ሂጅራ:- የወንድማማችነት መንገድ

1
8419

የአሁኖቹ ሙሀጂሮችና አንሷሮች እነማን ናቸው?

አላህ በቁርኣን:-

وَالسَّابِقُونَ الْأَوَّلُونَ مِنَ الْمُهَاجِرِينَ وَالْأَنصَارِ وَالَّذِينَ اتَّبَعُوهُم بِإِحْسَانٍ رَّضِيَ اللَّهُ عَنْهُمْ وَرَضُوا عَنْهُ وَأَعَدَّ لَهُمْ جَنَّاتٍ تَجْرِي تَحْتَهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا أَبَدًا ذَٰلِكَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ
 

“ከስደተኞቹና ከረዳቶቹም ሲኾኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው አላህ ከእነሱ ወዷል ከእርሱም ወደዋል። በሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘለዓለም ነዋሪዎች ሲኾኑ ለእነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል። ይህ ታላቅ ዕድል ነው።” (አል-ተውባ 9፣ 100) ይላል። በሌላ የቁርኣን አንቀጽ ደግሞ:-

وَالَّذِينَ تَبَوَّءُوا الدَّارَ وَالْإِيمَانَ مِن قَبْلِهِمْ يُحِبُّونَ مَنْ هَاجَرَ إِلَيْهِمْ وَلَا يَجِدُونَ فِي صُدُورِهِمْ حَاجَةً مِّمَّا أُوتُوا وَيُؤْثِرُونَ عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ وَلَوْ كَانَ بِهِمْ خَصَاصَةٌ  وَمَن يُوقَ شُحَّ نَفْسِهِ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ
 

“እነዚያም ከበፊታቸው አገሪቱን መኖሪያ ያደረጉት እምነትንም የለመዱት ወደእነርሱ የተሰደዱትን ሰዎች ይወዳሉ። (ስደተኞቹ) ከተሰጡትም ነገር በልቦቻቸው ውስጥ ቅሬታን አያገኙም። በእነርሱ ላይ ችግር ቢኖርባቸውም በነፍሶቻቸው ላይ ሌላውን ይመርጣሉ። የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው።” (አል-ሀሸር 59፣ 9) ይላል።

ሂጅራ በኢስላም ታሪክ ቁንጮ ስፍራ ከሚሰጣቸው የታሪክ ክስተቶች አንዱ ሲሆን ኢስላማዊ እንቅስቃሴ መሰረታዊ ለውጥ ያስመዘገበበት ታሪካዊ ክንዋኔ ነው። በዚሁም ሙስሊሞች የመጀመሪያ የሰላም አየራቸውን ተንፍስውበታል፤ ወንድማማች ህዝቦች አንድነታቸውን ገንብተውበታል፤ ታሪካዊ ክስተቱም ለኢስላም የዘመን መቁጠሪያ በመሆን ለትወልድ የሚተላለፍ ትልቅ ቅርስ ሆኗል። በነቢዩ ሙሀመድ /ሶ.ዐ.ወ/ ከመካ ወደ መዲና የተደረገው ጉዞ- ሂጅራ የተስፋ መልዕክት ነበረ። በጉዞው ነቢዩ ለሶሀባቸው “አትዘን አላህ ከኛ ጋር ነው” በማለት ቃል እንደገቡለት በቁርዐን ተገልጧል። የስደቱን ችግርና መከራ ለመቋቋም ያስቻለውም ይሄው ጥልቅ ኢማንና በአላህ መተማመን ነው፤ የእምነት፣ የተስፋና የቁርጠኝነት ፋና ወጊ ሂጅራ!

አላህ በቁርዓኑ እንደገለፀው:-

إِلَّا تَنصُرُوهُ فَقَدْ نَصَرَهُ اللَّهُ إِذْ أَخْرَجَهُ الَّذِينَ كَفَرُوا ثَانِيَ اثْنَيْنِ إِذْ هُمَا فِي الْغَارِ إِذْ يَقُولُ لِصَاحِبِهِ لَا تَحْزَنْ إِنَّ اللَّهَ مَعَنَا  فَأَنزَلَ اللَّهُ سَكِينَتَهُ عَلَيْهِ وَأَيَّدَهُ بِجُنُودٍ لَّمْ تَرَوْهَا وَجَعَلَ كَلِمَةَ الَّذِينَ كَفَرُوا السُّفْلَىٰ  وَكَلِمَةُ اللَّهِ هِيَ الْعُلْيَا وَاللَّهُ عَزِيزٌ حَكِيمٌ

