ኢማም ሀሰን አል – በስሪ

1
6692

‹ሀሰን አል – በስሪን የመሠለ ሰው በነርሱ ውስጥ ያለ ህዝብ እንዴት ሊጠም ይችላል!› (መስለማ ኢብኑ ዐብዱልመሊክ)

ከእለታት በአንዱ ቀን ብሥራት ነጋሪ የታላቁ ነቢይ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሚስት ወደሆነችው የምእመናን እናት ኡሙ ሰለማ ዘንድ እየገሠገሠ መጣ፡፡ የብሥራቱ ዜናም አገልጋይዋ ኸይረት ወንድ ልጅ በሠላም መገላገሏ ነበር፡፡ የምእመናን እናት በደረሳት ዜና እጀጉን ተደሰተች፡፡

በሀሴትም ወስጧ ተሞላ፡፡ ወዲያውኑ የአራስነት ጊዜዋን በቤቷ ያሳልፉ ዘንድ እናትና አዲሱን ልጅ እንዲያመጡላት ሰው ላከች።

አሙ ሰለማ ኸይረትን እጅግ ትወዳትና ከሌሎችም ታስበልጣት ነበር፡፡ በመሆኑም አዲሱ ልጇን ለማየት ከፍተኛ  ጉጉት አደረባት፡፡ ኸይረትም ብዙ ሳትቆይ ልጇን ይዛ የምእመናን እናት ዘንድ ደረሠች፡፡ ኡሙ ሰለማም ህፃኑን ልጅ ባየች ጊዜ እጅግ ወደደችው፡፡ ትንሹ ልጅ ቆንጆና አስደሣች፣ አካሉ የተሟላ፣ ሲያዩት ልብን በሀሴት የሚሞላ ልጅ ነበር፡፡

ከቆይታ በኋላ ኡሙ ሰለማ ወደ አገልጋይዋ ዘወር በማለት ‹ለልጅሽ ሥም አወጣሽለት ወይ?› አለቻት፡፡ ‹ እናቴ ሆይ! አላወጣሁለትም፡፡› አለቻት ኸይረት፡፡ ‹ደስ ያለሽን ሥም እንድትመርጭለት ብዬ ላንች ነው የተውኩት፡፡› አለቻት አክላ፡፡ ኡሙ ሰለማም ‹እንግዲያውስ በአላህ ፈቃድ ሥም እናወጣለታለን፡፡  አል ሀሠን ብለነዋል፡፡› አለችና እጇን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ዱዓእ አደረገችለት፡፡

የአል ሀሠን የመወለድ ዜና በተሠማ ጊዜ ደስታው በምእመናን እናቶች ቤት ብቻ አልተወሠነም፡፡ ሌሎች የመዲና ቤቶችም የደስታው ተካፋይ ነበሩ፡፡ ከነኚህም መካከል የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የወህይ ፀሃፊ የሆነውና ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እጅግ የሚወዱትና የሚያቀርቡት የዘይድ ኢብኑ ሳቢት ቤት ነበር፡፡ ምክኒያቱም የሣር የሚባለው የኸይረት ባለቤት የአል ሀሠን አባት ሲሆን በነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቤቶች በአንዱ ማለትም ኡሙ ሰለማ በመባል በምትታወቀው የምእመናን እናት ሂንድ ቢንት ሱሀይል ቤት ነበር ያደገው፡፡

ኡሙ ሰለማ ከዐረብ ሴቶች መካከል እጅግ በሣል፣ ምርጥና ቆራጥ ከሆኑት ውስጥ የምትመደብ ናት፡፡ በእውቀታቸው ከሚታወቁና ብዙ ሀዲሦችን ከርሣቸው ከዘገቡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሚስቶች መካከልም አንዷ ናት፡፡ ሰማኒያ ሰባት ያህል ሀዲሦችን ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘግባለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከኢስላም በፊት ከነበረው በጃሂሊያው ዘመን መፃፍ ከሚችሉ ጥቂት ሴቶች መካከልም አንዷ ናት፡፡

