በኢማን ከፍ ማለት- ክፍል-3

0
4125

5. የመልካም ሥራ ወቅቶችንና በላጭ ጊዜያትን መሻማት

አላህ ሱ.ወ አንዳንድ ወቅቶችን ከአንዳንዶቹ አበላልጧል፡፡ ረመዷንን ከሌሎች ወራት አስበልጧል፡፡ ጁሙዓንም በሌሎች ቀናት ላይ አንግሷል፡፡ ለለይለቱልቀድርም ከሁሉም ለሊቶች ብልጫ ሰጥቷል፡፡ በቀንና ለሊት ውስጥም ሊነጋጋ ሲል ያለው ጊዜ በደራጃ ከሌሎች ጊዜያት ሁሉ የላቀ ነው፡፡ ቀልቡን ማሳመርና ይበልጥ ማስተካከከል የፈለገ እነኚህን ወቅቶች በአግባቡ ይጠቀም፡፡ ለአላህንም ረህመትም እራሱን ይጣድ፡፡ ከዚያች ወቅት ባገኘው ትሩፋት ዳግም  እድለቢስነት ላያገኘው ይችላልና፡፡

የረመዷን ወር

ከወራት ሁሉ በላጩ ወር ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

شَهْرُ رَمَضَانَ الَّذِي أُنزِلَ فِيهِ الْقُرْآنُ هُدًى لِّلنَّاسِ وَبَيِّنَاتٍ مِّنَ الْهُدَىٰ وَالْفُرْقَانِ

(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡ አል-በቀራህ 2፥185

በእርሱ ውስጥ ቁርኣን ወረደ፡፡ ፆምም ተደነገገ፡፡ ከበላጭ የአምልኮ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ወሩ ከመድረሱ በፊት በሚገባ ልንዘጋጅለት ይገባል፡፡ ሶሃቦች ረመዷን ከወጣ በኋላ ስድስቱን ወር በሙሉ በሱ ስሜት ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ የተቀረውን ስድስት ወር ደግሞ እሱን ለመቀበል ይዘጋጁበታል፡፡ ከረጀብ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ‹አላህ ሆይ! ረጀብ እና ሸዕባንን ባርክልን፡፡ ለረመዷንም አድርሰን፡፡› ልንል ይገባል፡፡ በረመዷን ወር ወስጥ የሰውነት ክፍሎቻችን በሙሉ እንዲፆሙ እንትጋ፡፡ የቻልነውን ያህልም መስጅድ እናዘውትር፡፡ ቁርኣንን የዘወትር ጓደኛችን እናድርገው፡፡ በማስተንተን እና በጥልቀትም እናንበው፡፡ በውስጡም ዚክር እና የለሊት ሶላትን እናብዛ፡፡ በመጨረሻዎቹ አሥር ቀናትም የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ ሲያደርጉ እንደነበረው ኢዕቲካፍ እናድርግ፡፡ ማን ያውቃል በነዚያ ቀናት ውስጥ አላህ ለይለቱልቀድርን  ሊወፍቀን ይችላል፡፡ በመጨረሻም ፆማችን ተቀባይነት ጋር የሚያገኘው ዘካተልፍጥርን ስንከፍል ነውና ይህንኑ መወጣት ይኖርብናል፡፡

