ግብጽ ውስጥ ነው፡፡ አንድ መስጂድ ላይ በአማኞች መካከል ግጭት ተከሰተ፡፡ መንስኤው የተራዊህ ሰላት ላይ ባለ ምልከታ ነበር፡፡ ገሚሶች ተራዊህ ሰላት 11 ረከዓ ነው የሚሰገደው ሲሉ፣ የተቀሩት ደግሞ 23 ነው በማለት ከፍተኛ ውዝግብ ተነሳ፡፡ ይህን የሰሙት ታላቁ ሰው ሸይኽ ሀሰን አልበናህ (ረ.ዐ) ያጣላቸው ምን እንደሆነ ጠየቁና ሰዎቹ የተፈጠረውን አስረዱ፡፡ ሸይኹ ጥያቄ አስከተሉ፤ የተራዊህ ሰላት በእስልምና ፍርዱ ምንድነው አሉ፡፡ የተጣሉት ሰዎችም በጋራ “ሱና” ሲሉ መለሱ፡፡ “ወንድማማችነትስ” ሲሉ ሌላ ጥያቄ ደገሙ፡፡ “ግዴታ (ፈርድ)” ነው በማለት መለሱ፡፡ እኚህ ጥበበኛ ዓሊም የልዩነትን ባሕርይ ጠንቅቀው ስለተረዱ በቀላሉ ሰዎችን የሚያስታርቁበት መንገድ አልጠፋቸውም ነበር፡፡
በእስልምና የአረዳድ ልዩነት ያለና ወደፊትም ሊኖር የሚችል ነው፡፡ እንኳን ዛሬ በትላንቱ ወርቃማ ትውልድ ውስጥም የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን የጥላቻና የአንጃ መፈልፈያ መሣሪያ አይሆንም፡፡ ብዙዎች ልዩነትን እና ባሕሪያቱን የሚስተናገድበትን ሥነ ምግባር ጠንቅቀው ባለማወቃቸው የሚፈጠር ነው፡፡ በዐረብኛ ቋንቋ “ኺላፍ” የሚለው ቃል መቃረን፣ መለያየት ማለት ሲሆን፣ “ኢኽቲላፍ” ማለት ደግሞ የተለያዩ ዕይታዎች፣ ዐይነታዎች የሚሉ ቃላትን የሚያመላክት ነው፡፡
እስልምና በዕይታ መለያየት (ኢኺቲላፍ)፣ ወደ ልዩነት (ኺላፍ) እና ወደ ጥላቻ አያመራም ሲል ይሰብካል፡፡ ሰዎች በአፈጣጠራቸው፣ በቀለማቸው፣ በአካባቢያቸውና በአስተዳደጋቸው ይለያያሉ፡፡ ይህ ልዩነት ተፈጥሮአዊና የተወደደ ነው፡፡ በእነዚህ ልዩነቶች መካከል መቀራረብ ውዴታን ይመጣል፡፡ ይህን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ) በቁርአኑ እንዲህ ይላል፡-
“ሰማያትንና ምድርን መፍጠሩ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት፣ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለአዋቂዎች ተዓምራቶች አልሉበት፡፡” አል-ሩም፤ 22
ይህ ዐይነቱ ልዩነት የሰው ልጅ ባሕርይ እና ሕይወት እስካለ የሚኖር ነው፡፡ ሰዎች እየተለያዩ መኖራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በመዝሀብና በአስተሳሰብ መለያየትም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ይስተናገዳል፡፡ ቁርአን ይህንን በተለያዩ አንቀጾች እየደጋገመ ይነግረናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በአል-በቀራህ ምዕራፍ ቁጥር 148 እንዲህ ይላል፡-
“ለሁሉም እርሱ (በስግደት ፊቱን) የሚያዞርበት አቅጣጫ አለችው” ይህ ማለት ልዩነትን አስመልክቶ እውነታን ማስተባበል እንደማይቻልና ማንም ሰው ባለው አስተሳሰብ እንደሚከበር ያስረዳል፡፡ በሌላ የቁርአን አንቀጽ ላይ ደግሞ፡-
“ጌታህም በሻ ኖሮ ሰዎችን ሁሉ አንድ ሕዝብ ባደረጋቸው ነበር፡፡ የተለያዩም ከመሆን አይወገዱም።” ሁድ፤118
