በኢማን ከፍ ማለት 2 አላህን ማውሣት ማብዛት

0
5560

2. አላህን ማውሣት ማብዛት

አላህ ሱ.ወ እንዲህ በማለት አዞናል

 

أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِذَا لَقِيتُمْ فِئَةً فَاثْبُتُوا وَاذْكُرُوا اللَّهَ كَثِيرًا لَّعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሰራዊትን በገጠማችሁ ጊዜ እርጉ፤ (መክቱ)፡፡ አላህንም በብዙ አውሱ፤ በእርግጥ ትድናላችሁና፡፡ አል-አንፋል 8፥45

በአቡ ደርዳእ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ ‹ ከሥራዎቻችሁ ሁሉ በላጭ፤ በጌታችሁ ዘንድ እጅግ ምርጡ፤ ደረጃችሁን ከፍ የሚያረግላችሁ፤ ወርቅና ብር ከመለገስ የሚበልጥላችሁን እንዲሁም ከጠላቶቻችሁ ጋር ተገናኝታችሁ አንገቶቻቸውን ከምትቆርጡና አንገታችሁን ከሚቆርጧችሁ በላይ የሆነውን ልንገራችሁን?› በማለት ጠይቀው ‹አላህን ማውሣት ነው፡፡› አሉ፡

አላህን ማውሣት ለቀልብ ህይወት ነው፡፡ ኢብኑ ተይሚያ እንዳሉት ‹ዚክር ለቀልብ ለዓሣ ውሃ › እንደማለት ነው፡፡ ዚክር በአላህ ከተረገመው ሸይጧን ጠንካራ መጠበቂያ ምሽግም ነው፡፡ አንድ ሰው በቀንና ለሊት የሚመፀውትበት ብዙ ምፅዋትም ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ ‹.. የጀነት ተክሎች ሱብሃነላህ፣ አልሀምዱ ሊላህ፣ ላ ኢላሀ ኢልለላህ፣ አሏሁ አክበር ናቸው፡፡›

በላጩ ዚክር በምላስ እና በቀልብ አንድ ላይ የሚደረገው ነው፡፡ በቀልብ ብቻ አላህን ማውሳት በምላስ ብቻ ከማውሣት በላጭ ነው፡፡ በዚክር ወቅት ምላስ እና ቀልብን ማገናኘት እጅግ ከባድ ነገር ነው፡፡ ነገርግን አላህ ላገራለት ሰው ገር ነው፡፡ ይህን ለማስገኘት ጉጉና ዝግጁ ለሆነ ሰው ማለት ነው፡፡ ኢብኑ አልቀይም በ ‹አልፈዋኢድ› ኪታባቸው ውስጥ እንዳሉት

‹‹ ከሰዎች መካከል ምንም እንኳ ቀልቡ ዝንጉ ቢሆንም በምላሱ ዚክር የሚጀምር አለ፡ ከዚያም በዚሁ መልኩ ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም ቀልብም ህያው ሆኖ ዚክሩን እስኪቀላቀለው ድረስ፡፡ ከሰዎች መካከልም ቀልቡ እስኪሰባሰብለት ድረስ በምላሱ ዚክርን የማይጀምር አለ፡፡ ቀልቡ ህያው ሲሆንለት በቀልቡና ምላሱ ዚክርን ይጀምራል፡፡››

ለእያንዳንዱ ወቅት ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተገኘ የተመረጠ ዚክር እና ዱዓ አለው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጠዋት እና ማታ፣ ምግብ ላይ፣ በእንቅልፍ ወቅት፣ ሲፀዳዱ እና በሌሎችም ጊዜዎች ዱዓእ አላቸው፡፡ እነኚህን የነቢዩን ሰ.ዐ.ወ ዱዓኦች በቃላችን መሸምደድ ይኖርብናል፡፡ በቀልባችን እና ምላሳችን በሁሉም ሁኔታዎቻችን ላይ በመደጋገም ከፀሃይ መውጣትና መግባት በፊት እነኚህን ዱዓኦች ልንላመድ ይገባል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ قَبْلَ طُلُوعِ الشَّمْسِ وَقَبْلَ غُرُوبِهَا ۖ وَمِنْ آنَاءِ اللَّيْلِ فَسَبِّحْ وَأَطْرَافَ النَّهَارِ لَعَلَّكَ تَرْضَىٰ

