የውዱእ ሱናዎች (ዉዱእ–3/ ጦሀራ – ክፍል 9)

1
3576

የውዱእ ሱናዎች ማለት ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተገኙ ንግግሮች እና ተግባሮች ሆነው ግዴታ ያልሆኑ እና እነርሱን የተወ ሰው የማይወቀስባቸው ነገርግን ከተገበራቸው የሚመነዳበት ነገሮች ናቸው። እንደሚከተለው ይብራራሉ።

1. በመጀመሪያው ላይ “ቢስሚላህ” ማለት

ለውዱእ ቢስሚላህ ማለት መኖሩን አስመልክቶ ብዙ ዶዒፍ ሐዲሶች ተገኝተዋል። ነገርግን የሐዲሶቹ መሰባሰብ እና የዘገባዎቻቸው ብዛት መበራከት ብርታትን ይጨምርላቸዋል። ስለዚህ ድርጊቱ መሰረት ያለው መሆኑን እንረዳለን። በተጨማሪም መልካም ነገሮችን በአላህ ስም መጀመር በራሱ መልካም ነገር ነው። በሸሪዓው ድጋፍ ያለው ተግባር ነው።

2. ሲዋክ

ሲዋክ ማለት መፋቂያ ማለት ይሆናል። የመፋቅ ድርጊትም ሲዋክ ይባላል። መፋቅ (ሲዋክ) በእንጨት ወይም እርሱን በመሰለ ማንኛውም ሸካራ፣ ጥርስን ንፁህ በሚያደርግ እና ቆሻሻን በሚያስለቅቅ ነገር ጥርስን ማሸት ማለት ነው። ሱናው የጥርስን ቢጫነት በሚያስወግድ፣ አፍን በመልካም መዓዛ በሚያውድ ማንኛውም ነገር ይገኛል። ለምሳሌ፦ አሁን ያሉት የጥርስ ቡሩሾች ሲዋክን ይተካሉ።

ከአቢ ሁረይራ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል:- “ህዝቦቼን አስቸግራለሁኝ ብዬ ባላስብ ኖሮ በእያንዳንዱ የዉዱእ ጊዜ ሲዋክ እንዲያደርጉ አዛቸው ነበር።” (ማሊክ፣ ሻፊዒይ፣ አል-በይሃቂይ እና አል-ሐኪም ዘግበውታል)

ሲዋክ በማንኛውም ወቅት ተወዳጅ ነው። ነገርግን በአምስት ወቅቶች ላይ እጅግ ጥብቅ የሆነ ተወዳጅነት አለው።

  1. በውዱእ ወቅት
  2. በሶላት ወቅት
  3. ቁርአንን ለማንበብ በሚፈልግበት ወቅት
  4. ከእንቅልፍ በሚነቃበት ወቅት
  5. የአፍ ንፅህና ሲለወጥ።

ሲዋክ የሚጠቀም ሰው ሲዋክ ከማድረጉ በፊት እንዲያጥበው ይወደድለታል። ከተጠቀመውም በኋላ ቢያጥበው መልካም ነው። ምክንያቱም ዓኢሻ (ረ.ዐ) በሐዲሳቸው እንደተናገሩት፦

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሲዋክ ይጠቀሙና እንዳጥበው ይሠጡኛል። እኔም በቅድሚያ እፍቅበትና ከዚያም አጥበዋለሁ። ከዚያም እሰጣቸዋለሁ” ይላሉ። አቡዳዉድ እና በይሃቂይ ዘግበውታል።

3. በውዱእ መጀመሪያ ላይ መዳፎችን ሦስት ጊዜ ማጠብ

ምክንያቱም በአውስ ቢን አውስ አስ-ሰቀፊይ ሐዲስ ውስጥ እንደተገለፀው፦

“የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዉዱእ ሲያደርጉ አይቻቸዋለሁ። መዳፋቸውን ሦስት ጊዜ አጥበዋል።” (አሕመድ እና ነሳኢይ ዘግበውታል)

4. መድመዷ (ሶስት ጌዜ መጉመጥመጥ)

ምክንያም በለቂጥቢያ ሲብራ ሐዲስ እንደተዘገበው፦

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ)፦

إذا توضأت فمضمض

“ውዱን ካደረክ ተጉመጥመጥ!” ብለዋል። (አኑዳውድ እና በይሀቂይ ዘግበውታል)

5. አል-ኢስቲንሻቅ (ሦስት ጊዜ በአፍንጫ ውሃን መሳብ)

ምክንያቱም በአቢሁረይራ ሐዲስ እንደተዘገበው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 إذا توضأ أحدكم فليجعل في أنفه ماء ثم ليستنثر