በተጠቀሱት አንቀጾች አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጆችን ሁሉ አንድ አይነት ፍጥረት አለማድረጉና፤ እርስ በእርሳቸው እንደሚለያዩ ይነግረናል፡፡ እንኳን በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ፤ በአንድ ቤተሰብ ያሉ ሰዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚለያዩ ያስተምራል፡፡ በአስተሳሰብ፣ አፈጣጠርና በመሰል ነገሮች ሁሉ የሰው ልጆች እርስ በርሳቸው እንደሚለያዩ በሚገባ ተተንትኗል፡፡ ሰዎች ቁርዐንን በሚገባ ፈትሸው ቢያስተነትኑ ልዩነት ጤናማ እንደሆነና እንዴት መስተናገድ እንዳለበት መረዳት አይከብዳቸውም፡፡
አላህ (ሱ.ወ) በቁርዓን፤ በዛሪያት – 20/21፣ በቀሰስ – 72፣ በዙኽሩፍ – 51፣ በጡር – 15 ምዕራፎች “አትመለከቱምን?” እያለ ወደ ፊት ስለሚመጡ ጉዳዮች በጥልቀት እንድንመረምርና እንድናስብ ይጣራናል፡፡
ቁርዓን ውይይትን ለማስተማርም በብዙ ቦታዎች ጥቆማዎችን አድርጓል፡፡ በከፊል እንመልከታቸው፤ አላህ (ሱ.ወ) መልዓክቶቹን አንዳወያየ በሱረቱል ጠሀ ቁጥር 116፣ ነብያቶቹን እንዳወያየ በአል-በቀራህ ቁጥር 260፣ ኢብሊስን በሱረቱል አእራፍ ከ11 እስከ 23 እና በሱረቱል ሁጁራት ከ15 እስከ 40 እንዳወያየ ይጠቁማል፤ ከንቧ ጋር እንዳወራም በሱረቱል ነህል ቁጥር 68 ይነግረናል፡፡ እነዚህ አናቅጽት ሰዎች ስለ ውይይት ሥነ ምግባር ለመማር ሩቅ መጓዝ እንደማይጠበቅባቸውና ቁርዓንን ቢከፍቱ ብዙ እንደሚማሩ ማሳያ እንደሆነ ዑለሞች ያስረዳሉ፡፡
ሰዎች እንኳን በዚህኛው ዓለም በወዲያኛውም ጌታቸውን አንዴት እንደሚያናግሩ ቁርዐን መንገዱን ሲያስተምር በጠሀ ምእራፍ፤ 125 እንዲህ ይላል፡፡ “ጌታዬ ሆይ! ለምን ዕውር አድርገህ አስነሳኸኝ በእርግጥ የማይ የነበርኩ ስኾን”፡፡
በተጨማሪም ነብያቶች ሕዝባቸውን እንዴት እንደሚያናግሩ አስቀምጦልናል፡፡ በሙጃደላ ምዕራፍ ከአንድ ቁጥር ጀምሮ የመጣውን ብንመለከት ኸውላ ቢንት ሰእለባ በምትባል ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ስትሞግት በነበረች እንስት ምክንያት የወረደ አንቀጽ ነው፡፡ በካህፍ ምዕራፍ ደግሞ ከቁጥር 34 እስከ 40 ብንከፍት ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚያደርጉትን የውይይት አይነቶች ያሳየናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማሳየት የተሞከረው የሐሳብ ልዩነት ያለና የሚኖር ሲሆን፣ መፍቻ መንገዱም ውይይት እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡ በየትኛውም ሐሳብ መካከል ሥርዐት ያለው ውይይትና መደማመጥ ካለ፣ ልዩነቶች የጥላቻና የጸብ መንስኤ እንደማይሆኑ ለማስረዳት በቅድሚያ ቁርዓኑን በጥልቀት ለሚፈትሽ ዐዋቂ ጠቃሚ መንገድ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ጌታችን አላህ (ሱ.ወ) ከመላዕክቶች፣ ነብያቶች፣ ከሰዎች እና ሌሎች ፍጥረታት ጋር የሚያወራበትን አንቅጾች ስንመለከት ከጀርባው ያዘለውን የውይይት ሥነ ምግባር አንድንወርስ ዓሊሞች ያስተምራሉ፡፡ በሱረቱል ሑጁራት፣ በሱረቱል ካህፍና ሌሎች ምዕራፎች ላይ የመጡ ርዕሰ ጉዳዮች የሰዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያሳዩ መንገዶች በመሆናቸው፣ ብዙ የምንማርባቸውና በሚገባ እንደንፈትሻቸው የሚመከሩ ናቸው፡፡
እስልምና እና ቁርዓን ምንም እንኳን ለአማኞችና አማኝ ላልሆኑ አካላት ባላቸው አስተሳሰብ የውይይት ሥነ ምግባር እንዲጠበቅና ውይይት ጤናማ ከሆነ ወደ ግጭትና ጸብ እንደማያስኬድ በሚገባ አስተምሮናል፡፡ ተከታዩን ምዕራፍ እንመልከት፡-
