የወሕይ መጀመር

0
1131

ኢማም አል-ቡኻሪ ከእመት ዓኢሻ (ረ.ዐ) የወሕይ አጀማመር እንዴት እንደነበር የገለጹበትን ዘገባ ዘግበዋል፡፡ ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) (ከወሕይ) የጀመራቸው መልካም ሕልሞችን በእንቅልፋቸው መመልከት ነው፡፡ ልክ እንደ ንጋት ጎህ ሆና የምትከሰት ብትሆን እንጂ ሕልም አያዩም ነበር፡፡ መገለልን ወደዱ፡፡ በሒራእ ዋሻ ውስጥ ብቻቸውን ለዚህ የሚሆን ስንቅን ለመሰነቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሳይመለሱ ብዙ ሌሊቶችን ያሳልፉ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ኸዲጃ (ረ.ዐ) ይመለሱና ስንቅ ይሰንቃሉ፡፡በሒራእ ዋሻ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከጌታቸው የሆነው እውነት እስከመጣላቸው ድረስ ቀጥለው ነበር፡፡››

መልአክ መጥቶ “አንብብ” አላቸው፡፡ ‹እኔ አንባቢ አይደለሁም› በማለት መለሱ፡፡በጣም እስክደክም ድረስ ጭምቅ አደረገኝና ለቀቀኝ፡፡ እንደገና ‹አንብብ› አለኝ፡፡ ‹እኔ አንባቢ አይደለሁም› ስል መለስኩኝ ፡፡ ይዞኝ በድጋሚ በጣም እስክደክም ድረስ ጭምቅ አድርጎኝ ለቀቀኝና ‹አንብብ አለኝ› እኔም ‹አንባቢ አይደለሁም› አልኩት፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ በጣም እስክደክም ድረስ ጨምቆ ለቀቀኝና እንዲህ በማለት ተናገረኝ፡-

اقْرَأْ بِاسْمِ رَبِّكَ الَّذِي خَلَقَ

“አንብብ፥ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም፡፡ ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)፡፡አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲኾን፤ያ በብርዕ ያስተማረ፤ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን፡፡” (አል-ዐለቅ፡ 1-5)

አላህ በፍፁም የማያዋርዳቸው ሰዎች ባሕሪያት

የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ልባቸው በጣም እየመታና እየተርገፈገፉ ወደ ባለቤታቸው ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ (ረ.ዐ)ዘንድ ተመለሱ፡፡ ‹አከናንቡኝ፤ አከናንቡኝ› አሉ፡፡ የያዛቸው ፍርሃት እስኪለቃቸው ድረስ አከናነቧቸው፡፡ ለኸዲጃ(ረ.ዐ) ክስተቱን ሁሉ እንዲህ በማለት ነገሯቸው፡፡ “በእርግጥ እኔ ለነፍሴ ፈራሁ!”ኸድጃም (ረ.ዐ) “በፍፁም! በአላህ እምላለሁ! አላህ በጭራሽ አያዋርድህም አንተኮ ዝምድናን የምትቀጥል፤ የተቸገረን የምትረዳ፤ እንግዳን የምታከብር፤ ለሌላቸው ሰጪና ሐቅ ላይ የምትተባበር ነህ፡፡” አለቻቸው፡፡

የአዋቂ ምስክርነትና ቀደሞች ፈለግ

ኸዲጃ (ረ.ዐ) ነቢያችንን ወደ ወረቀት-ኢብኑ ነውፈል ዘንድ ወሰደቻቸው፡፡ ወረቀት ኢብኑ ነውፈል የኸድጃ አጎት ልጅ ሲሆን በጃሂሊያው ዘመን ክርስትናን የተቀበለ ሰው ነው፡፡ ከወንጌልም አላህ የፈለገለትን በኢብራይስጥ ቋንቋ ይፅፍ ነበር፡፡ከእርጅናም ብዛት ዓይኑ ታውሮ ነበር፡፡ ኸዲጃም(ረ.ዐ) “የወንድሜ ልጅ ሆይ! እስቲ የወንድምህ ልጅ የሚልህን ስማ፡፡” አለችው፡፡ ወረቀትም ለአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የወንድሜ ልጅ ሆይ ምንድነው የሚታይህ በማለት ጠየቃቸው፡፡

የአላህ መልዕክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) የታያቸውን ነገር ነገሩት፡፡ ወረቀትም፣ ‹‹ይህማ በሙሳ (ዐ.ሰ) ላይ የወረደው ሕግ ነው (ጂብሪል ወይም ወሕይ)፡፡››

ዋ! ጠንካራ ወጣት ሆኜ በነበር! ዋ! ያኔ ወገኖችህ ከሀገርህ ሲያስወጡህ በሕይወት ኖሬ በነበር!›› አለ፡፡ የአላህ መልዕክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹እውን ያስወጡኛልን?በማለት ጠየቁት፡፡›› “እሱም፣ አዎ አንድም ሰው አንተ በመጣህበት ተመሳሳይ የመጣ በጭራሽ የለም ጠላት የሚያፈራ ቢሆን እንጂ፣ ቀኑን ካደረሰኝ ሁነኛ እገዛን ባገዝኩህ ነበር››፡፡ ወረቀት ግን ብዙም ሣይቆይ ሞተ፡፡ ወህይም ተወሰኑ ጊዜያት ተቋረጠ፡፡

ቡኻሪ ከጃቢር ኢብኑ ዐብደላህ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ወሕይ መቋረጥ ሲናገሩ ‹‹በመሄድ ላይ ሳለሁ ከሰማይ አንዳች ድምጽ ሰማሁ፡፡ዓይኔን ወደዚያው ቀና አደረግኩ፡፡ ያ ሒራእ ዋሻ ውስጥ የመጣብኝ መልአክ በምድርና ሰማይ መካከል በሆነ ዙፋን ላይ ተቀምጧል፡፡ በጣም ደነገጥኩኝ፡፡ በፍጥነትም ተመልሼ ‹አከናንቡኝ! አከናንቡኝ!› አልኩ፡፡ አላህም

يَا أَيُّهَا الْمُدَّثِّرُ

‹‹አንተ (ልብስህን) ደራቢው ሆይ ፡፡ ተነስ አስጠንቅቅም፡፡ ጌታህንም አተልቅ፡፡ ልብስህንም አፅዳ፡፡ ጣኦታትንም ራቅ፡፡ ማብዛትንም የምትፈልግ ኾነህ(በረከትን) አትለግስ፡፡ ለጌታህም ታገስ፡፡›› አልሙደሲር፤ 1-5 የሚለውን አንቀድ አወረደ፡፡ ቀጥሎም ወሕይ ተቋረጠ”

ወህይ የተቋረጠበትን የጊዜ ቆይታ በተመለከተ የተለያዩ ንግግሮች የተሠነዘሩ ሲሆን ትክክለኛው ለተወሰኑ ቀናት ነበር የሚለው ነው፡፡ ኢብኑ ሰዕድ ከኢብኑ ዐባስ ያወሩት ይህን የሚደግፍ ነው


(አር-ረሒቁል- መኽቱም፣ ሰፊዩ አር-ረህማን አል-ሙባረኸፋሪ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here