“አንዳችሁ ዉዱእ ሲያደርግ አፍንጫው ውስጥ ውሃ ያድርግ፤ ከዚያም ይናፈጠው።” (ቡኻሪይና ሙስሊም፣ እንዲሁም አቡዳዉድ ዘግበውታል)

ሱናው በቀኝ እጁ ውሃውን ወደ አፍንጫው ማስገባትና በግራው መናፈጥ ነው። ምክንያቱም ዓሊይ (ረ.ዐ) በሐዲሳቸው፦

“ውሃ አስመጡና ተጉመጠመጡ። ከዚያም በግራ እጃቸው ተናፈጡ። ይህንን ድርጊት ሦስት ጊዜ ደጋገሙት። ከዚያም “ይህ ነበር የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዉዱእ።” አሉ።” (አሕመድና ነሳኢይ ዘግበውታል)

6. ፂምን መፈላፈል፦

ዑስማን በሐዲሳቸው፦ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ፂማቸውን ይፈላፍሉ ነበር።” ብለዋል። (ኢብኑ ማጀህ እና ቲርሙዚይ ዘግበውታል። ቲርሙዚይ ሶሒህ ነው ብለውታል)

7. ጣቶችን መፈላፈል፦

ምክንያቱም በኢብኑ ዐባስ ሐዲስ ውስጥ እንደተዘገበው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 إذا توضأت فخلل أصابع يديك ورجليك

“ውዱእ ስታደርግ የእጆችህ እና የእግሮችህን ጣቶች ፈልፍላቸው።” (አሕመድ፣ ቲርሙዚይ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)

በእርግጥም ቀለበትን እና እርሱን የመሰሉ – እንደ አንባር ያሉ- ነገሮችን ማንቀሳቀስ ወይም ማወዛወዝ እንደሚወደድ የሚጠቁም ሐዲስ ተገኝቷል። ነገርግን ለሶሒህነት የደረሰ አይደለም። ቢሆንም ግን በርሱ መስራት ይገባል። ምክንያቱም ድርጊቱ ውዱእን ማሳመር እንደሚገባ በሚያስተምሩ ሐዲሶች መልእክት ውስጥ የሚካተት ነው። ልብ እንበል።

8. ትጥበትን ሦስት ዙር ማድረግ፦

ሦስት ጊዜ ማድረግ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አብዝተው የሰሩበት ሱና ነው። ከዚህ ውጪ ከርሳቸው የተዘገበው ሁሉ ከሦስት ያነሰ እንደሚፈቀድ ለመጠቆም የተገኙ ድርጊቶች ብቻ ናቸው።

ዐምር ቢን ሹዐይብ፣ ከአባታቸው (አባታቸው ደግሞ) ከአያታቸው ይዘው በዘገቡት ሐዲስ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ባላገር ወደ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መጣና ስለውዱእ ጠየቃቸው ሶስት ሶስት ጊዜ እያጠቡ አሳዩት። ከዚያም፦

هذا الوضوء ، فمن زاد على هذا فقد أساء وتعدى وظلم

“ይህ ውዱእ ነው። ከዚህ የጨመረ ሰው በእርግጥ ክፋት ሰራ፤ ወሰን አለፈ፤ በደለ።” አሉ።  (አሕመድ፣ ነሳኢይ እና ኢብኑ  ማጀህ  ዘግበውታል)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አንድ አንድ ጊዜ እና ሁለት ሁለት ጊዜ ውዱእ እንዳደረጉ በሶሒህ ዘገባ ተረጋግጧል። ይህ ትጥበቶችን አስመልክቶ ነው። ራስን ማበስ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚሰራው። ብዙ የተዘገበውም ይኸው ነው።

9. ቀኝን ማስቀደም

እጅና እግር ላይ ቀኝን ከግራ አስቀድሞ ማጠብ ሱና ነው።

ከዐኢሻ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው፦ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጫማ ሲጫሙ፣ ፀጉራቸውን ሲበጠሩ፣ ንፅህና ሲያደርጉ እና በሁሉም ነገራቸው ላይ ቀኝን ማስቀደም ይወዱ ነበር።” (ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል)

10. ማሸት

ማሸት ማለት የሚታጠበው አካል ላይ ከውሃው ጋር ወይም ከውሃው በኋላ እጅን መመላለስ ማለት ነው።

ዐብደላህ ቢን ዘይድ እንደዘገቡት “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የአንድ እፍኝ አንድ ሦስተኛ ውሃ መጣላቸው እና ውዱእ አደረጉ። ክንዳቸውን ማሸትም ጀመሩ።” (ኢብኑ ኹዘይማ ዘግበውታል)

