የኢባዳ ትክክለኛና ሁለንተናዊ ትርጉም

0
6716

አላህ ፍጹም ፍቅር በተቀላቀለው ፍጹም ታዛዥነት እንድናመልከው ፈጥሮናል፡፡ ይህ ታዛዥነት በምን መልኩ፣ በየትኛው አኳኋን ይገለጻል?  ለዚህ ጥያቄያችሁ የምንሰጠው መልስ አድማሰ-ሰፊ የሆነውን የኢባዳ ጽንሰ ሐሳብ ይከስትልናል፡፡

የሐይማኖት ክንውኖችን ማጠቃለሉ

ኢማም ቢን ተይሚያህ፡- ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ፣ ጌታችሁን አምልኩ፡፡››[1]

የሚለውን የቁርአን አንቀጽ በተመለከተ፡- ‹‹ኢባዳ ምንድን ነው?፣ ዘርፎቹስ?›› ተብለው ተጠይቀው እንዲህ ሲሉ መልሰዋል፡-

‹‹ኢባዳ አላህ የሚወዳቸውን ግልጽም ስውርም የሆኑ ተግባራት እና ንግግሮች ሁሉ ያጠቃለለ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሶላት፣ ዘካ፣ ጾም፣ ሐጅ፣ እውነት መናገር፣ አደራን ማድረስ፣ የወላጆችን መብት መጠበቅ፣ ዝምድናን መቀጠል፣ ቃልኪዳንን መሙላት፣ በመልካም ማዘዝ፣ ከመጥፎ መከልከል፣ ካህድያንንና ሙናፊቆችን መፋለም፣ ለጎረቤት፣ ለየቲም፣ ለድሃ፣ ለባሪያ፣ እንዲሁም ከሰው አልፎ ለእንስሳ በጎ መዋል፣ ዱዓ፣ ዚክር፣ ቁርአን መቅራትና መሰል መንፈሳዊ ተግባራት፣ አላህንና መልእክተኛውን መውደድ፣ አላህን መፍራት፣ ወደርሱ መመለስ፣ ስራን በኢኽላስ መፈጸም፣ ውሳኔውን በትእግስት ማስተናገድ፣ ለጸጋዎቹ ምስጋና ማድረስ፣ ፍርዱን መውደድ፣ በርሱ መመካት፣ እዝነቱን ተስፋ ማድረግ፣ ቅጣቱን መፍራትና መሰል ድርጊቶች ሁሉ ኢባዳዎች ናቸው’››

ኢብን ተይሚያህ እንዳብራሩት የኢባዳ መስክ እጅግ ሰፊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ኢባዳ በተለመዱ መንፈሳዊ ክንውኖች ብቻ የሚገደብ አይደለም፡፡ ከነርሱ በጣም ይሰፋል’ ከፈርድ በተጨማሪ ሱንና ኢባዳዎች፣ ቁርአን መቅራት፣ ዱዓ፣ ኢስቲግፋር፣ ተስቢህ፣ ተህሊል፣ ተክቢር፣ ተህሚድ እና ሌሎችንም ዚክሮች ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ የፍጡራንን መብት ሁሉም ያጠቃልላል፡፡ ለምሳሌ የወላጆችን መብት መጠበቅ፣ ዝምድናን መቀጠል፣ ለየቲም፣ ለድሃና መንገድ ላይ ስንቅ ላለቀበት በጎ መዋል፣ ለደካሞችና ለእንስሳት ማዘን፡፡ ሰብአዊ የሞራል ይዞታዎችን ሁሉም ያጠቃልላል፡፡ ‹‹አምላካዊ ስን ምግባሮች›› በመባል የሚታወቁትን ተግባራት፣ ለምሳሌ

