እርግጠኛ የሆኑበትን ነገር መያዝና ከአጠራጣሪ ነገሮች መራቅ (አሥራ አንደኛ ሐዲሥ)

0
356


عَنْ أَبِي مُحَمَّدٍ الحَسَنِ بْنِ عَليِّ بْنِ أَبِي طَالبٍ سِبْطِ رَسُول اللهِ صلى الله عليه وسلم وَرَيْحَانَتِهِ رَضِيَ اللهُ عَنْهُمَا، قَال: حَفِظْت مِنْ رَسُول اللهِ صلى الله عليه وسلم “دَعْ مَا يُرِيبُك إلى مَا لا يُرِيبُك”.

رَوَاهُ التِّرْمِذِيُّ وَالنَّسَائِيّ وَقَال التِّرْمِذِيُّ: حَدِيثٌ حَسَنٌ صَحِيحٌ.

ከአቢ ሙሐመድ አልሐሰን ኢብኑ ዐሊይ ኢብኑ አቢጣሊብ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የልጃቸው ልጅ እና ተወዳጃቸው ረ.ዐ. ከሆኑት እንደተወራው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “የሚያጠራጥረውን ነገር በመተው ወደማያጠራጥርህ ነገር አዘንብል።” ብለዋል። (ቲርሚዚይ እና ነሳኢ ዘግበውታል።)

የሐዲሡ ቃላት ትርጉም

  • ‹‹የሚያጠራጥርህን ነገር ተው››፦ ሐላል ሐራምነቱ ግልጽ ያልሆነውንና የተጠራጠርክበትን አሻሚ የሆነ ነገር ተው።
  • ‹‹ወደማያጠራጥርህ ነገር አዝንብል››፦ ወደማያጠራጥረውና ሐላልነቱ (መፈቀዱ) ግልጽ ወደሆነው ነገር ተመለሰ

የሐዲሡ አጠቃላይ ትርጉም

በአምልኮ ስራዎች፣ በስራ ግንኙነት፣ በጋብቻ ጉዳዮችና በሌሎችም ድንጋጌዎች ውስጥ አጠራጣሪን ነገሮች መተውና በሐላል ነገሮች ላይ መፅናት አንድን ሙስሊም ወደ አላህ ፍራቻ መንገድ ይመራዋል። ከዚህ ቀደም በስድስተኛው ሐዲሥ ላይ እንዳየነው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከአጣራጣሪ ነገሮች የተጠነቀቀ ሰው ለሃይማኖቱም ሆነ ለክብሩ ነፃ ወጣ /ክብሩን ጠበቀ/ ማለታቸውን አይተናል። ሐላልነቱ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር በሙስሊም ቀልብ ውስጥ አንዳችም ጥርጣሬ የሚጥል አይደለም። አጠራጣሪ ነገሮችን ግን አንድ ሰው እላዩን ሲታይ የወደደ ሊመስል ይችላል። ቀልቡን ከፍተን የማየት አቅሙ ቢኖረን ግን ውስጡ በሀሳብ፣ ባለመረጋጋትና በጥርጣሬ የተሞላ ሆኖ እናገኛለን። ለውስጣዊ ኪሳራም የዚህ ዓይነቱ የነፍስ ቃጠሎ ብቻውን በቂ ነው። ትልቁ ኪሳራና አደገኛው ጥፋት ደግሞ አጠራጣሪ ነገሮችን መላመድና በዚያውም በመቀጠል ሐራምን እስከመዳፈር መድረስ ነው። በጥብቅ ማሳ ዙሪያ ከብቶቹን የሚጠብቅ እረኛ አንድ ቀን ወደማሳው መግባቱ አይቀርም።

የጥርጣሬና የየቂን /እርግጠኛነት/ መጋጨት

ጥርጣሬ ከርግጠኛነት ጋር የተጋጨብን እንደሆነ እርግጠኛ የሆንበትን ነገር በመያዝና በማስቀደም ለአጠራጣሪው ነገር ጀርባ መስጠት ይኖርብናል። ግልጽ በሆኑ ሐራም ነገሮች ውስጥ የሚንቦጫረቅና ከተወሰኑ አጠራጣሪ ነገሮች መጠንቀቅ የሚፈልግ ሰው የሱ ጥንቃቄ የማካበድና የበደልም ጭምር ነው። ይህንን ድርጊቱንም በማውገዝ በቅድሚያ ግልጽ ከሆነው ሐራም እንዲታቀብ ልንመክረው ይገባል። ለዚህም ነው ኢብኑ ዑመር ረ.ዐ. የዒራቅ ሰዎች ስለ ትንኝ ደም በጠየቋቸው ጊዜ “ሑሴንን ያህል ታላቅ ሰው ገድለው እያለ ስለ ትንኝ ደም ይጠይቁኛልን?:: ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እኮ “እነርሱ (ሐሰንና ሑሴን) የዚህች ዓለም ተወዳጆቼ ናቸው።” ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ።” ያሉት። (ቡኻሪ ዘግበውታል።)

እውነት እርጋታ ሲሆን ውሸት ደግሞ ማወላወል ነው

የእውነት ምልክቱ ቀልብ በዚያ ነገር ላይ መርጋቱ ነው። የውሸት ምልክቱ ደግሞ በጥርጣሬ መሞላቱ ሲሆን ቀልብም እርጋታ አይኖረውም። ባይሆን ከዚያ ነገር ጋር ለመስማማት ያቅተዋል።

ሐዲሡ የሚያመላክተን

የምንመራባቸውን ህግጋትንና አጠቃላይ የህይወት ጉዳዮቻችንን በእርግጠኛነት ላይ እንድንገባ ነው። ሐላል ነገር፣ እውነት እና እርጋታ የውስጥ ውዴታና ቅበላ ሲሆን ሐራም ነገር፣ አልባሌ እና ውሸት ደግሞ ጥርጣሬ ጭንቀትና ሰላም ማጣት ነው። ሐዲሡ ከዚህም በተጨማሪ አላህን (ሱ.ወ) እንድንፈራና አጠራጣሪ የሆነን ነገር እንድንተው ያነሳሳናል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here