“ከሰማያትና ከምድር (ዝናብን በቃይን) የሚሰጣችሁ ማነው?” በላቸው፡፡ “አላህ ነው፡፡ እኛ ወይም እናንተ በትክክለኛው መንገድ ላይ ወይም በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነን” በላቸው፡፡ ሰበእ፤ 24
ይህን አንቀጽ ልብ እንበል፣ ሐቅ ማን ጋር እንኳን እንዳለ እየታወቀ ራስን ከማጥራትና ሌሎችን ከማሳነስ ይልቅ በክብር ውይይት እንደሚደረግ አመላካች ነው፡፡ ተቃራኒ ወገን ስህተት ላይ እንኳን ቢሆን ማድመጥና መከባበር የሚያስተምረን ቁርዓን ነው፡፡ ከእኛ ዕምነት ውጭ ያሉ ሰዎችን እንኳን ስንጣራ በጥበብና በተግሳጽ እንደሆነ ይናገራል፡፡
“ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሳጼ (በለዘብታ ቃል) ጥራ፡፡ በዚያችም እርሷ መልካም በኾነችው (ዘዴ) ተከራከራቸው፡፡ ጌታህ እርሱ ከመንገዱ የተሳሳተውን ሰው ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱም ቅን የኾኑትን ሰዎች ዐዋቂ ነው፡፡” ነህል፤125
መንስኤ እና መፍትሔ
የሰው ልጆች አፈጣጠር እንደ መልክና ስብእናቸው እንደሚለያየው ሁሉ በአመለካከትና አስተሳሰብ ሊለያይ ይችላል። ይህ ተፈጥሯዊና የሚኖር ነው። ይህንን ከላይ ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ ታዋቂው የቁርዓን ተንታኝ የሆነው ኑዕማን አሊ ኻንን ጨምሮ በርካታ ዱዓቶች ልዪነትን ወደ አላስፈላጊ ንትርክና አለመግባባት የሚያመጡ ሁለት መንገዶች ናቸው ይሉናል፡፡ አንደኛው ከቀልብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሊከሰት የሚችል ልዩነት ነው፡፡ ይህ ማለት በሥነ ልቦና ችግር የሚፈጠሩ ክስተቶች ናቸው። እነዚህ የልብ ችግሮች ለኺላፍ መፈጠርና ለተጠላ ልዩነት በር ከፋች ናቸው፡፡
በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዙ በግልጽ የሚታዩት፤ በራስ ሀሳብ መደነቅ፣ ወንድምን ባላሰበው ነገር መጠርጠር፣ ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸውን ባላንጣዎች ማዋረድ፣ ራስን አግዝፎ በመመልከት “እኔ እሻላለሁ” ማለት፣ የሌሎችን ሐሳብ አለማድመጥና ጭፍን ወገንተኝነት፣ ለመዝሀብና ለአስተሳሰቦች ጭፍን ውዴታ (ነቀፌታ)፣ ለጀመዐ ጭፍን ተከታይ መሆን፣ ለሀገርና ሕዝብ ጭፍን ውዴታና ጭፍን ጥላቻ፣ በጭፍኑ መከተልና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ የቀልብ በሽታዎች የማይወደዱ ልዩነቶችን የሚጠራ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ብዙኃኑ በጋራ ቤት እየጸለዩና በጋራ የሚፈጽሟቸው ብዙ ነገሮች ላይ እየተስማሙ በማይታወቅ ምክንያት ግጭቶች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ ግጭቱን ቀረብ ብለን ለመመልከት ስንሞከር ልዩነቱ የአስተሳሰብ ቢመስልም፣ እውነታው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሆኖ ይገኛል፡፡