አላህንና መልእክተኛውን መውደድ፣ አላህን መፍራት፣ ወደርሱ መመለስ፣ ኢኽላስ፣ ውሳኔውን መታገስ፣ ማመሰገን፣ ፍርዱን መውደድ፣ በርሱ መመካት፣ እዝነቱን ተስፋ ማድረግና መሰል የቀልብ ክንውኖችን ሁሉም ያጠቃልላል፡፡ የዲን አስኳል የሆኑትን  ክንውኖችም ያጠቃልላል፡፡ እነርሱም በመልካም ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል፣ እንዲሁም ካህድያንና ሙናፊቆችን በአላህ መንገድ መፋለም ናቸው፡፡ [2]

በሰው ልጅ ቁሳዊ ሕይወት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ስፍራ ያለውን አንድ ነገርም ያጠቃልላል፡፡ ሸይኹል ኢስላም ቢን ተይሚያህ ‹አል ዑበዲያህ›› ከተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ በሌላ ስፍራ አውስተውታል፡፡ እርሱም የምክንያትና ውጤት (Cause and Effect) ተፈጠሯዊ ሕግን በመረዳት ለመልካም ውጤት የሚያበቁ ምክንያቶችን መከተልና ከአላህ የተፈጥሮ ሕግ አኳያ ሕይወትን መምራት ነው፡፡ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹አላህ ባሮቹን ያዘዘበትን ሰበብ ሁሉ ማድረስም ኢባዳ ነው፡፡››

ከዚህ በተጨማሪ ሸይኹል ኢስላም ቢን ተይሚያህ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ሐይማኖት ባጠቃላይ በኢባዳ ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ ይካተታል፡፡ ምክንያቱም ዲን የሚለው ቃል መተናነስንና መዋረድን በውስጡ ይዟል፡፡ በዓረብኛ ‹‹ዲንቱሁ›› ማለት አዋረድኩት ማለት ነው፡፡ ‹‹የዲኑ ሊላሂ›› ስንል ‹‹አላህን ያመልካልም፣ ይታዘዛል ለርሱ ይተናነሳል›› ማለታችን ነው፡፡

የአላህ ዲን እርሱ ማምለክ፣ መታዘዝና ለርሱ መተናነስ ነው፡፡ ኢባዳም መሠረታዊ ትርጉሙ መተናነስ በመሆኑ የኢባዳ እና የዲን ትርጉሞች ከቋንቋም ከሸሪዓም አኳያ ይመሳሰላሉ፡፡

ኢባዳ ሕይወትን ሁሉ ያጠቃልላል

ኢባዳ መላ ሕይወትን ያስተካክላል፡፡ ጉዳዮቿን ያደራጃል፡፡ ከአመጋገብና ከአጠጣጥ ስርዓት ጀምሮ እስከ መንግስት አስተዳደር፣ የፍትህ እና የገንዘብ ስርዓት፣ እስቪልና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋት፣ እስከ መንግስታት የሰላምና የጦርነት ግንኙነት ድረስ ሁሉንም የሕይወት ዘርፎች ያካተተ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ቁርአን ለሙእሚኖች የተለያዩ የሕይወት ገጽታዎችን በማውሳት ትእዛዝ ሲያስተላልፍ እናነባለን፡፡ ለምሳሌ በአልበቀራህ ምእራፍ ውስጥ ‹‹ኩቲበ አለይኩም›› (በናንተ ላይ ግድ ሆኗል) በሚል መወጠኛ ተከታዮቹ ትእዛዛት ሰፍረዋል፡-

وَلَكُمْ فِي الْقِصَاصِ حَيَاةٌ يَا أُولِي الْأَلْبَابِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

ለእናንተም ባለ አእምሮዎች ሆይ! በማመሳሰል (ሕግ) ውስጥ ሕይወት አላችሁ፡፡ ትጠነቀቁ ዘንድ (ገዳይን መግደል ተደነገገላችሁ)፡፡ (አል በቀራህ ፤178)

