ማግራራትና አለማክረር (ዘጠነኛው ሀዲስ)

0
235

عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ عَبْدِ الرَّحْمَنِ بْنِ صَخْرٍ رضي الله عنه قَال: سَمِعْت رَسُول اللهِ صلى الله عليه وسلم يَقُول: “مَا نَهَيْتُكُمْ عَنْهُ فَاجْتَنِبُوهُ، وَمَا أَمَرْتُكُمْ بِهِ فَأْتُوا مِنْهُ مَا اسْتَطَعْتُمْ، فَإِنَّمَا أَهْلكَ الذِينَ مِنْ قَبْلكُمْ كَثْرَةُ مَسَائِلهِمْ وَاخْتِلافُهُمْ عَلى أَنْبِيَائِهِمْ “.

رَوَاهُ الْبُخَارِيُّ وَمُسْلِمٌ.

አቢሁረይራ (ረ.ዐ) አብዱረህማን ኢብን ሰኽር እንዲህ አሉ፡-‹‹“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ሰምቻለሁ፦ “የከለከላችሁን ነገር ተጠንቀቁ ያዘዝኳችሁን የቻላችሁትን ያህል ፈፅሙ። ከእናንተ በፊት የነበሩ ሠዎችን ያጠፋቸው ጥያቄ ማብዛታቸውንና ከነቢያቶቻቸው ጋር መለያየታቸው ነው።›› (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የሀዲሱ አሳሳቢነት

ይህ ሃዲስ ብዙ አሳሳቢ ትምህርቶችን የሚሰጥ ሀዲስ ነው። ልትጠብቀውና ብዙ ጥናትም ልታደርግበት ይገባል።ከታላላቅ የእስልምና መሠረቶች አንዱ ነው። የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከተሰጣቸው ጀዋሚዑል ከሊም ውስጥም አንዱ ነው።በውስጡ ተዘርዝረውየማያልቁ ብዙ ህግጋት ይጠቃለላሉ። ሀዲሱ ከታላላቅ የዲንመሰረቶች እና የኢስላም መርሆች አንጻር እጅግ ትልቅ ነው። ይህን መሸምደድ እና ትኩረት መስጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው።

ሀዲሱ የተነገረበት ሰበብ

ይህ ሃዲስ የተነገረበትን ሰበብ ሙስሊም ከአቡረይራ (ረ.ዐ) እንዲህ ዘግበውታል። “የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዲስኩር (ኹጥባ) ለማድረግ ከመሀላችን ቆሙ። እንዲህም አሉ “ሰዎች ሆይ! አሏህ በእናንተ ላይ ሀጅን ግድ አድርጓል ሀጅ አድርጉ።” አንድ ሰው ከመሃል ተነሳና እንዲህ አለ “በየአመቱ ነውን?” መልእክተኛውም ዝም አሉ። ሰውየውም ሦስት ጊዜ ጥያቄውን ደጋገመው።የአሏህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ “አዎን ብል ኖሮ ግዴታ ይሆን ነበር፤ እናንተም መፈጸሙን አትችሉም ነበር።” ከዚያም እንዲህ አሉ “የተውኳችሁን ተዉኝ ከናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የጠፉት ጥያቄ በማብዛታቸውና ነቢያቶቻቸውን በመንቀፋቸው ነው። አንዳች ነገር ባዘዝኳችሁ ጊዜ የቻላችሁትን ያህል ፈጽሙ፤ ከከለከልኳችሁም ሙሉ በሙሉራቁ።በአንዳንድ ዘገባዎች ላይም እንደተነገረው ጠያቂው አቅረዕ ኢብኑ ሃሲብ (ረ.ዐ) ነበር።

የቃላቶችና ሐረጎች ፍቺዎች

  • ‹‹የከለከልኳችሁን››፡- እንድትተውት ያዘዝኳችሁን ተግባር
  • ‹‹“ነህይ››፡- ክልክል
  • ‹‹ራቁ››፡- ተዉት
  • ‹‹የቻላችሁትን››፡- ችግር ውስጥ ሳትወድቁ መተግበር የቻላችሁትን
  • ‹‹“ያጠፋቸው››፡- የጥፋታቸው ሰበብ የሆነው
  • ‹‹ጥያቄዎችን ማብዛታቸው››፡- ከጉዳያቸው የማይገናኝ፤ አስፈላጊነት የሌለው ብዙ ጥያቄ