ሁለተኛ፣ አዕምሮ (አቅል) ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ልዩነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው፤ ዐይነታዎች (ተነዉእ)ን እንደሚያስከትል ስለሚታወቅ ከመነሻው አዎንታዊ እንደሆነ እስልምና ያስተምራል፡፡ በዋናነት የአስተሳሰብ መለያየት፣ በፖለቲካዊ ርዕዮት መለያየት፣ በዕውቀት ደረጃ መለያየት፣ በመዝሀብ መለያየት፣ በተለያዩ የዲኑ ሕግጋቶች፣ በቋንቋዊ ፍቺዎች፣ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር የአረዳድ ልዩነቶች ይከሰታሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች የተወደዱ ሲሆን፣ የበለጠ ማዳበርና እርስ በርስ ለመቻቻልና ዕውቀት ተለዋውጦ ለመተማመን፣ እንዲሁም በልዩነት ለመከባበር ይህኛው የልዩነት አይነት ይወደዳል፡፡ ለግጭትና ለጥልም መንስኤ አይሆንም፡፡ ቁርዓንና ሐዲስን ብንመረምር የአረዳድና የግንዛቤ ልዩነቶች እንዳሉ፤ ግን የመጣያ መንገድ እንዳልሆኑ፣ በተጨማሪም ይህን በአዕምሮና በአስተሳሰብ መለያየት ሳብያ የመነጩ የልዩነት መንገዶችን ለማከም ግንዛቤ ማዳበርና እውቀትን በመጨመር መረዳትን በማስፋት በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት በመከባበርና በመዋደድ ማሳለፍ ይቻላል፡፡ ይህን አስመልክቶ ታዋቂው ዓሊም ሸይኽ ረሺድ ሪዳ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፦ “በተስማማንበት ነገር አብረን እንሠራለን፣ በተለያየንበት ነገር ደግሞ አንዳችን ለሌላችን ምክንያት (ኡዝር) እና ዕውቅና እንሰጣጣለን።”
የሸይኹ ንግግር የአስተሳሰብ መለያየት ምዕመኑን እንደማያለያይና አብረው መሥራት እንደሚያስችላቸው የሚያመላክት የክፍለ ዘመኑ ድንቅ ንግግር ነው፡፡ ሰዎች ወደ ግጭትና ወደ ጸብ የሚያስኬዳቸው በአስተሳሰብ ወይም በአመለካከት መለያታቸው እንዳልሆነ ለመረዳት ፊቅህን ወይም ሐዲስን ስንመረምር በርካታ የአረዳድ ልዩነቶች ሲከሰቱ ስለሚስተዋል፣ ይህ በእውቀት እንደሚታከም መረዳት ያስፈልጋል፡፡
የቀድሞው የአለም ዑለሞች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንጋፋው የዘመናችን የ“ወሰጢያ” መሐንዲስ ተብለው የሚጠሩት ሸይኽ ዩሱፍ አልቀርዳዊ (አላህ ይጠብቃቸው) “ኺላፍ” በተሰኘው አንጋፋ መጽሐፋቸው ላይ ስለ ልዩነት ዳጎስ ያለ የጥናት ሥራ አበርክተዋል፡፡ ኺላፍን ከስር መሠረቱ በሚገባን ቋንቋ ጽፈውታል፡፡ (አንባቢያን የአማርኛውን ትርጉም እንድታነቡት እመክራለሁ፡፡ በሌሎችም የሀገራችን ቋንቋዎች ቢተረጎም አስተዋፅኦው ከፍ ያለ መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡) እኚሁ ታላቅ ሰው በዚሁ መጽሐፋቸው ላይ ስለተጠላው የልዩነት አይነት መንስኤ ሲናገሩ በሁለት ከፍለው ያዩታል፡፡ አንደኛው ኺላፉል ፊቅሂ (የአረዳድ ልዩነት) ሲሆን፣ ሁለተኛው ኺላፉል አኽላቅ (የሥነ ምግባር ልዩነት) ነው ይላሉ፡፡
የአረዳድ ልዩነትን በተመለከተ ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ ኢስላማዊ ፍርድ ላይ የተለያዩ ዕይታዎችን ማስተናገድን የመሰለ በርካታ ፊቂሀዊ ጉዳዮች ከአንድ ሺህ እንደሚበልጡ ይነገራል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚጋጩትና ወደ አላስፈላጊ ነገሮች የሚገቡት በሁለተኛው የሥነ ምግባር ልዩነት ነው፡፡ ብዙ ችግሮች የሚፈጠሩትም በዚሁ እንደሆነ ብዙ ዱዓቶች ይገልጻሉ፡፡ ለልዩነት ሰበብ ከሆኑ የሥነ ምግባር ችግሮች መካከል በዝና፣ በጥቅምና፣ በግለሰባዊ ችግሮች የሚከሰቱ ግጭቶች እንጂ አስተሳሰብ የጸብና የግጭት ሰበብ አይሆንም፡፡
