የአንብብ ትውልድ ለምን አያነብም ???

1
5621

ይህ ፅሁፍ መነሻ ያደረገው የአንድ ታላቅ የእስልምና ምሁር በሆኑት ሰው ንግግር ላይ በመመስረት ነው። በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ተናግረው ነበር፦ «ኡመቱን ኢቅራእ ላ የቅራእ»  “የአንብብ ትውልድ አያነብም!” በማለት በማህበረሰቡ ዘንድ የማንበብ ችግርን በማሰብ የታዘቡትን በአጭሩ በንግግራቸው ገልፀዋል። ፅሁፋችንም የችግሩን ግዝፈት ለማሳየትና በሀገራችን የንባብ ልምድ ይዳብር ዘንድ የበኩሉን ያበረክታል ተብሎ ይታሰባል። መልካም ንባብ!

ከእስልምና ቀደምት ህግጋት መካከል በግንባር ቀደምነት ከሚገኙ በርካታ ትእዛዛት ውስጥ ቀድሞ የምናገኘው የንባብ ጉዳይ ነው። አላህ(ሱወ) መልእክተኛውን  ታላቁን መልእክት “ኢቅራእ” “አንብብ” ሲል ነበር በቅድሚያ አዝዟቸው የነበረው። ይህ የ‘አንብብ’ መርህ ደግሞ በእምነቱ ጉልህ መመሪያ እንዲሆንም አስችሎታል። ንባብ ለህይወት መስተጋብር ሁሉ እጅግ ወሳኝ ነው።

ፍጥረት ሁሉ እንዲነበብ የተቃና  ለአስተሳሰብ አድማስ መስፋትም የተዋበ ነው። ህይወት ከንባብ ጋር ያላት ግንኙነትም እጅግ የጠነከረ ነው። በህይወታችን መርህም ምሉእ የሆነ ገፅታን ይገነባል። ስለንባብ ሲነሳ መፅሀፍን፣ ስለመፅሀፍ ሲወሳ አንባቢያንን መቃኘት የግድ ይላል። ወደ መረጃ መረብ ልመለስና አል አረቢያ ቴሌቪዥን ባለፈው ሃምሌ ወር ሮይተርስን በመጥቀስ ያወጣው ዜና የአረቡ አለም በንባብ ባህል በኩል በጣም ደካማ እንደሆነና ከምዕራብ ሀገሮች ጋርም ሲነፃፀር በጣም ያነሰ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ ይሄም በአረቡ አለም ዘንድ አስገራሚ ተብሎ ነበር፡፡ በተጠቀሰው የምርምር ስራ መሰረት አንድ አረብ በዓመት ስድስት ገፅ ብቻ የሚያነብ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ አንድ አሜሪካዊ በዓመት አስራ አንድ መፅኃፍት እንዲሁም አንድ እንግሊዛዊ በዓመት ሰባት መፅሃፍት ያነባል በማለት ፡፡ ‹‹እኛ የአረቡ አለም ነዋሪዎች ልጆቻችን በዓመት ስድስት ደቂቃ ብቻ ለልጆቻችን የንባብ ጊዜ ስናበረክት፤ በአንፃሩ ምዕራባዊያን ቤተሰቦች ደግሞ በዓመት አስራ ሁለት ሽህ ደቂቃዎችን ለልጆቻቸው የንባብ ጊዜነት ያውሉታል›› ይላል፡፡ ይህ የሚያሳየው የንባብ ባህል መኖር በእድገት እና በብልፅግና ላይ የሚያደርሱት ተፅእኖ ትልቅ መሆኑን ነው፡፡

አዎ! አንባቢዎች መሪዎች ናቸው (Readers are Leaders) እንዲሉ በህብረተስብ ውስጥ የበለጠና የተሻለ ያነበቡ ሰዎች መምራት እንደሚችሉ እሙን ነው። የንባብ መጠን ባደገና በበለፀገ ጊዜ ከመረዳት ጋር በተጣመረ ቁጥር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