በምእመናን እናት ጉያ የገባው እድለኛው  ህፃን እድለኛነቱ በዚህ ብቻ የተወሠነ አልነበረም፡፡ አንዳንዴ እናቱ ለጉዳይ ተልካ ወጣ በምትልበት ጊዜ ርቦት ሲያለቅስ ኡሙ ሰለማ ወደ ክፍሏ ትወስደውና ለማስታገስና የእናቱን አለመኖር ለማስረሳት ጡቷን ትሠጠው ነበር፡፡ እጅግ ትወደውም ስለነበር ጡቷ ወዲያውና ወተት ይሞላና ልጁም ይጠባል፡፡ በዚያውም ዝም ይላል፡፡

በዚህ መልኩ ኡሙ ሰለማ ለአል ሀሠን በሁለት መልኩ እናቱ ለመሆን ቻለች፡፡ የምእመናን ሁሉ እናት እንደመሆኗ በአንድ በኩል እናቱ ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ የጥቢ እናቱ ናት፡፡

የምእመናን እናቶች የሆኑት የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሚስቶች እርስ በርስ ያላቸው ጠንካራ ግንኙነትና የቤታቸው መቀራረብ ህፃኑ ልጅ በቤቶቹ  መካከል ተመላልሦ ያድግ ዘንድ እድል ፈጥሮለታል፡፡ በነርሱ መልካም ባህሪና ሥነምግባር ይታነፅ ዘንድም ምክኒያት ሆኖታል፡፡ እሱም ካደገ በኋላ ስለራሱ ሲናገር ይህንኑ ያስታውሣል፡፡ በማያርፈው የልጅነት እንቅስቃሴውና ጨዋታው እነኚህን ሁሉ ቤቶች ያዳርስ እንደነበረ ተርኳል፡፡ እየዘለለ የቤቶቹን ጣሪያ ይነካ እንደነበር ሁሉ ያስታውሣል፡፡ አቤት የነቢዩ ቤቶች! ለአላህ መተናነሣቸው ይሆን እንዲህ ዝቅ ያደረጋቸው!!!

አል ሀሠን በዚያ በሚያውድ መልካም የኢማን አየር ውስጥ ሲንቀሣቀስና ነቢያዊ ቤቶችን ሲዞር አደገ፡፡ ከምእመናን እናቶች ቤት ጣፋጭ ምንጭም በልጅነቱ መልካምን ነገር ሁሉ ተጎነጨ፡፡ ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ በአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መስጅድ በታላላቅ ሶሃቦች ረ.ዐ እጅ ዲናዊ እውቀት መቅሰሙን ተያያዘው፡፡ በመሆኑም ከዑስማን ኢብኑ ዐፋን፣ ከዐሊ ኢብኑ አቢ ጧሊብ፣ ከአቢ ሙሣ አል አሸዐሪይ፣ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር፣ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ፣ ከአነስ ኢብኑ ማሊክ፣ ከጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ እና ከሌሎችም ለመዘገብ ችሏል፡፡ ሆኖም ግን ትልቁን ትምህርት ያገኘው ከምእመናን መሪ ዐሊ ኢብኑ አቢ ጧሊብ ረ.ዐ እጅ ነበር፡፡

አል ሀሠን በሃይማኖቱ ውስጥ ባለው ጥንካሬ፣ አምልኮውን በማሣመሩ እና ዓለማዊነትን በመናቁ ይታወቃል፡፡ አስደናቂ ገለፃው፣ ጥበባዊ ንግግሩ እና ድንቅ አባባሎቹ ዘመናትን የሚሻገሩ ናቸው፡፡ ምክሮቹ ልብን ያርዳሉ፡፡ አል ሀሠን አላህን በመፍራት እና በዒባዳው በመበርታት ወደር አልነበረውም፡፡ ገለፃውና ቋንቋው አስደማሚና ውብ ነው፡፡