የጁሙዓ ቀን

ፀሃይ ከወጣችባቸው ቀናት ሁሉ በላጩ ቀን የጁሙዓ ቀን ነው፡፡  በውስጧ አንዲት ሰዓት አለች በዚያች ወቅት አንድ የአላህ ባሪያ ዱዓእ ደረገ እንደሆነ ምላሽ አይከለከልም፡፡ የጁሙዓን ቀን ቀልባችንን የምንሰበስብብት ቀን እናድርገው፡፡ ታጥበንና ሽቶ ተቀባብተን ጥሩ ሸተን አንዲሁም ምርጥ ልብሣችንን በመልበስ በጠዋት ወደ መስጅድ በመሄድ የኢማን ፕሮግራማችንን እንጀምር፡፡ በውስጡም በነቢዩ ሰ.ዐ.ወ ላይ ሶለዋት ማውረድ እናብዛ፡፡ ችክ ብለን ዱዓእ ማድረግን ልምዳችን እናድርግ፡፡ ለዚያች ወሣኝ ሰዓት አላህ ሊወፍቀን ይችላልና፡፡ የጁሙዓን ትሩፋት ከሚያመለክቱ ሀዲሦች መካከል ከአውስ ኢብኑ አውስ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ ‹ በጁሙዓ ቀን ያጠበ የታጠበና በጠዋት ማልዶ የወጣና እንዲወጡ ያደረገ እንሰሳ ሣይሣፈር በእግሩ በመሄድ ከኢማሙ ቀረብ ብሎ በጥሞና ሳይቀልድ ያዳመጠ ከቤቱ ወደ መስጅድ በሚያደርገው በያንዳንዱ እርምጃው የዓመት ያህል የመፆምና የመቆም ምንዳ አለው፡፡›

ከፈጅር ሶላት በኋላ ያለው ጊዜ

ከአነስ ረ.ዐ እንደተላለለፈልን የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ ‹ ሱብሂን በጀመዓ ሰግዶ ፀሃይ እስክትወጣ ድረስ አላህን እያወሣ ቁጭ ያለ ከዚያም ሁለት ረከዓ የሰገደ ሰው የሀጅ እና ዑምራ ሙሉ ሙሉ ምንዳ አለው፡፡›

6.ፆም ማብዛት

የፆም አስፈላጊነት

ፆም ወደ አላህ ፍራቻ የሚያደርስ መንገድ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ)    ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ አል-በቀራህ 2፥183

የአላህ መልእክተኛም ሰ.ዐ.ወ ሲመክሩ

عليك بالصوم فإنه لا مثل له

 ‹ በፆም ይሁንብህ እሱ አምሣያ የለውምና › ብለዋል፡፡

ፆም ከእሳት መከላከያ ጋሻ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል ‹ በአላህ መንገድ ላይ አንድ ቀን የፆመ ሰው አላህ በሱ እና በእሳት መካከል የሰማይና የምድር ያህል ቦይ ያደርጋል፡፡› ስለ ፆም ታላቅነት ከሚያመለክቱ ሀዲሦች መካከል አላህ ሱ.ወ በሀዲስ አልቁድሲ ከአቢ ሁረይራ ረ.ዐ እንደተላለፈው አላህ እንዲህ አለ ‹ የሰው ልጅ ሥራ ሁሉ ለሱ ነው ፆም ሲቀር፡፡ እሱ ለኔ ነው፡፡ እኔ ነኝ ምንዳውን የምከፍለው፡፡›

ፆም በርካታ ጥቅሞች አሉት

ቀልብን ያነፃል፣ እይታን ይጨምራል፣ ቀልብን ያለሰልሣል፣ ያነሳሣል፣ ለአላህ መተናነስና መዋረድ ነው፣ ኩራትንና ጉራን ያስወግዳል፣ ስሜትን ይገድላል፣ (በተለይ የግብረሥጋ ግንኙነት፣ የንግግርና የነፍስን ስሜቶች) አንቅልፍ እንዳይበዛ ይረዳል፣ ለሊት ብዙ ለመቆም ያግዛል፣ የሰውነትን ሀቅ ለመወጣት አስተዋፅኦ አለው፣ በሽታን ይከላከላል፣ ለዒባዳ ያነሣሣል፣፣ ቀልጣፋ ያደርጋል፣ ቀልብን ያለዝባል፡፡