ጥቅል ትርጓሜ

1. የከለከልኳችሁን ተከልከሉ

ክልክልነት በአላህ መጽሀፍ እና በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሀዲስ ላይ ለተለያዩ ጥቅሞች ሲውል እንመለከታለን። እዚህ ሀዲስ ላይ ክልክል በማለት ለመግለጽ የተፈለገው በእስላም እርም የሆነውንና የተጠላውን ተግባር ነው።

2. እርም የሆነ እግድ (ክልከላ)

የዚህ የክልከላ አይነት ምሳሌዎች ዝሙት፤ አልኮል መጠጣት፤ ወለድ መብላት፤ ስርቆትና ነፍስን ከአግባብ ውጪ ማጥፋትን መከልከል ናቸው።እነዚህን የመሳሰሉ መከልከሎችን በአንድ ጊዜ ማቆም ግዴታ ነው። ለጥያቄ የደረሰ፤ አእምሮው ጤናማ የሆነና ህፃን ያልሆነ ሰው ይህን ተግባር መፈፀም አይፈቀድለትም በወንጀልነትም ያስቀጣዋል። እነዚህን ተግባሮች ለመፈፀም ከባድ ችግር ያስገደደው እንደሆነ ግን ፍጹም ቀጥ ያለው የአላህ ሸሪዓ ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎችና አጥሮች መሰረት ብቻ ቢፈጽማቸው ወንጀል አይሆንበትም። (ምክንያቱም ተገዶና ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ስለሆነ)።

3. የመጥላት እገዳ (ክልከላ)

የዚህ እገዳ ምሳሌዎች ከሚሆኑት ጉዳዬች ውስጥ የጀመዓ ሰላት ለሚመጣ ሰው ሽንኩርት መብላት መከለከሉ ይጠቀሳል። ችግር ቢኖርም ባይኖርም እነኚህን እግዶች መስራት ይፈቀዳል። ነገር ግን ትኩረት የሚሰጠው አንድን ሙስሊም የሚያስከብረውና የሚያልቀው ነገር ከነዚህ ነገሮች መራቁና መጠንቀቁ ነው።

4. ክልክል ነገሮች መራቅና የርከሠትን ስር በማስወገድ (በመንቀል) ላይ ማክረር

የአላህ ሸሪአ ሁሌም ምድራዊው ስርኣት ላይ ርክሠት እንዳይኖር ለማገድ ይተጋል። የርከሠት ዘር እንዲሠክንም ይታገላል። ስለዚህም ነው ክልክል ነገሮች ላይ የሚያደርገው ትኩረት ትእዛዛት ላይ ከሚያደረገው ትኩረት የጠነከረ ሆኖ የምንመለከተው። ይህ ማለት ትእዛዝ ላይ ቸልተኝነት አለ ማለት ግን አይደለም። ክልክል ነገሮች ላይ መራቅ እንደሚገባ የሚያደርገው ቅስቀሳ ትአዛዛት ላይ ከሚደረገው ይለያል። በተለይም እርም የሆኑ ነገሮች ላይ ፍጹም ክልከላን ያበጃል። ምክንያቱም የሚከለከለው ነገር ላይ ግልጽ የሆነ ብክለት መኖሩ የተረጋገጡ በመሆናቸው የተከለከሉ ናቸው። ስለዚህ ማንም ሠው ክልክልን እንዲፈፅም ምንም ምክንያት አይሠጠውም።