كُتِبَ عَلَيْكُمْ إِذَا حَضَرَ أَحَدَكُمُ الْمَوْتُ إِن تَرَكَ خَيْرًا الْوَصِيَّةُ لِلْوَالِدَيْنِ وَالْأَقْرَبِينَ بِالْمَعْرُوفِ ۖ حَقًّا عَلَى الْمُتَّقِينَ

አንዳችሁን ሞት በመጣበት ጊዜ ሀብትን ቢተው ለወላጆችና ለቅርብ ዘመዶች በበጎ መናዘዝ በናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ (ይህ) በጥንቁቆቹ ላይ እርግጠኛ ድንጋጌ ተደነገገ፡፡ (አል በቀራህ ፤180)

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡(አል በቀራህ ፤183)

كُتِبَ عَلَيْكُمُ الْقِتَالُ وَهُوَ كُرْهٌ لَّكُمْ ۖ وَعَسَىٰ أَن تَكْرَهُوا شَيْئًا وَهُوَ خَيْرٌ لَّكُمْ ۖ وَعَسَىٰ أَن تُحِبُّوا شَيْئًا وَهُوَ شَرٌّ لَّكُمْ ۗ وَاللَّهُ يَعْلَمُ وَأَنتُمْ لَا تَعْلَمُونَ

መጋደል እርሱ ለእናንተ የተጠላ ሲሆን በእናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ አንዳች ነገርን እርሱ ለናንተ የበለጠ ሲሆን የምትጠሉት መኾናችሁ ተረጋገጠ፡፡ አንዳችንም ነገር እርሱ ለናንተ መጥፎ ሲሆን የምትወዱት መሆናችሁ ተረጋገጠ፡፡ አላህም (የሚሻላችሁን) ያውቃል ግን እናንተ አታውቁም፡፡(አል በቀራህ ፤216)

በነዚህ አናቅጽ የሰፈሩ የግድያ ወንጀል ቅጣትን፣ ኑዛዜን፣ ጾምንና ውጊያን የሚመለከቱ ትእዛዛት በአማኞች ላይ ግድ የተደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህን ትእዛዛት በመፈጸም አላህን ሊያመልኩ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡

የኢባዳ መስክ ከዚህም በጣም ይሰፋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

قُلْ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ
لَا شَرِيكَ لَهُ ۖ وَبِذَٰلِكَ أُمِرْتُ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُسْلِمِينَ

«ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው» በል፡፡ «ለእርሱ ተጋሪ የለውም፡፡ በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ፡፡ እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ» (በል)፡፡(አል በአንዓም ፤162-163)

እኛ በተለምዶ የምናከናውናቸውን የእለት ከእለት ተግባራት ሳይቀር ያካትታል፡፡ አቡ ኡማማን በመጥቀስ ኢማም አህመድ እንደዘገቡት ነቢዩ (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹አላህ፡- ባሪያ እኔን ከሚያመልክባቸው ነገሮች መካከል በላጩ ለኔ ታማኝ መሆኑ ነው፣ ብሏል፡፡›› አቡ ሁረይራ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹አላህ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ነገርን እንጅ አይቀበልም፡፡ አላህ መልእክተኞችን ባዘዘበት ነገር አማኞችንም አዟል፡፡›› እንዲህ ብሏል፡-

يَا أَيُّهَا الرُّسُلُ كُلُوا مِنَ الطَّيِّبَاتِ وَاعْمَلُوا صَالِحًا ۖ إِنِّي بِمَا تَعْمَلُونَ عَلِيمٌ

እናንተ መልክተኞች ሆይ! ከተፈቀዱት ምግቦች ብሉ፡፡ በጎ ሥራንም ሥሩ፡፡ እኔ የምተሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነኝ፡፡(አል ሙእሚኑን ፤51)

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُلُوا مِن طَيِّبَاتِ مَا رَزَقْنَاكُمْ وَاشْكُرُوا لِلَّهِ إِن كُنتُمْ إِيَّاهُ تَعْبُدُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከነዚያ ከሰጠናችሁ ጣፋጮች ብሉ፡፡ ለአላህም እርሱን ብቻ የምትገዙ እንደኾናችሁ አመስግኑ፡፡(አል በቀራህ ፤172)