“(ነቢዩን) ባትረዱት እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ኾኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ አላህ በእርግጥ ረድቶታል። ሁለቱም በዋሻው ሳሉ ለጓደኛው አትዘን አላህ ከእኛ ጋር ነውና ባለ ጊዜ አላህም መረጋጋትን በእርሱ ላይ አወረደ። ባላያችኋቸውም ሰራዊት አበረታው። የእነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ። የአላህም ቃል ለእርሷ ከፍተኛ ናት። አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።” ይላል (አል-ተውባ 9፣ 40)።

ነቢዩ ሙሀመድ /ሶ.ዐ.ወ/ ወደ መዲና እንደገቡ የፈፀሙት ሶስት ድንቅ ነገሮችን ነበር።እነሱም፡-

  1. በሙሀጂሮችና (የመካ ስድተኞች) አንሷሮች (የመዲና ሙስሊሞች) መሀከል ወንድማማችነትን መሰረቱ፤
  2. ለሶላት፣ ለስብሰባና ለመማሪያ በድረክ የሚሆን መስጅድ ገንብተዋል፤
  3. በመዲና በሚገኙ ሙስሊሞችና የሌላ እምነት ተከታዮች መካከል የሰላምና የመልካም ስምምነት ቃል ኪዳን እንዲፈረም አድርገዋል።

የሙስሊሞች የመዲና ህይወት ሦስት ዕቅዶችን ማስፈፀም ያዘለ ነበር። እነሱም፡-

  1. ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር፣
  2. ለአላህ ፍፁም ተገዥ መሆን፤
  3. ውጫዊ ሰላምን ማረጋገጥ፤

እስኪ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር (ሙአኻት) የሚለውን ነጥብ አንስተን ቀጥለን ለመዳሰስ እንሞክር።

ሙአኻት በዚያኔው ሙሰሊም መሀከል አንድነትና ትስስርን ለማምጣት የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ ነበር። የወንድማማችነቱ ዓላማ ከመካ የመጡትን ስድተኖች ማኗኗር ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም አዲስ ኢስላማዊ ማህበረሰብ መገንባትና የሰማያዊ አጀንዳውን መመሪያ መሰረት አድርጎ የሰውን ልጅ ወደ ኢስላም ጥሪ የሚያደርግ ትውልድ ማሰልጠን ነው።

የአረብ ማህበረሰብ የኢስላም መመሪያ በፊት የሚታወቀው ስር በሰደደ የጎሰኝነትና የዘረኝነት ባህል የተዘፈቀ መሆኑ ነው። ስለሆነም ህዝቦች ከጎሳቸው ውጪ ሀላፊነትንም ሆነ ክብርን ለማንም አይሰጡም ነበር። ኢስላም ግን አዲስ ራዕይና አቅጣጫ አሳያቸው። ይህም ጠባቡን ጎሳዊ አመለካከት ከማምለክ ይልቅ አላህን ወደ ማምለክ እንዲሸጋገሩ፣ ከዘረኝነት ጨለማ ወደ ወንድማማችነት ብርሃን እንዲራመዱ መንገድ መራቸው። በአጠቃላይ አላህ በነቢዩ ሙሀመድ በኩል የላከው መልዕክት ትውልዱ ድንቅ ህዝብ ይሆን ዘንድ የህይወት መስመር ዘርግቷል። አላህ በቁርዓኑ እንዲህ ይላል፡-

وَاعْتَصِمُوا بِحَبْلِ اللَّهِ جَمِيعًا وَلَا تَفَرَّقُوا وَاذْكُرُوا نِعْمَتَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ كُنتُمْ أَعْدَاءً فَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِكُمْ فَأَصْبَحْتُم بِنِعْمَتِهِ إِخْوَانًا وَكُنتُمْ عَلَىٰ شَفَا حُفْرَةٍ مِّنَ النَّارِ فَأَنقَذَكُم مِّنْهَا كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمْ آيَاتِهِ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ 

“የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ። አትለያዩም። ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ። በልቦቻችሁም መካከል አስማማ። በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ። በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ። ከእርስዋም አዳናችሁ። እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል።” (ኣሊ-ዒምራን 3፣ 103)