አዎ! አንባቢዎች መሪዎች ናቸው (Readers are Leaders) እንዲሉ በህብረተስብ ውስጥ የበለጠና የተሻለ ያነበቡ ሰዎች መምራት እንደሚችሉ እሙን ነው። የንባብ መጠን ባደገና በበለፀገ ጊዜ ከመረዳት ጋር በተጣመረ ቁጥር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ፤ ያለውን የንባብ ባህል በምርምር ስራ አስደግፎ ያቀረበ ምርምር ስራ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ ሊያገኝ አልቻለም ወይም ያሉትም የአንድ በጣም የተወሰነ ሁኔታን ብቻ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ነገር ግን ተያያዥ ሁኔታዎችን አብረን በማየት ያለውን የንባብ ባህል እና የመፅኃፍ ስርጭት የሚያመለክት ስዕል ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ስልጣን በያዘ ማግስት አላማው ማርክሲስት-ሌኒኒስት ሕብረተሰብን ለመገንባት በማሰብ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ካወጀ በኋላ፤ ማሀይምነትን ለማጥፋት በሚል ግብ በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የሚገኙ መሀይማንን ቁጥር ወደ ሀያ አራት በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ ለዚህም ስኬት በመላ ሀገሪቱ ከሰባት ሽህ በላይ ቤተ መፅኃፍት ተገንብተው እንደነበር በጊዜው የወጡ ሪፖርቶች ይገልፃሉ፡፡

ይሄም የማንበብ ባህልን ከማሳደግ አኳያ ታላቅ እምርታ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በወታደራዊ ዘመን የመፅኃፍት ሳንሱር በእጅጉ የበረታ ከመሆኑ የተነሳ መንግስታዊ ርዕዮተ ዓለም ከሆነው ማርክሲዝም- ሌኒኒዝም ውጭ ሌሎች ሀሳቦችን የሚያንፀባርቁ መፅሃፍት ‘የአድሃሪያን’ ናቸው፣ ‘የኢምፔሪያለዝም ጭምቅ መርዞች’፣ ‘የአቢዮት ቀልባሾች ማንፌስቶ ናቸው’ ወ.ዘ.ተ በሚሉ አልባሌ ምክንያቶች የሚታተሙት መፅኃፍት በእጅጉ በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ ነበሩ፤ ይሄም የንባብ ባህሉን እና የሀሳብ እንሽርሽሪቱን (Discourse) እድገት አንቆ ይዞት ነበር፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ የኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተርን አፀደቀ፡፡ ቻርተሩ ከያዛቸው ዋነኛ ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ያፀደቀውን እና ኢትዮጵያም ፈራሚ የነበረችበትን ‹‹አለማቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ(UDHR) ሙሉ ለሙሉ ተቀብላለች›› የሚለው ሃሳብ ይገኝበታል፡፡ ከነዚህ መብቶች አንዱ ሀሳብን በፈለጉት መንገድ የመግለፅ ነፃነት ነው፡፡ ይሄም በንባብ ባህሉ ላይ በአጠቃላይ፣ በመፅኃፍ ገበያውን ላይ ደግሞ በተለይ በአዎንታዊ መልኩ ተፅዕኖ እንደሚሳርፍበት በወቅቱ ተገጿል፡፡ ለዛም ይመስላል በኢህአዴግ መጀመሪያ የስልጣን አመታት በደርግ ጊዜ ታፍነው የነበሩ ድምፆች መተንፈስ የጀመሩት፡፡ ነገር ግን ከመፅኃፍት ገበያው ጎን ለጎን የግል ጋዜጦች ወደ ገበያው መግባታቸው አንባቢዎችን ከጠጣር (Hard) ወደ ስስ እና ለብ ለብ (Soft) የንባብ ባህል እንዲነዱ ተፅእኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይሄም መፅኃፍ ከጋዜጣ የደረሰበት የመጀመሪያው ጠንካራ ቡጢ ነበር፡፡ እንደዛም ሆኖ በነዚህ ዓመታት የመፅኃፍት ገበያው መልካም በሚባል ሁኔታ ላይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሂደት ግን የመፅኃፍት ገበያው እየተቀዛቀዘ መጣ፡፡ በ2001 ዓ.ል አካባቢ በሚዩዚክ ሜይ ዴይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ውስጥ የመማሪያ መፅኃፍትን ጨምሮ በቀን በአማካኝ አምስት መፅኃፍት ለህትመት ይበቃሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው በዓመት በመላ ሀገሪቱ በሁሉም ቋንቋዎች፤ በሁሉም ርእሰ ጉዳዮች ላይ የትርጉም ስራዎችን ጨምሮ ወደ 1800 አካባቢ መፅኃፍት ይታተማሉ ማለት ነው፡፡ ይሄን ቁጥር ለምሳሌ በአሜሪካ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010 በአሜሪካ ከታተሙት ሶስት መቶ ሃያ ስምንት ሽህ ሁለት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ (328,259) መፅኃፍት ጋር ስናነፃፅረው በሀገራችን የሚታተሙትን መፅሃፍት ቁጥር አናሳነት እንረዳለን፡፡ እንግዲህ ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለሚኖርባት ሀገር ይህ ቁጥር እጅግ ትንሽ ቁጥር ከመሆኑም በላይ፡፡ የአንባቢውን ውስንነት እና የንባብ ባህሉን ውድቀት ያሳያል፡፡ ለመሆኑ መፅኃፍ ለምን ተዘነጋ? የንባብን ሀገራዊ ተጨባጭ ከተመለከትን  በኃላ  አንዳንድ ከንባብ የራቅንበትንና መፅሀፎችን የዘነጋንበትን ምክንያቶች እንጥቀስ።

