ፍልስጤም (ክፍል 1)

0
7141

የፍልስጤም ምድር

ፍልስጤም በደቡብ ምዕራብ የኢስያ አህጉር የሚገኝ አገር ሥም ነው። በሰሜን በኩል ሊባኖስ፣ በሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ፣ በምሥራቅ ዮርዳኖስ፣ በደቡብ የቀይ ባህር፣ በደቡብ ምዕራብ የግብፁ የሲናእ በረሃ፣ እንዲሁም በምዕራብ በኩል ደግሞ የሜዴትራኒያን ባህር ያዋስኑታል።  ይህ ምድር በሰው ልጅ የሥልጣኔ ታሪክ ዉስጥ ቀደምቱ የተመዘገበበት ሲሆን ከአሥር ሺ ዓመታት በፊት የተመሠረተችው የኢያሪኮ ከተማ የምትገኝበት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ከነዓኖች እና ፈለስጢኖች በመባል የሚታወቁትና ኋላ ላይ ከቀደምት የአካባቢው ሰዎች ጋር የተዋሃዱት የባህር ስደተኞች ይኖሩበታል። ኋላም አካባቢው በሮማውያን፣ በሞንጎላውያንን እና በክርስቲያን መስቀለኞች ተደጋጋሚ ወረራ ደርሶበታል።

ከሰባተኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ ደግሞ አብዛኛው የፍልስጤም ምድር ነዋሪ እስልምናን ተቀብሎ ዘልቋል። እስከ 1917 የሙስሊም ኸሊፌት አገዛዝ መውደቅ ድረስም የሙስሊም ግዛት አካል ሆኖ ቆይቷል። በዚህ ዓመት ዉስጥ የሰፊው ኢስላማዊ መንግሥት መሪና አስተዳዳሪ የነበረው የኦቶማን አገዛዝ ወደቀ። ይህንንም ተከትሎ የኢስላማዊው መንግሥታት አካል የነበረችው ፈለስጢንም በብሪታኒያ የቅኝ አገዛዝ ሥር ወደቀች። ብሪታኒያም አይሁዶችን በፍልስጤም ምድር በማስፈር የፅዮናውያን ህልም ለማሳካት ተባባሪ ሆነች።

በ1948 በፍልስጤም ምድር የብሪታኒያ አገዛዝ አበቃ። ብሪታኒያ ስትወጣ አካባቢውም በነባር የዐረብ ህዝቦች እና በስደተኞቹ አይሁዶች መካከል ዉዝግብ ይነሳበት ጀመር። ዉዝግቡ ሰፍቶ ጦርነቶችም ተካሄዱ። ፅዮናውያን የምዕራቡ ዓለም ሙሉ ድጋፍ ነበራቸው። በመጨረሻም 900 ሺህ የቀደምት የከነዓን፣ የፊለስጢን እና እስልምናን ከተቀበሉ በኋላ በአካባቢው ሠፍረው የነበሩ የዐረብ ጎሣዎች ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ ከተደረገ በኋላ ከ77 በመቶ በላይ በሚሆነው የፍልስጤም መሬት ላይ የፅዮናዊት “ኢስራኤል መንግሥት” ተመሠረተ።

የአይሁዶች መስፋፋት ቀጥሎ በ1967 ዓ.ል በተካሄደው ጦርነት “ኢስራኤል” በዚያን ጊዜ በጎረቤት አገራት ሲተዳደሩ የነበሩ ተጨማሪ የፍልስጤም ግዛቶችን ተቆጣጠረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መላ ፍልስጤምን ለመቆጣጠርና የሶሪያ፣ የሊባኖስ እና የግብፅ ግዛቶችን ለመንጠቅ “ኢስራኤል” ቀጥተኛ የሆነ ወታደራዊ ኃይል ስትጠቀም ቆይታለች። ሆኖምግን የመስፋፋት ዓላማዋን ተከታታይ የሆነ ህዝባዊና ወታደራዊ መቋቋም ገድቦታል። በዚህና በመሰል ጉዳዮች አካባቢው ዛሬም ድረስ የዓለማቀፍ ሚዲያ ትኩረት ስቦ ይገኛል።

በዚህ አጭር መጣጥፍ የዚህን ትግል ባህሪ በመጠኑ እንዳስሳለን። ፍልስጤምን ህዝቦቿን ለመተዋወቅ እንሞክራለን። ስለ ፅዩናዊነት እና ፅዮናዊ መንግሥት እንዲሁም ከ80 ዓመት በላይ ስለዘለቀው የአካባቢው ዉዝግብ በጥቂቱ እንቃኛለን።

