አላህ የሰውን ልጅ የፈጠረበትን ዓላማ

3
8277
 
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ

ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡(አል ዛሪያት 56)


 ሀ) የሰው ልጅ የተፈጠረበት ዓላማ፡-

አላህ የሰውን ልጅ ለምን ፈጠረው? የሰው ልጅ የሕይወት ተልእኮ ምንድን ነው? እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ሊጠይቀው፣ መልሱንም በእርጋታ ሊያስብበት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ የትኛውም ስህተት መጥፎ ውጤቱ የቱን ያህል ቢሆንም ይቅር ሊባል ይችላል፡፡ የሰው ልጅ የሕልውናውን ሚስጥር፣ የሕይወቱን ዓላማ፣ በምድር ላይ ያለውን ተልእኮ አለማወቁ ግን ፈጽሞ ይቅር የሚባል አይደለም፡፡

አንድን ነገር የሚሰራ አካል፣ ያን ነገር የሰራበትን ዓላማና ሚስጥር ያውቃል፡፡ ስለዚህም የሰው ልጅ ፈጣሪና የጉዳዮቹ አስተናባሪ የሆነውን አምላክ ‹‹የሰውን ልጅ ለምን ፈጠርከው?›› በማለት እንጠይቀው፡፡ አላህ መልሱን በተከበረው መጽሐፍ ሰጥቶናል፡፡ የሰው ልጅ የተፈጠረው በምድር ላይ የርሱ ምትክ (ኸሊፋ) እንዲሆን መሆኑን ነግሮናል፡፡ አደምን የፈጠረበትን ዓላማ ሲያብራራ ይህንኑ ገልጿል፡፡ መላእክትም የርሱን ቦታ መመኘታቸውን ተመልክቷል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَإِذْ قَالَ رَبُّكَ لِلْمَلَائِكَةِ إِنِّي جَاعِلٌ فِي الْأَرْضِ خَلِيفَةً ۖ قَالُوا أَتَجْعَلُ فِيهَا مَن يُفْسِدُ فِيهَا وَيَسْفِكُ الدِّمَاءَ وَنَحْنُ نُسَبِّحُ بِحَمْدِكَ وَنُقَدِّسُ لَكَ ۖ قَالَ إِنِّي أَعْلَمُ مَا لَا تَعْلَمُونَ

(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤» ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ እነርሱም) «እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» አሉ፡፡(አላህ) «እኔ የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ» አላቸው፡፡ (አል በቀራህ 30)

የዚህ ኸሊፋነት የመጀመሪያው ሐላፊነት ሰውየው አምላኩን በሚገባ አውቆ፣ በአግባቡ ማምለኩ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ وَمِنَ الْأَرْضِ مِثْلَهُنَّ يَتَنَزَّلُ الْأَمْرُ بَيْنَهُنَّ لِتَعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ وَأَنَّ اللَّهَ قَدْ أَحَاطَ بِكُلِّ شَيْءٍ عِلْمًا

«አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፡፡ ከምድርም መሰላቸውን (ፈጥሮአል)፤ በመካከላቸው ትእዛዙ ይወርዳል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አላህም በነገሩ ሁሉ በዕውቀት ያካበበ መኾኑን በዕውቀት ያካበበ መኾኑን ታወቁ ዘንድ (ይህንን አሳወቃችሁ)፡፡» (አል ጦላቅ፤12)[1]

እንዲህም ብሏል፡-

وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ

ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ (አል ዛሪያት 56)

ይህ ቁርአናዊ መልእከት ከአራት ቃላት የተዋቀረ ቢሆንም የሕልውናችንን ታላቅ እውነታ፣ የመፈጠራችንን ጥበብ በውስጡ ይዟል፡፡ እርሱም አላህን በብቸኝነት ማምለክ ነው፡፡ ሙዓዝ ኢብን ጀበል የሚከተለውን አውግተዋል፡-