ከዚያም ረዥም መንገድ የተጓዙ፣ ጸጉ የተንጨባረረ፣ አቧራ የለበሰ፣ ወደ ጌታውም፡- አምላኬ ሆይ፣ እያለ እጁን የሚዘረጋ አንድ ሰው አወሱ፡፡ ‹‹ምግቡ ሐራም፣ መጠጡ ሐራም፣ አልባሳቱ ሐራምና አካሉ በሐራም የተገነባ ሆኖ እያለ ዱዓው እንዴት ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል?›› አለም’ (ሙስሊም)

ይህ ሐዲስ በስራ፣ በንግግርም ሆነ በእምነት ሐላል ነገሮችን ብቻ እንድንመርጥ ያነሳሳናል፡፡ አላህ በይዩልኝና በኩራት የተበከለን ስራ አይቀበልም፡፡  ከገንዘብም ሐላልን እንጅ  አይቀበልም፡፡ አቡ ሁረይራ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹የሰው ልጅ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሉ ምጽዋት አለበት፡፡ ጸሐይ በምትወጣበት በእያንዳንዱ ቀን ሁለት ሰዎችን በፍትህ መዳኘት ሶደቃ ነው፡፡ አንድን ሰው ከመጓጓዣው ማድረስህ ወይም እቃውን ማቀበልህ ሶደቃ ነው፡፡ ከመንገድ ላይ እንቅፋትን ማስወገድህ ሶደቃ ነው፡፡›› (ቡኻሪና ሙስሊም)

አቡ ዘር ባስተላለፉት ሐዲስ የአላህ መልእክተኛ ‹‹ከናንተ ውስጥ አንዳችሁ ጾታዊ ግንኙነት መፈጸሙ ሶደቃ ነው፡፡›› አሉ፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ ስጋዊ ስሜታችንን ስላረካን ምንዳ ይጻፍልናልን? ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ‹‹እስኪ ንገሩኝ፣ በሐራም አድርጋችሁት ቢሆን ኖሮ ወንጀል ይሆንባችሁ አልነበረምን? በሐላል ስታደርጉት ደግሞ ምንዳ ይጻፍላችኋል፡፡›› ሲሉ መለሱ፡፡ (ሙስሊም)

ሙስሊም መላ ሕይወቱንና ጊዜውን ኢባዳ ማድረግ ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው በእያንዳንዱ በጎ እንቅሰቃሴው የአላህን ውዴታ ሲነያ ነው፡፡ ይህ ሲሆን አካሉ በስራ  ሲደክም የዋለ ሰራተኛ አላህን አምላኪ

ይሆናል፡፡ እንቅልፍ አጥቶ ትምህርቱን ሲያጠና ያነጋ ተማሪ አላህን እያመለከ ነው፡፡ ተመራማሪ ምርምር ሲየደርግ አላህን እያመለከ ነው፡፡ ለልጆቿ እና ለባሏ ደስታና ረፍት ደፋ ቀና የምትል እንስት አላህን እያመለከች ነው፡፡