አል ሀሠን ከፍ ብሎ አሥራ አራት አመት በሆነው ጊዜ ከአባቱ ጋር ወደ ዒራቋ የበስራ ከተማ አቀና፡፡  ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆንም ቀሪ የምድር ላይ ህይወቱን እዚያው አሣለፈ፡፡ በዚህ መልኩ አል ሀሠን  ኑሮውን በበስራ በማድረጉ ‹አል ሀሠን አልበስሪ/ የበስራው ሀሠን/ በመባል ሊታወቅ የቻለው፡፡

አል ሀሠን አል በስራ በደረሠበት ዘመን ከተማዋ በእስልምናው መንግስት ውስጥ ትልቅ የእውቀት ማዕከል ሆና ታገለግል ነበር፡፡ ትልቁ መስጅዷ ታላላቅ ሶሃቦችንና ምርጥ የተባሉትን ታቢዒዮች ሁሉ አቅፏል፡፡ የኢልም ሀለቃዎችም (ቡድኖች/ማዕዶች) በመስጅዱ ውስጥ በዓይነት በዓይነቱ ይሠጣሉ፡፡ ተማሪዎችም የመስጅዱን ውስጥ እና ግቢውን ጭምር ይሞላሉ፡፡

አል ሀሠን ቤቱን በመርሣት መስጅድን መኖሪያው አደረገ፡፡ የነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ኡማ እጅግ አዋቂ  የሆነውን ሶሃባ የዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስንም ሀለቃ (የእውቀት ማዕድ) ፀንቶ ያዘ፡፡ ከሱም የተፍሲርን፣ የሀዲስንና ሌሎችን እውቀቶች ወሠደ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሱም ሆነ ከሌሎች የፊቅሂን፣ የቋንቋ እና ሌሎችንም ትምህርቶች አግኝቷል፡፡ በመጨረሻም ዓሊም፣ ፈቂህ እና በእውቀቱ የሚታመን ለመሆን በቃ፡፡ በመሆኑም ሰዎች ከሱ እውቀት ወደ መፈለግ ዞሩ፡፡ በሄደበትም ቦታ ሁሉ ከበቡት፡፡ እንባን ከሚያስረጩና የደረቀ ቀልብን ከሚያርሱ ምርጥ ምክሮቹ ለማዳመጥ ብለው ተጋፉ፡፡…

የአል ሀሠን አልበስሪ ጉዳይ በሰፊው ይሠራጭ ያዘ፡፡ በምእመናን መካከልም ዝናው ናኘ፡፡ በመሆኑም ኸሊፋዎች እና አሚሮች ጭምር እሱን ማፈላግና ማጠያየቅ ገቡ፡፡

ኻሊድ ኢብኑ ሶፍዋን እንዳስተላለፈው እንዲህ ይላል ‹ ሂራ ላይ መስለማ ኢብኑ ዐብዱልመሊክን  አገኘሁና ‹ ኻሊድ ሆይ! እስቲ ስለ ሀሠን አልበስሪ ንገረኝ፡፡ አንተ ስለሱ ሌሎች የማያውቁትን ታውቃለህ ብየ እገምታለሁ፡፡› አለኝ፡፡

እኔም ‹አላህ ሱ.ወ ለአሚራችን መልካሙን ሁሉ ይመርጥ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ በርግጥም ስለሱ ከኔ በላይ የሚነግርህ ሰው አይኖርም፡፡ እኔ በቤት ጎረቤቱ፣ በሚቀመጥበትም መጅሊስ አቀማማጩ ነኝ፡፡ ከበስራ ሰዎች ሁሉ ስለሱ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡› አልኩት፡፡

‹እንግዲያውስ የምትለውን በል እስቲ› አለኝ፡፡ እኔም

‹አል ሀሠን ማለት ውስጡ እና ውጭው፣ ንግግሩ እና ሥራው ተመሣሣይ የሆነ ሰው ነው፡፡ በአንድ ነገር ያዘዘ እንደሆ ከርሱ በላይ የሚሠራበት ማንም የለም፡፡ ከመጥፎ ነገር የከለከለ እንደሆነም ከርሱ በላይ ከዚያ ነገር የሚርቅ የለም፡፡ ከሰዎች የተብቃቃ፣ በእጃቸው ያለን ነገር የማይፈልግ ነው፡፡ ሰዎች ወደርሱ ፈላጊዎችና ከርሱ ዘንድ ያለውን ናፋቂዎች ናቸው፡፡›