ከአላህ መልእክተኛ ጋር አብረን በመጓዝ ላይ እያለን፡- ‹‹ሙዓዝ ሆይ፣ አላህ በባሮቹ ላይ ያለውን መብት ታውቃለህን?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ‹‹አላህና መልእክተኛው ያውቃሉ›› አልኳቸው፡፡ ‹‹አላህን በርሱ ላይ ምንንም ነገር ሳያጋሩ በብቸኝነት ሊያመልኩት ነው ›› አሉኝ፡፡   (ቡኻሪና ሙስሊም)

የሰው ልጆችና አጋንንት የተፈጠሩበት ዓላማ ዒባዳ በተሰኘው በዚህ ተግባር ይገለጻል፡፡ ይህን ተግባር በትክክል የፈጸመ የሕይወቱን ግብ አሳክቷል፡፡ በአግባቡ ያልተወጣው ደግሞ የሕልውናውን ዓላማ ስቷል፡፡ ሕይወቱም ተግባርና ዓላማ አጥታለች፡፡ የመጀመሪያና መሠረታዊ እሴቷን ከምታገኝበት የሕልውና ትርጉሟ ነጥፋለች፡፡ በዚህ ተግባር የሰው ልጅ፣ አላህ እርሱን የፈጠረበትን ዋነኛ ዓላማ ያከናውናል፡፡ እርሱም አላህን ማምለክ ሲሆን፣ በምድር ላይ ለአላህ ወኪልነት የሚያበቃውዋነኛ ተግባርም ይህ ነው፡፡›› [2]

አላህ በሐዲሰል ቁድስ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ባሮቼ ሆይ፣ እናንተን የፈጠርኳችሁ የብቸኝነት ስሜቴን እንድትገፉልኝ፣ የቁጥር አናሳነቴን እንድታበዙልኝ፣ የተሳነኝ አንዳች ነገር ኖሮ እርሱን ለመፈጸም እንድታግዙኝ፣ አንዳች ጥቅም እንድታስገኙልኝ ወይም ጉዳትን እንድትከላከሉልኝ አይደለም፡፡ የፈጠርኳችሁ ለረዥም ጊዜ እንድታመልኩኝ፣ ብዙ ጊዜ እንድታወሱኝና ጠዋት ማታ ክብሬን እንድትመሰክሩ ነው፡፡››

የሁሉም ነብያት ጥሪ

አላህን ብቻ ማምለክ አላህ ከሰው ልጅ ጋር የተጋባው እና ከአፈጣጠራቸው ውስጥ በቀደር ብእር የመዘገበው ቃል ኪዳን ነው፡፡ እንዲህ ብሏል፡-

۞ أَلَمْ أَعْهَدْ إِلَيْكُمْ يَا بَنِي آدَمَ أَن لَّا تَعْبُدُوا الشَّيْطَانَ ۖ إِنَّهُ لَكُمْ عَدُوٌّ مُّبِينٌ

የአደም ልጆች ሆይ! ሰይጣንን አትገዙ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና በማለት ወደእናንተ አላዘዝኩምን? ተገዙኝም፤ ይህ ቀጥተኘ መንገድ ነው፤ (በማለትም)፡፡ (ያሲን ፤60-61)

ቁርአን በተከታዩ አንቀጽ የገለጸው ይህን በአላህና በባሮቹ መካከል የተደረገ ቃል ኪዳን ነው፡-

وَإِذْ أَخَذَ رَبُّكَ مِن بَنِي آدَمَ مِن ظُهُورِهِمْ ذُرِّيَّتَهُمْ وَأَشْهَدَهُمْ عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ أَلَسْتُ بِرَبِّكُمْ ۖ قَالُوا بَلَىٰ ۛ شَهِدْنَا ۛ أَن تَقُولُوا يَوْمَ الْقِيَامَةِ إِنَّا كُنَّا عَنْ هَٰذَا غَافِلِينَ