አል ፉደይል እንዲህ ይላል ‹ሁለት ነገሮች ቀልብን ያደርቃሉ፤ ንግግር ማብዛት እና ምግብ ማብዛት፡፡›

ሉቅማን ለልጁ እንዲህ ይላል ‹ጠግበህ ሣለ አንድም ነገር አትብላ ከምትበላ ለቀልብህ ቦታ  ልትተውለት ይገባል፡፡›

ረመዷን የግዴታ ፆም የሆነ እድል ነው፡፡ እድሉን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የሱና ፆሞችንም ሰኞን ሀሙስን በሳምንት ውስጥ፤ ከየወሩ ሦስት ቀናትን፤ ሌሎች በላጭ ቀናቶችን ማለትም በሀዲስ የተነገሩ የዐረፋንና የዓሹራ ቀን ፀሞችንም ለመፆም እንነሣሣ፡፡

7.ማስተንተን

የማስተንተን  አስፈላጊነት

ኢማም አልገዛሊ እንዲህ ይላሉ ‹ አላህን ሱ.ወ ወደ ሚያሣውቀው መንገድ መጓዝ፣ ፍጥረታቱን በማስተዋል እሱን ማላቅ፣ ድንቅ ሥራዎቹን በጥልቀት ማስተንተን፣ የተለያዩ ፈጠራዎቹን በመቃኘት ግንዛቤን መውሰድ.. ኢማን በሰው ውስጥ እንዲረጋና እንዲሰርፅ ምክኒያት ይሆናል፡፡ የተከበረውና ሀያሉ አላህ የሰው ልጆች ወደራሣቸው በመመልከት ጭምር እንዲያስተነትኑ ጋብዟል፡፡

 فَلْيَنظُرِ الْإِنسَانُ مِمَّ خُلِقَ

ሰውም ከምን እንደተፈጠረ ይመልከት፡፡ አጧሪቅ 86፥5

አቡደርዳእ ‹ ማስተንተን ከሥራዎች ውስጥ ይመደባል ወይ?› ተብለው ተጠየቁ፡፡ እርሣቸውም ‹ አዎን እርሱ እርግጠኝነት/የቂን/ ነው፡፡› አሉ፡፡

ሀሠን እንዲህ ይላሉ ‹ ለአንድ ሰዓት ማስተንተን ለሊት ሙሉ ከመቆም ይበልጣል፡፡›

  • የማስተንተን ሜዳዎች

የሰው ልጅ ወደራሱ በመመልከት ማስተንተን ይችላል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَلَقَدْ خَلَقْنَا الْإِنسَانَ مِن سُلَالَةٍ مِّن طِينٍ

ثُمَّ جَعَلْنَاهُ نُطْفَةً فِي قَرَارٍ مَّكِينٍ

ثُمَّ خَلَقْنَا النُّطْفَةَ عَلَقَةً فَخَلَقْنَا الْعَلَقَةَ مُضْغَةً فَخَلَقْنَا الْمُضْغَةَ عِظَامًا فَكَسَوْنَا الْعِظَامَ لَحْمًا ثُمَّ أَنشَأْنَاهُ خَلْقًا آخَرَ ۚ فَتَبَارَكَ اللَّهُ أَحْسَنُ الْخَالِقِينَ

በእርግጥም ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው፡፡ ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍትወት ጠብታ አደረግነው፡፡ ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን፡፡ የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን፡፡ ቁራጯንም ሥጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን፡፡ አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው፡፡ ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረትን አድርገን አስገኘነው፡፡ ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ፡፡ አልሙእሚኑን 23፥12