መስለማም ‹ያልከው ይበቃል ኻሊድ.. በል ይብቃህ::› አለው .. ‹የዚህ ዓይነት ሰው በመካከላቸው ያለ ህዝቦች እንዴት ሊጠሙ ይችላሉ?› በማለትም በግርምት ጠየቀ፡፡

አል ሀጃጅ ኢብኑ ዩሱፍ አስ ሰቀፊ የዒራቅ ገዥ ሆኖ በአገዛዙ ድንበር በማለፍ የለየለት አምባገነን በሆነ ጊዜ አምባገንነቱን ከተጋፈጡትና በሰዎች መካከልም መጥፎ ድርጊቱን ካወገዙት እንዲሁም በፊት ለፊቱም እውነትን ሣይፈሩ ከተናገሩት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ አል ሀሠን አልበስሪ ነው፡፡

በአንድ ወቅት አል ሀጃጅ በኩፋና በስራ መካከል በምትገኝ አል ዋሲጥ በምትባል ቦታ ላይ ለራሱ ትልቅ ህንፃ ገነባ፡፡ ግንባታውም በተጠናቀቀ ጊዜ ሰዎች ወጥተው ደስታቸውን እንዲገልፁና አላህ እንዲባርክለትም ዱዓእ እንዲያደርጉ ጋበዛቸው፡፡ አል ሀሠን ይህን የሰዎች መሰባሰብ እንደ እድል በመጠቀም የሚፈልገውን መልእክት ለማስተላለፍ ወሠነ፡፡ በመሆኑም ሊመክራቸውና ሊያስታውሳቸው ወጣ፡፡ ዓለማዊነትን እንዲንቁና አላህ ዘንድ ያለውን እንዲከጀሉ ሊያነሣሣቸው ተነሣ፡፡

ቦታው ላይ በደረሠ ጊዜ ሰዎች አሰደናቂውን ግንባታ እየዞሩ ሲመለከቱና ሲገረሙ አገኛቸው፡፡ በግንባታው ስፋት ይደመማሉ፤ በጥበቡና በፈሠሠበት ውበት ይደነቃሉ፡፡ አል ሀሠን ሰዎች በዚሁ ሁኔታ ላይ እያሉ ንግግር ለማድረግ ተነሣ፡፡ እንዲህም አላቸው –

‹ሰዎች ሆይ! ከሁለቱ መጥፎዎች አንዱ የሆነው ሰው የገነባውን አየን፡፡ የፈርዖውን ግንባታ በርግጥ ከዚህ የላቀ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ነገርግን አላህ ፈርዖውንን ከነግንባታውና ህንፃው አጠፋው፡፡ ምናለ አል ሀጃጅ የሰማይ ነዋሪዎች የጠሉት፤ የምድር ነዋሪዎች ያታለሉት መሆኑን አውቆ በሆነ ኖሮ፡፡› በማለት የድፍረት ንግግር አደረገ፡፡

አል ሀሠን ንግግሩን አረዘመ፡፡ ከአድማጮች መካከል አንዱ የአል ሀጃጅን ቁጣና በቀል ፈርቶ ‹የሰዒድ አባት ጎይ ይብቃህ!›  እስኪለው ድረስ፡፡ አል ሀሠንም ‹ አላህ የእውቀት ሰዎች እውቀትን እንዲገልፁ እና እንዳይደብቁ ቃልኪዳን ወስዷል፡፡› በማለት መለሠለት፡፡

