ጠቃሚ በሆነ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ (አሥራ ሁለተኛ ሐዲሥ)

0
429

عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ رضي الله عنه قَال: قَال رَسُول اللهِ صلى الله عليه وسلم “مِنْ حُسْنِ إسْلامِ المَرْءِ تَرْكُهُ مَا لا يَعْنِيهِ”.

حَدِيثٌ حَسَنٌ رَوَاهُ التِّرْمِذِيُّ ابن ماجه

ከአቢ ሁረይራ ረ.ዐ. እንደተወራው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “የአንድ ሰው እስልምና ማማሩ ምልክት የማይመለከተውን ነገር መተዉ ነው።” ብለዋል።

የሐዲሡ አስፈላጊነት

ኢብኑ ረጀብ አልሐንበሊይ “ይህ ሐዲሥ ከመሰረታዊ የሥነምግባር አስተምህሮዎች መካከል ዋንኛውና ትልቁ ነው።” ብለዋል።

የሐዲሡ ቃላቶች ትርጉም

  • ‹‹የአንድ ሰው እስልምና ማማሩ ምልክት››፦ ማለት እስልምናው መስተካከሉና መሟላቱ እንዲሁም የኢማኑ እውነተኛ መሆን ምልክቱ ማለት ሲሆን ‹‹ሰው›› ስንል ደግሞ ወንዱንም ሆነ ሴቱን ጭምር ያጠቃልላል።
  • ‹‹የማይመለከተው ነገር››፦ ማለት ከሃይማኖቱም ሆነ ከዓለማዊ ጉዳዮች የማያስፈልገው የሆነውን ማለት ነው።

የሐዲሡ አጠቃላይ ትርጉም

እስልምና ለማህበረሰቡ ደህንነት በእጅጉ የሚጨነቅ ሃይማኖት ነው። ሰዎች በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲኖሩ ይፈልጋል። በመካከላቸው ውዝግብና ጭቅጭቅ እንዲፈጠር አይሻም። ከዚህም አልፎ ለያንዳንዱ ግለሰብ ደህንነት ያስባል። ማንኛውም ግለሰብ በዚህች ምድር ላይ ሲኖር ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ይሻል። የሚወድ የሚወደድ፣ የሚከበር ሌሎች የማያስቸግሩት ሆኖ ከሷም ስኬታማና አትራፊ ሆኖ እንዲለቅ ይፈልጋል። አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች መካከል ልዩነትን የሚያመጣው፤ የማህበረሰቡንም ትስስር የሚያበላሸውና ሰዎችንም ጥፋት ውስጥ የሚከተው አንደኛው በሌላኛው ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ነው። በተለይ በማይመለከታቸው ነገሮች ውስጥ። ለዚህም ነው እስልምና አንድ ሰው በማያገባው የሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መግባት መተውን ለአንድ ሰው እስልምና ላይ ቀጥ የማለትና የእውነተኛ ኢማን ባለቤት ስለመሆኑ ምልክት አድርጎ ያቀረበው።

ሙስሊም የሆነ ሰው በሚሰራቸው ነገሮች ላይ ሁሉ ተጠያቂ ነው። አንድ ሙስሊም በዙሪያው ባሉት ነገሮች ሁሉ ከተወጠረና በማያገባው ነገሮች ውስጥም ጭምር የሚገባ ከሆነ ይህ ሁኔታው የራሱን ግዴታዎች ከመፈፀም ያዘናጋዋል። ሀላፊነቱንም ከመወጣት ያግደዋል። በዚህም ምክንያት በዚህች ዓለምም ሆነ በመጨረሻው ዓለም ተጠያቂና ለቅጣት የሚዳረግ ይሆናል። በርግጥም ይህን ማድረጉ የእይታውን ደካማነት ያሳያል። ነቢያዊውንም ባህሪ በራሱ ላይ አለማንፀባረቁን ያመላክታል። ኢብኑ ሒባን በሶሒሕ መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳወሩት አቢ ዘር ረ.ዐ. “ለአንድ ሰው ክፋት ምልክቱ ራሱ ያለበትን ችግር ዘንግቶ በማያገባው ነገር ውስጥ ገብቶ መጨናነቁ በቂ ነው።” ብለዋል።