ጌታህንም ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት ከመግባትዋም በፊት የምታመሰግን ኾነህ አጥራው፤ (ስገድ)፡፡ ከሌሊት ሰዓቶችም በቀን ጫፎችም አጥራው፡፡ (በሚሰጥህ ምንዳ) ልትወድ ይከጀላልና፡፡ ጣሀ 20፥130

3.የለሊት ሶላት

የለሊት ሶላት ትሩፋትና አስፈላጊነቱ

ሰዎች በሚተኙበት የለሊት ሰዓት መነሳትና ከዓለማዊ ጉዳዮች እራስን በመነጠል ከአላህ ጋር በመገናኘት እዝነቱን፣ ብርሃኑን፣ ወደሱ መጠጋትን ማግኘት፣ ቁርኣንን ማንበብ፣ ፍጥረተ ዓለሙ ተኝቶ ባለበት ሁኔታ ከለዕላዩ ዓለም ጋር መገናኘት የአንድ አማኝ ነፍስ በሥጋው ላይ ስለመንገሷ ማሳወቂያ ነው፡፡ ለአላህ (ሱ.ወ) ጥሪ ምላሽ መስጠትና ከርሱ ጋር መወዳጀትን መምረጥም ነው፡፡ አላህን (ሱ.ወ) ማውሣት ጥፍጥና አለው፡፡ ለሱ መስገድና እሱን መፍራት እንዲሁም ከሱ ጋር ተገልሎ ማውራት ውስጥ ታማኝነትና ግልፅነት አለ፡፡ ይህ ነገር በቀን ጊዜ ሶላቶች ውስጥ የሚገኝ አይደለም፡፡

ሰይድ ቁጥብ እንዲህ ይላሉ ‹‹ የለሊት ሶላት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ አላህ ሱ.ወ ነቢዩን ሰ.ዐ.ወ አዟል፡፡  አላህን ፈሪዎችም በለሊቱ ሰዓት በመቆማቸው አወድሷቸዋል፡፡ ››

إِنَّ الْمُتَّقِينَ فِي جَنَّاتٍ وَعُيُونٍ

آخِذِينَ مَا آتَاهُمْ رَبُّهُمْ ۚ إِنَّهُمْ كَانُوا قَبْلَ ذَٰلِكَ مُحْسِنِينَ

كَانُوا قَلِيلًا مِّنَ اللَّيْلِ مَا يَهْجَعُونَ

وَبِالْأَسْحَارِ هُمْ يَسْتَغْفِرُونَ

አላህን ፈሪዎቹ በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡ ያንን ጌታቸው የሰጣቸውን ተቀባዮች ኾነው፤ (በገነት ውስጥ ይኾናሉ)፡፡ እነርሱ ከዚህ በፊት መልካም ሰሪዎች ነበሩና፡፡ ከሌሊቱ ጥቂትን ብቻ ይተኙ ነበሩ፡፡ በሌሊቱ መጨረሻዎችም እነርሱ ምሕረትን ይለምናሉ፡፡      አዛሪያት 51፥15-18

ተወዳጁ ነቢይም (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ አንድ ባሪያ ለጌታው እጅግ ቅርብ የሚሆነው በለሊቱ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ በዚያን ወቅት አላህን ከሚያወሱት መሆን ከቻልክ ሁን፡፡›› ብለዋል፡፡ ለሊት መቆም ለአንድ አማኝ ትልቅ ክብር ነው፡፡

ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)‹‹ የአንድ አማኝ ክብሩ በለሊት የሚቆመው ሶላት ነው፡፡ኩራቱ ደግሞ ከሰዎች እጅ ካለው መብቃቃቱ ነው፡፡››

