- ለኢባዳ ተቀባይነት ሁለት መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ እነርሱም
1) ስራው ለአላህ ብቻ ሲባል መፈጸም ይኖርበታል፡፡
2) አፈጻጸሙም አላህ በሸሪዓው ባስተማረው መልኩ ሊፈጸም ይገባል፡፡
የመጀመሪያውን መስፈርት በተመለከተ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹ ስራ የተባለ ሁሉ በኒያ ነው፡፡ ሁሉም ሰው የኒያውን ያገኛል፡፡ ስደቱ ለአላህና ለመልእክተኛው የሆነ ስደቱ ለአላህና ለመልእክተኛው ይሆናል፡፡ ስደቱ ሊያገኛት ላሰባት ዱንያ ወይም ሊያገባት ላሰባት እንስት ከሆነም ስደቱ ወደተሰደደበት ነገር ነው፡፡››
ይህ ሐዲስ የስራ ውስጣዊ መስፈርት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለአላህ ተብሎ ያልተሰራ ስራ ሁሉ ምንዳ አያስገኝም፡፡ ተቀባይነትም የለውም፡፡ ሰእድ ቢን አቡ ወቃስን በመጥቀስ ቡኻሪና ሙስሊም እንደዘገቡት ነቢዩ (ሶ.ወ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹የአላህን ውዴታ በመሻት በምትሰጠው ምጽዋት፣ ከሚስትህ አፍ ላይ በምታደርገው ጉርሻ ሳይቀር ምንዳ ታገኛለህ፡፡››
ሁለተኛውን መስፈርት በተመለከተ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹በዚህ በጉዳያችን ውስጥ የርሱ አካል ያልሆነን አዲስ ነገር የጨመረ ጭማሬው ውድቅ ነው፡፡›› (ቡኻሪና ሙስሊም)
ይህ ደግሞ የስራ ውጫዊ መስፈርት ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ወደ አላህ መቃረቢያ ባላደረጉት ስራ ወደ አላህ የተቃረበ ስራው ከንቱ ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለምሳሌ ዳንስን ወይም ሙዚቃን ማዳመጥን ወደ አላህ መቃረቢያ አድርጎ የያዘ፡፡ቀደምት ደጋግ ሙስሊሞች (ሰለፉነሷሊሂን) በዚህ ረገድ አርአያ ይሆኑናል፡፡ ዘይድ አልሻሚ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በሁሉም ነገር ላይ ኒያ እንዲኖረኝ እፈለጋለሁ፡፡ በምግብና በመጠጥ ላይ ሳይቀር፡፡››
ዳውድ ጧዊ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹መልካም ንያ የበጎ ነገሮች ሁሉ መቋጠሪያ ውል ሆኖ አገኘሁት፡፡››
ፉዳይል ቢን ኢያድ፡- ‹‹አላህ ከስራዎች መሐል ይበልጥ ንጹህና ትክክለኛውን እንጅ አይቀበልም፡፡›› በማለት ተናገሩ፡፡ ‹‹ይበልጥ ንጹህና ትክክለኛ ማለት ምን ማለት ነው፡፡›› ተብለው ተጠየቁ፡፡ ‹‹ይበልጥ ንጹህ ማለት ለአላህ ሲባል ብቻ የተፈጸመ ሲሆን፣ ይበልጥ ትክክለኛ ማለት የአላህ ሸሪዓ በደነገገው መልክ የተፈጸመ ማለት ነው፡፡›› ሲሉ መለሱ፡፡
****