ቀልብና አቅል ሲጣመሩ በልዩነት የመስማማት ብሎም የአስተሳሰብ ልዩነትን በማክበር መተባበርና መስማማትን ይፈጥራል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከአንገት በላይና ከአንገት በታች እያሉ ነገሩን ይገልጹታል፡፡ ከአንገት በላይ የሚባለው፣ አዕምሮን ሲወክል ከአንገት በታች ልቦናን ይወክላል፡፡ ከአንገት በላይ ባሉ ጉዳዮች ልዩነት መከሰት ጤናማና በቀላሉ የሚታከም ሲሆን፣ ከአንገት በታች ያለው በልቡና ምክንያት የሚከሰተው ለመቆጣጠር በጣም አዳጋች ነው፡፡ ልዩነቶችን ሥርዐት ለማሲያዝ ከዚህ በታች የጠቀሱትን ሁለት ነገሮች ማጤን ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ግድ የሆነው መለያየት
ሙስሊሞች በቅርንጫፋዊና ጥቃቅን በሚባሉ ጉዳዮች መለያየታቸው የግድ መሆኑን ማመንና መቀበል አስፈላጊ ነው፡፡ በእይታዎች፣ በመዝሀብ ጉዳዮችና ተመሳሳይ ጉዳዮች ሰዎች አንድ ይሁኑ ተብሎ አይገደዱም። ምክንያቱም የነዚህ ጉዳዮች መነሻው አዕምሮ መሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡። ሰዎች ባላቸው ግንዛቤ መሠረት የሚለኩም ጉዳዮች እንደመሆናቸው በዕውቀትና በማስረጃ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻልበት አጀንዳ ነው፡፡
በአካባቢያዊ ሁኔታዎችም ልዩነቶች ይፈጠራሉ፡፡ ሰሜንና ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ፣ ሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ እሳቤዎች በመነሳት ልዩነቶችና የእሳቤዎች መለያየት ይፈጠራል፡፡ ኢማሙ ሻፊዒ (ረ.ዐ) ኢራቅ በኖሩበት ጊዜ ያደረጓቸው ምርምሮች ግብጽ ከመጡ በኃላ ይለያዩ ነበር፡፡ በነባሩና በአዲሱ (ቀዲምና ጀዲድ) በሚል ሰፍረው ይገኛሉ። ይህ ማለት ሁለቱም ጋር ሐቅ እንደነበረ በቦታው ሁሉም ትክክል እንደነበረ አመላካች ነው፡፡ ሰዎችም በሚኖሩባቸው አካባቢዎችና በመጡበት አስተዳደግ ልክ ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ይህ አይነቱ ልዩነት ግዴታና የሚወደድ ብሎም በሰዎች መካከል መግባባትና መዋደድን የሚያመጣ ነው፡፡
ለሚለዩን ሰዎች ምክንያት እንስጥ
በከፊል ጥቃቅን የሆኑ አጀንዳዎችን ከትላልቆቹ ጉዳዮች እንለይ፡፡ መሠረታዊ በማይባል ጉዳይ ከሌሎች ጋር በሐሳብ አልተግባባንም ይሆናል፣ ግና ትልቅ በሚባሉና በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራትና ለመተባበር ጥቃቅን የሚባሉ ጉዳዮችን ሁሉ ለሠሪው መተውና በሚሰበስብ አጀንዳ ላይ መሆን በልዩነት መቻቻልን ያመጣል፡፡ ዘወትር እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት ልዩነትን ማጥበብ ይቻላል፡፡ እኛ የምንለያቸው ወንድሞቻችን እንደኛው ሙስሊሞች አይደሉምን? እኛ አንድ ነገር ስናገኝ ልቦናችን እንደሚረጋጋው እነርሱስ ይህ አይገባቸውም? ለራሳችን የወደድነውን ለሌላው መውደድን አልተማርንም? መሠረታዊ የምንለያይበት ጉዳይስ ምንድነው? ለምንድነው የእኛ ሐሳብ እነርሱ ጋር የእነርሱ ሐሳብ ደግሞ እኛ ጋር ቦታ የሌለው? ለምንድነው ፍቅርና መዋደድ የማይገባን? ለምንስ ይሆን ወደ መረዳት የማንጣራው?