በቀጣዩ ቀን ሀጃጅ እሣት ለብሦ እሣት ጎርሦ ወደ እልፍኙ ገባ፡፡ አማካሪዎቹንም ተቆጣ ‹ጥፉ ከዚህ የማትረቡ!› አላቸው .. ‹ከበስራ ባሪያዎች መካከል አንዱ የሆነው በኛ ጉዳይ ላይ ተነስቶ እንደፈለገው ሲናገር ከናንተ መካከል የሚያወግዘው አንድም ሰው እንዴት ይጠፋል? እናንተ ፈሪዎች ሆይ! ወላሂ ከደሙ አጠጣችኋለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ከዚያም ሰይፍ እና አለንጋ እንዲያመጡለት አዘዘ፡፡

ገራፊዎቹ ተጠሩና መጥተው ፊቶ ፊት ለፊቱ ቆመ፡፡ የተወሰኑ ፖሊሦችም ሄደው ሀሠንን እንዲያመጡ ታዘዙ፡፡ ብዙም ሣይቆይ አልሀሠንን ይዘውት መጡ፡፡ ዓይኖች ሁሉ በፀጥታ ወደርሱ ተመለከቱ፡፡ ልቦችም በፍርሃት ራዱ፡፡

አል ሀሠን ሠይፍ፣ አለንጋና ገራፊውን ባየ ጊዜ ከንፈሩን አንቀሣቀሠ፡፡ ከዚያም በአማኝ ግርማ ሞገስ ላይ ሆኖ በሙስሊም ጥንካሬ ተሞልቶና በዳዒ እርጋታ ተሸፍኖ ወደ ሀጃጅ ቀረበ፡፡ አል ሀጃጅ በዚህ ሁኔታው ላይ ባየው ጊዜ አል ሀሠንን በእጅጉ ፈራው፡፡ ማንም ባላሠበ መልኩ የጠራበትን በመተው ‹የሰዒድ አባት ሆይ! ና እዚህ ጋ እዚህ ጋ ና ፡፡› በማለት ጋበዘው፡፡ ሰዎች ባለማመንና በግርምት ይመለከቱታል፡፡ እያዩትም ሄዶ ፍራሹ ላይ ቁጭ አለ፡፡

ቦታው ላይ ቁጭ ባለ ጊዜ አል ሀጃጅ ስለ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ይጠይቀው ገባ፡፡ አል ሀሠንም በአስተማማኝ ማስረጃ፣ በሚደንቅ ገለፃ እና ሰፋ ባለ እውቀት መለሠለት፡፡

አል ሀጃጅም ‹የሰዒድ አባት ሆይ! አንተ የዑለማኦች ሁሉ ታላቁ ነህ፡፡› አለው፡፡ ሽቶ አስመጣና ፂሙ ላይ በመቀባት ሸኘው፡፡

አል ሀሠን ከአል ሀጃጅ ዘንድ በወጣ ጊዜ የሀጃጅ አሣላፊ ተከተለውና ‹ የሰዒድ አባት ሆይ! ሀጃጅ የጠራህ ለሌላ ጉዳይ ነበር፡፡ ወደርሱ ስትሄድ እና ሰይፍ፣ አለንጋውንና ገራፊውን ባየህ ጊዜ ከንፈርህን ስታንቀሣቅስ አይቼህ ነበር፡፡ ምን ነበር ያልከው?›  አለው፡፡ አል ሀሠንም ‹የፀጋዬ ባለቤት፣ የጭንቀቴ ጊዜ መሸሻዬ የሆንከው ሆይ! ለኢብራሂም እሣትን ቀዝቃዛ እና ሠላም እንዳደረግከው ሁሉ የዚህንም ሰው ቁጣና በቀል ቀዝቃዛና ሠላም አድርገው፡፡› ነው ያልኩት፡፡› አለው፡፡

አል ሀሠን ከታላላቅ ሹማምንቶች ጋር የነበረው ገጠመኞች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ከሁሉም ዘንድ ሲወጣ ግን በነርሱ ዓይን ዘንድ እጅግ ታላቅ እና የተከበረ ሆኖ  በአላህ ተመክቶና በሱ ተጠብቆ አንገቱን ቀና አድርጎ ነው፡፡

ዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ወደ አላህ ረህመት በተሸጋገረ ጊዜ የኸሊፋነቱን ቦታ የዚድ ኢብኑ ዐብዱልመሊክ ተረከበ፡፡ እሱም ዑመር ኢብኑ ሁብራህ አልፈዛዚን የዒራቅ ገዥ አድርጎ ሾመው፡፡ ሥልጣኑንም በማስፋት የኹራሣንንም ምድር የማስተዳደሩን ሀላፊነት ጨመረለት፡፡

ኸሊፋው የዚድ ከዚህ ቀደም የነበሩ የምርጥ በጎ ሰዎችን አካሄድ ይጥስ ነበር፡፡ እያከታተለም ለዑመር ኢብኑ ሁብራህ መልእክቶችን በመላክ አድሎና በደል የሚታይበትን ትእዛዝ ሳይቀር እንዲፈፅም ያዘው ነበር፡፡ ጉዳዩ ያሣሰበው ዑመር ኢብኑ ሁብራህ አል ሀሠን አልበስሪን እና አሽ ሽዕቢ በመባል የሚታወቀውን ዓሚር ኢብኑ ሸርሃቢልን በመጥራት እንዲህ አላቸው፡፡

‹የምእመናን መሪ የሆነውን የዚድን ኢብኑ ዐብዱልመሊክ አላህ ሱ.ወ በባሮቹ ላይ ኸሊፋ አድርጎታል፡፡ እሱን መታዘዝንም በሰዎች ላይ ግዴታ ነው፡፡ እንደምታዩት በዒራቅ ላይ ገዥ አድርጎ ሹሞኛል፡፡ ከፋርስ ምድርም ከፊሉን ጨምሮልኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መልእክት ይልክብኝና ፍትሃዊነቱን የማላምንበትን ነገር እንድፈፅም ያዘኛል፡፡ የዲንን አስተምህሮ በመፃረር የሱን ትእዛዝ ሊተግብር ወይንስ ምን ይሻለኛል?›  አላቸው፡፡

አሽ ሸዕቢ ከኸሊፋው ጋር በሠላም ለመኖር ያስችላል ያለውን ማግራራት የታየበት መልስ መለሠለት፡፡ ሀሠን ዝም ብሎ ያዳምጠው ነበር፡፡ ዑመር ወደ አል ሀሠን በመዞር ‹የሰዒድ አባት ሆይ! አንተስ ምን ትላለህ?› አለው፡፡

አል ሀሠንም ‹የሁበይራህ ልጅ ሆይ! በየዚድ ጉዳይ አላህን ፍራ እንጂ በአላህ ጉዳይ የዚድን አትፍራ፡፡ የተከበረውና ሀያሉ አላህ ከየዚድ ሊያስጥልህ ይችላል፡፡ የዚድ ግን ከአላህ ፈፅሞ አያስጥልህም፡፡›

‹የሁበይራህ ልጅ ሆይ! አላህ ያዘዘውን ከመፈፀም ወደኋላ የማይል ሀይለኛና ጨካኝ መልዓክ ወርዶብህ ከዚህ ዙፋንህ ላይ እንዳያስወግድህና ከሰፊው ቤተመንግስትህ ወደ ጠባቡ መቃብርህ እንዳይጎትትህ እሠጋለሁ፡፡ እዚያም የዚድን አታገኝም፡፡ እዚያ የምታገኘው ነገር የየዚድን ጌታ የተፃረርክበትን ሥራህን ነው፡፡›

‹የሁበይራህ ልጅ ሆይ! ከአላህ እና እሱን ከመታዘዝ ጋር የሆንክ እንደሆነ ይህ በዚህች ዓለምም ሆነ በመጨረሻው ዓለም ከየዚድ በቀልና ቁጣ ሊጠብቅህ በቂህ ነው፡፡ አላህን ባለመታዘዝ ከአል ሀጃጅ ጋር ያበርክ እንደሆነ ግን ሀያሉ አላህ ለየዚድም አሣልፎ ይሠጥሃል፡፡›