ሙሀጂሮችና አንሷሮች ለአላህ ሲሉ ተዋደዋል፤ የመተሳሰብን ፅዋ እርስ በርስ ተጎነጫጭተዋል፤ እንደ አንድ ቤተሰብም ኖረዋል። የነበሩትን የጎሳ፣ የቀለምና፣ ወዘተ ጥላቻዎች ሁሉ አራግፈው ጥለዋል። እንደ አንድ ህዝብ በአላህ መልዕክት ጥላ ስር አድረዋል፤የኢስላምን መልዕከት በጋራ ተምረዋል፤ ልጆቻቸውንም አስተምረዋል፤ ለትልቅ ዓላማ በጋራ ለፍተዋል፤ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ በጋራ ለኢስላም ለፍተዋል፣ በጋራ እምነቱን ጠብቀዋል፣ በጋራም ለመልዕክቱ ተሰውተዋል። በዚህ ድንቅ ተግባራቸው አላህ ሁሉንም የበረከቱን ሸማ አለበሳቸው፤ ያላሰቡትን ፀጋም አጎናፀፋቸው። በቁጥር እጅግ አናሳ የነበሩ ቢሆንም አስቸጋሪ አቀበቶችን በማለፍ ለስኬት በቅተዋል፤ በዚህም ለሰው ልጆች የመሪነት ቦታን ለመረከብ ችለዋል። በዚያ በጎሰኝነትና በዘረኝነት ተከፋፍለውና ተለያይተው ቢሆን ኖሮ ይህንን የተሳካ አብዬት በዚህ አጭር ጊዜ ለመፈፀም የሚቻላቸው አልነበረም።

በአሁኑ ጊዜ ሙሀጂሮችና አንሷሮች የት ነው ያሉት? ማነው ይህንን የሙሀጂሮችና የአንሷሮች ቦታ ሊጫወትስ የሚችለው? ማነው ያንን የፍቅርና የደስታ፣ የእዝነትና የርህራሄ፣ የፍትህና የነፃነት፣ የብልፅግናና የታላቅነትን ህይወት መልሶ ሊያመጣ የሚችለው? እንዴትስ ነው የዚያን ህዝብ ምሳሌና ዱካ ልንከተል የምንችለው? እነርሱ የለውጥ ጀማሪዎች (ሳቢቁን) እንደሆኑት እኛስ ታማኝ ተከታይ (ላሂቁን)መሆን እንችላለን? የነሱ ለአላህ ሲሉ መፋቀር፣ መረዳዳት፣ መፈቃቀር ወዘተ ምን ማለት እንደሆነ ይገባናል?

እነዚህን ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያጤናቸው ይገባል። ለእነዚህ ጥያቆዎች መልስ ሳንሰጥ ወደፊት መራመድ አይታሰብም። ብዙ የሚያግባቡን አጀንዳዎች፤ ብዙም በጋራ ልንተገብራቸው የምንችላቸው የስራ መስኮች አሉ። አትኩረን ከተመለከትን የእኛን የመለያየት ችግር ከያኔው ትውልድ አንፃር እጅጉን መቅረፍ የሚቻል ነው። በትክክልም ችግሩን መቅረፍ ቀላል ነው። ግን ይህን ጉዳይ አሁን ከየት ጀምረን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል? እንዴት ወደ ቀድሞው ኢስላማዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ልንመለስ እንችላለን? እስቲ ቆም ብለን እናስተውል። የሚከተሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ከራሳችንና ከወንድሞቻችን ጋር እንወያይ፣ እናቅድ፣ መንገድም እናብጅ።

  1. እንዴት የበለጠ አንድ ሆነን ውጤታማ ህዝብ እንሆናለን?
  2. እንዴትስ ራሳችንን ህብረተሰባችን ብሎም የሰው ልጅን ከችግር እንታደጋለን?
  3. እንዴትስ ሰላምን፣ ፍትህንና፣ ፍቅርን በዓለም እናሰፍናለን?

እንደ አንድ ሙስሊም ዜጋ በህብረተሰባችን መሀከል ከፍተኛ ሚና መጫወት እንችላለን። ከሌሎችም ጥሩ አለመካከት ካላቸው ወገኖች ጋር በጋራ በመስራት ለራሳችንም ሆነ ለህዝባችን ብዙ አስተዋፅኦ ማበርከት እንችላለን። ያሉብን አደራዎች ብርቱና ብዙ ናቸው፤ ለልዩነቶቻችን ቦታ አንስጥ። ምክንያቱም ልዩነቶቻችን በጋራ ተደማምረው ከምንስማማባቸው ጉዳይ ውስጥ የአንዱን ሚዛን መድፋት አይችሉም። የነዚያም ድንቅ ትውልዶች ባህሪ ለልዩነቶቻቸው ቦታ አለመስጠት ነበር። እንነሳ እናስተውል በቁርጠኝነት እነዚያን ህዝቦች ተከትለን ለአንድነት ቅድሚያ እንስጥ። እንደ ሙሀጂሮችና አንሷሮች በጋራ በመነሳት ለውጥ እናምጣ።

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here