ዉዱእ – 1 (ጦሀራ – ክፍል 7)

0
3925

ዉዱእ ፊትን፣ እጆችንና እግሮችን የሚያካትት በውሃ የሚደረግ ንፅህና ነው። ዉዱእ በማንኛውም ለአቅመ አዳም የደረሰ፣ አዕምሮው ጤናማ የሆነ ሰው ላይ የሶላት ወቅት በገባ ጊዜ ወይም እርሱን ለመስራት ዉዱእ ሸርጥ የሆነለትን – ሶላትን ወይም ጠዋፍን የመሰለ- ድርጊት ለመፈፀም የፈለገ ሰው ላይ ግዴታ ነው። በርሱ ዙሪያ የሚሰጡ ትንታኔዎች በተከታታይ ፖስቶች እናያቸዋለን።

1. ህጋዊነቱና ድንጋጌውን አስመልክቶ

ህጋዊ መሆኑና መደንገጉ በሦስት ማስረጃዎች ተረጋግጧል።

የመጀመሪያው ማስረጃ የተከበረውን ቁርአን ነው። አሏህ እንዲህ ብሏል፦

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِذَا قُمْتُمْ إِلَى الصَّلَاةِ فَاغْسِلُوا وُجُوهَكُمْ وَأَيْدِيَكُمْ إِلَى الْمَرَافِقِ وَامْسَحُوا بِرُءُوسِكُمْ وَأَرْجُلَكُمْ إِلَى الْكَعْبَيْنِ وَإِن كُنتُمْ جُنُبًا فَاطَّهَّرُوا وَإِن كُنتُم مَّرْضَىٰ أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ أَوْ جَاءَ أَحَدٌ مِّنكُم مِّنَ الْغَائِطِ أَوْ لَامَسْتُمُ النِّسَاءَ فَلَمْ تَجِدُوا مَاءً فَتَيَمَّمُوا صَعِيدًا طَيِّبًا فَامْسَحُوا بِوُجُوهِكُمْ وَأَيْدِيكُم مِّنْهُ مَا يُرِيدُ اللَّهُ لِيَجْعَلَ عَلَيْكُم مِّنْ حَرَجٍ وَلَٰكِن يُرِيدُ لِيُطَهِّرَكُمْ وَلِيُتِمَّ نِعْمَتَهُ عَلَيْكُمْ لَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁን፣ እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ። ራሶቻችሁንም (በውሃ) አብሱ። እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶች (እጠቡ)። (ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክንያት «ጀናባ») ብትኾኑ (ገላችሁን) ታጠቡ። በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም ወይም ከእናንተ አንዳችሁ ከዓይነ ምድር ቢመጣ ወይም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ። ከሱም ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን አብሱ። አላህ በእናንተ ላይ ምንም ችግር ሊያደርግ አይሻም። ግን ታመሰግኑ ዘንድ ሊያጠራችሁና ጸጋውን በእናንተ ላይ ሊሞላ ይሻል።” (አል-ማኢዳ፤ 6)

ሁለተኛው ማስረጃ የነብዩ ሱና (ሐዲስ) ነው። አቡሁረይራ እንደዘገቡት “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፦

 لا يقبل الله صلاة أحدكم إذا أحدث حتى يتوضأ

“ዉዱ ከፈታ በኋላ – ዉዱ ሳያደርግ- የአንዳችሁንም ሶላት አሏህ አይቀበልም።” (ቡኻሪ፣ ሙስሊም እና ቲርሚዚዬ ዘግበውታል)

ሦስተኛው ማስረጃ አል-አጅማዕ – የዑለሞች ስምምነት- ነው። ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጀምሮ እስከ አሁን ዘመን ድረስ ሙስሊሞች በሙሉ በውዱእ ድንጋጌ ተስማምተዋል። ስለዚህ ዉዱእ ከዲን መሆኑ መታወቅ ያለበት (መዕሉም ሚነድ-ዲን ቢድ-ዶሩራ) ሆኗል።

2. የዉዱእ ቱሩፋት

የውድእን ቱሩፋት እስመልክቶ ብዙ ሐዲሶች ተገኝተዋል። የተወሰኑትን በመጠቆም እንብቃቃለን።

ከዐብደላህ እስ-ሶንሐጂይ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

عن عبد الله الصنابجي رضي الله عنه أن رسول الله صلى الله عليه وسلم : قال إذا توضأ العبد فمضمض خرجت الخطايا من فيه ، فإذا استنشر خرجت الخطايا من أنفه ، فإذا غسل وجهه خرجت الخطايا من وجهه حتى تخرج من تحت أشفار عينيه ، فإذا غسل يديه خرجت الخطايا من يديه حتى تخرج من تحت أظافر يديه . فإذا مسح برأسه خرجت الخطايا من رأسه حتى تخرج من أذنيه ، فإذا غسل رجليه خرجت الخطايا من رجليه حتى تخرج من تحت أظافر رجليه . ثم كان مشيه إلى المسجد وصلاته نافلة . رواه مالك والنسائي وابن ماجه والحاكم 