ወደ ጠብታ ፈሣሽ (ስፐርም) እንመልከት፡፡ ደካማና ዝልግልግ ፈሣሽ ነው .. ሲያዩት የሚቀፍ፡፡ ትንሽ ደቂቃዎች ቢቆይ የሚሸት የሚያስጠላ፡፡ አዋቂ እና በሁሉም ነገር ላይ ቻይ የሆነው የጌቶች ሁሉ ጌታ አምላክ ግን በችሎታው እና በፈቃዱ ከጀርባ እና ደረት መካከል እንዴት እንዳወጣው… እንዴት ወንድና ሴትን እንዳገናኘ እናስተንትን፡፡ እንዴት የማይተዋወቁ ባልና ሚስት መካከል መዋደድን እንዳኖረ.. እንዴትስ ለልጅ መፈጠር ምክኒያት ወደሆነው የስሜት ፍላጎት እንደመራቸው እናስተውል፡፡ ያንን ዝልግልግ ውሃ ወደ ማህፀን ውስጥ በመውሰድ ከብርድ እና ሙቀት እንዲሁም ከሌላ ሊያበላሸው ከሚችል ነገር ሁሉ ጠብቆት አመቺ ቦታ ላይ እንዳስቀመጠው እናስተንትን፡፡ ነጩ ንፍጥ መሣይ ነገር ኋላም ወደ ጥቁር ቀጥሎም ወደ ቀይ በመለወጥ ከዚም ወደ ተላመጠ ሥጋ የሚመስል ነገር በመቀየር ከዚያም ወደ ሥጋና አጥንት ያድጋል፡፡

እያደገ ከመጣው ሥጋ የተለያዩ ሰውነት ክፍሎች አጥንት፣ እጅና እግር፣ ጭንቅላት… እንዴት እንደሚፈጠሩ እናስተንትን፡፡ እነኚህ የሰውነት ክፍሎች እንዴት እንደተያያዙና እንደተጠነካከሩ  እናስተውል፡፡ ሥጋ የቆመው አጥንት ላይ ነው፡፡ አጥንትም የሚጠበቀው በሥጋ ነው፡፡ ይህን ሁሉ እንዴት እንዳስተካከለና እንዳሣመረ፤ ዓይንን፣ አፍንጫን፣ አፍን .. ሌሎችንም ቀዳዳዎች እንዴት እንዳበጃጀ፤ እጅና እግርን እንዴት እንደዘረጋና ጫፎቻቸው ላይም ጣቶችን እንዳኖረ እንመልከት፡፡ የውስጥ የሰውነት ክፍሎችን ልብን፣ አንጀትን፣ ጉበትን፣ ኩላሊትን፣ ማህፀንን ለሁሉም በሚስማማው መልኩ በቂ ቦታና የራሱ የሆነ አገልግሎት ዘርፍ ሰጥቶት እንዴት እንዳስቀመጠ እናስተውል፡፡

ይህ ሁሉ የታላቁ እና ጥበበኛ፤ ሁሉን ቻይና አዋቂ የሆነው ጌታ አላህ ሱ.ወ ድንቅ ሥራ  ነው፡፡ ከትንሽ ጠብታ እስከ ትልቅ ፍጥረት …፡፡ ወየውላቸው ለአስተባባዮች ! ወየውላቸው ለከሃዲያን!! ነገሩ በርግጥም ከምናስበው በላይ ነው፡፡ ለመናገርም ቃላት ያጥራል፡፡ እንዲሁ አንድ አማኝ በዙርያው ስለሚገኘው ፍጥረተ ዓለምም ሊያስተነትን ይገባል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

قُلِ انظُرُوا مَاذَا فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ

«በሰማያትና በምድር ያለውን (ተዓምር) ተመልከቱ» በላቸው፡፡ ዩኑስ 10፥101

ስለሆነም በዙሪያችን ስላለው ሰማይ ስለ ከፍታውና ስፋቱ፣ ስለ ክብነና ወጥነቱ እናስተውል፡፡ በርግጥም ምንኛ ግዙፍ ነው! እንዴት ያምራል! ፀሃይ፣ ኮከብና እና ጨረቃው ምንኛ ደማቅ ናቸው! ይዘታቸውና ቅርፃቸውስ ምን ይመስላል!? የምስራቅና ምእራብ መለዋወጡስ? ሁሉም ጥበቡንና ችሎታውን የሚያሣዩ ናቸው፡፡ እነኚህ ሁሉ ከሰው ልጅ አፈጣጠር አንፃር ሲታዩ ግዙፍ የሆኑ እጅግ የሚደንቁ ፍጥረታት ናቸው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

أَأَنتُمْ أَشَدُّ خَلْقًا أَمِ السَّمَاءُ ۚ بَنَاهَا

ባፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይንስ ሰማይ? (አላህ) ገነባት፡፡ አናዚዓት 79፥27