ከላይ በተጠቀሰው ማብራሪያ ዙሪያ የብዙ ሙስሊሞች የአካሄድ ችግር ይገለፃል። በተለይም በዚህ ዘመን በአብዛሃኛው የህይወት ተግባሮቻቸው ላይ መጋጨትን ትመለከታለህ። የአሏህን ትእዛዝ ለመፈፀምና ግዴታቸውን ለማድረስ ሲተጉ ይስተዋላል፤ አንዳንዴም ግዴታ ባልሆኑና ተወዳጅ ስራዎች ላይ የሙጥኝ ብለው ታገኛቸዋለህ። ይህ የተወደደ ቢሆንም በዛው ልክ ግን ክልክል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሲዘናጉ መመልከት አዲስ አይደለም። ከዚህም ብሶ ከባድ ወንጀሎች ውስጥም ይዘፈቃሉ። ጾመኛን በሪባ ሲገበያይ፤ ሀጅና ዘካ ላይ የበረታችው ሴት ያለ ሂጃብ ስትጓዝ መመልከት ዘመነኝነት እስኪመስል በርክቷል።

ይህ ግን የአላህ ሸሪአ ካስከመጠው ውጭ ነው። የኢስላም የአምልኮት መሰረቱ አላህ እርም ያደረገውን መራቅ ነው። የመዳን መንገድም ነፍስንና መጥፎ ዝንባሌን ወይም ሀዋእን መታገል ነው። የዚህ ደሞዝ ደግሞ አብዛኛውን ግዴታን በመፈጸም ከሚገኘው ምንዳ በላይ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፤

‹‹እርምን ተጠንቀቅ ከሰዎች መሀል ይበልጥ አላህን የምታመልክ ትሆናለህ።›› ቲርሚዝይ ዘግበውታል።

አኢሻም(ረ.ዓ.) እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹ታጋይ ሙጃሂድን (በደረጃ) መቅደም የሚፈልግ ካለ ከወንጀል ይራቅ።››

ዑመርም (ረ.ዐ.) ሀጢያትን የሚሹ ግን ስለማይሰሯት ሰዎች ተጠይቀው እንዲህ አሉ፦ ‹‹እነዚህ አላህ ልባቸውን ለተቅዋ ያዘጋጃቸው ናቸው። ምህረትና ታላቅ ምንዳ አለላቸው።››በማለት መልሰዋል።

ዑመር ኢኑ ዓብዱል ዓዚዝ (ረ.ዐ.) እንዲህ አሉ። ‹‹ተቅዋ ማለት ሌሊቱን መቆም ቀኑን በጾም መዋል ከዚያም በመሀል ወንጀልን መቀላቀል አይደለም፤ ነገር ግን ተቅዋ አላህ ያዘዘውን መፈጸም የከለውን መከልከል ነው። ከዚህ በኋላ ሌሎች ትርፍ ሥራዎች ካሉ መልካም ላይ መልካም ላይ እንደ መጨመር ነው።››

ቀደምት ህዝቦች የጠፉባቸው ምክንያቶች

የተከበሩት የአላህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ቀደምት ህዝቦች ከጠፉባቸው፤ ኃይላቸውን ያደከሙባቸው፤ አንዳንዴም ሁሉን የሚያጠቃልል ቅጣት የተቀጡባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ሁለቱ ነገሮች እንደሆኑ ገልፀዋል። አንደኛው አላስፈጊና ፋይዳ ቢስ ጥያቄዎችን ማብዛት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትእዛዛትን መንቀፍ እና የአላህን ድንጋጌዎች አለመፈጸም ናቸው።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሰሀቦቻቸውን በሙሉ ጥያቄ ማብዛትን ከልክለዋል። የከለከሉበትም ምክንያት ግዴታዎች እንዳይበዛባቸው በመስጋት ነው። በከንቱ ነገር ከመጠመድና በማይረቡ ነገሮች ከመዋከብ ለማቀብም ነው። ጥቅም የሌለውን ነገር መጠየቅ ባይጐዳም እንኳ የተጠላ ነገር ነው። ከሙጊራ ኢብኑ ሹዕባ ቡኻሪይ እንደዘገቡት ‹‹የአላህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) አሉባልታን፤ ጥያቄ ማብዛትን እና ገንዘብ ማባከንን ከልክለዋል።››

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here