ፍልስጤም – ሥሙ እና ትርጉሙ

የፍልስጤም፤ በዐረብኛ ደግሞ የ“ፈለስጢን” ምድር ሥሙን ያገኘው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከደቡብ ግሪክ ደሴቶች ተነስተው ወደዚያ በተሰደዱ የሜዴትራኒያን ባህር ስደተኞች ነው። ስደተኞቹ “የባህር ህዝቦች” በመባል ይታወቃሉ። በቀደምት ጥንታዊ የግብፅ ሥነፅሑፎች ዉስጥ “ፈለስጢ” በመባል የሚታወቁ ሲሆን “ን” የመጣችው በኋላ ላይ ምናልባት ሥሙን ለማግነን ተብሎ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል – ፈለስጢን። ምድሩ ቀደምት ላይ የከነዓን ምድር በመባል ነበር የሚታወቀው። ኋላ ላይ ግን የአዲሦቹን የባህር ሰዎች የሰፋሪዎቹን ሥም በመውሰድ “ፈለስጢን” ሊባል ችሏል። በሙስሊሞቹ የበርካታ ምዕተ ዓመታት የአካባቢው አገዛዝ ታሪክ ዉጥ ፈለስጢን “ቢላደ ሻም/ የሻም ምድር” ወይም “ታላቋ ሶሪያ” ተብሎ የሚጠራው ግዛት አካል የነበረ ሲሆን በዚያ ጊዜ በነበረው አጠራር ክፍለግዛቱ “ጁንድ” በመባል ይታወቅ ነበር። የፍልስጤም ክፍለግዛትም የዛሬውን የፍልስጤም ግዛት አብዛኛውን ክፍል ያካተተ ነበር።

የፍልስጤም አዲሱ ድንበር የተሰመረው በብሪታኒ የቅኝ አገዛዝ ዘመን (1918-1948) ሲሆን ይህም የሆነው የተበታተነውን የሙስሊሙን የኦቶማን አገዛዝ ግዛቶች ለመቀራመት ፈረንሳይ እና ብሪታኒያ ባደረጉት የ “ሳይኬስ ፒኮት/Sykes-Picot” ስምምነት ጊዜ ነበር። በሶሪያ እና በሊባኖስ በኩል ያለው ድንበሩ ደግሞ የተሰመረው በ1920 እ.ኤ.አ. በተደረገው የፈረንሳይ-ብሪታኒያ ስምምነት ነው። ከዮርዳኖስ ጋር የሚያዋስነው ድንበር ደግሞ የተሰመረው በ1922 በብሪታኒያ ከፍተኛ ኮሚሽነሮች ሲሆን ከግብፅ ጋር የሚዋሰነው ድንበሩ ደግሞ የተካለለው በ1908 በኦቶማን ኸሊፋዎች እና በግብፅ ገዢዎች መካከል በተደረገው ስምምነት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፍልስጤም ምድር ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ የሚገኘው አካባቢ እና ከደቡብ ሊባኖስ ተራራ ቀጥሎ ያለውን ምድር አካቶ ይገኛል።

መልክዓም ምድር እና የአየር ፀባይ

የፍልስጤም ምድር አጠቃላይ ስፋት 27,009 ስኩዌር ኪሜ  ሲሆን በዉስጡም 704 ስኩዌር ኪሜ የውሃ አካል አለው። ከውሃ አካላት መካከል የአል-ሁላ ሐይቅ፣ የጠበሪያ ሐይቅ እና የሙት ባህር ግማሹ ክፍል ይገኙበታል። ፍለስጤም በአጠቃላይ በአራት ዓይነት መልክዓ ምድራዊ ሁኔታዎች ትከፈላለች።