አንድ ሙስሊም ግዴታውን ያወቀ እንደሆነ፤ ሀላፊነቱንም በትክክል ከተረዳ በዚህን ጊዜ በራሱ ጉዳዮች ብቻ የሚወጠር ይሆናል። በዚህችም ሆነ በመጨረሻው ዓለም ሊጠቅሙት በሚችሉ ነገሮች ላይ ይበረታል። ከትርፍ አላስፈላጊ ነገሮችም ይርቃል። ከተራ ነገሮችም ከፍ ይላል። ወደሚመለከቱት ነገሮችና ጉዳዮችም ፊቱን ያዞራል።

ሀያሉንና የተከበረውን አላህን ልክ እንደሚያየው አድርጎ የሚያመልክና አላህ (ሱ.ወ) ለሱ ቅርብ፤ እሱም ለአላህ (ሱ.ወ) ቅርብ መሆኑን በውስጡ የተረዳ አንድ ሙስሊም ይህ ሁኔታ ከማይመለከተው ነገር እንዲቆጠብ ያደርገዋል። የማይመለከተው ነገር ውስጥ አለመግባቱ ደግሞ ከአላህ (ሱ.ወ) ጋር ያለውን እውነተኛትና እሱም የሚቆጣጠረው መሆኑን እንዳወቀ ማሳያ ነው። በማይመለከተው ነገር ላይ አትኩሮ የሚሰራ ሰው አላህ (ሱ.ወ) ለሱ ቅርብ መሆኑን አልተረዳም። ከሱ ጋርም እውነተኛ መሆን አልቻለም። ስራውም የተበላሸ ሲሆን ከከሳሪዎች መካከልም ነው የሚሆነው።

ከአልሐሰን አልበስሪ እንደተወራው እንዲህ ብለዋል፦ “ከአላህ (ሱ.ወ) የመራቅ ምልክቶች መካከል አንድ ሰው በማይመለከተው ነገር ራሱን መወጠሩ ነው።”

አንድን ሰው የሚመለከተውና የማይመለከተው ነገር

ከሚመለከተው ነገር ውስጥ ለምሳሌ፦ በኑሮው ውስጥ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ማለትም ከምግብ፣ ከመጠጥ እና ከመጠለያ ጋር የተያያዙ ነገሮችና የመሳሰሉት ሲሆኑ በዚህም ሆነ በመጨረሻው ዓለም ደህንነቱን ሊያስጠብቁለት የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ከነኚህ ውጭ ያሉ ነገሮች በማይመለከቱት ነገሮች ውስጥ ይካተታሉ።

አንድን ሰው ከማይመለከቱ ነገሮች መካከል፦ ትርፍ የሆኑ ዓለማዊ ጥቅሞች ለምሳሌ ለዚህ ዓለም ጥቅም ብቻ መኖር፣ በምግብም ሆነ በመጠጥ ጉዳይ ከሚገባው በላይ ዓይነቶችን በማብዛት መጨናነቅ፣ ለጉራና ለማስመሰል ሲባል በተለይ ደግሞ ዲንን ሽፋን በማድረግ ለስልጣን መጓጋትና ሹመትን መፈለግን የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።

በማይመለከት ነገር ውስጥ በመግባት የሚደረግ ትርፍ ንግግር አንድን ሙስሊም ወደ ሐራም ንግግር ሊመራው ይችላል። በመሆኑም በሁሉም አሉባልታዎች ውስጥ በመግባት ማውራትና ማቡካት የአንድ ሙስሊም ባህሪ አይደለም። አትቲርሚዚ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “የአደም ልጅ ንግግር ለሱ ሳይሆን በሱ ላይ ነው። በመልካም ማዘዝ፣ ከመጥፎ መከልከልና የልዕልና ባለቤት የሆነውን አላህን ማውሳት ሲቀር።” ብለዋል።

ከሐዲሡ የምናገኛቸው ጠቃሚ ትምህርቶች

  • በላቁና ምርጥ በሆኑ ነገሮች ራስን መወጠር፣ ከተራና ርካሽ ውዳቂ ነገሮች መራቅ የሙስሊም ባህሪ መሆኑን
  • ከርካሽና አስነዋሪ ነገሮች ትርቅ ዘንድ ነፍስን ማግራትና ማሰልጠን እንዲሁም ፋይዳ ከሌላቸው ጥቅም አልባ ነገሮች መራቅ እንዳለብን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here