ሀሠን እንዳለው ‹‹ አንድ ሰው ከሚስቱ ጋር በመተኛት ላይ እያለ ለሊቱን ሙሉ እሷ ምንም  ሣታውቅበት ረጅም ለቅሦ ሊያለቅስ ይችላል፡፡ አንድን ለሊት መጠቀም የሚችለው ፍጡር ዝር በማይልበትና ፈጣሪ ብቻ ባለበት በዚያ ሰዓት እውነተኛ ሆኖ ወደ አላህ የተመለሠ ሰው ብቻ ነው፡፡ የለሊት ቀስት ዒላማውን አይስትም፡፡››

ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል ‹‹ የተባረከውና ከፍ ያለው ጌታችን የለሊቱ አንድ ሦስተኛ ሲቀር በየለሊቱ ወደ ቅርቢቱ ሰማይ ይወርዳል፡፡›› ‹ማነው ለምኖኝ ምላሽ የምሠጠው?› ማነው ጠይቆኝ ምላሽ የምሠጠው? ማነው ከኔ ምህረት ጠይቆ የምምረው?› ይላል፡፡› ይህ የተወዳጁ ነቢይ ሰ.ዐ.ወ መንገድ ነው፡፡ በሀገር እያሉም ሆነ መንገደኛ ሆነው፤ በጤና ሳሉም ሆነ ታመው አልተውም፡፡ ዓኢሻ ረ.ዐ እንዲህ ብላለች ‹‹ የለሊት ሶላትን አትተው፡፡ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ ታመውም አይተውም ነበር፡፡ ሲደክማቸው ቁጭ ብለው ይሰግዳሉ፡፡››

ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ በተለይ ትልቅ ችግር ሲገጥማቸው የለሊት ሶላትን አጥብቀው ይይዛሉ፡፡ በበድር ቀን የሆነውን ሲናገር ዐሊ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላል ‹ ሁላችንም ተኝተን ባለንበት ሁኔታ እርሣቸው በአንዲት ዛፍ ሥር ሲሰግዱና ሲያለቅሱ ለሊቱ ሲነጋባቸው አይቻለሁ፡፡› የሶሃቦቻቸውም (ረ.ዐ) መንገድም እንዲሁ ነበር፡፡ ዐባስ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ እንዲህ ይላል     ‹‹የዑመር ጎረቤት ነበርኩኝ፡፡ ከሰዎች ሁሉ እርሱን የሚበልጥ አንድም  ሰው አላየሁም፡፡ ለሊቱን ይሰግዳል፡፡ ቀኑን በፆም እና የሰዎችን ሃጃ ሲፈፅ ተጠምዶ ያሣልፋል፡፡››

የለሊት ሶላት ለመቆም የሚያግዙ ነገሮች

  • ለመቆም ትክክለኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ማሣየት፤ ለማሣካትም በዱዓ መታገዝ
  • ከወንጀል መራቅ፤ ትክክለኛ ተውባ ማድረግ፡፡ አንድ ሰው በሚሰራው ወንጀል /ሀጢኣት/ ምክኒያት የለሊት ሶላትን ሊከለከል ይችላል፡፡
  • በጦሃራ ላይ ሆኖ መተኛት፤ በእንቅልፍ ጊዜ የሚደረጉ ዱዓኦችን ማድረግ
  • ከተቻለ የቀይሉላ እንቅልፍ መተኛት (ቀን ላይ የሚተኛ መጠነኛ እንቅልፍ)

እንግዲያውስ ይህን ትልቅ ችሮታ ለመቋደስ እንበርታ፡፡ በዒሻና ፈጅር መካከል የተወሰኑ ረከዓዎችን ለመስገድ እንሞክር፡፡ በመዝገቡም ላይ ለመፃፍ እንችል ዘንድ በለሊቱ መጀመሪያ፣ በመካከሉና በመጨረሻው ላይ አላህ ያገራልንን ያህል እንስገድ፡፡

4. መስጅድን ማዘውተር

መስጅዶች በምድር ላይ የአላህ ቤቶች ናቸው፡፡ መስጅዶችን የሚገነቡት ዘወትር እነርሱን የሚጎበኙ ናቸው፡፡  በሷ ውስጥ አላህን ስለሚያልቁና ስለሚቀድሱም ‹ወንዶች!› ለመባል በቅተዋል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