إِنَّ فِي خَلْقِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافِ اللَّيْلِ وَالنَّهَارِ لَآيَاتٍ لِّأُولِي الْأَلْبَابِ

ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀንንም በመተካካት ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ፡፡ አልዒምራን 3፥190

በዚህ የቁርኣን አንቀፅ አላህ ሱ.ወ ስለ ሰማያትና ምድር እንድናስተነትን ጋብዞናል፡፡ ይህም በቁርኣን ውስጥ ብዙ ቦታ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ደጋግሞ የሚያወሣውም ባሮቹ እነሱን በመመልከት ባሮች ፈጣሪያቸው ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ እንዲያስተነትኑ እድል ለመስጠት ፤ አላህ (ሱ.ወ) በትንሣኤ ቀን ቃል ለገባው ነገር እነርሱን እንደማስረጃ ለማቅረብ፤ ስለ ጌትነቱና አንድነቱ ለማመላከት፤ ከሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ ስለመሆኑ ለማሣየት እንዲሁም ሰዎች ወደሰማይ በመመልከት ምንም እንከን የሌለባት ፍፁም መሆኗን በሚገነዘቡበት ጊዜ የሱን ጥበብ እና ችሎታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ነው፡፡

እስቲ ዐይንህን ወደ ሰማይ መልስ፡፡ አንዳች ስንጥቅ ፣ ቀዳዳ አሊያም እንከን ታያለህን? ወደ ኮከቦቿ ድምቀት፣ ወደ ፀሃይ እና ጨረቃ መግቢያ መውጫቸው ስለመለያየቱ ወደማያቋርጥ አንቅስቃሴቸው፣ ዝንፍ ወደማይለው አካሄዳቸው ተመልከት፡፡ ሣይድሙ ሣይዘገዩ ሁሉም በተደበላቸው ጊዜና ሰዓት አንዲሁም መስመር ይንቀሣቀሣሉ፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸው እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ፡፡

የጨረቃን አስደናቂ አፈጣጠር እንመልከት፡፡ አላህ ትንሽ ክር በሚመስል መልኩ አወጣው፡፡ ከዚያም እየጨመረ እየጨመረ ሄዶ በመጨረሻም ሙሉ ጨረቃ ይሆናል፡፡ ኋላም ዳግም ተመልሦ ይቀንሣል፡፡ ወደ መጀመሪያ ሁኔታው እስኪመለስ ድረስ፡፡ በዚህ ሁሉ ክስተቱ ባሮች ለኑሮአቸውና ለአምልኮአቸው ተግባራቶች ነገሮችን መስመር ያስይዙባቸዋል፡፡ ወራት እና ቀናትን ይለዩባቸዋል፡፡ ዓለማት ለቀናት ቆጠራ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ እኛ የማናውቃቸው አላህ ብቻ የሚያውቃቸው ጥበቡ ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

ኢብኑ አልቀይም አንዲህ ይላሉ ‹ አላህ አንድ እና ከሱ በስተቀር አምላክ የሌለና አንድም አምሣያ የሌለው እንዲሁም ከሱ በላይ ታላቅ፣ ምሉእ አዛኝ እና ሩህሩህ የሌለ መሆኑን የሚያመላክቱ የሚታዩ ተዓምራት እና ማሰረጃዎችን ማምጣት ብንፈልግ እኛም ሆንን የቀደሙንና ከኋላችን የሚመጡት አንድ አሥረኛውን እንኳን ማምጣት ይቸግረናል፡፡ ነገርግን ሙሉ ነገሩ ተጠቃሎ የማይደረስበትን ነገር ሙሉ በሙሉ መተው አያስፈልግም፡፡ ቢያንስ ወደዚያ ነገር የሚያመለክተውን ነገር ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡›