11. ማከታተል

አካላቱን አንዳቸውን ከሌላው ቶሎ እንዲከተል ማድረግ። በተለምዶ ውዱእን ትቶታል ተብሎ ለሚታሰብበት ያህል ጊዜ ከዉዱእ ስራ ውጭ በሆነ ድርጊት ውዱእን አለማቋረጥ። ይህ ድርጊት ሱናው የተተገበረበት እና ቀድሞም ይሁን በኋላ የመጡት ሙስሊሞችም ድርጊታቸው የተገኘበት ነው።

12. ጆሮዎችን ማበስ

ሱናው ውስጣቸውን በጠቋሚ ጣት፣ እጆቻቸውን ደግሞ በአውራ ጣት ከጭንቅላት በተረፈው ውሃ ማበስ ነው። ምክንያቱም ጆሮዎች ከጭንቅላት የሚደመሩ ናቸው።

ከሚቅዳም ቢን መዕዲከሪበ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) በዉዱእ ጊዜ ራሳቸውን እና ጆሮአቸውን ውስጡን እና ውጪውን አበሱ። ጣታቸውንም በጆሮዎቻቸው ሽንቁር ውስጥ ከተቱ።” (አቡዳዉድ እና ጦሐዊይ ዘግበውታል)

13. ቦቃና አሻላን ማስረዘም

ቦቃን ማስረዘም ከራሱ የፊተኛው ክፍል የተወሰነውን ክፍል በማጠብ ይገኛል። ከፊት ውስጥ መታጠብ ግዴታ ከሆነበት ክልል አልፎ ማጠብ ማለት ነው። አሻላን ማስረዘም ደግሞ ከክርኖች እና ከቁርጭምጭሚቶች አልፎ በማጠብ ይገኛል።

በአቢሁረይራ ሐዲስ እንደተገኘው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

إن أمتي يأتون يوم القيامة غرا محجلين من آثار الوضوء

“ህዝቦቼ በዉዱእ ምክንያት የቂያማ ቀን ቦቃና አሻላ ሆነው ይመጣሉ።” አቢሁረይራ እንዲህ ይላሉ። “ከእናንተ መሀል ቦቃውን እና አሻላውን ማስረዘም የሚሻ ሰው እንዲያ ያድርግ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ቦቃ ማለት የፊት እና የአንገት ንጣት ማለት ነው። አሻላ ማለት ደግሞ የእግር እና የእጅ ንጣት ነው።

14. ከባህር ውስጥ ቢጨልፍም ውሃ አጠቃቀም ላይ መሀለኛ መሆን፦

አነስ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) በአንድ ቁና ውሃ (4.4 cm3) እስከ አምስት አፍኝ ድረስ ይታጠቡ ነበር። በአንድ እፍኝ ውዱእ ያደርጉ ነበር።”

ከዐብደላህ ቢን ዑመር እንደተዘገበው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሰዕድ ውዱእ እያደረገ ሳለ ካጠገቡ አለፉ። ከዚያም፦

ما هذا السرف يا سعد ؟

“ሰዕድ ሆይ ምንድን ነው ይሄ ማባከን?” አሉት። “ውሃ ላይ ማባከን አለ እንዴ?” አላቸው።

نعم وإن كنت على نهر جار

“አዎን ከወራጅ ወንዝ አጠገብ ብትሆንም እንኳን!” አሉት።” (አሕመድ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል። ሰነዱ ላይ ግን ድክመት አለው።)

15. ከውዱእ በኋላ ዱዓ ማድረግ

በዑመር ሐዲስ ውስጥ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

ما منكم من أحد يتوضأ فيسبغ الوضوء ثم يقول : أشهد أن لا إله إلا الله وحده لا شريك له وأشهد أن محمدا عبده ورسوله إلا فتحت له أبواب الجنة الثمانية يدخل من أيها شاء

“ከእናንተ መሀል ዉዱእ የሚያደርግና የሚያሳምረው ከዚያም “አሽሀዱ አል-ላኢላሃ ኢል-ለሏህ ወህደሁ ላሸሪከ ለሁ ወአሽሀዱ አን-ነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ…” (ከአሏህ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እና ብቸኛና ሸሪካ የሌለው መሆኑን እመሰክራለሁ። ሙሐመድም የአላህ ባርያው እና መልእክተኛው መሆናቸውን እመሰክራለሁ።) የሚል ማንም ሰው አይኖርም ስምንቱም የጀነት ዳጃፎች ተከፍተውለት በፈለገው በኩል የሚገባ ቢሆን እንጂ።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

ከአቢ ሰዒድ አልኹድሪይ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

من توضأ فقال: سبحانك اللهم وبحمدك ، أشهد أن لا إله إلا أنت ، أستغفرك وأتوب إليك. جعل في طابع فلم يكسر إلى يوم القيامة