فِي بُيُوتٍ أَذِنَ اللَّهُ أَن تُرْفَعَ وَيُذْكَرَ فِيهَا اسْمُهُ يُسَبِّحُ لَهُ فِيهَا بِالْغُدُوِّ وَالْآصَالِ

رِجَالٌ لَّا تُلْهِيهِمْ تِجَارَةٌ وَلَا بَيْعٌ عَن ذِكْرِ اللَّهِ وَإِقَامِ الصَّلَاةِ وَإِيتَاءِ الزَّكَاةِ ۙ يَخَافُونَ يَوْمًا تَتَقَلَّبُ فِيهِ الْقُلُوبُ وَالْأَبْصَارُ

አላህ እንድትከበርና ስሙ በውስጧ እንዲወሳ ባዘዘው ቤቶች ውስጥ (አወድሱት)፡፡ በውስጧ በጧትና በማታ ለእርሱ ያጠራሉ፡፡ አላህን ከማውሳትና ሶላትን ከመስገድ ዘካንም ከመስጠት ንግድም ሽያጭም የማያታልላቸው ልቦችና ዓይኖች በእርሱ የሚገላበጡበትን ቀን የሚፈሩ የኾኑ ሰዎች (ያጠሩታል)፡፡ አል-ኑር 24፥36-37

በመስጅድ ውስጥ ሶላትን መከወን ብቻውን የልብ መስጅድ መንጠልጠልን አያመለክትም ፡፡ ነገርግን ከመስጅድ ከወጡ በኋላ ወደዚው ለመመለስ መጓጓት፣ ወደ መስጅድ መመላስ ማብዛት፣ እዚያው ቆይቶ አንድ ሶላት ወጥቶ ሌላኛው እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ… ይህ ሁሉ ቀልብ በመስጅድ ስለመንጠልጠሉ አመላካች ነው፡፡

ተወዳጁ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ አላህ ወንጀልን የሚያብስበትን፤ ደረጃን ከፍ የሚያረግበትን ልጠቁማችሁን እንዴ?›› በማለት ጠየቁ፡፡ ሰሃቦችም ‹አዎን የአላህ መልእክተኛ ሆይ!› አሏቸው፡፡ ‹‹ለነፍስ በሚከብድበት ጊዜ ወዱእ አሟልቶ ማድረግ፣ ወደ መስጅድ መመላለስ ማብዛት፣ ከሶላት በኋላ ሶላትን መጠበቅ፡፡ ይህ ነው በአላህ መንገድ ዋርዲያነት ይህ ነው በአላህ መንገድ ዋርዲያነት፡፡›› አሉ፡፡

የልብ በመስጅድ መንጠልጥል ትሩፋቶች

ለመልካም ኑሮ ያበቃል፣ መጨረሻን ያሣምራል፣ በጀነት ውስጥም ማረፊያን ያስገኛል፡፡ አንድ ሰው መስጊድ ውስጥ ሆኖ መስገጃ ቦታው ላይ እስከቆየ ድረስ መላእክቶች የአላህን እዝነት ይለምኑለታል፣ የትንሣኤ ቀን ምሉእ የሆነ ብርሃን እንደሚያገኝም ብሥራት አለው፣ የአላህን እዝነትም ያገኛል፣ ሲራጥንም ያልፋል፡፡  ልባቸው በመስጅድ የተንጠለጠለ ሰዎች ከመላእክት ጋር ልዩ ግንኙነት አላቸው፡፡ ቢጠፉ ይጠይቋቸዋል፣ ቢታመሙ ይጎበኟቸዋል፣ በጉዳዮቻቸውም ላይ ይደግፏቸዋል፡፡

ስለሆነም በመስጅድ የጀመዓ ሶላት ላይ እንበርታ፡፡ የመጀመሪያው ሶፍ እንሽቀዳደም፡፡ ከመስጅድ በምንወጣበት ወቅት ለለመለስ ሀሳብ እናኑር፡፡ በመስጅድ ውስጥ ሆነንም ሶላትን የምንጠብቅበት ጊዜም ይኑረን፡፡ ዚክር፣ ዒልም እና ዲናዊ መልእክት በሚተላለፍባቸው ስብስቦችም ላይ እንገኝ፡፡

******* ይቀጥላል

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here