የኢማንና የስነ ምግባር ትስስር

1
4180

1) የመልካም ስነ ምግባር ክብደትና ፋይዳ

ስነ ምግባር በእስልምና ከፍተኛ ስፍራ ተሰጥቶታል፡፡ የአላህ መልእክተኛ የተላኩበትን ዓይነተኛ ዓላማ፣ የዳዕዋቸውን ጉልህ ሚና እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፡-

‹‹እኔ የተላክኩት መልካም ስነ ምግባራትን ለመሙላት ነው፡፡››

አላህ እርሳቸውን ሲያሞግስ እንዲህ ብሏል፡-

وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ

‹‹አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡›› (አል ቀለም 4)

ሙስሊሞች ከዓለም መሪነት ሚናቸው የተወገዱት ኢስላም ካመጣው መልካም ስነ ምግባር ርቀው በልዋጩ አንዴ የምእራቡን፣ ሌላ ጊዜ የምስራቁን እሴቶች በማማተራቸው ነው፡፡

ከአላህ መልእክተኛ ትምህርት በጥቂቱ

ኡሳማ ቢን ሸሪክ እንዲህ ሲል አስተላልፏል፡-

ከአላህ መልእክተኛ ዘንድ፣ ከራሳችን ላይ በራሪ ያረፈ ያህል አንገታችንን ደፍተን በጽናት ተቀምጠን እያለ ሰዎች መጡና፡-

‹‹ከአላህ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑ የአላህ ባሮች እነማን ናቸው?›› ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ‹‹ስነ ምግባራቸው የበለጠ መልካም የሆነው›› በማለት መለሱ፡፡ (ጦበራኒ)

በሌላ ዘገባ፡- ‹‹የሰው ልጅ ከሚታደላቸው  ስጦታዎች ሁሉ በላጩ የትኛው ነው?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ነቢዩም፡- ‹‹መልካም ስነ ምግባር›› በማለት መለሱ፡፡ (ቲሚዚ)

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ብልግና መናገርና መፈጸም የእስልምና አካል አይደለም፡፡ ከሰዎች መካከል እስልምናው ይበልጥ ያማረው በስነ ምግባር በላጬ ነው፡፡›› (ቲርሚዚ)

አብደላህ ቢን ዓምር እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ፡-

‹‹ከኔ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅና በእለተ ቂያማም ለኔ ይበልጥ የቀረበ ማረፊያ የሚኖረው ሰው ማን እንደሆነ ልንገራችሁን?›› በማለት ሁለት

ወይም ሦስት ጊዜ ደጋግመው ጠየቁ፡፡ ‹‹አዎ›› አሏቸው፡፡ ‹‹ስነ ምግባሩ ይበልጥ ያማረው ሰው ነው፡፡›› ሲሉ መለሱ፡፡ (አህመድ)

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በእለተ ቂያማ ከሙእሚን ሚዛን ላይ ከመልካም ስነ ምግባር የሚከብድ ነገር የለም፡፡ አላህ ባለጌን አይወድም፡፡ የልካም ስነ ምግባር ባለቤት ጿሚዎችና ሰጋጆች ከሚደርሱበት ደረጃ ይደርሳል፡፡›› (አህመድ)

2) መልካም ስነ ምግባር የኢማን ፍሬ ነው

ኢስላም ለስነ ምግባር ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቱ የተነሳ የኢማን ፍሬ አድርጎ ቆጥሮታል፡፡ ከዚህም በላይ የኢማን ሕልውና ተግባራዊ መገለጫ አድርጎታል፡፡ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በአላህና በመጭው ዓለም የሚያምን እንግዳውን ያክብር፡፡ በአላህና በመጭው ዓለም የሚያምን ዝምድናውን ይቀጥል፡፡ በአላህና በመጭው ዓለም የሚያምን መልካም ይናገር ወይም ዝም ይበል፡፡›› (ቡኻሪ)

ኢማን  የሚረጋገጠው በስነ ምግባርና በጥሩ ባህሪያት እሴቶች ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢስላም የደነገጋቸው የአምልኮ ተግባራት እንኳ ከሚያስገኟቸው በጎ ፍሬዎች መካከል አንዱ ስነ ምግባር ነው፡፡

ሶላትን አላህ ግዴታ ሲያደርግ እርሷን በአግባቡ የመስገድን ጥበብ እንዲህ ሲል ገልጿል፡-

إِنَّ الصَّلَاةَ تَنْهَىٰ عَنِ الْفَحْشَاءِ وَالْمُنكَرِ ۗ وَلَذِكْرُ اللَّهِ أَكْبَرُ ۗ وَاللَّهُ يَعْلَمُ مَا تَصْنَعُونَ

‹‹ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፡፡ ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡ አላህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው፤ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ያውቃል፡፡ ›› (አል አንከቡት 45)