1-ቁርአንን ከማንበብ መዘናጋት  ለማንበብ መዳከም መንስኤ ነው።

ቁርአን እለት ተእለት የምናነበው ትልቁ መመሪያችን ሲሆን በተለይም በጠዋቱ ክፈለ ጊዜ ምእመኖች አዘውትረው ያነቡታል። ትርጉሙን ለመገንዘብም ያጤኑታል በርካታ ቁርአናዊ መሰረት ያላቸውን መርሆችም በተለያዪ ሁኔታዎች ይማሩበታል። በንባብ ጉዳይም ትኩረትም ሰጥቶ የአለቅ አንቀፅ ላይም “ኢቅራእ” (አንብብ) ሲለንም ወሳኝ የእውቀት ጉዳዮችን አስተምሮናል። በሌሎችም አንቀፅ ስለ ንባብና እውቀት አላህ (ሱወ) እንዲህ ይለናል።

 ምእምናንም (ከነቢዩ ጋር ካልኾነ) በሙሉ ሊወጡ አይገባም፡፡ ከእነሱ ውስጥ ከየክፍሉ አንዲት ጭፍራ ለምን አትወጣም፡፡ (ሌሎቹ) ሃይማኖትን እንዲማሩና ወገኖቻቸው ወደነርሱ በተመለሱ ጊዜ እንዲጠነቀቁ ይገስጹዋቸው ዘንድ (ለምን አይቀሩም)፡፡ ተውባህ፤122

እነዚያ የሚያውቁና እነዚያ የማያውቁ ይስተካከላሉን? ዙመር፤9

ነብዩ(ሰአወ) በታወቀው ንግግራቸው ላይ ” እውቀትን መፈለግ በሁሉም ሙስሊም ወንዶችና ሴቶች ላይ ግዴታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ቁርአንን ስለማንበብ ተምሮ ስለማስተማርና መሰል የእውቀት ተግባር ያለውን ታላቅ ደረጃ  በእስልምና የተላቀና የተወደደ እንደሆነም ቀርቧል።

2-የእነፃና የካሪኩለም ችግር

በቀደምት የሀገራችን የእስልምና አስተምህሮት ዘይቤዎቻችን ንባብንና እነፃን ማእከል ያደረገ እንደነበር ይታወቃል። አንድ ተማሪ ከአስተማሪ ስር ሆኖ ሲማርና ሲቀራ በተጨማሪ የስነምግባር እነፃና እንዲሁም በቂ እውቀት ያገኝ ዘንድ የመሸምደድ ብሎም በርካታ ነገሮች እንዲያነብ ይደረግ ነበር። ከዛ በላይ የሚማረው ኪታብ(ኢስላማዊ መፅሀፍቶች) ስርአነትን የተከተሉና የተደራጁ መሆናቸው የንባብን ጥራት ይጨምረው ነበር። ምሳሌ፦ ከቁርአንን አነባብ ይጀምርና ወደ ፊቂህ ከዚያም ወደ ቋንቋ ከዚያ ቀጥሎ የሀዲስና የተፍሲር ትምህርትን እንዲማር ይደረግ ነበር። እያንዳንዳቸው አስተምህሮቶች ሰፋፊና ጊዜን የሚወስዱ እጅግ ጥናትና ንባብ እንደሚያሻቸውም በሚገባ ይታወቅ ነበር። ዛሬ ዛሬ የሚቀሰሙ እውቀቶች የተደራጁ አለመሆናቸውና ሁሉን ነገር በቀላሉ መገኘት መቻሉ ከንባብና ከልፋት መራቅ ሰበብ ሆኗል።