  1. የባህር ዳርቻዎች፡- የሜዴትራኒያንን ባህር ተከትሎ የሚገኝ ሲሆን ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚዘልቅ ለጥ ያለ ሜዳ ነው። ከፍታማ ቦታው ከባህር ወለል በላይ 180 ሜትር ይደርሳል። ሥፍራው  እጅግ ለም ከሆኑ የፍልስጤም አካባቢዎች አንዱ ሲሆን አራቱን ዓመታዊ የሜዴትራኒያን የአየር ሁኔታ የሚያገኝ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፍራፍሬዎችንና አበቦችን ለማብቀል ተስማሚ ሲሆን ዛሬም ድረስ በዚሁ ምርቱ ይታወቃል።
  2. ተራራማ ቦታዎች፡- በምስራቅ ዳርቻዎች አካባቢ ዳርቻዎቹን ተከትሎ የሚገኝ አካባቢ ነው። ከፍታማ ቦታው እስከ 1208 ሜትር የሚደርሰው ሲሆን በሰሜን ፍልስጤም የሚገኘው የአል-ጀርመቅ (ሜሮን) ተራራ ትልቁ ነው። ይህ አካባቢ ከዳርቻዎቹ በተለየ መልኩ ቀዝቃዛ/ ብርዳማ ነው። ሆኖምግን የሜዴትራንያን ባህር የአየር ተፅእኖም አለው። የምድር ገፁ ምንም እንኳን ደረቃማ ቢሆንም አካባቢው የተለያዩ እህሎች፣ ባቄላና አተር፣ በለስ፣ ዘይቱንና ወይን ለማምረት ተስማሚ ነው። ለከብት እርባታም በሰፊው የሚውል አካባቢ ነው።
  3. አል-ጎር (የስምጥ ሸለቆ)፡- የዮርዳኖስ ሸለቆ በመባልም ይታወቃል። ይህም የሆነው የዮርዳኖስ ወንዝ ከሁለት በኩል ምሥራቅ እና ምዕራብ አድርጎ ስለሚከፍለው ነው። ምሥራቁ የፍልስጤም ምድር ሲሆን ምዕራቡ ክፍል ደግሞ የዮርዳኖስ ግዛት ነው። አል-ጎር አትክልት፣ ፍራፍሬዎችንና ተምርን ለማብቀል ለም የሆነ መሬት ነው። ይህ ሸለቆ በምድር ላይ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ደረቅ ቦታ የሚገኝበት ነው። ቦታውም ከባህር ወለል በታች 395 ሜትር ይደርሳል። ሥፍራው የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ሙት ባህር የሚገባበት ነው። ሸለቆው በደቡብ አቅጣጭ ደግሞ ወደ ቀይ ባህር 460 ሜትር ስኩዌር ስፋት አለው። የሙት ባህር የምድራችን እጅግ ጨዋማ የሆነ ባህር ሲሆን ምንም ዓይነት ሕይወት ያለው ፍጡር አይኖርበትም። አል-ጎር በአጠቃላይ ሞቃታማ እና በአንፃራዊነት ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ደረቃማ የሆነ አካባቢ ነው።
  4. በረሃማ ቦታዎች፡- ይህ ሥፍራ ደቡብ ፍልስጤም አካባቢ የሚገኘው ነው። አል-ነቀብ (ነጌቭ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ዋና የዉሃ ምንጩም ቢእር አስ-ሰበእ (ቤርሳቤህ) ነው። አል-ነቀብ የፍልስጤምን ግማሽ ክፍል የሚሆን አካባቢ የያዘ ሥፍራ ነው። በምሥራቅ ከአል-ኸሊል (ሄብሮን) ጀምሮ ወደ ምዕራብ ገዝዛ ድረስ በመስፋት ወደ ሰሜን እስከ ቀይ ባህር ዳርቻ ድረስ ይዘልቃል። አል-ነቀብ ሞቃታማ እና ደረቃማ አካባቢ ሲሆን በንፋስ አማካይነት የሚነሳ አሸዋ እና ጥቂት የዉሃ ምንጮች የሚገኙበት ነው።

ለማጠቃለል – ፍልስጤም በመልክዓ ምድሩ ልዩ ምድር ሲሆን በዓመት ዉስጥ አራት ዓይነት የአየር ፀባዮች (ወቅቶች) አሉት። በአንድ በኩል ዓለም ላይ እጅግ ዝቅተኛ ቦታ የሚገኝበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከመሬት ወለል በላይ እስከ 1200 ሜትር ከፍታ የሚደርሱ ተራሮችም የሚገኙበት ነው። የተለያዩ ሐይቆችም ያሉት ምድር ሲሆን በአካባቢው የሚገኝ ባህር ደግሞ ምንም ዓይነት ሕይወት ያለው ፍጡር የማይታይበትና በጨዋማ ይዘቱ ዓለም ላይ የሚስተካከለው የለም። አስገራሚው ነገር ይህ ሁሉ አስደናቂ ተፈጥሯዊ ትዕይንትና እሴት ኢስያንና አፍሪካን በሚያገናኝ ከ27,009 ስኩዌር ኪሜ ያልበለጠ አነስተኛ የመሬት ክፍል ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው።

ዋና ዋና ከተሞች

የመጀመሪያዋ የፍልስጤም ከተማ ኢያሪኮ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ8,000 ዓመት ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ የፍለስጤም ምድር ወደተለያዩ ክልሎቿ ለተስፋፉ ሥልጣኔዎች ዋና ማዕከል ሆና ቆይታለች። አብዛኞቹ የሥልጣኔ እንቅስቃሴዎችና ምልክቶች ተከማችተው የሚገኙት በዳርቻዎች እና ተራራማ ቦታዎች አካባቢ ሲሆን በዮርዳኖስ ሸለቆ አካባቢ ደግሞ በመጠኑ አነስተኛ፣ ለበርካታ ሺህ ዓመታት ቤዴዊኖች በኖሩበት በረሃማ አካባቢዎች ደግሞ ሥልጣኔው እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ እናገኛለን።

በባህር ዳርቻ አካባቢ ከሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች መካከል ያፋ (ጃፋ)፣ ዐካ (ዐክር)፣ ሐይፋ፣ ገዝዘህ እና አሽዶድ ይጠቀሳሉ። በተራራማ አካባቢዎች ከሚገኙት ደግሞ አል-ቁድስ (ኢየሩሳሌም)፣ አል-ኸሊል (ሄብሮን)፣ ራመላህ፣ ናቡሉስ፣ ቤይተ ለሕም (ቤተልሄም)፣ ናዝሬት፣ እና ሰፈድ ይጠቀሳሉ። በጆርዳን ሸለቆ የምትገኝ ትልቋ ከተማ ኢያሪኮ ስትሆን በበረሃማው አካባቢ ደግሞ ቢእር አስ-ሰበእ (ቤርሼባ) ከተማ ትጠቀሳለች።


ምንጭ፡- ዶ/ር ሙህሲን ሙሃመድ ሷሊህ “ሒሰቶሪ ኦፍ ፓለስታይን”።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here