“አንድ ባሪያ ውዱእ ሲያደርግ ሲግሞጠሞጥ ከአፉ ኃጢያቱ ይወጣል። ከአፍንጫው ውሃ ሲያስወግድ ከአፍንጫው ኃጢያት ይወጣል። ፊቱን ሲያጥብ ከፊቱ ኃጢያቱ ይወገዳል። ከአይኑ ሽንቁር ውስጥ እንኳን ኃጢያቱ ይወጣል። ከእጁ ጥፍሮች እንኳን ኃጢያቱ ይወገዳል። ራሱን ሲያብስ ከራሱ ላይ ኃጢያቱ ይወገዳል። ከጆሮው ውስጥ እንኳን ኃጢያቱ ይወጣል። እግሮቹን ሲታጠብ ከእግሮቹ ኃጢያት ይወጣል። ከእግሮቹ ጥፍሮች እንኳን ኃጢያት ይወጣል። ከዚያም ወደ መስጂድ የሚያደርገው ጉዞ እና ሶላቱ ድራቢ ይሆኑለታል።” (ማሊክ፣ ነሳኢይ፣ ኢብኑ ማጂህ እና አል-ሐኪም ዘግበውታል)።

አሁንም ከዐብደላህ እስ-ሶንሐጂይ እንደተዘገበው፦ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ መቃብር ሥፍራ መጡና እንዲህ አሉ፦

عن عبد الله الصنابجي  رضي الله عنه أن رسول الله صلى الله عليه وسلم أتى المقبرة فقال :  السلام عليكم دار قوم مؤمنين ، وإنا إن شاء الله بكم عن قريب لاحقون ، وددت لو أنا قد رأينا إخواننا . قالوا : أو لسنا إخوانك يا رسول الله ؟ قال أنتم أصحابي وإخواننا الذين لم يأتوا بعد . قالوا : كيف تعرف من لم يأت بعد من أمتك يا رسول الله ؟ قال : أرأيت لو أن رجلا له خيل غر محجلة بين ظهري خيل دهم بهم ألا يعرف خيله ؟  قالوا : بلى يا رسول الله ، قال :  فإنهم يأتون غرا محجلين من الوضوء وأنا فرطهم على الحوض ، ألا ليذادن رجال عن حوضي كما يذاد البعير الضال أناديهم : ألا هلم ، فيقال :  إنهم بدلوا بعدك . فأقول : سحقا سحقا ( رواه مسلم ).

“እነናንተ የዚህ ቀብር ሙእሚን ነዋሪዎች ሆይ ሰላም በእናንተ ላይ ይሁን። እኛም -በቅርቡ- ወደናንተ ተጠጊዎች ነን። ወንድሞቻችንን ባየን ኖሮ ብዬ ተመኘሁ።” አሉ። አብረዋቸው የነበሩ ባልደረቦቻቸው፦ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ እኛስ የርሶ ወንድሞች አይደለንምን?” አሏቸው። “እናንተ ባልደረቦቼ ናችሁ። ወንድሞቻችን እስከ አሁን ያልመጡ ናቸው።” አሉ። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ ከህዝቦችዎት እስከ አሁን ያልመጡትን (ወደ ፊት የሚመጡትን) እንዴት ያውቋቸዋል?” ሲሉ ጠየቁ። እርሳቸውም፦ “እስቲ ንገሩኝ አንድ ሰው ቦቃና አሻላ (ቦቃ የፊት እና የአንገት ንጣት ነው፤ አሻላ ደግሞ የእጅና የእግር  ንጣት ነው) ያለው ፈረስ ቢኖረው እና በጥቁር ፈረሶች መሀል ቢሆን ፈረሱን  አያውቀውምን?” “አዎን!” (ያውቀዋል) አሉ፤ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.)። አርሳቸውም፦ “እነርሱ የቂያም ቀን ቦቃና አሻላ ሆነው ይመጣሉ። እኔ ደግሞ  ሐውዱ ላይ ተቀዳሚያቸው ነኝ። ልክ የጠፋ ግመል እንደሚከለከለው ብዙ ሰዎች ከሐውዱ ይከለከላሉ። እኔም “ኣረ ወዲህ ኑ!…” እላለሁ።” “እነርሱ ካንተ በኋላ መንገድህን ለውጠዋል።” እባላለሁ ከዚያም “አርቋቸው! አርቋቸው!” እላለሁ።” (ሙስሊም ዘግበውታል)።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here