ውዱእ የሚወደድላቸው ነገሮች (ዉዱእ–6/ ጦሀራ – ክፍል 12)

0
6668

ለሚከተሉት ሁኔታዎች ውዱእ ማድረግ ይወደዳል።

1. አላህን ለማውሳት

በሙሃጂር ቢን ቁንፉዝ ሐዲስ እንደተዘገበው “እርሳቸው (ሙሃጂር) መልእክተኛው በዉዱእ ላይ ሳሉ ሰላምታ አቀረቡላቸው። ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) መልስ አልመለሱም። ልክ ዉዱእ ሲጨርሱ መልስ ሰጧቸው እና እንዲህ አሉ፦

إنه لم يمنعني أن أرد عليك إلا أني كرهت أن أذكر الله إلا على الطهارة

“አላህን ያለንፅህና እንዳላስታውስ ፈልጌ ነው እንጂ ሰላምታህን ከመመለስ የሚያግደኝ ነገር የለም ነበር።”

ይህ ከተመራጭነት እና ከተወዳጅነት አንፃር ካየነው እንጂ አላህን ማስታወስ እና ዚክር ማድረግ ውዱእ ላደረገም ላላደረገም -ጀናባ ለሆነ ሰው እንኳን ሳይቀር-፣ ለተቀመጠም፣ ለቆመም፣ ለሚራመድም፣ ለተንጋለለም… ያለመጠላት እና ያለገደብ የተፈቀደ ነገር ነው።

ምክንያቱም ከዓኢሻ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው፦ “የአላህ መላእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሁሉም ሁኔታቸው ላይ አላህን ያወሱ ነበር።” ከነሳኢይ በስተቀር አምስቱም ዘግበውታል። ቡኻሪይ ያለሰነድ ጠቅሰውታል።

2. በእንቅልፍ ጊዜ

በበራእ ኢብኑ ዐዚብ ሐዲስ እንደተገለፀው፦ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፦

إذا أتيت مضجعك فتوضأ وضوءك للصلاة

 “ወደ መጋደሚያ ስፍራ ስትመጣ ለሶላት እንደምታደርገው አይነት ዉዱእ አድርግ።”

3. ጀናባ ለሆነ ሰው

ጀናባ የሆነ ሰው መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት እና ተመልሶ ወሲብ መፈፀም ከፈለገ ዉዱእ ማድረግ ይወደድለታል።

ከዓኢሻ እንደተዘገበው፦ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ጀናባ ሆነው መብላት፣ መጠጣት እና መተኛት ሲፈልጉ ውዱእ ያደርጉ ነበር።”

ከአቢ ሰዒድ የአላህን ነብይ ዋቢ በማድረግ እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፦

إذا أتى أحدكم أهله ثم أراد أن يعود فليتوضأ

“እያንዳንዳችሁ ሚስቱን ከተገናኘና ከዚያም መድገም ከፈለገ ዉዱእ ያድርግ።” (ከቡኻሪይ በስተቀር ጀመዓዎች ዘግበውታል።) ኢብኑ ኹዘይማ፣ ኢበኑሒባን እና አል-ሐኪምም ዘግበውታል። እንዲህ የሚልም ጨምረዋል፦

فإنه أنشط للعود

“እርሱ (ውዱእ ማድረግ) ለመድገም ያበረታዋል።”

4. ከትጥበት በፊት

ትጥበት ግዴታም ይሁን ሱና ከመጀመሩ በፊት ውዱእ ማድረግ ተወዳጅ ነው።

አኢሻ እንደዘገቡት፦ “የአላህ ነብይ(ሰ.ዐ.ወ) ከጀናባ ሲታጠቡ እና ሲጀምሩ ሁለት እጆቻቸውን ያጥባሉ። ከዚያም ውሀን በቀኛቸው ወደ ግራቸው እያፈሰሱ ብልታቸውን ያጥባሉ። ከዚያም ለሶላት የሚደረገውን አይነት ውዱእ ያደርጋሉ።” ሐዲሱ በረዥሙ ተቅሷል። ጀመዓዎቹ ዘግበውታል።

5. እሳት የነካው ነገር በመብላት ምክንያት

ውዱእ ማድረግ ሱና ነው።

ኢብራሂም ቢን ቃሪዝ እንዲህ ይላሉ፦ “አቡሁረይራ (ረ.ዐ.) ውዱእ እያደረጉ እያለ በአጠገባቸው አለፍኩኝ። “በምን ምክንያት ውዱእ እንደማደርግ ታውቃለህ? በእሳት የተጠበሰ የሆነ ደረቅ ወተት በመመገቤ ሰበብ ነው። ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፦

توضئوا مما مست النار

“እሳት በነካው ነገር ምክንያት ውዱእ አድርጉ።” ሲሉ ሰምቻለሁ።” አሉኝ” (አሕመድ፣ ሙስሊም እና አራቱ ዘግበውታል)

እነዚህ ዘገባዎች ላይ ዉዱእ ማድረግ መታዘዙን ተወዳጅ ከመሆን አንፃር እንቃኘዋለን።

ዐምር ቢን ኡመያ አድ-ዶምሪይ በሐዲሳቸው ላይ እንዲህ ብለዋል “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የፍየል አጥንት ሲግጡ ተመልክቻቸዋለሁ። ምግብ ተመገቡ። ነገርግን ወደ ሶላት ሲጠሩ ቢላዋውን ጣሉት። ተነሱና ሰገዱም። ዉዱእ ግን አላደረጉም።” (ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል)

6. ለየሰላቱ ውዱእን ማደስ

ቡረይዳ በሐዲሳቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል፦ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) በየሶላቱ ወቅት ዉዱእ ያደርጋሉ። መካ የተከፈተ ቀን ሲሆን ግን ዉዱእ አደረጉና በኹፋቸው ላይ አበሱ። ከዚያም ብዙ ሶላቶችን በአንድ ዉዱእ ሰገዱ። ዑመር እንዲህ አሏቸው “የአላህ መልእክተኛ ሆይ ከዚህ በፊት የማያደርጉት ነገር ፈፅመዋል?” እርሳቸውም፦

عمدا فعلته يا عمر

“ዑመር ሆይ አውቄ ነው ያደረኩት።” አሉ።” (አሕመድ፣ ሙስሊም እና ሌሎችም ዘግበውታል)

ከአቡሁረይራ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

لولا أن أشق على أمتي لامرتهم عند كل صلاة بوضوء ، ومع كل وضوء بسواك

“ህዝቦቼን አስቸግራለሁ ባልል ከያንዳንዱ ሶላት ጋር ውዱእ፣ ከእያንዳንዱ ዉዱእ ጋር ሲዋክ እንዲጠቀሙ አዛቸው ነበር።”  (አሕመድ የሐሰንነት ደረጃ ባለው ሰነድ ዘግበውታል)

ከኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይሉ ነበር፦

من توضأ على طهر كتب له عشر حسنات

“በውዱእ ላይ ውዱእ ያደረገ ሰው አስር ሐሰናት ይፃፍለታል።” (አቡዳውድ፣ ቲርሙዚይ እና  ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here