‹የሁበይራህ ልጅ ሆይ! የፈለገ ሰው ቢሆንም ፍጡርን ለመታዘዝ ተብሎ ሀያሉንና የተከበረውን ፈጣሪ አለመታዘዝ የለም፡፡›

ዑመር ኢብኑ ሁብራህ አለቀሠ፡፡ እንባውም ፈሦ ፂሙን አራሠ፡፡ ከአሽ ሸዕቢ ሀሣብም ይልቅ ወደ አል ሀሠን ሀሣብ አዘነበለ፡፡ አል ሀሠንንም ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ አከበረው፡፡ ከርሱ ዘንድ ሲወጡ ሁለቱ ሰዎች ወደ መስጅድ አመሩ፡፡ ሰዎች በዙሪያቸው ተሰባሰቡ፡፡ ከዒራቁ ገዥ ጋር ያደረጉትንም ውይይት ይጠይቋቸው ገቡ፡፡

አሽ ሸዕቢ ወደ ሰዎቹ በመዞር ሰዎች ሆይ! ከናንተ መካከል በሁሉም ቦታዎች ላይ በፍጡራኑ ላይ ሀያሉን እና የተከበረውን አላህን ማስበለጥ የቻለ ሰው ይህንኑ ያድርግ፡፡ ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታዬ እምላለሁ! አል ሀሠን ለዑመር ኢብኑ ሁበይራህ የተናገረው ነገር እስከዛሬ ድረስ የማላውቀውንና ያላስተዋልኩትን ነው፡፡ እኔ በተናገርኩት ነገር አስቤ የነበረው በኢብኑ ሁበይራህ ዘንድ መወደድንና ቦታ ማግኘትን  ነበር፡፡ አል ሀሠን ግን የፈለገው አላህ ዘንድ መወደድን ነው፡፡ በመሆኑም አላህ እኔን ከኢብኑ ሁበይራህ ዘንድ አራቀኝ፡፡ እሱን ደግሞ ወደርሱ አስወደደው፡፡›

አል ሀሠን አልበስሪ በዚህች ምድር ላይ ለሰማኒያ ዓመታት ኖሯል፡፡ በነኚህ አመታት ውስጥም በእውቀት፣ በጥበብ እና ፊቅሂ ምድርን ሞልቷል፡፡

ለተከታዩ ትውልድ ካወረሣቸው መካከል ለዘመናት ቀልብ አለስላሽ ሆነው የኖሩ፤ ልብን የሚያርዱ የሆኑ አጠቃላይ ምክሮቹ ይገኙበታል፡፡ ጣፋጭ ምክሮቹ በርግጥም የአላህ መንገድ የጠፋባቸውን አመላካች፣ የዚህችን ዓለም ጠፊነት ዘንግተው የተዘናጉትን ቀስቃሽ ናቸው፡፡

ከነኚህም መካከል አንድ ሰው ስለዚህች ዓለም ሁኔታ በጠየቀው ጊዜ  እንዲህ በማለት የመለሠለት ይጠቀሣል ‹ ስለዚህች ዓለም እና ስለመጨረሻው ዓለም ነው የምትጠይቀኝ?  የዚህች ዓለም ምሣሌ ከመጨረሻው ዓለም አንፃር እንደ ምሥራቅ እና ምዕራብ ነው፡፡ ከአንደኛው በራቅክ ቁጥር ወደሌላኛው መቅረብህ ግድ ነው፡፡ የዚህችን ዓለም ሁኔታ ግለፅልኝ ነው ያልከኝ? መጀመሪያዋ ድካም መጨረሻዋ መጥፋት ስለሆነው ዓለም ምንና እንዴት ብዬ ልገልፅልህ እችላለሁ? ሀላል ነገሯ ምርመራ አለው፡፡ ሀራም ደግሞ ቅጣት አለው፡፡ ከሷ የተብቃቃ መፈተኑ አይቀርም፡፡ በሷ ውስጥ የደሀየ ደግሞ ሀዘን ማብዛቱ ግድ ነው፡፡›