ይህ ሲሆን ኢባዳ ለአላህ የመታዘዝና የመተናነስ፣ ለፈቃዱ የማደር እና የፍጹም ፍቅር ዳርቻ ይሆናል፡፡ ፍቅር፣ አቅም በፈቀደ መጠን የአላህን ዲን ለመርዳት የመስራትንና የማይነጥፍን የበጎ ስራ ስሜት ያቀጣጥላል’ ሰውየው እንቅስቃሴና ረፍቱን፣ ስሜቱን እና ጉጉቱን ሁሉ እውነትን፣ ፍትህንና ዲኑን ለመርዳት ተግባር እንዲያውለው ያደርገዋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا ارْكَعُوا وَاسْجُدُوا وَاعْبُدُوا رَبَّكُمْ وَافْعَلُوا الْخَيْرَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ
وَجَاهِدُوا فِي اللَّهِ حَقَّ جِهَادِهِ ۚ هُوَ اجْتَبَاكُمْ وَمَا جَعَلَ عَلَيْكُمْ فِي الدِّينِ مِنْ حَرَجٍ ۚ مِّلَّةَ أَبِيكُمْ إِبْرَاهِيمَ ۚ هُوَ سَمَّاكُمُ الْمُسْلِمِينَ مِن قَبْلُ وَفِي هَٰذَا لِيَكُونَ الرَّسُولُ شَهِيدًا عَلَيْكُمْ وَتَكُونُوا شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ ۚ فَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَآتُوا الزَّكَاةَ وَاعْتَصِمُوا بِاللَّهِ هُوَ مَوْلَاكُمْ ۖ فَنِعْمَ الْمَوْلَىٰ وَنِعْمَ النَّصِيرُ

እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! (በስግደታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣ ጌታችሁንም ተገዙ፣ በጎንም ነገር ሥሩ፣ ልትድኑ ይከጀልላችኋልና፡፡ በአላህም ሃይማኖት ተገቢውን ትግል ታገሉ፡፡ እርሱ መርጧችኋል፡፡ በናንተም ላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ምንም ችግር አላደረገባችሁም፡፡ የአባታችሁን የኢብራሂምን ሃይማኖት ተከተሉ፡፡ እርሱ ከዚህ በፊት ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል፡፡ በዚህም (ቁርኣን)፤ መልክተኛው በእናንተ ላይ መስካሪ እንዲሆን እናንተም በሰዎቹ ላይ መስካሪዎች እንድትኾኑ (ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል)፡፡ ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፣ ዘካንም ስጡ፣ በአላህም ተጠበቁ፣ እርሱ ረዳታችሁ ነው፡፡ (እርሱ) ምን ያምር ጠባቂ! ምን ያምርም ረዳት! (አል ሐጅ ፤77-78)

አላህ በዚህ አንቀጽ በመጀመሪያ በስግደት፣ ቀጥሎም በኢባዳ አዘዘ፡፡ ኢባዳ ከሶላት የሰፋ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ኢባዳ የግዴታ (ፈርድ) ነገሮችን ሁሉ ያካትታል፡፡ መስኩ ሰፍቶም የሰውን ልጅ እንቅስቃሴና ውስጣዊ ስሜት ሁሉም ያጠቃልላል፡፡ ቀልብ ወደ አላህ ከዞረ የሰው ልጅ የሕይወት እንቅስቃሴ ሁሉ፣ ከሕይወት ጸጋዎች የሚያገኛቸው ጣፋጭ ነገሮች ሁሉ ሳይቀሩ፣ የበጎ ስራ መዝገቡን የሚያወፍሩ ኢባዳዎች ይሁኑለታል፡፡[3]

የቀንና የሌሊት አደቦች፣ ሰውየው ምንጊዜም ከአላህ ጋር እንዳለ እንዲሰማው ያደርጉታል፡፡ ጠዋት ነቅቶ ማታ ተመልሶ እስኪተኛ ድረስ፡፡ ለምሳሌ ከእንቅልፉ ሲነቃ አላህን ያወሳል፡፡ የአብሮነት ስሜት ይሰማዋል’ እንዲህ ይላል፡-

‹‹ከገደለን በኋላ ሕያው ያደረገን አምላክ ምስጋና የድረሰው፡፡ መመለሻም ወደርሱው ነው፡፡››

ልብሱን ሲለብስ፣ መሰታውት ሲያይ፣ ከቤቱ ሲወጣ፣ ወደ ገበያ ቦታ ሲገባና ሲወጣ ወዘተ ማታ ተመልሶ እስኪተኛ ድረስ የአላህ አብሮነት ለአፍታ ሳይለየው ይውላል፡፡ ይህን በተመለከተ የኢማም ነወዊን ‹‹አደቡል የውሚ ወለይላ›› እና የሸህ አቡበክር ጀዛኢሪን ‹‹ሚንሐጀል ሙስሊም›› እንዲያነቡ ተጋብዘዋል፡፡