ከመጥፎ ንግግሮች እና ድርጊቶች መራቅ የሶላት አብይ ውጤት ነው፡፡ በሐዲሰል ቁድስ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

‹‹ሶላቱን የምቀበለው በርሷ አማካይነት ለልዕልናዬ ሲል ለተናነስ፣ በርሷ ሰበብ ከፍጡራኔ ላይ ላይኮፈስ፣ እኔን በመሐጥየት ላይ ላልዘወተረ፣ ቀኑን እኔን በማሰታወስ፣ ለድሆች፣ መንገድ ላይ ስንቅላቋረጣቸው፣ ባሎቻቸውን በሞት ላጡ እንስቶችና አንዳች መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች በማዘን ላሳለፈ ነው፡፡›› (በዛር)

ዘካ ከሰዎች እጅ በሐይል የሚወሰድ ግብር ሳይሆን የማዘንን ስሜት ለማስረጽ፣ በተለያዩ መደቦች መካከል የመተዋወቅ፣ የመረዳዳትና የመግባባት ስሜት ይጠናከር ዘንድ ታልሞ የተደነገገ ኢባዳ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

خُذْ مِنْ أَمْوَالِهِمْ صَدَقَةً تُطَهِّرُهُمْ وَتُزَكِّيهِم بِهَا وَصَلِّ عَلَيْهِمْ

‹‹ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በእርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ፡፡ ለነሱም ጸልይላቸው፡፡›› (አል ተውባህ 111)

እንዲሁም የጾም ዓላማ ከምግብና ከመጠጥ ለተወሰነ ጊዜ ሰዎችን አቅቦ ማዋል አይደለም፡፡ ነፍስ ከሐራም የምትጠበቅበትን ስልጠና መስጠት እንጅ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ይህን እውነታ እንዲህ ሲሉ አጽንተዋል፡-

‹‹የሐሰት ንግግርንና በርሱ መስራትን ያልተዎ፣ ምግብና መጠጥ መተው ብቻ ለአላህ ግድ አይሰጠውም፡፡›› (ሙስሊም)

ቁርአን የጾምን በጎ ውጤት እንዲህ ሲል ዘክሯል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

‹‹ እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ ›› (አል በቀራህ 183)

ወደተቀደሰው የመካ ምድር በመሄድ ኢስላም አቅም ላላቸለው ተከታዮች ግዴት ያደረገውን የሐጅ ስርዓት ማከናወንን ምንም ዓይነት መልእክት

እና ጥበብ የሌለው ተራ ጉዞ አድርገው ሰዎች ሊያስቡት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሐይማኖቶች ትርጉም አልባ መንፈሳዊ ክንውኖችን መያዛቸው የተለመደ ነውና፡፡ በእርግጥ ይህ ከእስልምና ጋር በተያያዘ ስህተት ነው፡፡ አላህ ስለሐጅ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-

لَيْسَ عَلَيْكُمْ جُنَاحٌ أَن تَبْتَغُوا فَضْلًا مِّن رَّبِّكُمْ ۚ فَإِذَا أَفَضْتُم مِّنْ عَرَفَاتٍ فَاذْكُرُوا اللَّهَ عِندَ الْمَشْعَرِ الْحَرَامِ

‹‹ ሐጅ (ጊዜያቱ) የታወቁ ወሮች ናቸው፡፡ በእነርሱም ውስጥ ሐጅን (እንዲሠራ) ነፍሱን ያስገደደ ሰው በሐጅ ውስጥ ሴትን መገናኘት ማመጽም ክርክርም የለም፡፡ ከበጎም ሥራ የምትሠሩትን ሁሉ አላህ ያውቀዋል፡፡ ተሰነቁም፤ ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ (አላህን መፍራት) ነው፡፡ የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ! ፍሩኝ፡፡›› (አል በቀራህ 197)

ከላይ የሰጠው ጥቅል ማብራሪያ ሐይማኖት ከስነ ምግባር ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማሳየት በቂ ይመስለናል፡፡ በይዘትና በቅርጽ የሚለያዩ ዒባዳዎች የአላህ መልእክተኛ እንዲህ በማለት ካስቀመጡት ዓላማ ላይ ይገናኛሉ፡፡

‹‹እኔ የተላክኩት መልካም ስነ ምግባራትን ለማሟላት ነው፡፡››

እንዲህም ብለዋል፡-

‹‹ኢማን ከስልሳ ወይም ከሰባ በላይ ዘርፎች አሉት፡፡ ከፍተኛው ላኢላሐ ኢለላህ የሚለው ቃል ሲሆን፣ ዝቅተኛው ከመንገድ ላይ እንቅፋትን ማስወገድ ነው፡፡ ይሉኝታ (ሐያእ) የኢማን ዘርፍ ነው፡፡›› (ሙስሊም)