ጌታህም ከአደም ልጆች ከጀርቦቻቸው ዘሮቻቸውን ባወጣና «ጌታችሁ አይደለሁምን» ሲል በነፍሶቻቸው ላይ ባስመሰከራቸው ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)፡፡ «ጌታችን ነህ መሰከርን» አሉ፡፡ «በትንሣኤ ቀን ከዚህ (ኪዳን) ዘንጊዎች ነበርን እንዳትሉ፡፡» ወይም «(ጣዖታትን) ያጋሩት ከእኛ በፊት የነበሩት አባቶቻችን ብቻ ናቸው፡፡ እኛም ከእነሱ በኋላ የኾን ዘሮች ነበርን፡፡ አጥፊዎቹ በሠሩት ታጠፋናለህን» እንዳትሉ (አስመሰከርናችሁ)፡፡ (አል አዕራፍ ፤172-173)

ከዚህ አኳያ ወደ ሰው ልጆች የተላኩ የአላህ መልእክተኞች ሁሉ ዋነኛ ጥሪ ይህን መልእከት የሚያስታውስ መሆኑ አያስገርምም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ

«በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፡፡»(አል ነህል ፤36)

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ

«ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡» (አል አንቢያእ ፤25)

የበርካታ ነብያትን ካወሳ በኋላ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّ هَٰذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاعْبُدُونِ

«ይህች (ሕግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ፡፡»(አል አንቢያእ ፤92)

ሁሉም በኢባዳ ታዘዋል፡፡ ነቢዩ ሙሐመድንም እንዲህ ሲል አዟቸዋል፡-

وَاعْبُدْ رَبَّكَ حَتَّىٰ يَأْتِيَكَ الْيَقِينُ

«እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡» (አል ሂጅር ፤99)

ኢሳ ሕዝባቸው በርሳቸው ላይ የለጠፈውን ቅጥፈት ካስተባበሉ በኋላ የተገዥነትን አደብ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡-

مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَا أَمَرْتَنِي بِهِ أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ ۚ وَكُنتُ عَلَيْهِمْ شَهِيدًا مَّا دُمْتُ فِيهِمْ ۖ فَلَمَّا تَوَفَّيْتَنِي كُنتَ أَنتَ الرَّقِيبَ عَلَيْهِمْ ۚ وَأَنتَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ شَهِيدٌ

«በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በነርሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርኩ፡፡ በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ፡፡ አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ፡፡»(አል ማኢዳህ ፤117)

ትክክለኛው ሐይማኖት ከጥንት ይዞ እስከዛሬ አላህን በብቸኝነት ማምለክን አስተምሯል፡፡ ሁሉም ነብያት ወደዚህ ቁም ነገር ተጣርተዋል ስለዚህም በሁሉም የአላህ መልእክተኞች እንደተሰበከው የሰው ልጅ አይነተኛ ዓላማ ኢባዳ ነው፡፡[3]

ለ) በሰው ልጅና በዙሪያው ባለው ዓለም መካከለ ያለው ግንኙነት

አላህ ይህን ድንቅና ውብ ዓለም ለሰው ልጅ ፈጠረ፡፡ ነብያትን ሁሉ ወደ ቅኑ ጎዳና ይመሩት ዘንድ አስነሳ፡፡ በሐዲሰል ቁድስ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአደም ልጅ ሆይ፣ ሁሉንም ነገሮች ላንተ ፈጥሬያቸዋለሁ፡፡ አንተን ግን የፈጠርኩህ ለኔ ነው፡፡ ላንተ በተፈጠረው ነገር መጠመድህ በተፈጠርክበትን ዓላማ እንዳያዘናጋህ ተጠንቀቅ፡፡››

አላህ በቁርአኑ ለሰው ልጅ የዋለውን ውለታ ካወሳ በኋላ የሰው ልጅ በምላሹ ይህን ጸጋውን በመካድ ያሳየውን አስገራሚና በዳይ አቋም ይሐይሳል፡-

اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَأَنزَلَ مِنَ السَّمَاءِ مَاءً فَأَخْرَجَ بِهِ مِنَ الثَّمَرَاتِ رِزْقًا لَّكُمْ ۖ وَسَخَّرَ لَكُمُ الْفُلْكَ لِتَجْرِيَ فِي الْبَحْرِ بِأَمْرِهِ ۖ وَسَخَّرَ لَكُمُ الْأَنْهَارَ
وَسَخَّرَ لَكُمُ الشَّمْسَ وَالْقَمَرَ دَائِبَيْنِ ۖ وَسَخَّرَ لَكُمُ اللَّيْلَ وَالنَّهَارَ
وَآتَاكُم مِّن كُلِّ مَا سَأَلْتُمُوهُ ۚ وَإِن تَعُدُّوا نِعْمَتَ اللَّهِ لَا تُحْصُوهَا ۗ إِنَّ الْإِنسَانَ لَظَلُومٌ كَفَّارٌ

 

‹‹አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ከሰማይም ውሃን ያወረደ በእርሱም ከፍሬዎች ሲሳይን ለእናንተ ያወጣ መርከቦችንም በፈቃዱ በባሕር ላይ ይንሻለሉ ዘንድ ለናንተ የገራ ወንዞችንም ለናንተ የገራ ነው፡፡፤ ፀሐይንና ጨረቃንም ዘወትር ኼያጆች ሲኾኑ ለእናንተ የገራ ሌሊትንና ቀንንም ለእናንተ የገራላችሁ ነው፡፡፤ከለመናችሁትም ሁሉ የሰጣችሁ ነው፡፡ የአላህንም ጻጋ ብትቆጥሩ አትዘልቋትም፡፡ ሰው በጣም በደለኛ ከሓዲ ነው፡፡›› (ኢብራሂም ፤32-34)

የፈጠረ አላህ፣ ሲሳይ የሚሰጥ፣ ያስተማረ አላህ፣ ለሰው ልጅ ክብርን ያጎናጸፈ አላህ፡፡ የሰው ልጅ ለዚህ ሁሉ ጸጋ እውቅና አይሰጥምን? በሐዲሰል ቁድስ እንዲህ ተብሏል፡-

‹‹ እኔ በአንድ በኩል፣ አጋንንትና ሰዎች በሌላ በኩል በአስገራሚ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ እኔ ፈጥሪያቸው ሌላን  ያመልካሉ፡፡ ሲሳይ የለገስኳቸው እኔ ሆኜ እያለሁ ሌላን ያመሰግናሉ፡፡››

ሱዩጢ አቡ ደርዳእን ዋቢ አድርገው ዘግበውታል፡፡ አላህ እንዲህም ብሏል፡-

كَلَّا إِنَّ الْإِنسَانَ لَيَطْغَىٰ
أَن رَّآهُ اسْتَغْنَىٰ
إِنَّ إِلَىٰ رَبِّكَ الرُّجْعَىٰ

‹‹ በእውነቱ ሰው ወሰንን ያልፋል፤ራሱን የተብቃቃ (ባለ ሀብት) ኾኖ ለማየቱ፤መመለሻው ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡›› (አል ዓለቅ፤6-8)

******* ይቀጥላል፡፡


[1] አል ኢባዳህ ፊል ኢስላም ዶክተር ዩሱፍ አልቀረዷዊ

[2] ሰይድ ቁጥብ ፊዚላሊል ቁርአን

[3] አል ኢባዳህ ፊል ኢስላም ዶክተር ዩሱፍ አልቀረዷዊ

 

3 COMMENTS

  1. ተጠናክራቹ ዲናዊ እዉቀቶችን ልቀቁልን አህለል ቢዳዓዎች በተለይ ገጠር አካባቢ እየፈተኑን ስለሆነ ማስረጃዎች ያስፈልጉናል እስፔሻሊ (ተዉሒድ) በተመለከተ ተጠናከሩ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here