በላጩ ኢባዳ

ኢባዳ በኢስላም እይታ ከላይ እንደተብራራው ሁለንተናዊ ከሆነ ከኢባዳዎች መካከል የትኛው በላጬ፣ ከአላህ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ፣ ደረጃውም ይበልጥ ከፍ ያለው ኢባዳ የትኛው ነው?  ኢማም ቢን አልቀይም ‹‹መዳሪጁ ሳሊኪን›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ በላጬ ኢባዳ እንደየ ወቅቱ እንደሚለያይ ጽፈዋል፡፡ እንዲህ ይሉናል፡-

በላጩ ኢባዳ በየትኛውም ጊዜ አላህ የሚወደውንና ወቅቱ የሚጠይቀውን በጎ ተግባር መፈጸም ነው፡፡ በጅሃድ ወቅት በላጩ ኢባዳ ጅሃድ ይሆናል’

ሱንና ዚክሮችን፣ የሌሊት ሶላቶችንና ሱንና ጾሞችን ሌላው ቀርቶ ፈርድ ኢባዳን ማሟላትን የሚያስቀር ቢሆንም እንኳ፡፡ እንግዳ በሚመጣ ጊዜ እንግዳውን ማስተናገድ እና ሱንና ኢባዳዎችን ትቶ እርሱን መንከባከብ በላጭ ኢባዳ ይሆናል፡፡ የባለቤትንና የቤተሰብን መብት ማድረስ ተገቢ በሚሆንበት ሰአትም እንደዚሁ፡፡ በሱህር ወቅት በላጩ ኢባዳ በሶላት፣ በቁርአን፣ በዱዓ፣ በዚክርና በኢስቲግፋር መጠመድ ይሆናል፡፡ በትምህርት ወቅት በላጩ ኢባዳ ተማሪውን በሚገባ ማስተማር፣ አላዋቂን ማሳወቅ ይሆናል፡፡ በአዛን ወቅት በላጩ ኢባዳ ሌሎች ኢባዳዎችን ትቶ ለሙአዚኑ ምላሽ መስጠት ይሆናል፡፡ በአምስት ወቅት ሶላቶች ጊዜ በላጩ ኢባዳ ሶላቶችን አሟልቶና አጣርቶ በወቅታቸው መፈጸም ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት ወደመስጊድ መሄድም ተገቢ ነው፡፡ መስጊዱ ራቅ ካለ ምንዳው የበለጠ ይበረክታል፡፡ የተቸገረን መርዳት ግድ የሚሆንበት አጋጣሚ ሲፈጠር በላጩ ኢባዳ ሌሎች ሰናይ ተግባራትን ትቶ እሱን መርዳት ይሆናል፡፡ በቁርአን ወቅት ቁርአን መቅራት መልእክቱን ለመገንዘብና ለማስተንተን፣ አላህ የሚያናግርህ ያህል ተሰምቶህ ቀልብህን መሰብሰብና ትእዛዙን ለመፈጸም መወሰን በላጭ ኢባዳ ነው፡፡

አረፋ ላይ በቆሙ ጊዜ በላጩ ኢባዳ በዱዓና በዚክር መመሰጥ ነው፡፡ አካልን በማድከም ከዚህ ተመስጦ የሚያቅብን ጾም መከልከልም ተገቢ ነው፡፡ በአስሩ የዙል ሂጃ ቀናት በላጬ ኢባዳ አምልኮንና ዚክርን፣ በተለይም ተክቢር፣ ተህሊል እና ተህሚድ ማብዛት ነው፡፡ በረመዳን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት በላጬ ኢባዳ ከሰዎች ጋር መቀላቀልን አቁሞ መስጊድ ውስጥ በመገለል ኢእቲካፍ ማድረግ ነው፡፡ ሙስሊም ወንድምህ በታመመ ወይም በሞተ ጊዜ በላጬ ኢባዳ እርሱን መጠየቅ፣ ጀናዛውን መሸኘት ይሆናል፡፡››

