማሳመር መስራት። ይህም ኢስላም ይዞት የመጣውና የሚተጋለት ትልቅ ዓላማ ነው።
  • ከምቀኝነት ማስጠንቀቅ። ምቀኝነት ከተሟላ እምነት ጋር ተፃራሪ ነውና። ምቀኛ ሰው አንድም ሰው በመልካም ነገር እንዲበልጠው አሊያም እንዲስተካከለው አይፈልግም። እንዲያውም እሱ ዘንድ ሳይደርስ መልካም ነገሩ እንዲጠፋበት ይመኛል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here