“ውዱእ ያደረገ እና ከዚያም – ሱብሐነከል-ሏሁም-መ ወቢሐምዲከ አሽሀዱ አል-ላኢላሃ ኢል-ላ አንተ አስተግፊሩከ ወአቱቡ ኢለይከ (አላህ ሆይ ከምስጋና ጋር ጥራት የሚገባው ላንተ ነው። ከአንተ በስተቀር አምላክ የለም። ምህረትን እለምናለሁ፤ ወደ አንተ ንስሀ እገባለሁ።) ያለ ሰው (ከእሳት) ነፃ ተደርጎ ይፃፍና (የተፃፈው) ይታሸጋል። ከዚያም እስከ ቂያማ ቀን ድረስ (የታሸገው) አይሰበርም።” ጦበራኒይ “አል-ወሲጥ” ላይ ዘግበውታል። ዘጋቢዎቹም ትክክለኞች ናቸው። ቃላቶቹም (አገላለፁም) የርሳቸው ናቸው። (ነሳኢይም ዘግበውታል) ነገርግን መጨረሻው ላይ፦

ختم عليها بخاتم فوضعت تحت العرش فلم تكسر إلى يوم القيامة

“ትታሸግና ከዐርሽ ስር ትደረጋለች። ከዚያም እስከ ቂያማ ቀን ድረስ አትሰበርም።” ብለው ጨምረዋል። ሐዲሱም የሶሐባ ንግግር በመሆን ላይ የቆመ መሆኑን ትክክል ነው ተብሏል።

أللهم اجعلني من التوابين ، واجعلني من المتطهري

“አል-ሏሁም-መጅዐልኒ ሚነት-ተውዋቢን ወጅዐልኒ ሚነል-ሙተጦሂሪን (አላህ ሆይ ከንሰሀ ሰዎች /ከተውበተኞች/ እና ንፅህናን ከሚያዘወትሩት አድርገኝ።)” የሚለው ዱዓ ግን የቲርሚዚይ ዘገባ ነው። በሐዲሱ ላይ “የሰነድ መገጫጨት (ኢድጢራብ) አለበት። አብዛኛው ዘገባም ትክክል አይደለም።” ብለው – ቲርሙዚይ- አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

16. ከዉዱእ በኋላ ሁለት ረከዓ መስገድ

በአቢሁረይራ ሐዲስ ላይ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ቢላልን እንዲህ ብለው መጠየቃቸው ተዘግቧል፦

يا بلال حدثني بأرجى عمل عملته في الاسلام إني سمعت دف نعليك بين يدي في الجنة

“ቢላል ሆይ ኢስላም ውስጥ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ምን አይነት ስራ እንደሰራህ ንገረኝ። እኔ የጫማህን ኮቴ በጀነት ውስጥ ከፊት ለፊቴ ሰማሁት።”

ቢላልም “እኔ በማንኛውም የለሊትም ሆነ የቀን ሰዓት ዉዱእ ካደረኩኝ በዚያ ንፅህና የተፃፈልኝን ያህል ከመስገድ ውጪ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ስራ አልሰራሁም።” አለ።” (ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል)

ከዑቅባ ቢን ዓምር (ረ.ዐ.) በተዘገበው ሐዲስ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

ما أحد يتوضأ فيحسن الوضوء ويصلي ركعتين يقبل بقلبه ووجهه عليهما إلا وجبت له الجنة

“ዉዱእ ሲያደርግ ዉዱኡን የሚያሳምርና በልቡ እና በፊቱ ትኩረት አድርጎ ሁለት ረከዓዎችን የሚሰግድ ማንም ሰው የለም ጀነት የተረጋገጠችለት ቢሆን እንጂ።” (ሙስሊም፣ አቡዳዉድ፣ ኢብኑ ማጀህ እና ኢብኑ ኹዘይማ “በሶሒሃቸው” ላይ ዘግበውታል)

ሌሎች የቀሩ ሱናዎች አሉ። እኛ አልነካካናቸውም። ለምሳሌ፦ የዐይን ሽንቁሮችን መጠንቀቅ እና የፊትን ስንጥቆች መጠንቀቅ፤ ቀለበትን ማንቀሳቀስ፤ አንገትን ማበስ እና ሌሎችም አሉ። ነገርግን ሐዲሶቻቸው የሶሒሕነት ደረጃን ስላልደረሱ አልጠቀስናቸውም። በነርሱ የሚሰራባቸው ንፅህናን ይበልጥ ለማሟላት ብቻ ነው።

ውዱእ ላይ የሚጠሉ ነገሮች

ዉዱእ የሚያደርግ ሰው ካለፉት ሱናዎች አንዱን መተው ይጠላበታል። ምክንያቱም የስራዎቹን ምንዳ ማጣት የለበትም። በመሰረቱ የተጠላ (መክሩህ) የሆነን ነገር መፈፀም ምንዳ የሚያሳጣ ከሆነ ሱናን መተው ደግሞ መጠላትን (ከረሃን) ያመጣል።

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here