በአንድ ወቅትም አንድ ሰው ስለርሱ እና ስለ ሰዎች ሁኔታ በጠየቀው ጊዜ እንዲህ ብሎታል ‹ ወየውልን ለራሣችን! ጥፋታችንን እንመልከት..  ዲናችንን ጣልን፤ ዱኒያችንን አደለብን፤ ባህሪያችንን አበላሸን፤ መኝታችንን እና ልብሣችንን አሳመርን፡፡ በእግራችን ላይ እንጋደማለን፤ የራሣችን ያልሆነን ገንዘብ እንበላለን፤ ነጥቀን ነው የምንበላው፤  አገልጋዮቻችንን እንበድላለን፤ ጣፋጭ በጣፋጭ ላይ እናጣጥማለን፤ ቀዝቃዛ ጠጥተን ትኩስ እናዛለን፤ እሸት በልተን ደረቀ እንመገባለን… ሆዳችን እስኪወጠር ድረስ፡፡ ከዚያም ለአገልጋዩ በማሾፍ መልክ  ‹እስቲ ምግብ የሚበትን ነገር አምጣልኝ፡፡› እንላለን .. ወላሂ አንተ ቂላቂል ሆይ! ዲንህን ነው እየበተንክ ያለሀው .. የተቸገረውን ጎረቤትህን ለምን አታስታውስም? የተራበው ወላጅ አጥ ዘመድህን ለምን ትዝ አይልህም? እጅ እጅህን የሚያየውን ድሃውንስ ምነው ረሣህ?  አላህ ባዘዘህ ነገር የምትሠራው መቼ ነው?.. ምናለ አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ቁጥር መሆንህን በተረዳህ! ፀሃይህ በጠለቀች ቁጥር አንተም ቀንህ ይቀንሣል ከፊልህም ይሄዳል፡፡›

አል ሀሠን የሙእሚንን ሁኔታ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-

‹ሙእሚን ሀዘንተኛ ሆኖ ያነጋል፡፡ ሀዘንተኛ ሆኖም ያመሻል፡፡ የሚሻለውም ነገር ይሀው ነው፡፡ ምክኒያቱም እሱ በሁለት ፍራቻ መካከል ነውና የሚኖረው፡፡ አላህ በዚያ ምክኒያት ምን እንደሚደያርገው በማያውቀው ባለፈው ወንጀሉ እና በቀረው እና በውስጡ ምን አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል በማያውቀው ዕድሜው መካከል፡፡›

ረጀብ ወር መጀመሪያ ላይ ጁሙዓ ቀን ለሊት 110 አመተ ሂጅራ አል ሀሠን አልበስሪ እንደቀደሙት ምርጥ ደጋግ ሰዎች ሁሉ የተላከለትን የአላህ ጥሪ ተቀበለ፡፡ ንጋት ላይ የመሞቱ ዜና በፍጥነት ሰዎች ዘንድ በተዳረሠ ጊዜ በስራ ከተማ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ወደቀች፡፡

ታጠበ፤ ተከፈነ ከጁሙዓ በኋላም አብዛኛውን ዕድሜውን በሙሉ ተማሪ፣ አስተማሪ እና ወደ አላህ ሱ.ወ መንገድ ተጣሪ ሰባኪ ሆኖ ባሣለፈበት መስጊድ ውስጥ ተሠገደበት፡፡ ወደ መቃብር ሲሸኝም አንድም ሣይቀር ሁሉም ሰው ተከተለው፡፡ በታላቁ የአል በስራ መስጅድ በዚያን ቀን የዐስር ሶላት አልተሠገደም ነበር፡፡ ምክኒያቱም ሁሉም ሰው አል ሀሠንን ወደ መጨረሻው ዓለም ለመሸኘት ሄዶ ነበርና ነው፡፡ የአል በስራ መስጅድም ከተገነባበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ መልኩ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሣይሰገድበት ቀረ፡፡

አላህ ለሀሠን አል በስሪ ይዘንለት፡፡

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here