ውዱእን የሚያፈርሱ ነገሮች (ዉዱእ–4/ ጦሀራ – ክፍል 10)

0
6613

ውዱእን የሚያፈርሱት እና አገልግሎት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ነገሮች አሉ። እነርሱን በመቀጠል እንዘረዝራለን፦

1. ከሁለቱ መንገዶች ከፊት ለፊተኛው ወይም ከኋለኛው ከአንዱ የወጣ ማንኛውም ነገር፦

ይህ የሚከተሉትን ያካትታል።

  1. ሽንት
  2. ዐይነ-ምድር

 “… ወይም ከእናንተ አንዳችሁ ከዓይነ ምድር ቢመጣ…” (ማኢዳ፤ 6)

ይህ ንግግር ከሽንትም ሆነ ከዓይነ-ምድር መፀዳዳትን ይጠቁማል።

  1. ፈስ

በአቡሁረይራ ሐዲስ ውስጥ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

لا يقبل الله صلاة أحدكم إذا أحدث حتى يتوضأ

“አንዳችሁ ሶላት ውስጥ ሆኖ ሐደስ (ዉዱእ የሚያፈርስ ነገር) ካጋጠመው ዉዱእ እስካላደረገ ድረስ ሶላቱን አላህ አይቀበለውም።” ከዚያም ከሐድረመውት የመጣ አንድ ሰው “አቡሁረይራ ሆይ ሐደስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እርሳቸውም “ድምፅ የሌለው ወይም ድምፅ ያለው ፈስ ነው።” አሉ።” (ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል)

አሁንም እርሳቸው በዘገቡት ሐዲስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦

إذا وجد أحدكم في بطنه شيئا فأشكل عليه أخرج منه شئ أم لا ؟ فلا يخرجن من المسجد حتى يسمع صوتا أو يجد ريحا

“አንዳችሁም ቢሆን ሆዱ ውስጥ አንዳች ነገር አጋጥሞት የሆነ ነገር ወጥቶኛል ወይስ አልወጣኝም ብሎ ከጠረጠረ ድምፅ አስካልሰማ ወይም ሽታውን እስካላገኘ ድረስ ከሶላቱ አይውጣ።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

ድምፅ መስማት ወይም ሽታ ማግኘት ግዴታ አይደለም አንዳች ነገር መውጣቱን ካረጋገጠ ዉዱኡ ተበላሽቷል። አላህ የተሻለ ያውቃል።

2. መንይ፣ መዝይ እና ወድይ

መንይ ማለት የፍትወት ፈሳሽ ማለት ነው። መዝይ የሚባለው ደግሞ በወሲብ ጨዋታ ጊዜ የሚወጣውን የሚምዘለገለግ ፈሳሽ ነው። ወድይ ማለት ደግሞ በድካም ወይም በድንጋጤ ጊዜ ከሽንት ጋር አብሮ የሚወጣ ወፍራም ፈሳሽ ነው። “ውዱእ አለበት።” ብለዋል ስለ መዝይ ሲናገሩ፤ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)

ኢብኑ አባስም እንዲህ ብለዋል፦ “መኒይ ትጥበት ግዴታ የሚሆንበት ፈሳሽ ነው።” መዝይ እና ወድይ ላይ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል “ብልትህን እጠብ እና ለሶላት የሚደረገውን ውዱእ አድርግ።”

3. ግንዛቤ የሌለበት፣ መቀመጫ (ቂጥ) በመሬት ላይ ያልተደላደለበት ያለ እንቅልፍ

በሶፍዋን ቢን አስ-ሳል (ረ.ዐ) ሐዲስ ላይ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መንገደኞች የሆንን ጊዜ ለሦስት ቀናት ከነለሊታቸው ለጀናባ ካልሆነ በስተቀር ኹፋችንን (ጫማችንን) እንዳናወልቅ ያዙን ነበር። ነገርግን ለዓይነምድር፣ ለሽንት እና ለእንቅልፍ (አናወልቅም ነበር)።” ነሳዒይ እና ቲርሙዚይ ዘግበውታል። ቲርሙዚይ “ሶሒሕ” አድርገውታል።

የተኛው ሰው መሬት ላይ መቀመጫውን አደላድሎ የተቀመጠ ከሆነ ውዱእ አይፈርስበትም።

አነስ (ረ.ዐ) በሐዲሳቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች የመጨረሻውን ዒሻእ (መግሪብን የመጀሪያው ዒሻ ስለሚሉት ነው) አናታቸው እስከሚያቀረቅር ድረስ ይጠብቁት ነበር። ከዚያም ይሰግዳሉ። ውዱእ አያደርጉም።” ሻፊዒይ፣ ሙስሊም፣ አቡዳዉድ እና ቲርሙዚይ ዘግበውታል። የቲርሙዚይ ቃላት ሹዕባ ባሉበት ሰነድ እንዲህ ነው የሚለው፦ “የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሶሐቦች ማንኮራፋት ካለበት እንቅልፍ ለሰላት ሲቀሰቀሱ አይቻቸዋለሁ። ከዚያም ይሰግዳሉ፤ ውዱእ አያደርጉም።” ኢብኑል-ሙባረክ “ይህን እኛ ተቀምጠው ተኝተው እንደነበረ ነው የምንረዳው።” ብለዋል።

4. አእምሮን መሳት

በማበድ፣ ራስን በመሳት፣ በስካር ወይም በመድሀኒት አእምሮን መሳት ጥቂትም ሆነ ይብዛ መቀመጫ መሬት ላይ የተደላደለ ይሁንም አይሁንም ውዱእን ያፈርሳል። ምክንያቱም በእነዚህ ክስተቶች ጊዜ ራስን አለማወቅ ከእንቅልፍ የከፋ ነው። በዚህ አቋም ላይ የዑለሞች ንግግር ተጋጥሟል። ሁሉም እንዲሁ አይነት እምነት አላቸው።

5. ብልትን ያለግርዶሽ መንካት

በቡስራ ቢንት ሶፍዋን ሐዲስ ላይ እንደተገኘው፦

من مس ذكره فلا يصل حتى يتوضأ

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) “ብልቱን የነካ ሰው ዉዱእ ያድርግ” ብለዋል።”

ቡኻሪይ “ይህ (ሐዲስ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከተዘገቡ ሐዲሶች የተሻለው ነው።” ብለዋል።

በተጨማሪም ይህን ሐዲስ ማሊክ፣ ሻፊዒይ አሕመድ እና ሌሎችም ዘግበውታል። አቡ ዳዉድ እንዲህ ብለዋል፦ “አህመድን “የቡስራ ሐዲስ ሶሂህ አይደለምን?” ብዬ ጠየኳቸው። እርሳቸውም “አረ ሶሒህ ነው።” አሉ።

በሌላ ዘገባ አሕመድ እና ነሳኢይ -ከቡስራ- በዘገቡት ሐዲስ -እርሷ- የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምታቸዋለች፦

ويتوضأ من مس الذكر

“ብልትን በመንካት ምክንያት ውዱእ ይደረጋል።”

ይህ የራሱን ብልትም ሆነ የሌሎችን ብልት ያካትታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here