በጥቅሉ በየትኛውም ጊዜ በላጬ ኢባዳ በዚያ ወቅት የአላህን ትእዛዝ ከምንም ነገር ማስቀደም፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ተግባርና ሐላፊነት መወጣት ነው፡፡ ኢብኑል ቀይም እንዲህ አይነት ሰዎችን ‹‹ያልተገደበ አምልኮ (ኢባዳ ሙጥለቃ) ባለቤቶች›› ይሏቸዋል፡፡ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

‹‹የዚህ አይነት ኢባዳ ባለቤት ዓላማው የአላህን ውዴታ የትም ቢሆን መከተል ነው፡፡ የኢባዳ ምህዋሩ እርሱ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ የኢባዳ እርከኖች ውስጥ ያለ ገደብ ይንቀሳቀሳል፡፡ አንዱ እርከን በተገለጸለት ጊዜ ሌላኛው እስኪከሰትለት ድረስ ወደርሱ ይሄዳል፡፡ በርሱ ይጠመዳል፡፡ የጉዞ ባህሪው እስከ ፍጻሜው ይህን ይመስላል፡፡ አሊሞችን ስታይ ከነርሱ ጋር ታየዋለህ፡፡ አቢዶችን ስታይ ከነርሱ ጋር ታየዋለህ፡፡ ሙጃሂዶችን ስታይ ከነርሱ ጋር ታየዋለህ፡፡ ዛኪሮችን ስታይ ከነርሱ ጋር ታየዋለህ፡፡ በጎ ሰዎችን ስታይ ከነርሱ ጋር ታየዋለህ፡፡ ገደብ አልባ ባሪያ ማለት ይህ ነው፡፡ ለአምልኮው ወሰን የለውም፡፡ በጎ ስራውን አንዳች ርእስ አይገድበውም፡፡ ለነፍሱ ሳይሆን ለአላህ ፈቃድና ፍላጎት ያድራል፡፡ ነፍስያው የምትወደውን ነገር ትቶ አምላኩን የሚያስደስትን በጎ ነገር ይፈጽማል፡፡ ‹አንተን ብቻ እናመልካለን፣ አንተን ብቻም እገዛ እንጠይቃለን›› የሚለው ቁርአናዊ መልእክት በእርግጥ የተተገበረው በዚህ ሰው ነው፡፡

የአላህ ትእዛዝ በዞረበት ሁሉ ይዞራል፡፡ ልጓሙን ለርሱ አስረክቦ እርሱን ብቻ ይከተላል፡፡ ከገባበት ይገባል፣ ከወጣበት ይወጣል፡፡ እርሱን ያጸደቀውን ያጸድቃል፣ የጠላውን ይኮንናል፡፡ የትም ቦታ ቢያርፍ ጠቃሚ እንደሆነ ዝናብ ወይም ደግሞ ቅጠሏ እንኳ በከንቱ እንደማይወድቅ፣ ሁለነገሯ እሰኋ ሳይቀር እንደሚጠቅም የዘንባባ ተክል ማለት ነው፡፡ የአላህ ትእዛዝ ሲጣስ፣ ክልክሉ ሲደፈር ይቆጣል፡፡››[4]


[1] አል በቀራህ ፤21

[2] አል ኢባዳ ፊል ኢስላም- ዶክተር ዩሱፍ አልቀረዷዊ

[3] አል ኢባዳ- ጀውሃሩሃ ወአፋቁሐ፣ አል ሸይኽ ሙሐመድ አብደላህ አል ኸጢብ (በማሳጠር)

[4] መዳሪጀ አሳሊኪን ቢን አልቀይም ቅ 1

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here