ከላይ የተጠቀሰው የአላህን ፍጥረታት ለማስተንተን መጠነኛ ማሣያዎች ናቸው፡፡ ስለ ቀንና ለሊት ስለ እንሰሣትም ሆነ ስለ ሌላ የተቀረውንና በዙሪያችን ያለውን ነገር ለማስተንተን ይህንኑ መንገድ ልንከተል ይገባል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

اللَّهُ الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ اللَّيْلَ لِتَسْكُنُوا فِيهِ وَالنَّهَارَ مُبْصِرًا ۚ إِنَّ اللَّهَ لَذُو فَضْلٍ عَلَى النَّاسِ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَشْكُرُونَ

አላህ ያ ለእናንተ ሌሊትን በውስጡ ልታርፉበት (ጨለማ) ቀንንም (ልትሠሩበት) የሚያሳይ ያደረገላችሁ ነው፡፡ አላህ በሰዎች ላይ በእርግጥ የችሮታ ባለቤት ነውና፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያመሰግኑም፡፡ ጋፊር 40፥61

ስለ ተለያዩ እንሰሣት ስናስተነትንም እንዲሁ

أَفَلَا يَنظُرُونَ إِلَى الْإِبِلِ كَيْفَ خُلِقَتْ

(ከሓዲዎች) አይመለከቱምን? ወደ ግመል እንዴት እነደተፈጠረች! አልጋሺያ 88፥17

 ስለ ተራሮች፣ ባህሮች፣ አዝርእቶች፣ አየር እና ሌላም ፍጥረታት ስናስተነትን ተያያዥ ከሆኑ ውዳሴዎች /ተስቢሆች  እና ተህሊሎች/ ጋር ማያያዝ ይኖርብናል፡፡

ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ)  እንዲህ ይላሉ

 تفكروا في آلاء الله ولا تفكروا في ذات الله

‹ስለ አላህ ዛት (አካላዊ ምንነት) ሣይሆን ስለ አላህ ፀጋዎቹ አስተንትኑ፡፡›

የአላህ ፀጋዎች ማስተንተን ቅናቻ ነው፡፡ ወደ አንድ ነገር ይመራል፡፡ በአላህ ዛት ማስተንተን እና መመራመር ግን ጥፋት ነው፡፡ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ይላሉ

يأتى الشيطان أحدكم فيقول من خلق كذا حتى يقول من خلق ربك ؟ فإذا بلغه فليستعذ بالله ولينته

‹ሸይጧን ወደ አንዳችሁ ይመጣና ይህን ማን ፈጠረ?? ይላል፡፡ ‹ጌታህን ማን ፈጠረ?› እስኪል ድረስ፡፡ እዚያ ደረጃ ከደረሠ ከሱ በአላህ ይጠበቅ፡፡ ይመለስም፡፡›

በሀዲስ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዴት ማስተንተን እንዳለብንና መጨረሻውም እስከምን እንደሆነ አስተምረውናል፡፡ አንድ ሰው ስላለፉት ህዝቦች ታሪክ ማስተንተን ይችላል፡፡ ከነርሱ ምክርና ታላቅ ትምህርት ይገኛልና፡፡ ለዚህም ነው አላህ ሱ.ወ ለነቢዩ ሰ.ዐ.ወ እነኚህ ታሪኮች የሚነግረው፡፡

إِنَّ هَٰذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاعْبُدُونِ

ይህች (ሕግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ፡፡ አልአንቢያ 21፥92

ስለሆነም ወደ ሰፊውና በግልፅ ወደሚታየው ፍጥረተ ዓለም ገፅ በመመልከት የምናስተነትንበት ጊዜ ሊኖረን ይገባል፡፡ ለምሣሌ ፀሃይን በመውሰድ አፈጣጠሯን፣ አሰራሯን እና ይህ ሁሉ እንዴት ወደ አላህ መኖርና አንድ ስለመሆኑ እንዲሁም እሷን በመፍጠሩ የአላህ ፀጋ በኛ ላይ ታላቅ ስለመሆኑ ለናውቀም ይገባል፡፡

*********

ይቀጥላል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here