የዉዱእ ግዴታዎች (ዉዱእ–2/ ጦሀራ – ክፍል 8)

0
3868

ዉዱእ ማንነቱን የሚያሟሉለት ግዴታዎች እና ማእዘናት አሉት። ከእነርሱ መሀል አንዱ ግዴታው ከጎደለ ውዱእ አይገኝም፤ አይቆጠርም። እነርሱን እነሆ እንደሚከተለው እናብራራለን።

1. አንደኛው ግዴታ

ኒያ ነው። ኒያ ማለት ወደ ድርጊት የሚያቀና ፍላጎት ማለት ነው። የአላህን ውዴታ እና ህጉን መፈፀምን ማሰብ ማለት ነው። ኒያ ንፁህ የልብ ሥራ ነው። ግዴታነቱን የሚጠቁሙ ማስረጃ የኡመር ሐዲስ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦

 إنما الاعمال بالنيات وإنما لكل امرئ ما نوى

“የስራዎች ተቀባይነት በኒያዎች ብቻ ነው። ሁሉም ሰው የነየተው አለው።” (ጀመዐዎቹ ዘግበውታል)

2. ሁለተኛው ግዴታ

ፊትን አንድ ጊዜ ማጠብ። ማለትም ውሃን በፊት ላይ በሚገባው መጠን ማፍሰስ። ምክንያቱም ማጠብ ማለት ውሀን የሚታጠበው ነገር ላይ ማፍሰስ ማለት ነው። ከማበስ የሚለየው ውሃው እስከሚንጠባጠብ ድረስ እላዩ ላይ ስለሚፈስበት ነው። ፊት ማለት በቁመት ከግንባር መጣያ ከላይኛው ክፍል ተነስቶ እስከ አገጭ መጨረሻ ድረስ ነው። በአግድመት ደግሞ ከጆሮ ጫፍ እስከ ጆሮ ጫፍ ድረስ ነው።

3. ሦስተኛው ግዴታ

እጆችን እስከ ክርን ድረስ ማጠብ ነው። ክርን ማለት በጡንቻ እና በክንድ መሃል ያለ መገጣጠሚያ ነው። ክርንን -ራሱን- ማጠብ ግዴታ ከሚሆነው የእጅ ክፍል ጋር የሚካተት ነው። ይህንን ነው  ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በስፋት የተገኙት ማስረጃዎች የሚጠቁሙት። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ክርንን ማጠብ ትተዋል የሚል ምንም ማስረጃ አልተገኘም።

4. አራተኛው ግዴታ

ራስን ማበስ ነው። ማበስ ማለት እርጥበትን ማስነካት ማለት ነው። የሚያብሰው አካል የሚታሰበውን በመነካካቱ እና እርሱ ላይ በመንቀሳቀሱ እንጂ ይህ አይገኝም። ስለዚህ እጅን ወይም ጣትን ራስ ላይ ማድረግ ብቻውን ማበስ አይባልም። በተጨማሪም አላህ “ራሶቻችሁንም (በውሃ) አብሱ።” ማለቱ ሙሉ ራስን ማበስ ግዴታ መሆኑን አያስረዳም። እንደውም ራስን በከፊል ማበስ እንደሚበቃ ይጠቁማል።

5. አምስተኛው ግዴታ

እግሮችን እስከ ቁርጭምጭሚት ድረስ ማጠብ ነው። ይህ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ድርጊት እና ንግግር የተገኘው እና የተረጋጠው መንገድ ነው። ኢብኑ ዑመር እንዲህ ብለዋል፦

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በአንድ ጉዞዋቸው ላይ ከእኛ ወደ ኋላ ቀሩ። የዓስርን ሶላት ካዘገየን በኋላ ግን ደረሱብን። ከዚያም ዉዱእ ማድረግ እና እግራችንን ማበስ ጀመርን። ከዚያም እርሳቸው ከፍ ባለ ድምፅ ተጣሩን።

( ويل للاعقاب من النار ) مرتين أو ثلاثا

“እነዚህ ተረከዞች ከእሳት ወየሁላቸው!” አሉ። ሁለት ጊዜ ወይም ሦስቴ።” (ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል)

6. ስድስተኛው ግዴታ

ቅደም ተከተልን መጠበቅ ነው። ምክንያቱ አላህ በተጠቀሰው አንቀፅ ውስጥ የውዱእን ግዴታዎች በቅደም ተከተል ጠቅሷቸዋል። እግርን ከእጅ ነጥሎት የሁለቱም ግዴታዎች ማጠብ ከመሆኑ ጋር ራስን ማበስ በመሃል አስገብቷል። ራስ ላይ ያለው ግዴታ እንደተገለፀው ማበስ ነው። ዐረቦች ተመሳሳይነት ያላቸውን ነገሮች የማይመሳሰላቸውን ነገር በማስገባት ከነጠሉ አንዳች ፋይዳ መኖሩን ይጠቁማል። እዚህ ጋር በማጠቦች መሀል ማበስ የተቀላቀለበት የሚያስረዳው ፋይዳ ቅደም-ተከተልን ነው። አንቀፅዋ ግዴታዎችን ለማብራራት የመጣች ናት።

በተጨማሪም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሐዲሳቸው “አላህ በጀመረበት ጀምሩ” ማለታቸውን በጥቅል ይዘነው ቅደም ተከተል ግዴታ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።

በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተግባር የተገለጠውም ይህ ቅደም ተከተል ግዴታ መሆኑን አበክሮ ያስረዳል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቅደም-ተከተል ሳይጠብቁ ዉዱ አድርገዋል የሚል አንዳችም ነገር አልተገኘም። ውዱእ ዒባዳ (አምልኮ) ነው። የአምልኮ መዘውሩ መልእክተኛውን መከተል ነው። ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተገኘውን የዉዱ አደራረግ ማንም ሰው ሊነቅፈው አይገባም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here