በዚህ አኳኋን መልካም ስነ ምግባሮች፣ ኢምንት ብለን የምናስባቸው ድርጊቶች ሳይቀሩ የትክክለኛው ኢማን አካሎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህም በላይ ምሉእ ኢማንን መጎናጸፍ ከስነ ምግባር መስተካከል ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ)፡-

‹‹ከሙእሚኖች መካከል እምነቱ ይበልጥ ምሉእ የሆነው የትኛው ነው?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፡- ‹‹ስነ ምግባሩ የበለጠ ያማረው፡፡›› በማለት መልሰዋል፡፡

አንድ ሰው በእምነቱ አማካይነት ቀልቡ ካልጸዳና ከአላህና ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ካልተስተካከለ ከስሯል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّهُ مَن يَأْتِ رَبَّهُ مُجْرِمًا فَإِنَّ لَهُ جَهَنَّمَ لَا يَمُوتُ فِيهَا وَلَا يَحْيَىٰ
وَمَن يَأْتِهِ مُؤْمِنًا قَدْ عَمِلَ الصَّالِحَاتِ فَأُولَٰئِكَ لَهُمُ الدَّرَجَاتُ الْعُلَىٰ
جَنَّاتُ عَدْنٍ تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا ۚ وَذَٰلِكَ جَزَاءُ مَن تَزَكَّىٰ

‹‹ እነሆ ከሓዲ ኾኖ ወደ ጌታው የሚመጣ ሰው ለእርሱ ገሀነም አለችው፡፡ በውስጧም አይሞትም ሕያውም አይኾን፡፡በጎ ሥራዎችን በእርግጥ የሠራ ምእመን ኾኖ የመጣውም ሰው እነዚያ ለእነሱ ከፍተኛ ደረጃዎች አሏቸው፡፡ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው የመኖሪያ ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ (አሏቸው)፡፡ ይህም የተጥራራ ሰው ምንዳ ነው፡፡ ›› (ጧሃ 74-76)

ቁርአን በመልካም ስነ ምግባር ከማዘዙ በፊት ‹‹ሙእሚኖች ሆይ፣›› በማለት ኢማንን እንደ ቀዳሚ መስፈርት ማቅረቡ የተለመደ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ትእዛዙን ያስከትላል፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَكُونُوا مَعَ الصَّادِقِينَ

‹‹ እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከእውነተኞቹም ጋር ኹኑ፡፡›› (አል ተውባህ 119)

የአላህ መልእክተኛ ተከታዮቻቸውን ከአልባሌ ንግግር አንደበታቸውን ያቅቡ ዘንድ ሲመክሩም ኢማንን እንደ መስፈርት አስቀድመው እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በአላህና በመጭው ዓለም ያመነ መልካም ይናገር ወይም ዝም ይበል፡፡››(ቡኻሪ)

በዚህ አኳኋን ቁርአንና ሱንና የእምነትን እውነተኛነትና ምሉእነት መሠረት አድርገው ፍሬያቸው በሕይወት መድረክ ላይ የሚታዩ መልካም ስነ ምግባሮችን በሰው ልጅ ልቦና ውስጥ ማስረጻቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ቁርአን ውስጥ በአልማኡን ምእራፍ በፍርዱ ቀን የማያምኑ ሰዎች ባህሪያት እንዲህ ተገልጾ ብታገኘው አይግረምህ፤

فَذَٰلِكَ الَّذِي يَدُعُّ الْيَتِيمَ
وَلَا يَحُضُّ عَلَىٰ طَعَامِ الْمِسْكِينِ
‹‹ ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው፡፡ ›› (አል ማኡን 2-3)

ገጽታው የጨለመ፣ ባህሪው የተወላገደ፣ ለማንም ደንታ ሳይኖረው እኩይ ድርጊት የሚፈጽምን ሰው አስመልክተው የአላህ መልእክተኛ  (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ሐያእና ኢማን የማይነጣጠሉ ባልንጀሮች ናቸው፡፡ አንደኛው ሲወገድ ሌላኛውም አብሮ ይወገዳል፡፡›› (ሐኪምና ጦበራኒ)

ጎረቤቶቹን በሚያውክን ግለሰብ እስልምና ጨካኝ ፍርድ ያስተላልፍበታል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ)፡- ‹‹በአላህ እምላለሁ አላመነም፡፡›› በማለት ሦስት ጊዜ ደጋግመው ተናገሩ፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ ማነው ያላመነው?›› ተብለው ተጠየቁ፡፡ ‹‹ጎረቤቱ ተንኮሉን የሚሰጋው ሰው፡፡›› ሲሉ መለሱ፡፡ (ቡኻሪ)


*****

 

1 COMMENT

  1. Comment:
    this is very interesting specially for youth brothers and for all Muslims. So keep it up to write such important ideas.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here