በመልእክተኛው ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዘመን የነበሩ የእርሳቸው ባልደረባዎች አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በሐሳብ ተለያይተው ያውቃሉ፡፡ በልቦናቸው ግን አልተለያዩም በአስተሳሰባቸው (አዕምሮአዊ ጉዳዮች) ላይ ቢሆን እንጂ፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)ን በቅርብ ያገኙ፣ ብዙ ነገር ያወቁ ናቸው፡፡ እንግዲህ ለመለያየት የደረሱት እነዚህ ናቸው፡፡ በዘመናችን የምንወዛገብባቸው ጉዳዮች እጅግ ከመሠረታዊነት ሐሳብ የራቀና የማያጣላው ነው፡፡
ከሰሐቦች በኃላም በነበሩ ታላላቅ ዑለሞች ዘንድ ልዩነቶች ተከስተው ያውቃሉ፣ የመለያያና የጥል መንስኤዎች ሆነው ግን አያውቁም፡፡ በኢማሙ አቡ ሐኒፋ (ረ.ዐ) እና በኢማሙ ሻፊዒ (ረ.ዐ) ዘንድ የሐሳብ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ኢማሙ ሻፊዒ (ረ.ዐ) ድምጽ በሚወጣበት ሰላት ላይ “ቢስሚላህ” በድምጽ መቀራት አለበት ይላሉ፡፡ በተጨማሪ በፈጅር ሰላት ላይ ቁኑት ይቀሩ ነበር፡፡ በአቡ ሐኒፋ (ረ.ዐ) አመለካከት “ቢስሚላህ” በውስጥ ይነበብ ይሉ ነበር፡፡ ቁኑትም አይቀራም ይሉ ነበር፡፡ የሁለቱም ተከታዮች ግን በዚህ ቀላል በሚባል ልዩነት እንዳይጋጩም፣ ለማስተማር ኢማሙ ሻፊዒ ትልቅ ገድል ሠርተዋል፡፡ በአንድ ወቅት በአቡ ሐኒፋ መቃብር ዘንድ የተገኙት እኚሁ ታላቅ ሰው አቋማቸው ያልሆነውን ቁኑት በመቅራት ለአካባቢው መዝሀብ ክብር ሰጥተው አሰግደዋል፡፡ በሐሳብ ልዩነት ለተከታዮቻቸውና ለማኅበረሰቡ አስተምረዋል፡፡
የሰዎችን አዕምሮ ከማሳመን የሰዎችን ልቦና መቅናትና መርታት ይቀላል፡፡ ለወንድም መተናነስ፣ በክፉም በደጉም መቀራረቡን ማሳመርና መተጋገዝ፣ በልቦና መዋደድና በልዩነት መከባበርን ያመጣል፡፡ የልዩነት መኖር ከመፋቀርና ከመዋደድ ስለማያድግ በልዩነት ላይ ለመከባበር ፍቅርን እናስቀድም፡፡
በዓብዱረዛቅ ነጋሽ
(ከቅጽ 01፣ ቁጥር 08 – ግንቦት 2011 እትም የተወሰደ))