3-መሀይምነት

ይህ ችግር በራሱ ሰዎች ስለንባብና እውቀት ያላቸውን የተንሻፈፈ ግንዛቤ ያስወርሳል። ከ84 በመቶ በላይ ህዝብ በገጠር በሚኖርባት ኢትዮጵያ የመሃይሙ መጠንም በዚያው ልክ ብዙ እነደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2005 ዓ.ል፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) በወጣው ሪፖርት መሰረት 45 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ብቻ የተማሩ (Literate) እንደሆኑ ሲገልጽ፤ ቀሪዎቹ 55 በመቶዎቹ ደግሞ ያልተማሩ (Illiterate) ናቸው ይላል፡፡ ይሄም የሚያሳየው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን አያነቡም አይፅፉምም ማለት ነው፡፡ በጣም የሚያስገርመው በመሰረተ ትምህርት ዘመቻ አመካኝነት ማንበብ እና መፃፍ ይችሉ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ዝንጋኤ ውስጥ (Memory loss) ሆነው የተማሩትን መዘንጋታቸው ነው፡፡ እናም የመሃይሙን ቁጥር ከፍ አድርጎታል፡፡ እንግዲህ በሀገሪቱ የመሃይማኑ ቁጥር ከተማረው ይልቅ ማየሉ በንባብ ባህሉ እና በመፅኃፍ ገበያው ላይ የሚያስከትለው ተፅእኖ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሄን ስንል ግን ተምረው – ያልተማሩትን (Functionally Illiterate) ማለትም ፊደል የቆጠሩ ነገር ግን ስለመፅኃፍ ምንም ሀሳብ የሌላቸውን ዜጎች ሳንጨምር ነው፡፡

ዕውቀት ተኮር ህብረተሰብ ወዴት ነው?

«የመሃይማኑ ቁጥር ከላይ እንደተቀስነው ከተማረው ዜጋ ቁጥር በላይቢሆንም፤ በተማረው ህብረተሰብ ዘንድ ያለው የመፅኃፍ ግንዛቤም ሌላው ከንባብ ባህሉ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የንባብ ምሽቶች፣ የማንበቢያ ቦታዎች (Reading Buzz) መኖር፣ ህፃናት ለማንበብ ያላቸው ተነሳሽነት እንዲጨምር እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ወ.ዘ.ተ ስንመለከት የችግሩ ስር ወዴት ሊሄድ እንደሚችል መገመት ያስችለናል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህሉ እድገት የሰጡት ትኩረት ምን ያህል ነው? በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉት ንባብ ተኮር ዝግጅቶች ምን ያክል ናቸው? ተማሪዎች ‘የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን’ እንዲመለከቱ ትኩረት ተሰጥቶ በሚሰራበት መጠን፤ ለመፅኃፍ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግስ ይደረጋል ሆይ? እያልን ስንጠይቅ፤ መልሱን ለጥያቄዎቹ ከምንሰጠው መልስ ጀርባ እናገኝዋለን፡፡»

4-የሶሻል ሚድያ አጠቃቀም ችግር

ዛሬ ዛሬ የኢንተርኔቱ አለም በተራቀቀበት ጊዜ በርካታ ሰዎች ከንባብና ከመፅሀፍ ጋር ሆድና ጀርባ ለመሆን ሰበብ ምክንያት ሆኖል። በርካታ ሰዎች አጫጭር መረጃዎችን በተከሸነ መልኩ ከፌስቡክ፣ ከቲውተርና መሰል ሚድያዎች ስለሚያገኙ  መፅሀፍቶችን ከማንበብ ተሰላችቷል። ከዚህም ውጭ በ24 ሰአት ውሎ ላይ በርካታ ጊዜውን በመሻማት መልኩ በቻትና በ”ቀልዳቀልድ” ወጎች እንዲሁም በወቅታዊ አጅንዳዎች ላይ በበርካታ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚወጡ መፅሀፍቶችን ከማንበብ ተዘናግቷል። እነዚህንና መሰል የሶሻል ሚድያ ችግሮች ንባብን የመገደብ ሚናው ከፍተኛ ሲሆን ይስተዋላል።  ውድ የዚህ ፅሁፍ አንባቢያን ይህ ፅሁፍ የንባብን አስፈላጊነት ለማሳየት የሚሞክር ፅሁፍ ነው። በተለይም ከንባብ ለመራቅ ያደረጉንን መሰረታዊ ችግሮችንም ለማየት ሞክረናል ችግሮች ከታወቁ መፍትሄውን ለማገኘት ይረዳልና፤ በቀጣይ የንባብን ክህሎትን ሊጨምሩ የሚችሉ ወሳኝ ነጥቦችን አካተን እስክንገናኝ ቸር ያገናኘን እንላለን።


 

1 COMMENT

  1. አሰላም አለይኩም ወራህመቱላህ ወበረካቱ
    በስንት ጊዜ ቁይታ ተመልሸ ከናንተ በመቀላቀሌ ደስ ብሉኛል አልሀምዱሊላህ አላህ ይጨምርላችሁ ቀጥሉበት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here