የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሒራእ ዋሻ ውስጥ መገለል

0
1375

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እድሜያቸው ወደ 40 እየተቃረበ ሲመጣ፥ ከወትሮው በተለየ ከሰው መነጠልን በተለያዩ ጊዜያት እየወደዱት መጥተዋል፡፡ አላህም ለመገለያው ቦታ የሒራእ ዋሻን እንዲወዱት አድርጓቸዋል፡፡ ሒራእ ማለት ከመካ በሰሜን ምዕራብ በኩል የሚገኝ ተራራ ሲሆን ነቢያችንም (ሰ.ዐ.ወ) ዋሻው ውስጥ ለብዙ ሌሊቶች፣ አንዳንዴም አስር፣ ሌላ ጊዜም ከዚያም በላይ እስከ ወር ለሚዘልቁ ቀናት አላህን በመገዛት ያሳልፉ ነበር፡፡

ከዚያ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ለሚቀጥለው ኸልዋ በአዲስ ስንቅ ይቋጥሩ ነበር፡፡ በእነዚህ ኸልዋዎች (መገለሎች) በአንደኛው ላይ ወሕይ እስከመጣላቸው ድረስ በዚህ ሁኔታ አሳልፈዋል፡፡

            ኸልዋ /አላህን ለመገዛት መገልል/

የነቢያችንን(ሰ.ዐ.ወ) ልቦና እንዲህ በፍቅር የገዛው ኸልዋ፥ ለአጠቃላይ ሙስሊሞች በተለይ ደግሞ ወደ ኢስላም ለሚጣሩ ዳዒዎች እጅግ የላቁ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከዚህም መካከል፡-

  1. በልቦና ውስጥ እጅግ የተላቀውና የተከበረው አላህ ፍቅር እንዲጎለብት ማስቻል

አላህን (ሱ.ወ) እንደሚወድ አእምሯዊ መረጋጋት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ኦሬንታሊስቶች[1]አላህንና ነቢያችንን /ሰ.ዐ.ወ./ ወዳጅ ከሆኑት ተርታ ይሰለፉ ነበር፡፡ ለመሆኑ ለአንድ ሂሳባዊ የስሌት ህግ አለያም አል-ጀብራ ጥያቄ ከምሁራን ራሱን አሳልፎ መስዋእት ስላደረገ አንድ ምሁር ሰምታችኋልን; ታውቃላችሁን?… በእርግጥ በአላህ ከማመን በኋላ ወደ እሱ ውዴታ መዳረሻ መንገዶች በዋነኝነት የሚከተሉት ናቸው፡-

ሀ. የታላቅነቱ ማረጋገጫ የሆኑ ምልክቶችን፤ ውለታውና ፀጋዎቹን በብዛት ማስተንተን፣

ለ. በአንደበትና በልቦና እሱን (አላህን) ማውሳት ማብዛት፣

ሐ. ግዴታ የሆኑ ተግባራትን በጥንቃቄ ተጠባብቆ መሥራት ሱንና /ነዋፊል/ የሆኑትንም ማብዛት፡፡

ይህ ሁሉ ሊገራ የሚችለው በተደጋጋሚ ከአላህ ጋር መገለልን /ኸልዋ/ በማዘውተር ነው፡፡

  1. የነፍስን ወለምታዎች ማከምና በስንክ-ሳሮቿ ላይ እሷን መተሳሰብ

የሰው ልጅ ነፍስ ከሰዎች ተነጥሎ  በመተሳሰብና ያለፈቻቸውን ድንበሮች እያስታወሱ ጉድለቶቿን ማስተዋል እንጂ የማይታከሙ የብዙ በሽታዎች መናኸሪያ ናት፡፡

አንዳንዴ የሰው ልጅ በውጫዊ ገጽታው በበርካታ መልካምና አምልኮታዊ ተግባራት የታጀበ፣ ሌሎች ሰዎች ወደ መልካም ነገር በመጥራት ላይ የተሰማራ በሆነበት ሁኔታ እነኳን በልቦና ውስጥ ስር ሰደው ልቦናን የሚቆጣጠሩና ብርሃኑንም የሚያከስሙ በሆኑት ራስን መኮፈስ፣ ጉራ፣ ታይታ፣ ምቀኝነትና ዓለማዊ ፍቅር ችግሮች ሊጠቃ ይችላል፡፡

ብቻውን ሆኖ ሲያስተነትን ግን የሰው ልጅ የነፍስያ እውነታ ይገለጽለታል፡፡ ምን ያህል ነፍስ አላህን ፈላጊና ደሀ እንደሆነች፣ በያንዳንዷ ቅጽበት የሱን (የአላህን) እርዳታ ፈላጊ መሆኗ፤ ሰዎች እሱን ለመጥቀምም ሆነ ለመጉዳት የማይችሉ ደካሞች መሆናቸውን ይደርስበታል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሙገሳቸውም ሆነ ወቀሳቸው ውጤት አልባ እንደሆነ ይገለጥለታል፤ ይህና ሌሎችም መሠል እውነታዎች ፍንትው ብለው ሲታዩት ሥራውን ለአላህ ብቻ አጥርቶ ይሰራል፤ ይተናነሳል…ወዘተ.፡፡ በተደጋጋሚ መገልልን /ኸልዋን/ በማብዛቱ የተነሳ ባገኘው ብርሃን የነፍሱ በሽታዎች ፍንትው ብለው ይገለጣሉ፡፡

ተግባራዊ እሳቤዎች

ይህ ሁሉ እውን የሚሆነው ራስን ከዓለማዊ ጭንቀቶችና ሁከቶች፣ ከከንቱ ብለጭልጯ በቀን፣ በለሊት፤ በወራትና፤ በዓመታት ለተወሰኑ ግን ተደጋጋሚ ለሆኑ ወቅቶች ገለል ብሎ ራስን መመልከት ሲቻል ነው፡፡ ለምሳሌ

  1. በረመዷን የመጨረሻው አስር ቀናት ወይም በየወሩ አንዲት ምሽት በመስጂድ ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ፣
  2. በየሌሊቱ የመጨረሻው 1/3ኛ ክፍል የኢስቲግፋር ወቅት፣
  3. በጠዋት እና በማታ ውዳሴ /አዝካር/ ወቅት አዝካሮችን ማድረግ፣
  4. ከመኝታ በፊት ነፍስን መተሳሰቢያ አጋጣሚ መኖርና የመኝታ ዚክር ማድረግ፣
  5. መስጂድ ለመስገድ በጊዜ መሄድ፣ ለሰላት ቁጭ ብለውም ሲጠባበቁ፣
  6. ከሰላት በኋላ ቁጭ ብሎ ዱዓ በማድረግ ወቅት ላይ፣
  7. ሌላው ቢቀር አዛን እየሰማ ከሙአዚኑ ተከትሎ ካለ በኋላም ሊሆን ይችላል፣ከላይ የተጠቀሱት ጊዜያት ሁሉም ቀልብ ከዱንያ ጋ ያለውን መገናኛ በመቁረጥ ትኩረቱን ትልቅና አሸናፊ ወደ ሆነው አላህ በአዲስ መልክ የሚያቆራኝበት ወቅቶች ናቸው።


[1] ሙስሊም ያልሆኑ ኢስላምንና ሌሎች ሃይማኖትን የሚያጠኑ ሃይማኖተ-አልባ፣ የሩቅ ምስራቅን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here